ኢሕአዴግ በውሕድ ፓርቲነት ስሙን “የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ” (ኢብፓ) በሚል ሊቀይር ነው
በአብዩታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲመራ የኖረው ኢሕአዴግ ብዙ ዘግናኝ ግፍ ሲፈጽምበት የኖረውን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ የሚጠላውን “የጥፋት ስሙን” ሊቀይር መሆኑ ታወቀ:: በዚህ መሠረት ኢሕአዴግ ወደ ኢብፓ (የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ) ወደ ተሰኘ አዲስ ስያሜ ይለወጣል::
ከመስከረም 8 ቀን ጀምሮ ለአምስት ቀናት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ አካሂደው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይተካል ብለው ባመኑት አዲሱ የፖለቲካ ፍልስፍና በሆነው “የመደመር ፖለቲካ ቀመር” ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ከታማኝ ምንጮቻችን ማረጋገጥ ችለናል::
ኢሕአዴግ ተዋህዶ አንድ ወጥ ፓርቲ ለመሆን ፍላጎት እንዳለው የገለጸው ድርጅቱን ለጥቂት የማፍያ ቡድኖች እና ለአምባገነን ስርዓት መምቹ በሆነ መንገድ ጠፍጥፈው በሠሩት በመለስ ዜናዊ አማካይነት ከ17 ዓመት በፊት ነበር:: ያኔ ባሕር ማዶ በተደረገ አንድ የኢትዮጵያውያን ጉባኤ ላይ መለስ ዜናዊ ሃሳቡን ያንሱት እንጂ በተለይ አጋር በሚል ስያሜ ከተራ አሻንጉሊትነት ውጪ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የሌላቸውን የክልል አጋር ድርጅቶችን ማዋሀድን ፈጽሞ የማይሹ በመሆናቸው እውን ሳይሆን ቀርቷል::
አሁን ላይ ግን ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አጋር ድርጅቶቹን ያካተተ ውህደት ለመፈጸም ቆርጠው ተነስተዋል:: ይህን ውህደት ከጅምሩ ሲቃወም የቆየው ሕወሓት አብሮ ይዋሃዳል ወይ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም የነአቦይ ስብሓት ፈርጣጬ ቡድን በአካሄዱ ተስማምቶ ራሱን በማክሰም ውሕድ ፓርቲ ይሆናል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው ይላሉ::
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በረሃ እያሉ በ19 81 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሚል መጠሪያ ኢሕአዴግን መመስረታቸው አይዘነጋም::
የነብርሃኑ ነጋ ኢዜማ በዓለም 70 ሀገራት ደጋፊዎቻቸውን ማደራጀት ጀመሩ
ከውህድ ምሥረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን በሚወዱ ሀገር ወዳድ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ኢዜማ ፖ
ፓርቲ ከ70 በላይ በሚሆኑ የዓለም ሀገራት የደጋፊዎች ማህበርን እያደራጀ መሆኑን አስታውቋል::
በበሳል ፖለቲከኞቹ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና አንዷለም አራጌ የሚመራው ኢዜማ ከተመሠረተ ገና የአምስት ወራት ዕድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም በሀገር ውስጥ በ400 የምርጫ ወረዳዎች አባላትንና ደጋፊዎችን አደራጅቶ ለቀጣዮ ምርጫ ዝግጁነቱን አረጋግጧል:: ይህንን አካሄድ በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃም ደጋፊዎቹን ለማደራጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል::
ኢትዮጵያውያን ይኖሩባቸዋል ተብለው በተለዮ 70 የዓለም ሀገራት በየከተሞቹ የደጋፊ ማህበር የሚቋቋም ሲሆን የእነዛ ም/ቤት አባላት የሆኑ ግለሰቦች አመራርነት ተመርጠው የክፍለ ዓለም ደጋፊ ማስተባበሪያ የሚኖረው አደረጃጀት እንደሆነ በተሠጠው መግለጫ ላይ ተገንዝበናል::
ኢዜማ ይህን መንገድ የተከተለው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ይመለከታቸዋል ብሎ ስለሚያምን መሆኑንም አስታውቋል::
አንጋፋው ቀስተ ደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ዛሬ በዱከም ተቃጠለ
ዱከም የሚገኘው አንጋፋው ቀስተ ደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ዛሬ ረፋድ ላይ ባልታወቀ ምክንያት መቃጠሉን የደረስን ዜና ያስረዳል:: ከባድ ኪሳራ በፋብሪካው ላይ እንዳደረሰ የሚነገርለት የእሳት ቃጠሎ መነሻ ምክንያቱ ምን እንደሆነም አልታወቀም::
