የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም

በደምበጫው ዘግናኝ የመኪና አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 23 ደረሰ

ትናንት በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን በደምበጫ ወረዳ በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ 16 የነበረው የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ፖሊስ ዛሬ አስታውቋል::

በአሳዛኙ የመኪና አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሰባት ጨምሮ 23 መድረሱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ባለሙያ የሆኑት ምክትል ኮማንደር መሠረት ላቀ አረጋግጠዋል:: በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ 6 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ መሆኑንም አስረድተዋል::

በትራፊክ አደጋው 17 ወንዶችና 6 ሴቶች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን በሕዝብ ማመላለሻ ውስጥ የነበሩት ተሳፋሪዎች የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን የሚናገሩት  ም/ኮማንደሩ፤ ትናንት መስከረም 12 ከሰዓት በኋላ አንድ የጭነት ማመላለሻ አይሱዙ ከሁለት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና አንድ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በመግጨቱ አደጋው መድረሱን አስታውሰው እስካሁን ድረስ አንድ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገለቢቢሲ ገልጸዋል::

የደምበጫ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ ልንገርህ ይታይህ በበኩላቸው ትናንት በወረዳቸው ከቀኑ 6፡30 አካባቢ አደጋው መድረሱን ጠቁመው ፤ ከደምበጫ ከተማ ወደ ፍኖተ ሰላም በሚወስደው ቁልቁለታማና ጠመዝማዛ መንገድ ላይ ልዩ ስሙ “ድፍር ” በሚባል አካባቢ ግጭቱ እንደተከሰተ ይናገራሉ::

ይህንን አደጋ ያደረሰው አይሱዚ ከፍኖተ ሰላም አቅጣጫ ወደ ደምበጫ በቆሎ ጭኖ እየመጣ የነበረ ሲሆን፣ ሁለት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች እና አንድ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ደግሞ ከደምበጫ ከተማ ተነስተው ወደ ፍኖተ ሰላም አቅጣጫ የሚጓዙ ነበሩ:: መኪኖቹ በጠመዝማዛው መንገድ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ተከታትለው ይጓዙ እንደነበር የገለጹት አቶ ልንገርህ በአንደኛው ሚኒባስ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪው ሙሉ በሙሉ መሞታቸውን አረጋግጠዋል::

21ዱ የጉዳቱ ሰለባዎች ሕይወታቸው ያለፈው እዚያው አደጋው የደረሰበት ስፍራ ምንም ዓይነት እርዳታ ሳያገኙ መሆኑን የጠቀሱት ሓላፊው መኪኖቹ ፊት ለፊት ሲጋጩ ተጣብቀው ስለነበር እነርሱን ማላቀቅ በርካታ ሰዓት መውሰዱን ይናገራሉ:: አስክሬኖችን ክፉኛ ከተጋጨው መኪና ውስጥ ለማውጣት ፖሊስና ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን በአደጋው ወዲያው ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 15 ወንዶችና 6 ሴቶች በአደጋው ስፍራ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ለሕክምና ከተላኩ በኋላ ከመካከላቸው አንድ ሴትና አንድ ወንድ ሞተው አስከሬናቸው ወደ ደምበጫ መጥቷል:: የሟቾቹንአስክሬን ማንነት የመለየት ሥራ ፈታኝ እንደነበር የሚገልጹት ሓላፊ በመታወቂያቸውና በሚያውቋቸው ሰዎች እንዲለዩ ተደርጎ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ሁሉም አስክሬኖች ወደ አካባቢያቸው መሸኘታቸውንና ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን ተናግረዋል::

በህዝብ ትራንስፖርት ሲጓዙ ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች በተጨማሪ የደረቅ ጭነት መኪናውና የአንደኛው ሚኒባስ አሽከርካሪዎችም በአደጋው ሕይወታቸው ሲያልፍየሌላኛው የሚኒባስ ሹፌር የአካል ጉዳት ደርሶበት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል ተልኳል:: የባጃጅ አሽከርካሪው ግን ቀላል ጉዳት ስለደረሰበት ሕክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል::

በወረዳቸው ስድስት አምቡላንስ መኖሩን ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ልንገርህ አራቱ ለጥገና ወደ ጋራዥ በመግባታቸው አደጋው ባጋጠመበት ወቅት ሁለት አምቡላንሶች ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አስታውቀዋል::

