የእስክንድር ነጋና የኤርሚያስ ለገሠ ጥምረት ወደ ቴሌቪዥን ሊሸጋገር ነው
በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ያቋቋመው ሰናይ ሚዲያ እና በኤርሚያስ ለገሠ የሚመራው ኢትዮ 360 ጥምረታቸውን ከፍ ባደረገ መልኩ በቅርቡ በሳተላይት ቴሌቪዥን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሊገናኙ መሆኑን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል።
በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከፍተኛ መሰዋዕትነት ከከፈሉ ጋዜጠኞች መሀል ግንባር ቀደም የሆነውና በወያኔ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የታሠረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በአሁኑ ሰዓት ከ25 ዓመት ሲያሳትማት የነበረችውንና ሕወሓት መራሹ መንግሥት ከ24 ዓመት በላይ አግዷት የቆየችውን ኢትኦጲስ ጋዜጣን ዘወትር ቅደሜ ለሕትመት እያበቃ ይገኛል። እስክንድር ነጋ ከአንድ ዓመት ወዲህ እየገነነ የመጣውን “ፊንፊኔ ኬኛ” ፖለቲካን እና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና የሁሉም ኢትዮጵያዊ መናኸሪያ የሆነችውን አዲስ አበባን ለመጠቅለል የሚደረገውን ሴራ በተደራጀ መልኩ በመጋፈጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይዞት የመጣው ለውጥ የይስሙላ ከመሆኑ ባሻገር የሕወሓት የበላይነት ጽንፍ በያዙ የኦሮሞ ብሔርተኞች እንደተተካ ደጋግሞ በመናገር የሚታወቀውና በሚከተለው የፖለቲካ አቋምና ትንታኔ የተነሳ ኢሳትን በገዛ ፍቃዱ የወጣው ኤርሚያስ ለገሠ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን 360 የተሰኘ የኢንተርኔት ሚዲያ በመክፈት በመሥራት ላይ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ባላደራ ም/ቤት ያቋቋመው እስክንድር ነጋ ማህበሩ ከጅምሩ ከታከለ ኡማ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ በበጎ አለመታየቱና በአባላቱ ላይ በሚደርሰው ዕስር ምክንያት እንቅስቃሴውን ዓለም አቀፍ ለማድረግ በማሰቡ ኤርሚያስ ለገሠ የም/ቤቱ ም/ሊመንበር እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል:: ኤርሚያስ ለገሠ ሓላፊነቱን ከተቀበለበት ጊዜ አንስቶ በአውሮፓና በአሜሪካ የተለያዮ ከተሞች በመዘዋወር ሰፋ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
እስክንድር ነጋ ከተለያዮ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰናይ ቴሌቪዥንን ለመመሥረት የጀመረውን ጥረት በዚህ ወቅት በማገባደድ ላይ ቢሆንም የነኤርሚያስ ለገሠ 360 ሚዲያ ከሰናይ ቲቪ ጋር ሊዋኻድ የሚችልበትን ስምምነት መፈጸማቸውን ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ነግረውናል።
በዚህ መሠረት የእስክንድር ነጋና የኤርሚያስ ለገሠ ጥምረት በቅርቡ በሳተላይት ቴሌቪዥን ዕውን ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮቻችን አዲሱ ቴሌቭዥን በእስክንድር እየተመራ ከአዲስ አበባ እነሀብተሙ አያሌውና ምናላቸው ስማቸውን የሚያቅፈው በኤርሚያስ ለገሠ የሚመራው ቡድን ከአሜሪካ ስርጭቱን የሚያስተላልፍበት አሠራር እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ቀሲስ በላይና ግብረ አበሮቻቸው ይቅርታ ባለመጠየቃቸው በሕግ ሊጠየቁ ነው
የአሮሚያ ቤተክህነት የማቋቋም ጥያቄን እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ይፋ አደረጉ። “ጥያቄውን ያቀረበው ቡድን ከአድራጎቱ እንዲቆጠብ ሲኖዶሱ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል።
