የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ታሪክ እና የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት ይቋቋምልን ጥያቄን...

የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ታሪክ እና የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት ይቋቋምልን ጥያቄን በጨረፍታ || ተረፈ ወርቁ

1) ታሪካዊ መንደርደሪያ

ጤሶ በንቲ (ዶ/ር) የተባሉ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁር ‘‘Oromo Indigenous Religion and Oromo Christianity: Contradictory or Compatible?’’ በሚል አርእስት እ.ኤ.አ. በ2018 ጀርመን ሀገር በሚገኘው የሐይልድሸም ዩኒቨርሲቲ ባሳተሙት የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳናቸው፤ በወቅቱ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ግዛት ክፍል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ መንፈሳዊ አገልግሎት ጅማሬ ምን ይመስል እንደነበር እንዲህ ገልጸውታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1898 ዓ.ም. ከኤርትራ ወደ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የመጡት መምህሬ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ካህን የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከተረጎመው ከአናሲሞስ ነሲብ/ከአባ ገመችስ ዘንድ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን በሚገባ አጠንተው ነበር፡፡ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን በግላቸው ያጠኑት እኚህ ካህን በወቅቱ የነቀምት ገዢ ከነበሩት ከፊታውራሪ ዲባባ ፊት ለመቅረብ ዕድሉን አግኝተው ነበር፡፡

መምህር ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ከፊታውራሪ ዲባባ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከሐዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በአፋን ኦሮሞ ካነበቡላቸውና መዝሙር ከዘመሩላቸው በኋላ ፊታውራሪ ዲባባ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቃለ-እግዚአብሔርን በመስማታቸው እጅግ ከመደስተቻውም በላይ፤ ‘‘ለካ በአፋን ኦሮሞ ወንጌል መስበክ፣ መቀደስ፣ መዘመር፣ እግዚአብሔርን ማወደስ ይቻል ኖሯል?!’’ በሚል ከፍ ባለ አድናቆትና አግራሞት ተመልተው እኚህን ካህን የቦጂ ቃርቃሮ ማርያም ቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ ሾሟቸው፡፡

መምህሬ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ በወለጋ ጠቅላይ ግዛት በግእዝና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለአካባቢው ሕዝብ ወንጌልን የሰበኩና መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ካህን መሆናቸውን ዶ/ር ጤሶ በንቲ በዚሁ ጥናታዊ ድርሳናቸው ያትታሉ፡፡

ይህን ከመቶ ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ታሪክ መሠረትነት ከሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያናችን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ‘‘የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት ይቋቋምልን!’’ በሚል የተነሳውን ውዝግብ መነሻ አድርጌ፤ ጥቂት ለውይይት መነሻ የሚሆነን ሐሳብ ለመሰንዘር ነው፡፡

በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ግን ለመግቢያ ያህል እንዲሆነኝ ስለአፍ መፍቻ ቋንቋን በተመለከተ አንድ ታሪካዊ ክስተትን በአጭሩ ለማስታወስ እወዳለኹ፡፡

2) እንደ መግቢያ

እ.ኤ.አ. የካቲት 21 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዓለም ‘የአፍ መፍቻ ቋንቋ’ ቀን ነው፡፡ ቀኑ በUNESCO አባል አገራት የቋንቋ እና ባሕል ልዩነቶችን እና ብዝኃ ቋንቋዊነትን ለማበረታታት ይከበራል፡፡ ዕለቱ በተለይም በባንግላዴሽ እ.ኤ.አ. ከ1952 ጀምሮ ‹ኤኩሼ የካቲት› በመባል የሚታወቀው የቋንቋዎች ንቅናቄ ቀንን ዕውቅና ለመስጠት ነው፡፡ ዕለቱ የካቲት 14 (እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 21) ተደርጎ የተመረጠው በባንግላዴሽ (የዛኔዋ ምሥራቅ ፓኪስታን) በዕለቱ እ.ኤ.አ. በ1952 በዳካ ዓመፅ ላይ ሳሉ በጥይት ለተገደሉ ‹የቋንቋ ሰማዕታት› መታሰቢያ እንዲሆን በማለት ነው፡፡

