አብዱልፈታ አልሲሴ ኢትዮጵያ ግድቡን የጀመረችው ባልተረጋጋንበት ወቅት ነው ሲሉ ከሰሱ
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ መሙላት ሂደትን በተመለከተ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ምንም ውጤት አላመጣም ሲሉ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹህሪ ተናገሩ። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካይሮ ውስጥ ከኬኒያዋ አቻቸው ሞኒካ ጁማ ጋር አንድ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ይህንን ያሉት።
ሀገራቸው ከአባይ የምታገኘውን የውሃ ድርሻን በከፍተኛ ደረጃ እስካልቀነሰው ድረስ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ያላትን መብት ግብጽ እውቅና ትሰጣለች ብለዋል ሚኒስትሩ። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግዙፍ ግድብ 6 ሺህ ሜጋዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ መጀመሩን ተከትሎግብጽም ከወንዙ የማገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል የግድቡን ግንባታ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየተከታተለች ትገኛለች።
የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሱዳንና ግብጽ የሚሳተፉበት የሦስትዮሽ ውይይት በግድቡ ዙሪያ ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም።
ከሁለት ቀን በፊት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት የጀመረችው ሃገራቸው እ.አ.አ. በ2011 የገባችበትን ቀውስ ተከትሎ መሆኑን ‘አህራም ኦንላየን’ ከተባለው የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ መግለጻቸው በሁለቱ ሀገራት መሀል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የይምሰል እንደሆነ አመላካች ነው።
”ግብጽ በዛ ወቅት አለመረጋጋት ውስጥ ባትሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት አትጀምርም ነበር” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ”ከ2011 ግርግር ግብጻውያን ብዙ መማር ያለባቸው ነገሮች አሉ። ይህንን ትልቅ ሃገራዊ ስህተት ልንደግመው አይገባም” ሲሉም የአገራቸውን ሕዝብ ለአመጽ የሚያነሳሳ ንግግር አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብጽ የተከሰተውን ህዝባዊ አብዮት ተከትላ ግድቡን መገንባት፣ ይፋዊ የግድብ ግንባታው መጀመር ምርቃት የተደረገው እ.ኤ.አ 2011 ላይ ቢሆንም ግንባታው የተጀመረው የፈረንጆቹ 2010 ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሆነ በመግለጽ የግብጽን ወቀሳ አጣጥለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግብጽ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስትሮች የሚያድርጉት ውይይት ትናንት በካይሮ ተጀምሯል። ውይይቱ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ከነበረው ስብሰባ የቀጠለ ነው።
የካይሮው ውይይት ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው ሀገራቱ በቀሪ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በባለሙያዎች የቀረበለትን ሪፖርት እና ምክረ-ሃሳቦች መርምሮ የወደፊት መመሪያዎችን ለማበጀት ሲሆን፣ ሀገራቸውን ወክለው በውይይቱ የተገኙት የግብጹ የውሃ ሚኒስትር ዶክተር ሞሐመድ አብድል አቲ ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየታየ ያለው የትብብር መንፈስ ለሌሎች ሀገራትም አርአያ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ታከለ ኡማ እሬቻን በአዲስ አበባ ለማክበር አስፈላጊውን መሰናዶ አጠናቅቂያለሁ አሉ
ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ለማክበር የታቀደው የእሬቻ በዓል ከተለያየ አቅጣጫ በርካታ ትችቶችና ድጋፎችን እያስተናገደ ነው።
በርካቶች በዓሉ በዋና ከተማዋ መከበሩ ያልተለመደና ያልነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሐሐድ መንግሥት ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመ መሆኑን ይናገራሉ። በአንፃሩ የኦሮሞ ሕዝብ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንኳን በሸገር በሌሎች የክልል ከተሞችም በድምቀት ቢከበር በማለት ሀሳቡን የሚጋሩም አሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ የመጠቅለል የኦዴፓን ፍላጎት ያለ መታከት ደፋ ቀና እያሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ መስከረም 24 ቀን በአዲስ አበባ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው ከወዲሁ ከአባገዳዎች፣ ቄሮዎችና ከፎሌ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት ጀምረዋል።
አሁን ላይ በዓሉን አስመልክቶ እየተደረጉ ባሉ ቅድመ ዝግጅቶች ዙሪያ ውይይቶች እየተደረጉ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩም የኢሬቻ በዓል ከምንጊዜውም በላይ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስረድተዋል።
