ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋን በተመለከተ አዲስ ፖሊሲና አዋጅ አወጣች
በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋን ለማጠናከር፣ በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደምርት ለመግባት የሚያስችል የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ መዘጋጀቱታወቀ።
የነዳጅ ፖሊሲና አዋጅ ረቂቆች ላይ የመከረ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ሲካሄድ፤ በተለይ የፖሊሲው መውጣት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ከማጠናከር ባለፈ የአገሪቱን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደምርት ለማስገባት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው በሚኒስቴሩ የነዳጅ ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ ገልጸዋል።
የነዳጅ አልሚዎች ተሳትፎን ውጤታማ ማድረግ፣ በዘርፉ ልማት ዙሪያ በፌደራልና ክልል መንግስታት መካከል የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ከፖሊሲው ዓለማዎች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳል። ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥና የቀጣናውን የገበያ ዕድል በመዳሰስ የተሻለ የገበያ አማራጭ መፈለግና ተወዳዳሪ የሆነ የገበያ ስርዓት መዘርጋትም እንዲሁ ሌሎቹ ዓላማዎች እንደሆኑም ታውቋል።
ለነዳጅ ፍለጋ አመቺ ናቸው የተባሉ አካባቢዎች፣ ፍለጋው የሚካሄድበት መንገድ፣ በፍለጋው ህዝቡንና አካባቢውን በማይጎዳ መልኩ የአገርን ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም በፖሊሲው ጥናት ከመቃኘታቸው ባሻገር፤ ፖሊሲው ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ ስልጠና የሚወስዱበትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ የሚቻልበት አቅጣጫዎችን ያማከለ መሆኑም በውይይቱ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የተረቀቀው የነዳጅ ሥራዎች አዋጅ ደግሞ በ1978 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ የሚተካ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ቀፀላ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ለረጅም ጊዜ የቆየ ከመሆኑ ጋር የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስተናግድ ባለመሆኑ መሻሻሉ ተገቢነት አለው ይላሉ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም በበኩላቸው፤ አገሪቷ በዘርፉ ፖሊሲ አልነበረታም ሲሉ ጠቅሰው በዚህም የተነሳ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን በሚጠበቀው መጠን መሳብ አለመቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በነዳጅ ፍለጋ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙት ኩባንያዎች ከአምስት አይበልጡም። በመሆኑም በመስኩ ፖሊሲና የነዳጅ ሥራዎች ረቂቅ መዘጋጀቱ እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ክልል ነዳጅ መገኘቱን ያረጋገጠው የማዕድንና የነዳጅ ሚኒስቴርበክልሉ በኦጋዴን አካባቢ 6 ነጥብ 3 ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ ድፍድፍ ነዳጅ ክምችት መኖሩንም ይፋ አድርጓል።
በአክሱም የሚገኘው የሃ ሆቴል በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ሊሠራለት ነው
በአክሱም ከተማ ከተገነባ ከግማሽ መዕተ ዓመት በላይ የሆነው የሃ ሆቴል በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ማስፋፊያ ሊደረግለት መሆኑ ታወቀ። በዕድሳትም ምክንያት ሆቴሉ ለ18 ወራት አገልግሎት አይሰጥም።
ከ11 ዓመት በፊት በ20 ሚሊዮን ብር ወደ ግል ይዞታ የተዘዋወረው የሃ ሆቴል በሁለት ዙር ግንባታው የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያው ዙር የዕድሳት ጊዜ ስምንት ወራትን ይፈጃል። በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባውና በቱሪስት መዳረሻዋ አክሱም ከተማ የሚገኘው ይህ ሆቴል 60 መኝታ ቤቶች ያሉት ሲሆን ማስፋፊያው ቁጥሩን ወደ 254 ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በላሊበላ ከተማ ከሚገኘው ሮሃ ሆቴል እና በጎንደር ከሚገኘው ጎሃ ሆቴል ጋር በተመሳሳይ ወቅት የተገነባው የአክሱሙ የሃ የሚሠጠው አገልግሎት ደካማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለገቢ ማነስ እና የደንበኛ እጦት ተዳርጎ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ፀጋዬ አለማየሁ የተባሉ ባለሀብት ንብረት የሆነው የሃ ሆቴል በተሠራው ዲዛይን አማካይነት ከዘመናዊ ክፍሎች ባሻገር መሰብሰቢያ አዳራሾችና የሔሊኮፕተር ማረፊያ ይኖረዋል ተብሏል። ከአክሱም ሐውልት 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ሆቴል ዕድሳቱ እንዲከናወን ከኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ፈቃድ ተሠጥቶታል።
አማራ ባንክ በሦስት ወር ውስጥ 2 መቶ ሚሊየን ብር አክሲዮን ሸጫለኹ አለ
