የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ጭስ አልባ የትራንስፖርት ኢንዱስትሪን ልታስገባ ነው

ኢትዮጵያ ጭስ አልባ  የትራንስፖርት ኢንዱስትሪን ወደ ሀገሯ ለማስገባት ማቀዷን የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አወል ወግሪስ ገለጹ:: ጉዳዮን አስመልክቶም ሚኒስትር ዲኤታው ከቻይና ልዑካን ቡድን ጋር መክረዋል::

በውይይት መድረኩ ላይ የልዑካን ቡድኑ ጭስ አልባ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ያለውን ጠቀሜታ በተመለከት ሰነድ አቅርበው ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ ከመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ከሰው ሀብት ወይም ከባለሙያ አቅም ግንባታና መሰል ቅድመ ሥራዎች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተው በልዑካን ቡድኑ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

ቴክኖሎጂውን በኢትዮጵያ ለማስጀመር በመንግስት በኩል የፖሊሲ እና የህግ ጉዳዮችን በትኩረት ተከታትሎ ማስፈጸም እንደሚገባም ከመነሳቱ ባሻገር ፤ በመንግስትም ሆነ በግል ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት እና አገልግሎቱን ለመስጠት ለሚፈልጉ አካላት ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈለጊ ነው ተብሏል።

ጭስ አልባ ተሽከርካሪ ዓለምን እየተፈታተናት ካለው የአየር ንብረት ለውጥ አንጻር ለነገ ሊባል እንደማይገባውም ልዑካኑ ጠቁመው፤ የዘርፉ አገልግሎት ቀላል፣ ወጪ፣ ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ፣ ከየትኛውም የአየር ንብረት ጋር የሚስማማና ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ምቹ እንደሆነና የተፈጥሮ ነዳጅ ለሌላቸው ሃገራት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል::

አሜሪካ በሕክምና ላይ ያሉት ሚሚ ስብሓቱ ዛሚ ራዲዮ አልተሸጠም አሉ

በሕወሓት ደጋፊነት የሚታሙት የዛሚ ራዲዮ ባለቤት ወ/ሮ ሚሚ ስብሓቱ በአሁኑ ሰዓት ከሚገኙበት አሜሪካ ራዲዮ ጣቢያቸው የስም ለውጥ እና የሽርክና ስምምነት ከመፈጸሙ ውጪ ሙሉ ለሙሉ ለሌላ ወገን እንዳልተሸጠ ተናገሩ::

በቅብርቡ ጣቢያቸው ለጃዋር መሐመድ ተሽጧል የሚሉ ዜናዎች ሲናፈሱ ቆይቷል:: እኛም ጉዳዮን አስመልክቶ ከሳምንታት በፊት ሁለቱ ግለሰቦች በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው የስያሜ ለውጥ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል::

የአምባገነኑ መንግሥት ዋነኛ ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ተመርቀዋል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትርፍ ጊዜ ይሠሩ የነበሩት ፣  ከተመረቁ በኋላም የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽንን ተቀላቅለው ዘጋቢ ፊልሞችን ሠርተዋል። የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ፤ ኒዮርክ ፣ በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ያላማራቸው ሚሚ፤ እዚያው ለመቆየት ወስነው በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም ተቀጥረው በጋዜጠኝነት ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል::

ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላም ዛሚ 90.7 ራዲዮ ጣቢያን አቋቁመው እየሠሩ  ሲሆን ይህ ራዲዮ ጣቢያ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ባላቸው አካላት ትችቶች ሲሰነዘርበትቆይቷል።