ሰማዕታቱ ሰልፍ የወጡት በወቅቱ ለተመሠረተችው አዲሷ ፓኪስታን የሥራ ቋንቋ ከሆነው ኡርዱ ጎን ለጎን ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ የአፍ ቋንቋ መፍቻቸው ሆኖ እንዲመረጥ ነበር፡፡ ጭፍጨፋው በተፈፀመበት ቦታ ላይ የቆመው መታሰቢያ ሐውልትም የባንግላዴሽ ብሔርተኝነት ትእምርት ሆኖ አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ኢ.ኤም. ሲዮራን የተባለ ትውልደ ሮማኒያዊ ፈረንሳዊ ፈላስፋ፤ “አንድ ሰው በአገሩ አይኖርም፤ በቋንቋው ውስጥ ግን ይኖራል፡፡” ብሏል፡፡ ለዚያም ይመስላል ብሔርተኝነት በዓለም ዙሪያ በአብዛኛው በቋንቋ ላይ መሠረት አድርጎ ሲቀጣጠል የምንመለከተው፡፡

የተለያዩ የጥናት ድርሳናት፤ ሰባት ቢሊዮን የሚደርሰው የዓለማችን ሕዝብ (የተናጋሪዎቻቸው መጠን የተለያየ) ወደ 6,064 የሚደርሱ ቋንቋዎችን በአፍ መፍቻነት እንደሚናገር ይጠቁማሉ፡፡ David Crystal የተባለው እውቁ እንግሊዛዊ የቋንቋ ምሁር “English as a Global Language” (1997) በተባለው መጽሐፋቸው ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣሉ፡፡ ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ወደ 2,000 ገደማ የሚሆኑት ደግሞ የሚነገሩት በዚችው በእኛዋ አህጉር (በአፍሪካ) ሕዝቦች ነው፡፡ ይህም ማለት እንግዲህ፣ በዓለም ላይ ከሚነገሩት ቋንቋዎች ሲሦ ያህሉ የአፍሪካ ቋንቋዎች ናቸው ማለት ነው፡፡

አፍሪካ ውስጥ ከሚነገሩት 2,000 ገደማ ከሚደርሱት ቋንቋዎች መካከል 13 የሚሆኑት እያንዳንዳቸው ከአምስት ሚሊዮን የበለጠ ተናጋሪ አላቸው፡፡ ከእነዚህም ከፍተኛ የተናጋሪ ቁጥር ያላቸው ቋንቋዎች ዐረብኛ፣ ሓውሳ፣ ዩርባ፣ አማርኛ እና ኦሮሚኛ (አፋን ኦሮሞ) ናቸው፡፡ (የእኛዎቹ አማርኛ እና ኦሮሚኛ/አፋን ኦሮሞ በተናጋሪ ብዛት ከአፍሪካ ቋንቋዎች ከመጀመሪያዎቹ ረድፍ መቀመጣቸውን ልብ ይሏል፡፡)

3) አፋን ኦሮሞን በላቲን ፊደላት የመተካት ዘመቻውና ውጤቱ    

ከላይ በመግቢያዬ እንዳነሳሁት የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በአፋን ኦሮሞ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከጀመረች በርካታ ዓመታትን እንዳስቆጠረች የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ‘ይህ አገልግሎት ምን ያህል ተቋማዊ መልክ ነበረው፣ ምን ያህልስ ስኬታማ ነበር?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም ቅሉ አንዳንዶች እንደው በደፈናው ያለ እውቀት እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ጠላትም ባዕድም አልነበረችም፡፡ ይሁንእንጂ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በሀገሪቱ ላይ ያለ ቅጥ የተራገበው ቋንቋን መሠረት ያደረገው የብሔር ፖለቲካ የቤተ ክህነቱን ተቋም ሳይቀር በቋንቋና በብሔር ከመከፋፈል አልፎ ቤተክርስትያኒቱን አሁንም ድረስ ላልሻረው መንፈሳዊና አደስተዳደራዊ ቀውስ እንደዳረጋት በግልጽ ታይቷል፡፡

