የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም

~ ምርጫ ቦርድ ለአራት ድርጅቶች የዕውቅና እና የስያሜ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰጠ

በፓርቲ ስያሜ ባለቤትነት እና የክልል እንሁን ጥያቄዎች የተጠመደው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ዕውቅና እና የስያሜ ለውጥ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠቱ ተነገረ::

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና እና የስም ቅየራ የተሰጣቸው ፓርቲዎችን ለህዝብ ማሳወቅ አለበት በሚለው የህግ ድንጋጌ መሰረት ፤ የዕውቅና ሰርተፊኬት መሰጠቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል::

በወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው እና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከመጭበርበር የፀዳ ምርጫ ያከናውናል ተብሎ የሚጠበቀው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የስያሜ ለውጥ ሰርተፊኬት እውቅና የሰጠው ለአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ ለኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ፣ ኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና ለጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላም እና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ እንደሆነ ሰምተናል::

~ በተመድ ጉባዔ ላይ ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአማርኛ ለግብፅ ትክክለኛ ምላሽ ሰጡ

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሃገራት የጋራ ሃብት እንጂ የፍጥጫ ምንጭ ሊሆን እንደማይገባ አስታወቁ::

በ74ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ላይ በአማርኛ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን ፤ በማጠቃለያቸው ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት ከእርሳቸው ቀደም ብለው አባይን በተመለከ ለገለጹት ስጋት አዘል አስተያየት ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችውን ግድብ በተመለከተ የሚደረገው ድርድር ውጤት ላይ አለመድረሱ በአካባቢው ላይ አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል ማለታቸው አይዘነጋም::

ለዚህ የግብጹ ፕሬዝዳንት ንግግር ምላሽ በሚመስል ሁኔታ “የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም” ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሃገራቱ የወንዙን ውሃ በጋራ መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል:: የተፋሰሱ ሃገራት የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል::

አብዱል ፋታህ አልሲሲ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ከሰባት ዓመት በፊት በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት የጀመረችውን ግዙፉን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ቅሬታና ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። አሁንም የዓለም ሀገራት መሪዎች ስለሀገራቸውና በተለይ እንዲሁም ስለዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ንግግር በሚያደርጉበት ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የግድቡን ጉዳይ አንስተዋል::

በሚገነባው ግድብ ዙሪያ ለዓመታት እየተካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር ውጤት አለማስገኘቱ እንዳሳሰባቸው ጠቁመው፤ ከግድቡ ግንባታ ባሻገር ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚጀመረውን የውሃ አሞላልና አያያዝን በተመለከተ ለዓመታት የተደረጉትን ውይይቶች እንደተፈለገው ውጤታማ ሊሆኑ እንዳልቻሉ ለጉባኤው ታዳሚዎች ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ ግድቡን ያለ በቂ ጥናት ለመገንባት መነሳቷን አመልክተው በዚህም ሃገራቸው ቅሬታ እንዳልነበራት ፕሬዝዳንቱ ቢገልጹም በወቅቱ በስልጣን ላይ ከነበሩት የግብጽ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር ይታወቃል::

~ የአዲስ አባባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በውሃ አቅራቢዎች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ ነው

የ አዲስ አባባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን “ውሃ በተሽከርካሪ እናቀርባለን “የሚሉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል::

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አምርቶ ለኅብረተሰቡ በማሰራጨት የአገልግሎት ክፍያ እንደሚሰበስብ ይፋ አድርጓል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ስልጣን ያልተሰጣቸው ግለሰቦች “ውሃ እናቀርባለን” በሚል ጥራቱ ያልተጠበቀ እና ከየት እንደተቀዳ የማይታወቅ የውሃ ሽያጭ በስፋት እያካሄዱ ይገኛሉ ሲል እርሱ ሊያካሂድ የሚገባውን ተግባር በሕገ ወጥ ግለሰቦች እየተነጠቀ እንደሚገኝ ተናግሯል::

በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከባለስልጣኑ ዕውቅና ውጭ የሆኑ ግለሰቦች ለሽያጭ የሚያቀርቡት ውሃ የጥራት ደረጃው ያልተረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር ለጤና ጠንቅ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾ ፤ በዚህን መሰሉ ያለፍቃድ ውሃ በመሸጥ ላይ የተሰማሩ አካላትም ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቦ ይህንን ማሳሰቢያ በቸልታ ያለፈ እና በተግባሩ የቀጠለን ግለሰብ በህግ እንደሚጠይቅ አረጋግጧል::

