ሙስጠፌ ሞሐመድ በቀጣይ ዓመትም ለለውጡ እንደሚሠሩ አረጋገጡ
በሶማሌ ክልል የተጀመሩ የህግ የበላይነት ማስከበርና የልማት ስራዎች በአዲሱ ዓመትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህዝቡ ባገኘው ነፃነት እንዲጠቀም በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ሙስጠፌ ሞሐመድ ገለጹ::
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የዘመን መለወጫን ምክንያት ባስተላለፋት መልዕክት እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና የዜጎች አለመረጋጋት የተከሰተበት እንደነበር አስታውሰውችግሩ በመንግስትና ህዝብጥረት በፍጥነት መቅረፍ መቻሉን አስታውሰዋል::
“ዓመቱ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት የተቻለበት ዓመት ነበር ፤በዚህም ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛሉ፤ የህግ የበላይነት የበለጠ የሚጠናክሮበት ዓመት ይሆናል ብለን እንጠብቃልን” ያሉት ሙስጠፌ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በጅግጅጋ የነበረው ችግር ተወግዶ አሁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በፍቅር የሚኖርበት ከተማ መሆኗ በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል::
አዲሱ ዓመት የህብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የተያዙ እቅዶች የምንተገበርበትና ህዝቡ ያገኘውን ነፃነት የበለጠ የሚጠቀሚበት እንደሚሆን የተናገሩት ለውጡን በትክክል የተገበሩት የክልሉ ፕሬዝዳንትየክልሉ መንግስት ሰላምና አንድነት እንዲጠናክር እንደሚሰራ አመልክተው ህዝቡም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል
መስከረም 4 በመላ ሀገሪቱ የተጠራውን ሠልፍ የኦሮሚያ ፖሊስ አልቀበልም አለ
ፖለቲካዊ ይዘትን ተላብሶ በጽንፈኛ ብሔርተኞች እየተቀነቀነ ያለው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት የማቋቋም ጥያቄን የተመለከቱ ተቃውሞዎችና አመጾች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረበት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መስከረም 4 ቀን የተጠራው ሰልፍ ዕውቅና የለውም ብሏል::
ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ ሰልፉን የጠሩት አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጉዳዮን አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ ፤ ምዕመኑ ለሰልፍ የተጠራው አወዛጋቢ ከሆነው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት የማቋቋም ጥያቄ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው መግለጻቸው አይዘነጋም::
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰባት ያለውን ጥቃት ለማውገዝ የተጠራውን የሕዝበ ክርስቲያኑን አቤቱታ ለማገድ የቆረጠ የሚመስለው የኦሮሚያ ፖሊስ ፤ እሁድ መስከረም 4 ቀን በመላ አገሪቱ የተጠራው ሰልፍ በክልልሉ ምንም ዓይነት ዕውቅና የለውም ብሏል::
ቀሲስ በላይና ግብረ አበሮቻቸው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚንድ ተግባር ሲፈጽሙ አንዳችም ተቃውሞ ያላሰማውና በአንጻሩ አበጣባጩን ግለሰብ በፖሊስ ሲያስጠብቅ የሰነበተው ኮሚሽኑ የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ ለማፈን የቆረጠ መስሏል::