የእሳት ቃጠሎው ዛሬ መስከረም 10 ቀን ጠዋት 4፡10 አካባቢ እንደጀመረ የተናገሩት የፋብሪካው የሰው ኃይልና ሀብት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሳሉ አመኑ፤ በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ቢያጋጥምም ቃጠሎው ሰው ላይ ጉዳት አለማድረሱን ተናግረዋል::
ለበርካታ ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቀስተ ደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ዱከም አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ የአገልግሎት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ማሽኖች ከአውሮጳ መጥተው በዘመናዊ መልኩ ከተገነባ ዓመት ከስድስት ወር ብቻ እንደሆነው ለማወቅ ተችሏል::
የእሳት ቃጠሎው በምን ምክንያት እንደተነሳ የታወቀ ነገር የለም ያሉት አቶ አምሳሉ፤ የፋብሪካው ዋና ዋና ክፍሎች በብዛት በቃጠሎው መውደማቸውን ጠቁመው፤ በተጨማሪም ውጪ የነበሩ ኬሚካሎች፣ ውስጥ በሂደት ላይ የነበሩ ምርቶች ሙሉ በሙሉ እንደነደዱና የተረፉት አንድ የምርት ክፍል እንዲሁም የተወሰኑ ኬሚካሎች ብቻ እንደሆኑ ይፋአስታውቀዋል። አድርገዋል::
በቃጠሎው ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል የሚያስረዱት ሓላፊ አብዛኛው በቃጠሎ ወድሟል ማለት እንደሚቻል አስረግጠው ተናግረዋል:: እሳቱን ለማጥፋት የተለያዩ አካላት መረባረባቸው በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መወሉ ተሰምቷል:: ዕድሜ ጠገቡ የስፖንጅ ፋብሪካ፣ በፋብሪካውና በሽያጭ ሱቆቹ 390 ሠራተኞች ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ሠምተናል::
ታህሪር አደባባይ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ሥልጣን እንዲለቁ በጠየቁ ግብፃውያን ዳግም ተናጠች
ግብፅን እየመሩ ያሉት ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የመጀመሪያ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደባቸው:: ፕሬዝዲንቱን በመቃወም የወጡ ሰልፈኞችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል::
ግብፃውያን በታህሪር አደባባይ ሰልፍ ወጥተው፤ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ሥልጣን እንዲለቁ አብዝተው ጠይቀዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011ዱ ተቃውሞ ማዕከል ከነበረው ታህሪር አደባባይ በተጨማሪ፣ በሌሎች አካባቢዎችም ሰላማዊ ሰልፉ መካሄዱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ከግብፅ ምድር እየወጡ ነው::
በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ የተካሄደው አል-ሲሲ በሙስና መወንጀላቸውን ተከትሎ መሆኑም በይፋ እየተነገረ ነው:: ግብፃዊው ተዋናይና የቢዝነስ ሰው ሞሀመድ አሊ፤ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ በቅንጡ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ በርካታ ገንዘብ እያባከኑ እንደሚገኙ በመግለጽ ፣ ድርጊቱን የሚያሳዮ ቪዲዮዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሰራጭቶ ነበር::
በ ዚህ ወቅት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብፃውያን በድህነት እየማቀቁ ፣ ፕሬዝዳንቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያባከኑ ነው ሲልም ተዋናዮ ሞሀመድ አሊ ሥርዓቱን ክፉኛ ተችቷል። የተባለው ነገር “ውሸት እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው” ያሉት አል ሲሲ ግን ትችቱን አጣጥለዋል::
ይህንን ተከትሎ ትናንት በትዊተር ላይ በስፋት ሲሰራጩ የነበሩ መልዕክቶች ሕዝቡ አል-ሲሲ ከሥልጣን እንዲነሱ እንደሚፈልግ የሚጠቁሙ በመሆናቸው ፣ ዛሬበአሌክሳንድርያ እና ስዊዝ ከተሞችም በተጨማሪነት ሰላማዊ ሰልፉ እንዲካሄድ ዕድል ፈጥሯል::
