በቅርቡ የበርካታ ሚሊዬን ዶላሮች አሸናፊ ለመሆን የበቁት እና በአገራችፕው ኢትዬጵያ ውስጥ የችግረኞችን ህይወት ለመቀየር ውጥን የነበራቸው ትውልደ ኢትዬጵያዊው ሰሞኑን በአገራቸው ኢትዬጵያ ውስጥ ሞተው የመገኘት ዜና ቤተሰቦቻቸውን በእጅጉ አስደንግጧል።
በካናዳው ፣ቶሮንቶ ግዛት ውስጥ በአንድ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ ይሰሩ የነበሩት የአርባ እንድ አመቱ ትውልደ ኢትዬጵያዊው አቶ ሚካኤል ገብሩ የዛሬ ሁለት አመት(እኤአ ሰኔ 2017) የቆረጡት ሎተሪ ግፋ ቢል 14 የካናዳ ዶላር አሸናፊ ያደርገኛል ብለው ከመጠበቅ ውጪ ሌላ ሀሳብ አልነበራቸውም ነበር።
ይሁን እና ያቺ በድንገት የተቆረጠች ሎተሪ አቶ ሚካኤልን የ10 .7ሚሊዬን የካናዳ ዶላር ( ሁለት መቶ ሰላሳ ስምንት ሚሊዬን ብር በላይ)አሸናፊ እንዲሆኑ በማድረግ ህይወታቸውን በአንድ ቀን ጀንበር ሙሉ በሙሉ እንደቀየረው ብዙዎች በአግራሞት ይናገሩላቸዋል።
በወቅቱ ከሚሰሩበት ስራ ተቀንሰው (ተባርረው) በነበረበት ወቅት የሚሊዬነርነት ማድረጊያ ሎተሪ እድለኛ ለመሆን የበቁት አቶ ሚካኤል በወቅቱ ከካናዳው ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (CBC) ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ” ሎተሪ ባገኝ፣ ሎተሪ ቢደርሰኝ ፣ማረፊያ ቤት ገዝቼ፣ ወደ አገሬም ሄጄ ደሀዎችን እረዳበታለሁ” ሲሉ ምኞታቸውን ተናግረው ነበር። ምኞታቸውም ሳይውል ሳያድር ተሳካ ።
የአቶ ሚካኤል የቅርብ ዘመድ የሆኑት ሶስና አስፋው በትላንትናው አርብ እለት ለንባብ በበቃው ለሲቢሲ (CBC) ድህረ ገጽ በላኩት መረጃ ሎተሪውን ካሸነፉ ማግስት ጀምሮ ከቶሮንቶ ካናዳ ወደ ኢትዬጵያ እየተመላለሱ ሁኔታዎችን በማጥናት ላይ የነበሩት አቶ ሚካኤል ከሁለት ሳምንት በፊት ለተመሳሳይ ተልእኮ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመምጣት አሳዛኙ የኑሮ ውጣ ውረድ ጋር የሚጋፈጠው ማህበረስብን ለመርዳት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለመድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ሳሉ ባለፈው ቅዳሜ መንስኤው በውል ባልታወቀ ሁኔታ ሞተው መገኘታቸውን ሶስና በምሬት ተናግረዋል።
ህይወታቸው በአንድ ጀምበር ከተራ ጥሮ አዳሪነት ወደ ሚሌየርነት መለወጡ በካናዳ ፣ቶሮንቶ ከተማ ውስጥ በምትገኘው በግምት ስድስት መቶ ሺህ ነዋሪዎች በሚኖሩባት ስካርቦሮው ክፍለ ከተማ አልፎ ኢትዬጵያ ውስጥ በትውልድ አካባቢያቸው ሳይቀር ዝናቸው የናኘው አቶ ሚካኤል ገብሩ አሟሟት ድንገተኛ ሳይሆን “ተገድለው ነው” የሚል መረጃ እንደደረሳቸው የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው ከኢትዬጵያ ፖሊስ በኩል እስከአሁን ድረስ በቂ መረጃ ባለማግኘታቸው የካናዳ መንግስት (አ/አ የሚገኘው ኢምባሲ) በጉዳዩ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ እና እንዲያጣራላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በዜጋው መሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው የገለጸው የካናዳ የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ሁኔታው የግለሰብ ጉዳይ በመሆኑ ህጉ በሚደነግገው መሰረት ከቤተዘመድ ጋር ከመወያየት በቀር ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለዜና ሰዋች ከመስጠት ተቆጥቧል። ከስራ ገበታቸው በተቀነሱ ማግስት ሚሊየነር ለመሆን የበቁት አቶ ሚካኤል በትውልደ ኢትዬጵያዊ ከመሆናቸው ውጪ የትውልድ ስፍራቸው ሆነ አሳዛኙ ድርጊት የተፈጸመበት አካባቢ በዝርዝር በዘገባው ላይ አልተካተተም። ይሁን እንጂ ለጉዳዩ ቅርበት አለን የሚሉ አንዳንድ ያልተረጋገጡ ምንጮች ግን ግድያው ከዝርፊያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ስፍራውም በመዲናይቱ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመ መሆኑን ይናገራሉ።