ከጥንት ጀምሮ አስቀድሞ በሀገረ ኢትዮጵያ ላሉት የሕዝብ ቋንቋዎች ሁሉ በምልአት፣ በጥራትና በብቃት ሲያገለግል የነበረው፤ በተለምዶ ግእዝ ፊደል ተብሎ የሚጠራው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፊደል በ1983 ዓ.ም. በመንግሥት መለዋወጥ ተፈጥሮ በነበረው ክፍተት ጥቂት ግለሰቦች በፖለቲካ ስሜታዊነትና ግልፍተኝነት ወደፊት በቀጣዩ ሕዝቦች አብሮነት ላይ የሚያመጣውን ጣጣ፣ መዘዝና ቀውስ ሳያጤኑ የቀድሞ ያለፈው ፓለቲካዊ ችግር በፈጠረው ቁጣና ትኩሳት ብቻ በመነዳት አፋን ኦሮሞ ግእዙን እንዲተው አድርገዋል።

ከዚሁ ቋንቋን መሠረት ካደረገው ብሔርተኝነት ጋር ተያይዞ ‘አማርኛ-ጠል’ የሆነ የቁቤ ትውልድ መፈጠሩ አፍሪካዊ የሆነ ታሪክና ሥልጣኔ መነሻ ካለው የግእዙ ጥንታዊ ፊደል ይልቅ የአውሮፓውያኑ ቅኝ ገዢዎች ቋንቋ ይሻለናል ያሉ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች ከግእዙ ፊድል ይልቅ ላቲኑን መርጠው በዚሁ በላቲን ቋንቋ መጠቀም ከጀመሩ ሁለት ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህን ታሪካዊ ሥሕተት በተመለከተ መጽሐፈ ቅዳሴ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በተተረጎመበት ወቅት በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተደረገ የምርቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት፣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የኾኑት የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እንዲህ ነበር ያሉት፤

‘‘እንዴት ዓለም ሁሉ የሚያደንቀውና የሚገረምበት ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ሥልጣኔ መሠረትና መነሻ የኾነ ሺህ ዘመናት ያስቆጠረ የራሳችን የግእዝ/የሳባ ፊደል እያለን፣ ከታሪካችን፣ ከማንነታችንም ሆነ ከባህላችን ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የሌለውን የላቲንን/የባእዳንን ቋንቋ መመረጣችሁ ትክክል አይደለም፡፡’’ በማለት ነበር ቅሬታቸውን ሳይሸሽጉ የገለጹት፡፡

በተመሳሳይም ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት፤

“እኛ ኢትዮጵያውያን ጥንታውያን ሰዎች እንደመሆናችን ከሌሎች አገሮች በጣም ቀድመን ፊደል ብንፈጥር ብዙ አያስገርምም፡፡ ስለዚህ ላቲን ራሱ አንዳንድ ፊደሎችን ከኢትዮጵያ ፊደል የተዋሰ ወይም የሰረቀ በመሆኑ ለኦሮሞ ሕዝብ በላቲን ፊደል መጻፍ የሚያኮራ ተግባር  አይደለም፡፡ በርግጥ እነሱ ራሳቸው ከኛ እየቀላወጡ እኛ ለምን በአዉሮጳውያን የላቲን ፊደል እንጽፋለን?!’’ በማለት በአጽንኦት ጠይቀዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያን ፊደል በኮምፒውተር እንዲጻፍ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግእዝን ፊደል ዕውቅና እንዲያገኝ ያደረጉት ኢትዮጵያዊው ዕውቅ ሳይንቲስት ዶ/ር አበራ ሞላ አፋን ኦሮሞን በግእዝ ፊደል መጻፍ ያለውን ዘርፈ ጥቅም ሲያስረዱም፤

  1. አፋን ኦሮሞ የራሱን ግእዝ ኦርጅናል ፊደል እየተጠቀመ ከአማርኛ በተጎዳኘ አቻ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የስራና የኅብረት የጋራ መግባብያ አገራዊ ቋንቋ ቢሆንና በየትምህርት ቤት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጥ ለሕዝቦች ትስስር፣ ለማኅበራዊ መስተጋብርም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ትስስር ወይም ሳይኮሎጅያዊ አንድነት ተወዳዳሪ መተኪያ የሌለው አማራጭ መሆኑንና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ይበልጥ እንዲለመድና እንዲስፋፋ እንዲያብብ ያደርጋል፣
  2. ወጣቶች የትም ቦታ ሄደው ሥራ እንዲያገኙና እንዲሠሩ ያስችላል፣
  3. አፋን ኦሮሞ ተናጋሪውም የሌላውን ቋንቋ ፊደሉን በቀላሉ ተረድቶ በቶሎ መማር ይችላል፡፡ 60 በመቶ የሚሆነው ኦሮምኛ የማይችለው የኢትዮጵያ ሕዝብም በቀላሉ ፊደሉን ተረድቶ በቶሎ አፋን ኦሮሞን መማር ያስችላል፡፡ በማለት ያብራራሉ፡፡