በአውሮፓዊቷ ስፔን በስደት የሚኖረው ግብፃዊው ተዋናይና የቢዝነስ ሰው ሞሀመድ አሊ፤ የመጀመሪያ ቪድዮውን የለቀቀው መስከረም ሁለት ነበር:: በቪዲዮው ላይ ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን የሚወርዱበትን ቀነ ገደብ አስቀምጦ፤ አል-ሲሲ በተባለው ጊዜ ከሥልጣን ካልወረዱ በግብፅ ታላቅ ሰለማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አሳስቦ ነበር:: ሞሀመድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት፤ አል-ሲሲ ከሥልጣናቸው አለመነሳታቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብፃውያን ዛሬ ሰልፍ ወጥተዋል::
ግብፅ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞሀመድ ሙርሲን በማስወገድ አል-ሲሲ ስልጣን የጨበጡት 2013 ላይ መሆኑ አይዘነጋም:: የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን በማጣቀስ፤ የአል-ሲሲን አስተዳደር ክፉኛ በማውገዝ ላይ ናቸው:: 2018 ላይ በተካሄደው ምርጫ አል-ሲሲ ጠንካራ ተቀናቃኝ ሳይኖራቸው ሥልጣን መያዛቸው ይታወሳል::
አሜሪካ ኢራንን ለመምታት ጦሯን ወደ ሳዑዲ ልትልክ ነው
አሜሪካ በሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ወታደሮቿን ልትልክ ዝግጅት መጀመሯ ተሰምቷል::የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣንየሆኑት ማርክ ኤስፐር፤ በሳዑዲ የሚሰማራው ጦር “መከላከል ላይ ያተኮረ” ተልዕኮ ሊሰጠው እንደሚችል ፤ ምን ያህል ወታደር እንደሚሰማራ ግን ከመግለጽ ተቆጠበዋል::
በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቱ አማፂያን ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ ሁለት የነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ሓላፊነቱን እንወስዳለን ቢሉም ፤ አሜሪካም ሆነች ሳዑዲ አረቢያ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ኢራንን ነው። አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ወታደራዊ እሰጥ አገባ ውስጥ ላለመግባት በሚል “ከፍተኛ የሆነ” ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል መናገራቸው አይዘነጋም::
አዲሱ ማዕቀብ የሚያነጣጥረው የኢራን ማዕከላዊ ባንክንና ሉዓላዊ የሀብት ፈንድን መሆኑን ትራምፕ ተናግረዋል።ሚስተር ኤስፐር መግለጫ የሰጡት የጥምር ጦሩ የበላይ ሓላፊ ከሆኑት ጄነራል ጆሴፍ ደንፎርድ ጁኒየር ጋር ነው።ሳዑዲ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስን ድጋፍ ጠይቀዋል ያሉት ሚስተር ኤስፐር የሚላከው ኃይል የአየርና የሚሳኤል መከላከል አቅምን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ከመታቀዱ ፣ አሜሪካ ደግሞ ለሁለቱ አገራት “ወታደራዊ ቁሳቁስን ማቅረቡን ታፋጥናለች” ይላሉ::
የጥምር ጦሩ የበላይ ሓላፊ ጀነራል ደንፎርድ የወታደራዊ ስምሪቱን “የተለሳለሰ” ያሉ ቢሆንም ፣ ከዚህ ውጪ ግን ምን ዓይነት ጦር እንደሚሰማራ ፍንጭ አልሰጡም። እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ከሆነ፤ ጋዜጠኞች ሚስተር ኤስፐርን ኢራን ላይ የአየር ድብደባ ለማካሄድ ታቅዶ እንደሆነ ሲጠየቁ “በአሁኑ ሰዓት እዚያ ውሳኔ ላይ አልደረስንም” ማለታቸውን ዘግቧል። በአገሪቱ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ከደረሰው ጥቃት የተሰበሰቡ ናቸው ያላቸውን የድሮን እና የሚሳዔል ስብርባሪዎች በማሳየት “ጥቃቱን ያደረሰችው ኢራን ነች” ሲል የሳዑዲ መንግሥት ከሷል:: “18 ድሮኖች እና ሰባት ሚሳዔሎች ወደ ሳዑዲ ተተኩሰዋል” ያለው የሳዑዲ መከላከያ፤ የጥቃቶቹ መነሻ የመን አይደለችም በማለት ሓላፊነቱን ለኢራን ሰጥቷል::
አዲስ አበባን ለመጠቅለል የቋመጠው ኦዴፓ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በኦሮሚያ አዘጋጅነት ሸገር ላይ ሊያዘጋጅ ነው
ጊዜው የኔ ነው በማለት የደመደመው ኦዴፓ በእጅጉ በሚቋምጥባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት የሚከናወነውን 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሊያከብር መሆኑን ይፋ አድርጓል::
የፓርቲውና የክልሉ መንግሥት ቀጥተኛ የኢትዮጵያን ሕዝብ ንቀት የታየበት ውሳኔ መላውን ኢትዮጵያዊ እያበሳጨይገኛል:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ተስፋ አድርገው የቆዮ ዜጎችም ውሳኔው ተስፋ ያደረጉበትን ለውጥ እንዲጠራጠሩበት እያደረጋቸው እንደሚገኝ በመናገር ላይ ናቸው::