በቅርቡ የተመሠረተውና በሕወሓት ሹማምንት ለዕስር ተዳርገው በነበሩት በአቶ መላኩ ፈንታ የሚመራው “አማራ ባንክ” በሦስት ሳምንት ውስጥ 200 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ማካሄዱን ገለጸ።
በባህር ዳር ከተማ የአማራ ባንክን ለማቋቋም የሚያስችል የአክሲዮን ሽያጭ በጀመረ ሦስት ሳምንት ዕድሜው ይህን ያህል ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወኑ ባንኩ ከጅምሩ የሕዝብን ድጋፍ ያስገኘለት ነው ተብሎለታል።
የባንክ አደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ (የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ) አማራ ባንክ የሚቋቋመው የክልሉን ሕዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ሀገራዊ ልማትን ለመደገፍ መሆኑን ጠቁመው የአክሲዮን ሽያጬ ከ10 ሺኅ ብር እንዲጀምር የተደረገው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችንም ለማበረታታት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአማራ ባንክን 30 በመቶ ሼር ሊገዛ ደብዳቤ አስገብቷል በሚል የተሰራጨው ዜና ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ የአክሲዮን ሽያጬ እንደተጠናቀቀ ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሠራጨው መረጃም የተሳሳተ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ሰዓት የአክሲዮን ግዢ ፍላጎት በመጨመሩ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር በመተባበር ሽያጬ እስከ ቀበሌ ተደራሽ በማድረግ እየተሠራ በመሆኑ በሦስት ወራት ውስጥ ሽያጬ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ከሓላፊው መግለጫ ተረድተናል።
የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ለ18 ዓመታት በድብቅ ያሠራቸውን ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲፈታ ተጠየቀ
አምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት ከ18 ዓመት በፊት የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት በመተቸታቸው ምክንያት ለዕስር የዳረገቻቸውን 11 ፖለቲከኞችንና 17 ጋዜጠኞችን በአስቸኳይ እንድትለቅ አምነስቲ ኢንትርናሽናል ጠየቀ።
እነዚህ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በ1994 ዓ.ም የታሰሩ ቢሆንም ከዚያ ጊዜ በኋላ ግለሰቦቹ ላይ ይፋዊ ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን በአካል ታይተው እንደማይታወቅና ስላሉበት ሁኔታም ቢሆንምንም የተሰማ ነገር የለም የሚለው ዓለም አቀፍ ሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ የህሊና እስረኞች ናቸው ያላቸውን እነዚህን ታሳሪዎች የተያዙበትን 18ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እንዲለቀቁ በመጠየቅ ለ18 ቀናት የሚቆይ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በይፋ ጀምሯል።
አፋኙ አገዛዝ አስራ አንዱ ፖለቲከኞች ለዕስር የተዳረጉትፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምርጫ በማካሄድና ለሕግ የበላይነት በመገዛት ሕገ መንግሥቱን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ በመጻፋቸው ነው። 17ቱ ጋዜጠኞች ደግሞ ፖለቲከኞቹ ስለጻፉት ደብዳቤ በመዘገባቸው መሆኑ ተሰምቷል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ፣ አፍሪካ ቀንድና የግሬት ሌክስ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሰይፍ ማጋንጎ “ለታሳሪዎቹ ፍትህ ሲጠየቅ ሁለት አስርት ዓመታት ሊሆን ነው፤ ምጸት የሚሆነው ደግሞ ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባል መሆኗ ነው።” ሲሉ ገልጸው፤ “ይህ ከሕግ ውጪ የሆነው እስር የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ለመጨፍለቅ ምን ያህል እርቀት እንደሚሄድ የሚያመላክት ነው። በብዙ መቶዎች እንደሚቆጠሩት ሌሎች የህሊና እስረኞች ሁሉ እነዚህ 28 ታሳሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መለቀቅ አለባቸው” ብለዋል።
ለ18 ቀናት የሚያካሂደው የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን፤ የኤርትራ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ብርሐነ አብረሃ ከተያዙበት አንደኛ ዓመት ጋር በማያያዝ ይህ ወቅት ሊመረጥ ችሏል። አቶ ብርሐነ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሕዝቡ ለዲሞክራሲ ሰላማዊ ትግል እንዲያደርግ የሚቀሰቅስ መጽሐፍ ካሳተሙ በኋላ የዛሬ ዓመት ነበር።
የህሊና እስረኞቹና አቶ ብርሐነ ከውጪው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌለው ምስጢራዊ ስፍራ ውስጥ ተይዘው እንዳሉ የሚጠቁሙ ግምቶች ተሰምተዋል። ቤተሰባቸውም ስላሉበት የጤንንት ሁኔታና የት እንደሚገኙ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸውም አምነስቲ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስና መንግሥታቸው በእነዚህና በሌሎች የህሊና እስረኞች ላይ እየፈጸሙት ያለው ኢፍትሐዊነት እንደሚያሳስበውና “ዓለምም ከታሳሪዎቹና ከቤተሰባቸው ጎን በመቆም የኤርትራ ባለስልጣናት ያለቅድመ ሁኔታ በቶሎ ከእስር እንዲለቋቸው መጠየቅ አለበት” ብሏል።