ለማስታወስ ያህልም በኦሮምያ ከ43 ብሔር ብሔረሰቦች አባል የሆኑ ከ11-13 ሚሊዮን በላይ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ያልሆነ ሕዝብ እንደሚገኝ ያጤኗል፡፡ በአጠቃላይ የጋራ የሆነ ቋንቋንና ፊደልን ማበልጸግ በሕዝቡ ውስጥ የእኩልነት፣ የበጎነት፣ ስሜትን፣ የማኅበራዊና የብሔራዊ መግባባትንና የዕርቅ መንፈስን እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡

4) አፋን ኦሮሞ ቋንቋ አገልግሎት በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን

ከሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ‘‘የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት እናቋቁም፣ ቋንቋችን፣ ባህላችንን፣ ታሪካችንን በሚያውቁ ሰዎች እንማር፣ እንገልገል…ወዘተ.’’ በሚል የተነሳው ጥያቄ የውዝግብ ምክንያት ከመኾን ባሻገር ቋንቋን መሠረት ካደረገው ከወቅቱ የሀገራችን የብሔር የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተዳምሮ በሀገራችን ላይ ሌላ አደጋን ደቅኗል፡፡

በመሠረቱ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ የኾኑ የቤተክርስትያናችን አገልጋዮችና ምእመናን ያነሱት ይህ ጥያቄያቸው አዲስ አይደለም፡፡ ምናልባት አዲስ ሊያሰኘው የሚችለው ነገር ቢኖር የቤተክርስትያኒቱን አስተዳዳራዊ መዋቅርና መንፈሳዊ ልእልናን ጥያቄ/ቅርቃር ውስጥ ያስገባ በሚመስል እና ሀገሪቷን ክፉኛ እየናጣት ካለው ቋንቋን መሠረት ካደረገው የብሔር ፖለቲካ መግፍኤነት ጋር ተያያዞ ከፍና ጎላ ብሎ መሰማቱና እንዲሁም ኢ-ቀኖናዊ በሆነ አካሄድ በማስጠንቀቂያ መግለጫ ጭምር መታጀቡ ነው፡፡

የኦሮምያ ቤተክህነት ጽ/ቤት እናቋቁም የሚለው እሳቤ መነሻው፤ ሕዝባችን የራሱን ቋንቋ፣ ባህሉን፣ ታሪኩንና ትውፊቱን በሚያውቁ አገልጋዮችና ካህናት ይማር የሚለው ጉዳይ ቢሆንም አሁን ባለው አካሄድ ግን ጥያቄው መንገዱን ስቶ የቤተክርስትያኒቱን ክብርና መንፈሳዊ ልእልናን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ መሆኑ አደራጅ ኮሚቴው በኦሮምያ ባህል ማእከል በሰጠው መግለጫው/ማስጠንቀቂያው ማለት ይቀላል ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ኾኖ ወጥቷል፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ይህን የቤተክርስትያኒቱን ልጆች ጥያቄ ለመመለስ በተለይ ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ጋር በተያያዘ የሚገባውንም ያህል ነው ባይባልም በተለያዩ ጊዜያት መልስ ለመስጠት የሞከረችበት ጊዜ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ከላይ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የዶ/ር ጤሶ በንቲ የዶክትሬት መመረቂያ የጥናት ድርሳን ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረንና የቤተክርስትያን ታሪክም እንደሚመሰክረው ቤተክርስትያን ለሁሉም በየቋንቋው ሃይማኖትን ማስተማር እንዳለባት ከመንፈስ ቅዱስ በላይ ምስክር አያስፈልግም፡፡ ታላቁ የቤተክርስትያን አባት፣ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው በቤተክርስትያን የልደት ቀን ወይም በበዓለ ኀምሳ ቀን ለሐዋርያት ከተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መካከል አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ ይኼውም ሐዋርያት በተሰጣቸው የቋንቋ ስጦታ በዓለም ሁሉ ዙሪያ ወንጌልን እንዲያስፋፉ አስችሏቸዋል፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንም ከቤተ ክርስትያን የልደት ቀን/ከበዓለ ኀምሳ ጀምራ ወንጌልን ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ወንጌልን በቋንቋቸው ለማዳረስ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚመሰክሩት በሀገራችን በተለይም ደግሞ ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ጋር ተያይዞ በቂ ነው ባይባልም በተለያዩ ጊዜያት አንዳንድ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ አሁንም እየተሠሩ ነው፡፡ ለአብነትም ያህል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ልሞክር፤