” አሁን አሜሪካን አገር ነው ፣ በየዓመቱ የጤና ምርመራ አደርጋለሁ። በጣም ደህና ነኝ። በጣም በሚገርም ዓይነት ባለፈው ጊዜ ዐይኔን ቀዶ ሕክምና አድርጌ ነበር። የሚገርመው የምርመራ ውጤቴንም ተቀብያለሁ። በጥሩ ጤንነት ላይ ነው ያለሁት ፤ በዚህ እድሜ የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ- በእኔ እድሜ። ስለዚህ ከዚያ አንፃር ሲታይ፣ እ. . ከሥራዬ ‘ስትረስ ፉል’ [ውጥረት መብዛት] አንፃር ሲታይ፤ እነዚህ አስፈሪ የሆኑት እንደ ስኳር፣ ግፊት ምናምን ያሉት የሉብኝም። በዚያ ተደስቻለሁ። የሚገርምሽ ስፖርት አልሠራም። ምን አልባት አመጋጋብ ሊሆን ይችላል።” በማለት ስላሉበት ሁኔታ ለቢቢሲ የገለጹት ሚሚ ስብሓቱ፤ “አሁን ዛሚ ‘ሪ ብራንድ’ እየተደረገ ነው። እንደገና ደግሞ የ ‘ትሬኒንግ’ [ሥልጠና]፤ ጋዜጠኞችን በዘለቄታዊ የሥልጠና ተቋም የመገንባት ሥራ ላይ ነው ያለሁት። ብዙ ሥራዎች ላይ ነው ያለሁት፤ አሁን ሕክምና ላይ ብሆንም።” ሲሉ ተደምጠዋል::

ዛሚ ራዲዮ ተሸጧል እየተባለ ይወራል ፣ እውነት ነው ወይ ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሚሚ ስብሓቱ ዛሚ ብዙ ጊዜ የአየር ሰዓት ወስደው የሚሰሩ ‘ፓርትነርስ’ አሉት። በተለያየ መንገድ አብረውን የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች አሉ። ስለዚህ ከብዙ ሰዎች ጋር እንሠራለን። ዛሚ የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑ መርሁን እና ሥነ ምግባሩን ከሚያከብሩ፣ አላማው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እንደመሆኑ ያንን ማድረግ ከሚፈልጉ፣ መሠረታዊ በሆኑት የጋዜጠኞች መስፈርቶች ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለህብረተሰባችን አገልግሎት ከሚሰጡ፣ መስጠት ከሚፈልጉ፣ ከማናቸውም ወገኖች ጋር በትብብር እንሠራለን። አሁን የሚባለው ነገር በሙሉ ሀሰት ነው” ሲሉ አጣጥለዋል::

የኦዴፓ አባሉ አቶ ባልቻ ሬባ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

የወቅቱን የበላይነት መጨበጡን ያረጋገጠው የዶ/ር ዐቢይ ኦዴፓ ለኦሮሞ ተወላጆች አዳዲስና ወሳኝ ሹመቶችን መስጠቱን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል:: ዛሬ ይፋ በሆነው መረጃ መሠረት አቶ ባልቻ ሬባ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነቱን ቦታ ይዘውታል::

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሰረት፤ የቴሌኮም ዘርፉን በመቆጣጠር በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ተቋማት የውድድር ሜዳውን ምቹ ማድረግ የባለስልጣን መ/ቤቱ ሓላፊነት ነው::

ተቋሙን ከመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተሾሙት አቶ ባልቻ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፥ በኦሮሚያ ውሃ ሃብት ቢሮ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቆጣጣሪ በመሆን ሠርተዋል:: በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ከዋና ክፍል ሓላፊ እስከ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሆነው የሠሩት የኦዴፓ አባሉ ፤ ላለፈው አንድ ዓመት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴሌኮም፣ ፖስታ እና ኮሙዩኒኬሽን ቁጥጥር ላይ ያተኮረው የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደነበሩም ተገልጿል::

እሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሚካሄደው ሩጫ፣እሁድ የአዲስ አበባ መንገዶች ይዘጋሉ ተባለ

ለመጀመሪያ ጊዜ በዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና በታከለ ኡማ ከንቲባነት የእሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚካሄደውን ሩጫ፣ሰላማዊ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ::

እሁድ መስከረም 11 ቀን መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ፣ ከ50 ሺህ ሰው በላይ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው “እሬቻ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት፣ ሙዚቃ፣ ቲያትርና ስፖርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ዛሬ አረጋግጠዋል::