~ ሁሉንም ሥራ ጠቅልለው የያዙት ታከለ ኡማ መስቀል አደባባይን አፀዱ

ከተማዋን የግል ግዛታቸው ያደረጉት ይመስል መንግሥታዊ አስተዳደር  ከሚፈቅደው ሓላፊነት ውጪ ሁሉም ቦታ ላይ የሚገኙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ ደግሞ መስቀል አደባባይ ለጽዳት ተገኝተዋል::

በቀጣይ በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ በዋና ከተማዋ አንድም መቀመጫ እንደማያገኝ ግልጽ ቢሆንም የፊንፊኔ ኬኛን ፖለቲካ የሚያራምደው ድርጅታቸው ኦዴፓ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ፍላጎት ለማሳካት እንዲረዳቸው እና በምርጫ አሸናፊ ለመሆን በእጅጉ እየደከሙ ይገኛሉ::

የነዋሪውን ትኩረት ለመሳብ በሁሉም ተግባራት ላይ በመገኘት በከተማው አስተዳደር ውስጥ የተቋቋሙትን የሙያና የሥራ ዘርፎች ሓላፊነት ነጥቀው የወሰዱት ከንቲባ ዛሬ መስቀል አደባባይ ታይተዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከተለያዩ እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ነበር መስቀል አደባባይን ያፀዱት::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የሚከበረውን የደመራ በዓልን አስመልክቶ የከተማ ነዋሪዎች በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ እንዲያፀዱም አነጋጋሪው ከንቲባ ጥሪ አቅርበዋል:: የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጨምሮ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በዛሬው ዕለት በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

~ ፌስ ቡክ የላይክ ቁጥሮችን ያለማሳየት ሙከራ ዕርምጃውን ዛሬ ጀመረ

ዓለም ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ ኢንስታግራም ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በእያንዳንዱ የፌስ ቡክ የተጠቃሚዎች መልዕክት ስር የተሰጡ የመውደድ (ላይክ) ቁጥሮችን ያለማሳየት ሙከራ እርምጃውን አውስትራሊያ ውስጥ እንደጀመረ ይፋ አድርጓል::

ከመስከረም 16 (ዛሬ) ጀምሮ አውስትራሊያ ውስጥ ያሉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በሌሎች መልዕክት ላይ የተሰጡ የላይክ እንዲሁም ተዛማጅ ምላሽ ቁጥሮችን መመልከት የማይችሉበትን አሠራር በተግባር ላይ አውሏል::

የዘመኑ ተመራጭ ቴክኖሎጂ ፌስ ቡክ አወዛጋቢ የሆነው ውሳኔ የፌስቡክ ተዛማጅ ማኅበራዊ መድረክ በሆነው ኢንስታግራም ላይ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በበርካታ ሃገራት ውስጥ ተግባራዊ ማድረጉ የሚዘነጋ አይደለም::

ለአንድ መልዕክት የሚሰጡ የላይክ ቁጥሮችን ከባለቤቶቹ ውጪ ሌሎች እንዳያዩ የሚያደርገውን እርምጃውን ለመውሰድ የወሰነው ፣ በተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ማኅበራዊ ጫና ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነም ተነግሯል::የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በራሳቸው መልዕክቶች ስር የሚሰጡ የመውደድ ወይም ላይክ ምላሾችን መመልከት ግን ይችላሉ ተብሏል::

የፌስ ቡክ ካምፓኒ ቃል አቀባይ ሚያ ጋርሊክ ለአውስትራሊያ አሶሺየትድ ፕሬስ “የቁጥርን ነገር ከጉዳዩ ስናወጣ፤ ተጣቃሚው ዋና ትኩረትን በተሰጡ የላይክና የሌሎች ምላሾች ብዛት ላይ ሳይሆን በሚደረጉ ምልልሶችና በቀረቡ መረጃዎች ጥራት ላይ ብቻ እንዲወሰን ያደርጋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል::

ድርጅታቸው ይህንን ለውጥ ከማድረጉ በፊት የሥነ አዕምሮ ባለሙያዎችን ማንጓጠጥ እንዲሁም ማስፈራራትን የሚከላከሉ ቡድኖችን ማማከሩንም ቃል አቀባዮ ተናግረዋል::

በተለያዩ ዓለም ሀገራት የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ግን በአንድ መልዕክት ላይ የሚታይ የመውደድ አሃዝ ለሚያገኙት ገቢ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ እርምጃውን ተገቢ ያልሆነ ሲሉ አጣጥለውታል::

 

LEAVE A REPLY