  1. በ1845 ከዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌላት በከፊል በአፋን ኦሮሞ እንዲተረጎመው ሆኗል፣
  2. ከ140 ዓመታት በፊትም በኦሮሞው ሊቅ በአናሲሞስ ነሲብ (አባ ገመችስ) ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ ተተርጉሟል፣
  3. አናሲሞስ ነሲብ አስቴር ገኖ ከተባለች አንዲት የኦሮሞ ሴት ጋር ሆኖ በአፋን ኦሮሞ መዝገበ-ቃላትን ለመጻፈና በርካታ መዝሙራትንና ምሳሌያዊ አባባሎችን ለመሰብሰብ ችለዋል፣
  4. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ግእዝና አማርኛ ቋንቋዎች የታተሙ የትምህርተ ሃይማኖት እና የጸሎት መጻሕፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ አስተርጕሟል፤ ከእነዚህ መካከል የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ እና ሰይፈ ሥላሴ ተጠቃሾች ናቸው፣
  5. Dhangaa Lubbuu (ዳንጋ ሉቡ) የተሰኘችውን መጽሔት ለዅሉም ክርስቲያን በሚመጥን ዐምድ በየሦስት ወሩ በማዘጋጀት እያሠራጨ ይገኛል፣ በግቢ ጉባኤያት የምረቃ መጽሔት ላይ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ ጽሑፎችና መልእክቶችን በአፋን ኦሮሞ እያቀረበ ነው፡፡ በአፋን ኦሮሞ የመዝሙር አልበሞችን አሠራጭቷል፤ ኦርቶዶክሳዊ የመዝሙር ጥራዝም አሳትሟል፣
  6. በተጠኑ የክልሉ ቦታዎች አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት አፋን ኦሮሞ የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናትን እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌልን አስተምሮ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማሠማራት ላይ ሲኾን ለዚሁም በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የቂልጡ ካራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር ያለውን የአበልቲ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንደ ማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

‘‘በቋንቋችን አስተምሩን፣ በቋንቋችን እንገልገል’’ የሚለውን የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ በመፍታት ረገድም ቤተክርስትያናችን ባለፉት አሥርት ዓመታት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ ጳጳሳትን ከመሾም ጀምሮ በአፋን ኦሮሞ የሚስተምሩ ካህናትናና መምህራንን በማሠልጠን ረገድ በቂ ነው ባይባልም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፣ አሁንም እየተሠሩም ነው፡፡ እነዚህ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎችም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችም በቋንቋቸው ወንጌልን እንዲማሩና እንዲገልገሉ በማድረግ፣ አገልገሎቱን ማስፋፋት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ኩላዊት/ዓለም አቀፋዊት ተቋም እንደመሆኗ መጠንም ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ለሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ወንጌልን በቋንቋቸው ለማዳረስና ሐዋርያዊና ዓለም አቀፋዊ ተልእኮዋን ለመወጣት የሚስችላትን ስራቴጂ ነድፋ መንቀሳቀስ እንዳለባት ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተማሩና ዘመኑን በሚገባ የዋጁ መንፈሳዊ አገልጋዮችና መንፈሳዊ መሪዎችንና አባቶችን ማበራከት ያስፈልጋል፡፡

