የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም

በደመራ በዓል በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ የሆኑ አርማዎችን መያዝ አይቻልም ተባለ

ነገ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሚከበርባቸው ቦታዎች ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን፣ በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ የሆኑ የተለያዩ አርማዎችን ይዞ መገኘት እንደማይቻል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ::

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከናወን ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ በሀገሪቱ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ተከታዮች በጋራ በመሆን ተከባብረውና አንዱ በአንዱ እምነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሳያደርግ የየራሳቸውን እምነት እንዲያስፋፉና በሀገራቸው ሰላም ላይ በጋራ በመሆን መስራት እንዲችሉ እየተሰራ ነው ብሏል::

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ላነሳቻቸው ጥያቄዎች ከፍተኛ ትኩረትና አፅንዖት በመስጠት ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት በማድረግ ጥያቄዎቹ ደረጃ በደረጃ በሰላማዊ መንገድ በፌደራልና በክልል አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ተጀምሯል ያለው ኮሚሽኑ ፤ ይሁን እንጂ መንግስት ጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት የቤተ-ክርስቲያን ጥያቄን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ አካላት ጥያቄውን መስመር በማሳት፤ ህዝበ ክርስቲያኑን ለማሳሳትና የእምነቱ ወግና ስርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ለማስኬድ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ደርሼበታለሁ ሲል አስታውቋል::

በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ስነ-ስርዓት ለማወክ የተዘጋጁ ሃይሎች እንዳሉም መረጃው አለኝ ያለው ፌደራል ፖሊስ፤ ስለሆነም ከበዓሉ ስነ-ስርዓት ውጪ፣ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎች፣ አንዱን የሚያሞግስ ሌላውን የሚያንቆሽሽ ጽሁፍ፣ ብዝሃነትን የማይገልፁ ጽሁፎች በማንኛውም መንገድ ይዞ መገኘት የማይቻል መሆኑን አስታውቋል:: በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ እና የተለያዩ አርማዎችን ይዞ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ መምጣት የተከለከለ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ያረጋገጠው::

የደመራ በዓል ከሚፈቅዳቸው ስነ-ስርዓት ውጪ ሌሎች ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ የደመራ በዓሉን በኮሚቴነት የምታስተባብሩና የምትመሩት አካላት፣ ህዝበ ክርስቲያን እንዲሁም የሃገራችን ወጣቶች ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደረጉ መልዕክት አስተላልፏል::

ኢትዮጵያና ኮሪያ የ63 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

በኢትዮጵያና በኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ መካከል ለአዲስ አበባ ፈጣን የከተማ አውቶቡስ B6 ኮሪደር ፕሮጀክት የሚውል የ63 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት መፈረሙ ተነገረ::

በኢትዮጵያ በኩል በገንዘብ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ስምምነት ዳይሬክተር አቶ ኮከብ ምስራቅና የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ መስፍን መንግስቱ እና በኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የአፍሪካ ቡድን ዳይሬክተር ሚኒስተር ሙን ጃይ ጂኦንግ ስምምነቱን ፈርመዋል::

በአዲስ አበባ B6 ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ሥራ ሲጀምር የመዲናዋን ነዋሪዎች ዘመናዊ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፋፋት እገዛ ይኖረዋል ተብሏል:: ብድሩ በ40 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ሲሆን ፣ 15 ዓመት የእፎይታ ጊዜ ይኖረዋል ተብሏል::

የብድሩ ወለድ መጠን 0 ነጥብ 01 በመቶ እንደሆነ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል:: B6 ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት 11 ነጥብ 05 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ፤ ከመነሻው እስከ መድረሻው በአማካይ በ630 ሜትር ርቀት 17 የአውቶቡስ ፌርማታና ሁለት ተርሚናል ይኖሩታል:: B6 ኮሪደር ከጦር ኃይሎች አደባባይ ተነስቶ በካርል አደባባይ ፑሽኪን አደባባይን በመሻገር ፣ ጎተራን አቋርጦ ወሎ ሰፈርን በማለፍ መዳረሻው ቦሌ ኤርፖርት እንደሚሆን ተሰምቷል::

የኢትዮጵያ እና ሱዳን የንግድ ፎረም ዛሬ በሸራተን አዲስ ተጀመረ

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የንግድ ፎረም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በሸራተን ሆቴል መካሄድ ተጀመረ:: በሁለቱ ሀገራት የንግድ ፎረሙ ላይ የሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች፣ አባሳደሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የንግድ ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር  እንደሚያስችልና ኢኮኖሚያቸውንም እንደሚያሳድግ አብራርተዋል::

የሱዳን የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዋግዲ ሚርጋኒ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሱዳን ሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ፤ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉደዮች ዙሪያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው እና ለዘመናት እርስ በርስ የተቆራኙ መሆናቸውን መስክረዋል::

በአዲስ አበባ 7 ባለ ሰደፍ ክላሽን ኮቭ ጠብመንጃና 2 ማካሮቭ ሽጉጥ በቁጥጥር ስር ዋለ

በኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እየሆነ መጥቷል:: በተለይ እነዚህን ሕገ ወጥ መሣሪያዎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ነው የሚወጡት መረጃዎች የሚያሳዮት::

 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን  እንደገለጸው ከሆነ ሰባት ባለ ሰደፍ ክላሽን ኮቭ ጠብመንጃ፣ 265 ጥይት፣ 2 ማካሮቭ ሽጉጥ ከ22 ጥይት ጋር እንዲሁም 3 የሽጉጥ ካርታዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል::

በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት የጦር መሳሪያዎች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጎሮ ብርሃኑ ሆቴል አካባቢ አንድ ግለሰብ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው::

ኮሚሽኑ በተገኙት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ዝውውር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በመያዝ ምርመራ የጀመረ መሆኑም ጠቁሞ ፤ የጦር መሳሪያዎቹ በትናንትናው ዕለት በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት መያዛቸውን ገልጾ የሠላም ጉዳይ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ መሰል ጥቆማዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል።

እንዲህ ዓይነት የሀገር እና የሕዝብን ሠላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱት ሰዎች ሠላማዊ በመምስል መኖሪያ ቤት ፣ መጋዘን እና የንግድ ቤቶችን በመከራየት ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦች ፣ አከራዮች ይህን ተገንዝበው ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኮሚሽኑ መልዕክት አስተላልፏል::

LEAVE A REPLY