የክብረ በዓሉ ጉዳይ በአዲስ አበባ እንዲከናወን ሓላፊነት የተሰጣቸው አባገዳዎች በበኩላቸው በዓሉ ደማቅ እና ስኬታማ ሆኖ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የኢሬቻ በዓል የፊታችን መስከረም 24 ቀን በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑን የገለጸው የከንቲባው ጽ/ቤት አስፈላጊውን መሰናዶ እያጠናቀቅኩ ነው ብሏል።
ብሪታኒያ በአቪየሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ልትሠራ ነው
ታላቋ ብሪታኒያ በአቪየሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የመስራት ፍላጎት አለኝ ብላለች:: የብሪታኒያ የአፍሪካ የንግድ ኮሚሽነር ኢማ ዌድ ስሚዝ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸውን ተከትሎ ነው ጉዳዮን ግልፅ ያደረጉት።
ኮሚሽነሯ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የሃገሪቱን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ በጎበኙበት ወቅትበሰጡት መግለጫ ሃገራቸው ብሪታኒያ በአቪየሽን ዘርፍ ሰፊ ልምድና መልካም ስም ካለው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል። በተጨማሪም አየር መንገዱ በሚያከናውናቸው የማስፋፊያና የአስተዳደር ዘርፍ ላይ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳለም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ብሪታኒያ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ያነሱት ኮሚሽነሯ፥ ብሪታንያ የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆና ለዘመናት መዝለቋን አስታውሰው አሁን ላይ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን እናብሪታንያም በኢትዮጵያ ከአቪየሽኑ በተጨማሪ በግብርና ማቀነባበሪያ እና በታዳሽ ሃይል ልማት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ይፋ አድርገዋል።
የብሪታንያ ባለሃብቶችም በሃገሪቱ ያሉ የኢኮኖሚ አማራጮችን እየተመለከቱ መሆኑንእና በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ነዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት ኮሚሽነሯ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር በሀይል ልማት ዘርፍ ለብሪታኒያ ኩባንያዎች ስለሚኖረው አማራጭ የሥራ ጉዳይ ጥልቅ ውይይት አካሂደዋል።
አንጋፋው የጎንደር ዮንቨርስቲ የግዕዝ ቋንቋን ለመታደግ በዲግሪ ሊያስተምር ነው
በአማራ ክልል የሚገኘው አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግዕዝ ቋንቋን ለመታደግ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ እንደሚሠጥ ይፋ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ኢትዮጵያ የግዕዝ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ለቋንቋው ማደግና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነና፤ በዚህ ሳቢያም ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብራና መጽሃፍትን ለጥናትና ምርምር ስራ ማዋል ዕንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል። በርካታ ዘመን ያስቆጠሩናበቋንቋው የተጻፉ ለዘመናዊ ህክምና ሙያ የሚያግዙ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መጽሃፍቶች በኃይማኖት ተቋማትና ገዳማት ተገድበው መቀመጣቸውንም አስታውሰዋል።
ዕድሜ ጠገቡ ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጽሃፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግዕዝ ቋንቋን ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ያመላከቱት ሓላፊ፤ በትምህርት ዘመኑ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፥ ትምህርቱ በማታውና በክረምት መርሃ ግብሮች እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
መንግሥት ለቤተክርስቲያን መብት መከበር ቸልተኛ መሆኑን የደሴና የጎንደር ምዕመናን ገለጹ
ደሴ፣ ጎንደር እና ደብረ ታቦር ከተሞች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች ዋነኞቹ ሲሆኑ የሰልፉ ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያኗ፣ በሃይማኖት አባቶች እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ይቁም ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል::
ትናንት በደሴ ከተማ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ አሰፋ ሰልፉ መነሻውን ከደሴ ፒያሳ በማድረግ ከሁሉም አጥቢያ ቤተክርስቲያን የተወጣጡ ምዕመናን የተለያዩ መፈክሮች እያሰሙ ወደ ደሴ መስቀል አደባባይ ጉዞ ማድረጋቸውን ጠቁመው ”በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቤተ-ክርስቲያን ያቀጠሉ እና ምዕመናንን የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ፣ መንግሥት ቤተ-ክርስቲያንን ሊያከብር ይገባል” የሚል ይዘት ያላቸው ተጓዳኝ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ይናገራሉ::