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ከፍያለው ተፈራ በሰጡት መግለጫ መሠረት፥ በኦሮሚያ ክልል የተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሌለ እና የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መስከረም 04 ቀን 2012 ዓ.ም በመላው አገሪቷ እንዲካሄድ የጠራችው ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል እንዲካሄድ አልተፈቀደም ብለዋል::
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከ18 ማዕከላት ለተውጣጡ ሕጻናት ስጦታ አበረከቱ
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የዘመን መለወጫን በዓል በማሳደጊያዎች ሕይወትን ከሚገፉ ሕጻናት ጋር አሳለፉ:: የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ባለቤት በዓሉን ያከበሩት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የህፃናት ማሳደጊያ ከተውጣጡ 650 ታዳጊዎች ጋር ነው።
ዛሬ አንድ ብለን የጀመርነውን 2012 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተዘጋጀው ክብረ በዓል ላይ የቁርስ እና የምሳ ግብዣ ለህፃናቱ ተደርጓል። ከ18 ማዕከላት የተውጣጡት ህፃናቱም የተለያዩ ትእይንቶችን አቅርበዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በበኩላቸው አዲሱን በዓል ምክንያት በማድረግ የአልባሳት እና ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለህፃናቱ አበርክተዋል።
የኢዮሓ ዝርክርክነት፣ የሕዝብ ብስጭት በታየበት ምሽት የሶል ንግሥቷ ደመቀች
2012 ዓ.ም መቀበያን በአዲስ አበባ ከተማ ከተዘጋጁ በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶች መሀል በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው “ጨዋ” የተሰኘው በሸራተን አዲስ ሆቴል የተዘጋጀው ታላቅ ኮንሰርት በበርካታ ስህተቶች ታጅቦ ቢካሄድም የሶል ንግሥቷ አስቴር አወቀ ደምቃ አምሽታለች።
ኮንሰርቱን ያዘጋጀውና “ጨዋ” የተሰኘውን አልበም ለገበያ ያቀረበው ኢዮሓ ኢንቴርቴይመንት ከባዱን ኮንሰርት ለማዘጋጀት ከብዶት በታየበት የጳጉሜ ስድስት (የትናንቱ) ምሽት በታዳሚው ክፉኛ ሲወገዝና ሲሰደብ አምሽቷል።
ካለፋት ሦስት ዓመታት ወዲህ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተለያዮ የአውድ ዓመት ባዛሮችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ኢዮሓ የኢኮኖሚ አቅሙን በመተማመን ብቻ እንደገባ የሚያሣብቁ ስህተቶችን በኮንሰርቱ ላይ ፈጽሟል:: ከአንድ ሳምንት በፊት ዝግጅቱን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት አዘጋጆች አንዳችም ክፍተት እንደማይፈጠርና ሕዝቡንም ላለማጉላላት ኮንሰርቱ በተባለው ሰዓት እንደሚጀመር ገልጸው ነበር::
ይህንን ተከትሎ የሚኖረውን ግፊያና የቦታ ጥበት ግምት ውስጥ በመክተት ከቀኑ አስረ አንድ ሰዓት ጀምሮ የተሰለፈው ታዳሚ ደጅ ላይ ከፍተኛ መጉላላት የደረሰበት ከመሆኑ ባሻገር ወስጥ ከገባም በኋላ የኮንሰርቱን መጀመር ለሰዓታት ለመጠበቅ ተገዷል::
ራሔልና ወንዲማክን በተጨማሪ አድማቂነት የያዘው ጨዋ ኮንሰርት የሳውንድ መቋረጥ እና የመብራት መጥፋት የተስተዋለው ከጅምሩ ነው:: በተለይም በጉጉት የምትጠበቀው አስቴር አወቀ ወደ መድረክ ወጥታ እየዘፈነች ለሁለተኛ ጊዜ የተቋረጠው የመብራት መጥፋት ለ48 ደቂቃዎች በመዝለቁ ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲበሳጭ ምክንያት ሆኗል::