ቤተክርስቲያኒቱ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ፤ ያለ ምንም መድልዎ አገልግሎት ትሰጣለች ያሉት ፓትርያርኩ፤ ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍት በኦሮምኛ ቋንቋ መዘጋጀታቸውን አጣቅሰ። የተነሳውን ጥያቄም “አገርና ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል” ነው በማለት ኮንነውታል።
ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎት የሚሰጡባቸው በአገረ ስብከት ሥር ያሉ በርካታ ጽህፈት ቤቶች እንዳሉ ያስታወሱት አቡነ ማትያስ፤ “የተከበረውና የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለውለታ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብን ቤተ ክርስቲያን እንዳገለለችውና አቅዳ እንደበደለችው ለማስመሰል ያቀደ” ደርጊት ነው በማለት የአደራጅ ኮሚቴዎቹን አካሄድ ወቅሰዋል።
የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ለማዋቀር ጥያቄ ያቀረቡት ግለሰቦች፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ተጠይቀው ውይይት እንዳደረጉ ያስታወሱት ፓትርያርኩ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ ቢያሳውቅም፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ ግለሰቦቹ መግለጫ መስጠታቸው አግባብነት የጎደለው ድርጊት መሆኑንም መስክረዋል።
የአደራጅ ቡድኑም አባላት ይህንን አምነው “ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ” ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለዛሬ ጳጉሜን 2፣ 2011 ዓ.ም. ጠዋት ቢቀጠሩም፤ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን እንዳልተገኙና ሁለት የኮሚቴው አባላት ዘግይተው እንደደረሱ ፓትርያርኩ አስታውሰው ግለሰቦቹ ሕጋዊ ሥልጣን ሳይኖራቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አርማ፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ በመጠቀማቸው አስፈላጊው እርምጃ ለመውሰድ፤ “የጽህፈት ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ በሕገ ወጥ ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥብቅ አዟል” ሲሉ አስታውቀዋል።
በመሪ የክብር ደረጃ እንዳትቀብሩኝ ያሉት የአንደበተ ርዕቱው ሮበርት ሙጋቤ ማንነት
በ1924 (እኤአ) እጅግ አነስተኛ ገቢ ካላቸና የተወለዱት በእንጨት ሥራ ከሚተዳደሩ ቤተሰብ ነው የተወለዱት ሮበርት ሙጋቤ።
የልጅነት ጊዜያቸው በአብዛኛው በዝምታና በገለልተኝነት ያለፈ ሲሆን ፣ የተማሩት በሮማን ካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ነው:: በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኘው ፎርት ሀሬ ዩኒቨርስቲ ያገኙትን ነፃ የትምህርት እድል በመጠቀም የዕውቀት አድማሳቸውን አስፍተዋል።
የፓን አፍሪካዊው ክዋሜ ንክሩማ አስተሳሰብ አድናቂ የሆኑት ሙጋቤ የመምህርነትን ሙያ አሀዱ ብለው የጀመሩትም በጋና ከመሆኑ ባሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ በትዳር የተቆራኟት ሴት ጋናዊት ነበሩ።