ቤተክርስቲያን ለሁሉም በየቋንቋው ሃይማኖትን ማስተማር እንዳለባት መቼም ከመንፈስ ቅዱስ በላይ ምስክር አያስፈልግም፡፡ ስለሆነም በጎጠኝንትና በጠባብነት ምክንያት አንዱ ቋንቋ ከሌላው የሚበልጥ አስመስለው የሚናገሩ አላዋቂዎች ከመንፈስ ቅዱስ ተምረው ለሁሉም በየቋንቋው የእግዚአብሔርን ቃል ማቅረብን ሊደግፉ፣ ሊያበረታቱ ይገባል፡፡

ለቅዱሳን ሐዋርያት የየሀገሩ ሁሉ ቋንቋ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መገለጡ የተለያዩ ሕዝብ በሚናገሩበት ቋንቋ በመጠቀም ትምህርተ ወንጌልን፣ ሕገ ቤተክርስቲያንን ማስተማር የቤተክርስቲያን መምህራን መንፈሳዊ ግዴታ (ኃላፊነት) መሆኑን ያሳስበናል፡፡ ቋንቋ የሌለው ሕዝብ የለምና የየሀገሩን ቋንቋ ለሕዝብ ማስተማር በግንባር ቀደምትነት የመንግሥትና የማኅበረሱ እንጂ የቤተክርስቲያን ኃላፊነት ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡

ከዚህ እውነታ ባሻገር ግን እነዚህ ዐውቀው የተኙ ሰዎች ‘‘በቋንቋችሁ ፈጣሪያችሁን አታምልኩ ተባልን! ፈጣሪ ኦሮሚፋ አይሰማም ወይ?!’’ ወዘተ በማለት ያልተጻፈ የሚያነቡት ያልተባለ የሚተርኩት እውነት ጠፍቷቸው ሳይሆን ሌላ መሰሪ የፖለቲካ አጀንዳ ስላለላቸው ነው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ሲኖዶሳዊ መዋቅር በጎሳ ሸንሽነን በክልል እናቧድናታለን የሚለው አካሄድ ግን አንድም የቤተክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አሠራር የመናድ ሙከራ በሌላ በኩልም ሀገሪቱን ሰላም የማደፍረስ እኩይ ተልእኮ አካል ነው ሊሆን የሚችለው፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ‘‘ክልላዊት/ጎሳዊ’’ አይደለችም! ኦርቶዶክስ መሠረቷ ከምድር እስከ ሰማይ የሚዘልቅ በሁሉ ያለች፣ ሁሉን በፍቅር የምታቅፍ ዘላለማዊ፣ አንዲትና ቅድስት ተቋም ናት፡፡ ሐዋርያዊና ዓለም አቀፋዊ በኾነ የወንጌል አገልግሎቷም፤ ‘ሰው የመሆን የመለኮታዊ ባሕርይን የመካፈል ክብርን ከፍ በማድረግ፣ ከቤተልሔም ግርግም እስከ ቀራኒዮ አደባባይ በተከፈለ ክቡር የፍቅር መሥዋዕትነት ‘ሰው አምላክ፣ አምላክ ሰው የሆነበትን’ ዘላለማዊ እና ሕያው ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ አንዳች ልዩነት የጌታችንን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በቃልም በተግባርም የምታስተምር፣ ለማስተማር የምትተጋ ናት፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከዚሁ ሐዋርያዊና ዓለም አቀፋዊ ተልእኮዋና አገልግሎቷ ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ጃማይካና ካረቢያ ምድር ድረስ፤ ‘ሰው የመሆን ታላቅ ክብር ትእምርት/Symbol፣ ለሰው ልጆች ከፈጣሪ የተቸረ ነጻነትና ሰብአዊ ክብር/Freedom and Human Dignity ልዩ መገለጫ የሆነች ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ኩላዊት/ዓለምአቀፋዊት የሃይማኖት ተቋም ናት፡፡ ታሪክ እንደሚመሰክረው ለዚህም ነው በቅኝ ግዛት ሥር ይማቅቁ የነበሩ በአኅጉራችን በአፍሪካ ከሚኖሩ በርካታ ጥቁር ሕዝቦች ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ የሚኖሩ በሚሊዪን የሚቆጠሩ ጥቁር ሕዝቦች- የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንን የነጻነታቸው ተስፋ ቀንዲል፣ ሰው የመኾናቸው ክብርና ልእልና መገለጫና ሕያው፣ ጽኑ መሠረት ማድረጋቸው!!

ሰላም!!

LEAVE A REPLY