የሃይማኖት መቻቻልና የዜጎች ፍቅር ተምሳሌት የሆነው የደሴ ምዕመን ሰላማዊ ሰልፍ ጠዋት 12 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን እስከ ቀትር 6 ሰአት ድረስም ዘልቋል:: በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በግምት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ከ150 ሺ እስከ 200 ሺ የሚደርሱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እንደተሳተፉና ታላቁ ቤተክርስቲያንን የመታደግ ሰልፍምያለምንም የጸጥታ ችግር መጠናቀቁን ለቢቢሲ ገልፀዋል::
በሃገር አቀፍ ደረጃ በእምነቱ ተከታዮች ላይ እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከሚፈጸመው በደል ባለፈ በከተማችንም ብዙ ጥያቄዎች አሉን የሚሉት የደሴ ነዋሪ ” በከተማዋህጋዊ የሆነ ካርታና ሌሎች እንደ ግንባታ ፍቃድን የመሳሰሉ ሰነዶች ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ግንባታቸው ተከልክሏል። ህጋዊ እስከሆንን ድረስ መከልከል የለብንም። መንግስትም አፋጣኝ ምላሽና የህግ ከለላ ያድርግላቸው” የሚሉ መፈክሮች በምዕመናኑ መስተጋባታቸውን አመላክተውምዕመኑ ጥያቄውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ስላቀረበ መንግስት ቢቻል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቁን አብራርተዋል::
በተመሳሳይ ትናንት ከፍተኛ ንቅናቄ የተስተዋለባት የደብረታቦር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ አባተ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ከጨረሱ በኋላ ምዕመኑ ከየአቅጣጫው ወደ መስቀል አደባባይ ማምራቱን ገልጸው ” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሃገሪቱ ያበረከተችውን ከግምት ውስጥ በማስገባትና አስተዋጾዎችዋ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ በቤተክርስቲያኗ እና በእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መንገስት በአስቸኳይ ያስቁም” የሚል መልዕክት በአስተባባሪ ኮሚቴው በኩል መቅረቡን አስታውቀዋል::
የጎንደር ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ሕብረት ጸሐፊና የሰልፉ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ አያሌው በጎንደር ስለተከናወነው ሰልፍ ለቢቢሲ ሲናገሩ “ቤተክርስቲያንን ማቀጠል ኢትዮጵያን ማቃጠል ነው፣ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ በአስቸኳይ ይቁም፣ መንግሥት የቤተክርስቲያንን ደህንነት ማረጋገጥ አለበት፣ የተቃጠሉ አብያተ-ቤተክርስቲያናትን መልሶ መገንባት ይኖርበታል። ለተጎዱም ካሳ መክፈል አለበት” የሚሉ መፈክሮች መስተጋባታቸውንና በጎንደር በተካሄደው ሰልፍ ላይ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ምዕመናን ተሳታፊ እንደነበር አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ሳዑዲ በሠራተኛ ቅጥር ዙሪያ ተወያዮ
ኢትዮጵያውያን ሕይወትን ለማሸነፍ ስደትን ከሚመርጡባቸው ሀገራት መሀል አንዷ ከሆነችው ሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላሂ ጋር የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ መወያየታቸው ታወቀ:: ሚኒስትሯ ከአምባሳደሩ ጋር በሁለትዮሽና ለስራ ወደ ሳዑዲ በሚሄዱ ሰራተኞች ዙሪያ የደረሷቸውን ስምምነቶች ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል::
አምባሳደሩ ተቋርጦ የነበረው የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት ዳግም እንዲጀመር ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን አምባሳደር ሳሚ ጀሚል በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ህገ ወጥ የሥራ ስምሪትን በመከላከል ህጋዊ የሥራ ስምሪት እንዲኖር ያደረገውን ጥረትም አበረታተው ሃገራቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች በሳዑዲ ህጋዊ ሆነውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሃገራቱ ለሥራ ወደ ሳዑዲ በሚሄዱ ዜጎች አጠቃላይ ሁኔታ በጋራ ለመሥራትና መረጃ ለመለዋወጥ መስማማታቸውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከወዲሁ አረጋግጧል።
በመሬት መንሸራተት አደጋ ሦስት ሰዎች በሰሜን ጎንደር ሞቱ
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይዎት እና በንብረት ላይ ከባድ አደጋ መድረሱ ታወቀ።
በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ ወይና ቀበሌ ትናንት ረፋድ ላይ በደረሰው አደጋ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አሁን ላይ የወጡ መረጃዎች ያረጋገጡ ሲሆን የአደጋው መጠን ሊጨምር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በአደጋው ግምቱ በውል ያልታወቀ ንብረት እንደወደመና የመሬት መንሸራተት አደጋው ዝናብ ባልጣለበት ሁኔታ መከሰቱን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን አረጋግጧል።