መድረክ ላይ ከወጣችበት ቅፅበት አንስቶ ከአድናቂዎቿ ጋር የነበራት ቁርኝት እጅግ መሳጭ የነበረው አስቴር አወቀ እየዘፈነች ሳውንድ ሲስተሙ ሲቋረጥ ያላንዳች መደናገጥ ለሰባት ደቂቃዎች በማራኪ አደናነስ አድናቂዎቿን ለማዝናናትና ለማረጋጋት የሞከረችበት መንገድ ምስጋና አሰጥቷታል::
ኢዮሓና ሸራተን ያዘጋጁት ጀነሬተር ግዙፋን ሳውንድ ሲስተም ሊያንቀሳቅስ አለመቻሉ በግልጽ መታየቱ መብራት ከመጣም በኋላ የመድረክ ቅንጅቱ የተዝረከረከ መሆኑ አዘጋጆቹ ጥቅማቸውን ለማስከበር እንጂ የአስቴርን ክብር ለመጠበቅ እንዳልተጨነቁ አሳይቷል::
አሠልቺ በሆነ መልኩ ለረዥም ደቂቃዎች ኮንሰርቱ መቋረጡን ተከትሎ ተመልካቹ “ኢዮሓ ሌባ” በማለት ተቃውሞውን የገለጸ ሲሆን ከሠላሳ ደቂቃ በላይ የጠበቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚያን በብስጭት ግቢውን ለቀው ሲወጡ ተመልክተናል::
በድጋሚ ወደ መድረክ የወጣችው ተወዳጇ አስቴር አወቀ በትዕግስት የጠበቃትን ሕዝብ አመስግና በሁለት ዙር ሃያ ዘፈኖችን በሚገርም ብቃት በማቅረብ እያደር የሚጣፍጥ ወይን መሆኗን በተግባር አስመስክራለች:: የሶል ንግሥቷ ደምቃ በታየችበት ምሽት በተለምዶ የተመስገን ልጆች ተብለው የሚጠሩት የተወዛዋዥ ቡድን አባላትም በውዝዋዜ አጅበዋታል::
አዘጋጁ ኢዮሓ ከሸራተን ጋር በመተባበር እራት እንደሚያበላ በመግለጽ ከ800 ብር እስከ 4000 ብር ቢያስከፍልም በተለይ ከቪ አይ ፒ ውጭ የነበሩ ከአስር ሺህ በላይ የሚሆኑ ታደሚዎች በየመንደሩ ምግብ ቤቶች የሚገኙ ምስርና ሽሮ ወጥ በቀይና በአልጫ ማቅረቡ ሌላኛው ሕዝብን ያበሳጨ ድርጊት ነበር:: ቀኑ የጾም ዕለት ቢሆንም የተዘጋጀው ምግብ በጥራት ረገድ ሲታይ እውነት ምግቡን ያዘጋጀው ሸራተን ነው? የሚል ጥያቄን አጭሯል::
እያንዳንዱ ታዳሚ ከእራት ባሻገር ሦስት ቢራ በዋልያ ስፖንሰርነት ቢሠጥም በተለይ ትኬቱን በባንክ ቤት በኩል የቆረጡ በርካታ ሰዎች የምግብና የመጠጥ ኩፖኑን ባለማግኘታቸው በዕድሉ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል:: አዘጋጅ ክፍሎቹ ፍፁም ባልተቀናጀ ሁኔታ በመሥራታቸው በርካታ ስህተቶች እንደተፈጠሩ ተረድተው ለሰዓታት ከመድረኩ አካባቢ ሲሰወሩም ታዝበናል::
የባላደራው ም/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫውን ከእሁዱ ሠላማዊ ሰልፍ በኋላ አደረገ
በአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው የባላደራው ም/ቤት (ባልደራስ) ነገ ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረዙን አሳወቀ::
ም/ቤቱ እሁድ መስከረም 4 ቀን የተጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ ግን ለአገር ውስጥና ለውጭ ሚዲያዎች በጉዳዮ ላይ ሰፊ መግለጫ እንደሚሰጥ ከወዲሁ ጠቁሟል::
በጋዜጠኛና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ የሚመራው የባላደራው ም/ቤት በቅርቡ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን አቋቁማለሁ ስለሚሉት ቀሲስ በላይ ጉዳይ እንዲሁም አደራጅ ኮሚቴው ሥልጣን ላይ ካለው ኦዴፓ ጋር ስላለው ጥልቅ ግንኙነትና ስለተጠራው ሠልፍ መግለጫ ለመስጠት አቅዶ ነበረ::
ይሁንና የመስከረም አራቱ ሰልፍ በቀጥታ ግንኙነቱ ከቤተክርስቲያን ጥቃት ጋር የተገናኘ በመሆኑ የሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ በሰልፉ ወቅት ምዕመናኑን ስሜታዊ እንዳያደርግ በመስጋት መግለጫው መሰረዙን ከቅርብ ምንጮቻችን ተረድተናል::
የታከለ ኡማ አስተዳደር የእሁዱን ሰልፍ እንዳይካሄድ የተለያዮ ሥራዎችን ውስጥ ለውስጥ እያካሄደ እንደሚገኝ የደረሰበት ባላደራው ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማፈን የሚደረገውን እንቅስቃሴም እሰከ መጨረሻው ተረድቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት የአካሄድ አቅጣጫውን ለመቀየር ተገዷል::