የሩጫ ውድድሩ ከመስቀል አደባባይ በመነሳት በለገሃር፣ ቡናና ሻይ፣ ገነት መብራት፣ ቡልጋሪያ ማዞሪያ፣ ቄራ ጎተራ፣ አጎና ሲኒማ፣ ግሎባል ሆቴል እና በመሿለኪያ አድርጎ ስለሚካሄድ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሩጫው ፍፃሜ ድረስ በእነዚህ መስመሮች ላይ ለረዥምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ተከልክሏል

ውድድሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑት መንገዶች፡-

ከቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ወደ መስቀል አደባባይ፣ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከሃራምቤ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከልደታ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ወደ ቄራ፣ ከአፍሪካ ህብረት አደባባይ ወደ ቡልጋሪያ ማዞሪያ፣ ከሳርቤት አደባባይ ወደ ቄራ፣ ከጎፋ ገብርኤል ወደ ጎፋ ማዞሪያ፣ ከቂርቆስ አዲሱ መንገድ ወደ ጎፋ ማዞሪያ፣ ከቂርቆስ አዲሱ መንገድ ወደ ለገሃር፣ ከቂርቆስ ወደ ገነት ሆቴል፣ከመስቀል ፍላወር ወደ አጎና ሲኒማ የሚወስዱ መንገዶች ዝግ ሆነው እንደሚቆዮም ኮማንደሩ አስታውቀዋል::

በዉሃ እጥረት በጥቁር አንበሳ የአጥንት ሕክምና የሚያደረጉ ሕጻናት እየተሰቃዮ ነው

ተደጋጋሚ ወቀሳዎች የሚቀርብበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አሁን ላይ በከፍተኛ የውሃ ችግር ቀጠሮዎችን እስከማስተጓጎል በመድረሱ ታካሚዎች ለመጉላላት መዳረጋቸው ተሰማ::

የታካሚ ቤተሰቦች የውሃ ችግር በሆስፒታሉ የተያዙ ቀጠሮዎችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይከናወኑ በማድረግና ቆይታቸውን በማራዘም ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን አስታውቀዋል:: ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዋናነት ከሆስፒታሉ የህጻናት አጥንት ክፍል ውስጥ የተከሰተ እንደሆነም ጠቁመዋል::

በህጻናት የአጥንት ክፍል ውስጥ የሚየጋጥመው የውሃ እጥረት ለታካሚዎቹ ቀዶ ጥገና ለማድረግ የተያዘላቸውን የጊዜ ቀጠሮ በተደጋጋሚ ማስተጓጎሉን ተከትሎ ህመምና ስቃያቸውን አባብሶታል:: ከአዲስ አበባ ውጭ ከሆኑ አካባቢዎች ህመምተኞችን ይዘው ለሚመጡ የታካሚ ቤተሰቦች ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል::

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና አስፈፃሚ ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ በበኩላቸው የውሃ እጥረት በህጻናት አጥንት ክፍል ብቻ ሳይሆን ሆስፒታሉ እንደ አጠቃላይ የሚያጋጥመው ችግር መሆኑን ጠቁመውከሆስፒታሉ እድሜ አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መፍታት ባይቻልም ጊዜያዊ መፍትሄዎችን በመስጠት ቀስ በቀስ ችግሩን የሚቀንሱ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና ተቋሙ ውሃ በፈረቃ የሚያገኝና ውሃ የሚያቀርብ የራሱ መስመር የሌለው መሆኑ የችግሩ መንስኤ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል::

የውሃ መስመሮቹ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው ከ4ኛ እና 5ኛ ፎቅ በላይ ውሃ ማውጣት የማይችሉ ናቸው ያሉት ሓላፊ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታትም መስመሮቹን ለማደስ መሞከሩን ጠቅሰው፥ ከስራው ውስብስብነት አንፃር ተቋራጮች ማደስ እንዳልቻሉ አስረድተዋል::

ለእድሳቱ ያስፈልጋል የተባለው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑም ከአዋጭነት አንጻር ሳይሰራ መቅረቱን ጠቁመው፥ በተጀመረው እድሳት የተነካኩ ነገሮችም ተጨማሪ ችግር የፈጠረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ችግሩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በቂ ትኩረት እንዳገኘና ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ተገልጿል::

LEAVE A REPLY