በጋና የተወሰኑ ዓመታት ከቆዩ በኋላ በ1960 ወደ ትውልድ አገራቸው ዙምቧብዌ የተመለሱት ሮበርት ሙጋቤ በቅድሚያ ከጆሽዋ ንኮሞ ጋር በጋራ መሥራት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘ዚምባብዌ አፍሪካን ናሽናል ዩኒየን’ ወይም ዛኑ ፒ ኤፍን ፓርቲ መሠረቱ። ይህ ይሁን እንጂ የጆሽዋ ንኮሞ ፓርቲ ከሆነው ‘ዚምባብዌ አፍሪካን ፒፕልስ ዩኒየን’ ወይም ዛፑ ፓርቲ ጋር በቅርበት ከመሥራት ወደ ኋላ አላሉም።
ወደ ፖለቲካው ዓለም የገቡት ሙጋቤ ዛኑን በመሰረቱ በአራተኛው ዓመት ጠቅላይ ሚንስትር ኢን ስሚዝና አስተዳደራቸውን በመተቸታቸው ለዕስር ተዳረጉ። ሙጋቤ በዕስር ላይ እያሉ ልጃቸው ቢሞትም ቀብሩ ላይ ለመገኘት ፍቃድ ሳያገኙ ቀርተዋል። በ 1973 ዕሥር ቤት ሳሉ የፓርቲያቸው ዛኑ ፕሬዘዳንት ሆነው ተመረጡ። ከዕሥር ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሞዛምቢክ በመጓዝ ያኔ ‘ሮዴዢያ’ ትባል ወደነበረችው የአሁኗ ዚምባብዌ የጎሪላ ተዋጊዎች ልከው የትጥቅ ትግልም አካሂደዋል።
ሮዴዢያ ነፃነቷን እንድታገኝ ያደርጉት በነበረው ጥረት ወለም ዘለም የማያውቁ፣ ቆፍጣና ሰው መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከሩት ሮበርት ሙጋቤ፤ በፖለቲካዊ ድርድር ሀሳባቸውን በቅጡ መግለጽ የሚችሉና በተቀናቃኞቻቸውም ዘንድ ይህ ብቃታቸው የሚደነቅላቸው ታላቅ ሰው ነበሩ።
በ95 ዓመታቸው ሕልፈተ ሕይወታቸው የተሠማው፣ ዙምባብዌን ለአራት አስርት ዓመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ በኑዛዛዜያቸው በመሪ ደረጃ፣ በብሔራዊ ሥነሥርዓት እንዳይቀበሩ በመግለጻቸው ምክንያት ቀብራቸው ምን ዓይነት ይዘት ይኖረው ይሆን የሚለው እያነጋገረ ይገኛል።
ቤተ ክርስቲያንንና ሀገሪቱን ለማፈረስ የሚያሴሩ ከጠ/ሚ/ሩ ስር እንደተሰገሰጉ ሊቃነ ጳጳሳት አሳሰቡ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመሸርሸር እና ምዕመናኑን ለመለያየት፤ ብሎም ሀገር ለማፍረስየ ሚያሴሩ ሰዎች ከጠ/ሚኒስትሩ ስር ተሰግስገው እንደሚገኙ የሃይማኖቶች አባቶች ገለጹ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ አስኪጅ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ፣ የምስራቅ ወለጋ፣ የሆድሩ ጉድሩ ወለጋ እና የቄለም ወለጋ ሀገረስብከታ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁእ አቡነ ናትናኤል ሰሞኑን የኦሮሚያ ቤተክህነትን እናቋቁማለን በማለት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጀርባ ፖለቲካዊ አጀንዳ ከመያዙ ባሻገር፣ ከመንግሥት ጋር ግኑኝነት ያላቸው አካላትም በጉዳዩ ላይ እንዳሉበት ከሚታየው እንቅስቃሴ በመነሳት ዕውነታውን አስቀምጠዋል፡፡
በቤተክርስቲያን ዙሪያ ያሉ ችግሮችን እና አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መንግስት እንዲያነጋግራቸው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድረስ በደብዳዴ ቢጠይቁም፤ እስከ ነሀሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ምንም ዓይነት ምላሽ ካለማግኘታቸው ባሻገር ሰሞኑን ጥቂት ግለሰቦች ከቅዱስ ሲኖዶስ ፍቃድ ውጪ ሌላ ጽ/ቤት ለማቋቋም የሚደርጉትን ጥረት መንግስት እንዲያስቆምላቸው ቢማፀኑም፣ ጥሪያቸው ሰሚ ካለማግኘቱ ባሻገር፤ “አደራጅ ኮሚቴ ነን” ያሉት ግለሰቦች ይባስ ብለውበመንግሥታዊ ተቋም አዳራሽ ውስጥ የተመረጡ ሚዲያዎችን በመጥራት የጥፋት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ በዝምታ መታለፉ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እናቋቁማለን በማለት የሚውተረተሩት ግለሰቦች በቋንቋ መስበክ፣ መቀደስና መዘመር እንደተከለከለ አድርገው የሚያነሷቸው ነጥቦች ፈፅሞ ሀሰት መሆናቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በቋንቋው የመናገር ተፅእኖ ተደርጎብናል በሚል ሰበብ የራሳችንን ሀገረ ስብከት እናቋቁማለን ማለት ፈፅሞ ስህተት እንደሆነ ጠቁመው፤ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሲሰጡ የታዩት ሰዎች የቤተክርስቲያን አገልጋይ፣ የመንፈሳዊ ሰው ባህርይ እንደማይታይባቸው ንግግራቸው ይመሰክር ነበርም ብለዋል፡፡
