የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም

ዛሬ በአዲስ አበባ በኤሌክትሪክ አደጋ ሁለት ሰዎች ሞቱ

በአዲስ አበባ ከተማ በኤሌክትሪክ አደጋ የሁለት የሰው ሕይወት ማለፉ ተነገረ:: የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋየኤሌክትሪክሌክ አደጋውን ተከትሎ የሁለት ሰው ሕይወት ማለፉን አረጋግጧል::

ግለሰቦቹ ያለጥንቃቄ ብረት ይዘው በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት የያዙት ብረት ከከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ጋር በፈጠረው ንክኪ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል::

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11፣ ልዩ ቦታው ቡልጋሪያ አደባባይ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ ነው አደጋው የደረሰው:: ዛሬ ከረፋድ በኋላ የጣለውና ረዥም ሰዓት ያለማቋረጥ የዘነበው ከባድ ዝናብ ለአደጋው መፈጠር ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል:: ይህን ተከትሎ ኮሚሽኑ ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የሚያሳስብ መልዕክቱን አድርሷል::

የቀረበለትን 40 ሺህ ብር መደለያ ገፍቶ አገሩንና ሕዝብን የመረጠው የአፋር ፖሊስ በጠ/ሚ/ር ዐቢይ ተወደሰ

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሰዎች ያቀረቡለትን መደለያ ገንዘብ ሳይቀበል ሕዝብና ሀገሩን ያስቀደመው የአፋር ክልል ፖሊስ አባል ሲራጅ አብደላ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል::

ዛሬ ከሰዓት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ሀገሬና ሕዝቤ ይበልጥብኛል በማለት የሕግ የበላይነትን በማስከበሩ ያላቸውን አድናቆት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ገልጸውለታል:: ግለሰቡ ወጣት እንደመሆኑ በጣም ብዙ ለሀገሩ መሥራት እንደሚችልና በመልካምነቱ እንዲቀጥልም አበረታተውታል:: ሕግ አስከባሪዎች ለሀገርና ለወገናቸው ሰላምና ደኅንነት ዘብ በመቆም በሀቀኝነት ማገልገልን እንደ ሲራጅ ካሉ ምስጉን ኢትዮጵያውያን መማር ያስፈልጋልም ብለዋል::

ምስጋና የተቸረው የአፋር ክልል ፖሊስ አባል ኮንስታብል ሲራጅ አብደላ ባሳለፍነው ቅዳሜ ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በገንዘብና በመሳሪያ ስጦታ ሊደልሉት ሞክረው ነበር:: ሆኖም ሃገሬን በሚጎዳ ነገር አልደራደርም ብሎ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ኢትዮጵያውያንን ከጥፋት መታደግ ችሏል::

የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎቹ ኮንስታብል ሲራጅ አብደላ የያዙትን የጦር መሳሪያ እንዲያሳልፍላቸው የ40 ሺህ ብር እና አንድ የጦር መሳሪያ ጉቦ ሰጥተው ለማለፍ ቢደራደሩትም፤ ባለመሆኑ ወደ ሌላ ቦታ ሊዘዋወር የነበረ 29 ክላሽንኮቭ ከ25 ካርታ ጋር በቁጥጥር ስር አውሏል።

በዚህን መሰሉ አኩሪ ተግባሩ የአፋር ክልል መንግስት በትናንትናው እለት ለኮንስታብል ሲራጅ አብደላ የ50 ሺህ ብር ስጦታና የማዕረግ ዕድገት እንደሰጠው ታውቋል::

አዲስ አበቤ ሲሸበብ፤ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስና ወልድያ ትናንት በሠላማዊ ሰልፎች ደመቁ

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አንድነት ለመበታተን የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያወግዙ ሠልፎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ትናንትም ተካሂደዋል::

ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውኔ ጥቃት በማውገዝ በእምነቱ ተከታዮች የተቃውሞ ሰልፍ ከተካሄደባቸው ስፍራዎች መካከል፤ የአማራ ክልል መዲና የሆነችው ባህርዳር፣ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልዲያ እና ምሥራቅ ጎጃም ደብረ ማርቆስ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ::

የሰልፉ ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያኗ በኃይማኖት አባቶች እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው ወጥተዋል። ሰልፉ ላይ እየተሰሙ ከተሰሙ ድምጾች መካከል፤ ”በቤተ-ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች ይቁሙ፣ ጥፋተኞች ለሕግ ይቅረቡ” የሚሉ ይገኙበታል።