ተረኛነት የታየበት፣ አከባበሩም የተጋነነው እሬቻ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ

ግልጽ የሆነ የተረኝነት ፖለቲካ እንዲሁም የፊንፊኔ ኬኛ ግልጽ ፍላጎት ታይቶበታል በሚል በበርካታ ኢትዮጵያውያን እየተተቸ የሚገኘው እሬቻን በተጋነነ መልኩ ለማክበር የሚደረገው ሽር ጉድ ተጠናክሮ ቀጥሏል::

ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኦዴፓ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ እሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከናወነው ኤግዚቢሽንና ባዛር በይፋ ተከፍቷል:: በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር በዛሬው ዕለት ለጎብኝዎችና ለተሳታፊዎች ክፍት ሆኗል::

የኦሮሞን ህዝብ ባህል እና ትውፊት የሚያንጸባርቁ አልባሳት፣ የመመገቢያ ዕቃዎች፣ ባህላዊ ልብሶች፣ ባህላዊ ምግቦች እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ቀርበዋል።

እስከ መስከረም 23 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል የተባለው ኤግዚቢሽንና ባዘር የብሔረሰቡን ባሕልና ታሪክ ከማስተዋወቅ አኳያ መልካም ጎን ቢኖረውም  በዚህ ወቅት የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በከረረ ሁኔታ እያስተጋቡ ያሉ የኦሮሞ ልሂቃንን በሕጋዊ ከለለና ጥበቃ የያዘው ኦዴፓ ከሚያደርጋቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ብዙዎች ከአከባበሩ ጀርባ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሊኖር ይችላል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል::

አስቀድሞ ገንዘቡ የተበላው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሀል ክፍል አርማታ ሥራ ተጀመረ

ግንባታው ለዓመታት የተጓተተውና የተሰበሰበው ገንዘብ በአብዛኛው የት እንደደረሰ አለመታወቁ የሚነገርለት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሃል ክፍል የአርማታ ሙሌት ሥራ እንደተጀመረ ተነገረ:: የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም የግድቡ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነም ገልጸዋል።

የሁለቱ ቅድመ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የብረታ ብረት ገጠማ እና ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ ግማሽ ያህሉ ተጠናቋል ያሉት ሓላፊ የግድቡ አካል ከሆኑት አንዱ የሆነው ኮርቻ ግድብ (ሳድል ዳም) ግንባታው ከሁለት ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃልም ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል::

ከ16 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ አለት የተሞላ ሲሆን፥ ኮንክሪት ለብሶ የማጠናቀቂያ እና የለቀማ ሥራ የተከናወነለት ግድብ ሌላኛው አካል የሆነው ዋናው ግድብም በግራ እና በቀኝ በኩል የሚጠበቀው 145 ሜትር ከፍታ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የመሃል ክፍል አርማታ ሙሌት ሥራው እየተካሄደ ይገኛል::

ለታችኛው የውሃ ማፈሳሻ ቦይ የሚያገለግሉ ብረቶች ከውጭ ሃገር በመግባታቸው ከአንድ ወር በኋላም የገጠማ ሥራው ይከናወናል የሚሉት የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣን ፣አሁን ግድቡ አጠቃላይ ግንባታው 68 ነጥብ 3 በመቶ ስለደረሰ በቀጣዩ አመት 750 ሜጋ ዋት ያመነጫል በማለት ገልጸዋል::

በቅርቡ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲ ሲ የግድቡ ግንባታው የተጀመረው ግብፅ በፖለቲካ ቀውስ በተመታችበት ወቅት ነው የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸውን በተመለከተ፤ ሚኒስትሩ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ህዝብን ለማሳመን የቀረበና የተለመደ እንደሆነ በመጠቆም በግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይፈጥር መናገራቸው ይታወሳል::

የለዉጡ ቡድን መንግሥት ብዙ ችግሮች እየተነሱበት የሚገኘውና ከተሰበሰበሰው ገንዘብ ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ብሮች በአምባገነኑ ሕወሓት የሥልጣን ዘመን ተበልቷል የሚባለው የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታን በ2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል::

ቦይንግ ኩባንያ በማክስ 8 ለሞቱ ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 4 ሚሊየን ብር ካሳ ሊከፍል ነው

ከስድስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ከቦይንግ ኩባንያ ለእያንድንዱ ሟች 144 ሺህ 500 ዶላር ካሳ ክፍያ ሊፈጽም መሆኑ ተሰማ::

ኩባንያው በኢንዶኔዢያ ላየን ኤርና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በደረሰው አደጋ ለሞቱት 346 ሰዎች ከቦይንግ የገንዘብ ድጋፍ ፈንድ ወጪ ተደርጎ ለአደጋዎቹ ሰለባ ቤተስቦች እንዲከፈል 50 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል ተብሏል:: በሐምሌ ወር ቦይንግ ይፋ ያደረገው ቀሪ የ100 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ደግሞ ለትምህርትና ለልማት ፕሮግራሞች ይውላል ተብሏል። ገንዘቡን የሚከፍለው አካል የይገባናል ጥያቄዎችን መቀበል የጀመረ ሲሆን ጥያቄዎች ከፈረንጆቹ 2020 በፊት መቅረብ እንዳለባቸውም አሳስቧል::

የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ፤ ገንዘብ ለመስጠት የተወጠነው ሃሳብ መጀመሩ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችን ለመርዳት ኩባንያው ለሚያደርገው ጥረት “ጠቃሚ እርምጃ” ነው ሲሉ ካምፓኒው ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል::

አደጋው ከደረሰባቸው አውሮፕላኖች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በሙሉ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በመርማሪዎች የአውሮፕላኖቹ ደህንነት አስተማማኝነት እስኪረጋገጥ ድረስ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ቦይንግ ሐምሌ ወር ላይ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች ገንዘብ ለመስጠት እንዳሰበ ባሳወቀበት ጊዜ የአንዳንድ ቤተሰቦች ጠበቆች ከቦይንግ የቀረበው ገንዘብ በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ውድቅ በማድረግ በርካቶች ኩባንያው ላይ በፍርድ ቤት ክስ ከፍተውበታል።

ግዙፉ ካምፓኒ ለአደጋዎቹ ሰለባ ቤተሰቦች ሊሰጥ ያዘጋጀውን ገንዘብ የሚከታተሉት የሕግ ባለሙያ ኬኔት ፋይንበርግ እንደተናገሩት፤ ቤተሰቦች ገንዘቡን ሲወስዱ በሙሉ ፈቃዳቸው ሲሆን በኩባንያው ላይ የተናጠል ክስ ለመመስረት ያላቸውን መብት እንዲተዉ የማያስገድድ መሆኑን አስረድተዋል።

የሕግ ባለሙያው ለአደጋው ሰለባዎች የተዘጋጀን ገንዘብ የማከፋፈል ሥራን በመወጣት በኩል ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ዴኒስ ፋይንበርግ ከዚህ ቀደም ካከናወኗቸው ተመሳሳይ ተግባራት መካከል ለአሜሪካ የመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃት ሰለባዎች እንዲሁምዲፕዋተር ሆራይዘን ለተሰኘ የነዳጅ ዘይት ፍሳሽ የቀረቡ የገንዘብ ድጋፎችን በአግባቡ መፈጸማቸው በዋና አስረጅነት ይጠቀሳል::

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ቀዳሚዊት እመቤት ዝናሽ ይታያቸውን ሸለመ

ክልላዊ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለቤት ቀዳመዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከኦሮሚያ ክልል መንግሥታዊ  መሥሪያ ቤት ሽልማት እንደተሠጣቸው ሰምተናል::

ለቀደማዊት እመቤቷ የክብር ሽልማት እና የምስጋና ምስክር ወረቀት ያበረከተው መሥሪያ ቤት  የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ  እንደሆነም ታውቋል::

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው በክልሉ የዘርፉን መስፋፋትና ማደግ ለአደረጉት የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ወረቀት እና የትምህርት ልማት አጋርነት ሽልማት ሊሰጣቸው እንደቻለ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት::

ለቀዳማዊት እመቤቷ ከኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የተበረከተላቸውን የምስክር ወረቀት እና ሽልማት የቀዳማዊት እመቤት የጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፈንታ ዛሬ ተረክበው መለማበረታቻው ምስጋናቸውን አቅርበዋል::

በሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስጦታውን ለቀዳማዊት እመቤቷ ተወካይ ማስረከባቸውን ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ችለናል::

LEAVE A REPLY