“አዲስ አበባ ፊንፊኔ ነው፤ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነው፤ በኦሮሚያ ደግሞ ቅዳሴው በኦሮምኛ መቀደስ አለበት” የሚሉ ሰዎች የሚመሰርቱት ሀገረ ስብከት ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ ግራ የሚያጋባ ነው ያሉት፤ የአሜሪካና የኢትዮጵያው ሲኖዶሶች ዕርቅን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመረጡት አቡነ ዮሴፍ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጀርባ እነማን አሉ የሚለውን ለማወቅ ንግግራቸውን በጥሞና መስማት በቂነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች መዲና የሆነችው አዲስ አበባን የኦሮሚያ ናት የሚል ሰው ቤተክርስቲንን ለማፍረስ ሲነሳ ዓላማው ምን እንደሆነ ግልጽ ነው ያሉት አባት፤ ቤተክርስቲያናችን በኮሚኒስቱ ዘመን ያልደረሰባት ችግር በዚህ የዴሞክራሲ ዘመን እየደረሰባት ነው ይላሉ፡፡ ”አባቶች በአንድ እጅ አይጨበጨብም እንደሚሉት፣ ዶ/ር ዐቢይ ብቻቸውን ኢትዮጵያን ሊያቀኑ አይችሉም” ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦርቶዶክስ እንድትፀና ለማድረግ ብዙ ቢደክሙም፣ በውስጣቸው ግን ከእርሳቸው ያልሆኑ እንደተሰገሰጉ፣ ለውጡ እንዳይቀጥልና ሽግግሩ ቆሞ እንዳይሄድ የሚያሴሩ በውስጣቸው ሞልተዋል ሲሉም የችግሩን ምንጭ ከግዮን መጽሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል ፡፡
በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ በሰጡት አስተያት “ ከዚህ የቤተክርስቲያን አንድነትውጪ የሚታሰብ ከሆነ ለሃይማኖቴ እሰዋለሁ” ያሉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ እርሳቸው በሚያስተዳድሯቸው ምስራቅ ወለጋ፣ ሆድሩ ጉድሩ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ሦስት ሀገረ ስብከቶች በተወሰነ ደረጃ በኦሮሚኛ ቋንቋ የቅዳሴ አገልግሎት የሚሰጡ አገልጋዮች እጥረት ቢኖርም፣ ሕዝብ እስካሁን ድረስ የተባለው ዓይነት ጥያቄ አቅርቦላቸው እንደማያውቅ ይፋ አድርገዋል፡፡
በሀገረ ስብከታቸው በአማርኛ፣ ኦሮምኛና በግዕዝ ሕዝበ ክርስቲያኑ አገልግሎት ከማግኘቱ ባሻገር በምሥራቅ ወለጋ በመንበረ ጵጵስናው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ራሳቸው በኦሮምኛ በመቀደስና በመስበክ አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩን ያስታወሱት አባት፤ አሁን አደራጅ ኮሚቴን ነን የሚሉት ግለሰቦች የሚያቀርቡት ጥያቄ ፈፅሞ እውነታነት የሌለው መሆኑን ለግዮን መጽሔት ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በቤተክርስቲን ውስጥ ከፍተኛ ሓላፊነት የነበራቸው፣ አሁን ከቤተክርስቲን ውጭ የመንግሥት ባለሥልጣን የሆኑት የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ እና ባልደረቦቻቸው የመጡበት መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ በዝምታ ውስጥ የቆየው መንግሥት በፍጥነት ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበው፤ ምዕመናን ቤተክርስቲያናቸውን እና ሃይማኖታቸውን በያሉበት ሆነው በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