ከፍተኛ ንቅናቄ በታየበት በደብረ ማርቆስ ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ ከሚያስተባበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በሪሁንተስፋዬ እጅግ በርካታ ሰዎች ፣ ሰልፍ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንደተጠናቀቀና ”የቅዱስ ሲኖዶስ ድምጽ ይሰማ” ፣”የቤተክርሰቲያን እና የኦሮቶዶክሶዊያን መገደል ይቁም” የሚሉ መፈክሮች ጎልተው እንደተሰሙ ለቢቢሲ ገልጸዋል::

የተለያዮ የአማራ ክልል ከተሞች ባለፈው ሳምንት እሁድ እና ትናንት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚያወግዙ ታላላቅ ሠላማዊ ሰልፎችን ሲያካሂዱ የዋና ከተማዋ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዝምታ ፍርሃት ውስጥ ተሸብበው መክረማቸው መላው ኦርቶዶክሳዊያንን አበሳጭቷል::

በተለይ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እናቋቁማለን በሚል የፖለቲካ አጀንዳ ኦዴፓ ከተማዋን ለመጠቅለል ያለውን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ከጀርባ ሆኖ ግልጽ የሆነ እንቅስቃሴ የሚታወቀው የአዲስ አበባ ነዋሪ እጅ መስጠቱ ምዕመኑን አሳዝኗልም፣ አስቆጥቷልም::

“መደመር “የተሰኘው የዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ በአማርኛና ኦሮምኛ ሊወጣ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ” መደመር” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት አዲስ መጽሐፍ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በገበያ ላይ እንደሚውል ታወቀ::

የመደመር ፍልስፍናን ይዘው ብቅ ያሉት የዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ በሦስት መቶብር ለሀገር ውስጥ ገበያ ሲቀርብ ባሕር ማዶ በሠላሳ ዶላር ይሸጣል:: መጽሐፉ 365 ገጾች ሲኖሩት በ አስራ ስድስት ምዕራፎች ተከፍሏል::

ኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ወደ ዴሞክራሲ መሄድ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳየው መጽሐፍ ኦሮምኛው ታትሞ የተጠናቀቀ ሲሆን አማርኛው በዚህ ወቅት በሕትመት ላይ እንደሆነ ከምንጮቻችን ተረድተናል:: የእዚህ መጽሐፍ ገቢ በገጠር ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያ በዕርዳታነት ይውላል ተብሏል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “እርካብና መንበር”ን ጨምሮ የተለያዮ መንፈሳዊ መጽሐፎችን ጽፈው ለሕትመት እንዳበቁ በቅርቡ በሸገር ራዲዮ በነበራቸው ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል::

ራይድ እና ዛይ ራይድ በስያሜ ባለቤትነት መብት ዳግመኛ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጠረ

ከፈጠራ ባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ ራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት እና ዛይ ራይድ ሜትር ታክሲ  መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተከሰተ::

ከአራት ወራት በፊት ራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት የስያሜው መብት ባለቤትነት መብት ይገባኛል በማለት ለአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት እና ለንግድ ውድድር እና ሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን ማመልከቻ አስገብቶ ነበር:: ይህንንም ተከትሎ በባለሥልጣን መ/ቤቱ ምርመራ ተጀምሯል::

ራይድ የሚለው ቃል በራሱ አገልግሎትን የሚያመላክት ገላጭ ቃል እንጂ ስያሜ መሆን የሚችል አይደለም በማለት የሚከራከሩት የዛይ ራይድ ሜትር ታክሲ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ታደሰ ከራይድ አንድ ዓመት ቀድመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ይገልጻሉ::

ይህ እውነት ባለበት የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ለራይድ ከአንድ ዓመት በፊት የንግድ ስያሜ ባለቤትነት ማረጋገጫ መፍቀዱ አግባብ አለመሆኑን እያወቅን ያለው ገበያ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብረን ለመስራትና ለመነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ሲሉ አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ::

የራይድ ትራንስፖርት ባለቤቶች ዛይ ራይድ የሚለው ስያሜ ከእኛ ጋር በመመሳሰሉ ደንበኞች ላይ መደናገርን በመፍጠሩ አንዳንዶችም በቀጥታ እኛ እየመሰልናቸው ወደ ሌላኛው ተቋም እየሄድን ስለሆነ በአስቸኳይ መፍትሄ ሊበጅልን ይገባል ሲሉ ክስና ወቀሳ አሰምተዋል::

LEAVE A REPLY