14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የገለጹ ሲሆን፤ በበዓሉ ዝግጅት ዙሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል::በውይይቱ ላይም እስካሁን በተከበሩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጥቅሞች እና ጉድለቶች ዙሪያ ጥናት ተደርጓል ተብሏል::
መልካም ጎኖችን በማጠናከር በዘንድሮውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤዋ የዘንድሮው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህገ መንግስታዊ መከበር እና ሀገራዊ አንድነትን ታሳቢ አድርጎ እንደሚከበርም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ ልታመጥቅ የነበረውን ሳተላይት ወደ ታህሳስ ወር አራዘመች
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትየጵያ በዚህ ወር ልታመጥቀው የነበረው ሳተላይት፤ ወደ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ. ም. መዘዋወሩን፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ አስታወቁ: :ኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በዚህ ዓመት መባቻ ላይ ከቻይና ለማምጠቅ እቅድ ይዛ እንደነበረ ይታወሳል።
የተቋሙ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ሳተላይቱን የምትቆጣጠርበት እና የምታዝበትን ጣቢያ (ግራውንድ ስቴሽን) በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሞከር ስላልተቻለ፤ ሳተላይቱ የሚመጥቅበት ቀን ተሸጋግሯል ብለዋል:: የሳተላይት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን ለቢቢሲ የተናገሩት ፣ መቆጣጠሪያ ጣቢያው በአግባቡ ሳይሞከር ሳተላይቱን ማምጠቅ ስለማይቻል፤ ከቻይና አጋሮቻቸው ጋር በመመካከር ወደ ታህሳስ ለማዘዋወር መገደዳቸውን ይፋ አድርገዋል::
“የጣቢያው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፤ የሚቀረን መሞከር ነው። ታህሳስ ላይ መቶ በመቶ ይመጥቃል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።ይህ ሳተላይት ከምድር ወደ ህዋ ከተመነጠቀ በኋላ መሬትን እየቃኘ መረጃዎችን በፎቶ ይመዘግባል። እንደያስፈላጊነቱም መረጃውን ወደ ምድር ይልካል።” ሲሉም ተናግረዋል::
አፍሪካ ውስጥ እስካሁን ሳተላይቱን ያመጠቁ በጣት የሚቆጠሩ አገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያም የአምጣቂዎቹን ቡድን ለመቀላቀል ከሦስት ዓመት በፊት መሰናዶ መጀመሯ አይዘነጋም:: ዓለም ላይ ሳተላይት ማምጠቂያ (ላውንቸር) ያላቸው ጥቂት አገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት፤ ሳተላይቱ ከቻይና የሚመጥቅ ይሆናል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሳተላይቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደህንነትን ለመጠበቅ ወዘተርፈ ይውላል። የደን ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ እና መከላከል ይቻላል።
አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ፣ ስለ ውሀው፣ ስለ አፈሩ ዝርዘር መረጃ ይሰጣል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት፣ የምርት መጠንን በትክክል ማወቅም ይቻላል።ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡባት ኢትዮጵያ፤ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ የሳተላይቱ መረጃ መልስ ከመስጠቱ ባሻገር፤ ሕዝብ መቁጠር ሲያስፈልግ ከዘልማዳዊው መንገድ ሳተላይቱን መጠቀም ይመረጣል። ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት፣ ገንዘብና የሰው ሀይል ከማዳን አንጻርም የተሻለው አማራጭ እንደሆነናኢትዮጵያ እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ አገሮች ትሸምት እንደነበርም አስረተድተዋል::
የሳተላይቱ ግንባታ የተጀመረው ከቻይና በተገኘ 6 ሚሊየን ዶላር ሲሆን፤ ቻይናውያን ኢንጂነሮች ኢዮጵያውያንን እያሰለጠኑ ሳተላይቱ ቻይና ውስጥ እንዲሁም በከፊል ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑም ታውቋል::