የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም

በቢሾፍቱ መስቀል አደባባይ ደመራው እንዳይበራ ቄሮና ፖሊስ መከልከላቸው ተረጋገጠ

በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ከኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ተነስተው፤ ወደ ደመራ ለመሄድ መንገድ ላይ ሳሉ፤ “ያልተፈቀደ ሰንደቅ አላማ ይዛችኋል” በሚል ማለፍ የተከለከሉ ምዕመናን በክብረ በዓሉ ለተከሰተው ውዝግብ ቄሮ እና ፖሊሶች ዋነኛ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ገለጹ::

የዓደአ ወረዳ ቤተክህነት ጸሐፊ መጋቤ ጥበብ እውነቱ ጥላሁን፤ ከደመራው ዕለት ቀደም ብለው ከከተማው አስተዳደር ጋር በበዓሉ አከባበር ዙሪያ ለመነጋገር ስብሰባ ቢያደርጉም ባለመግባባት እንደተለያዩ ተናግረዋል:: የኢሬቻ እና የመስቀል በዓል በሰላም እንዲያልፍ ከአድባራት ኃላፊዎች፣ ከምንጣፍ አንጣፊ ማኅበራት እና ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን ውይይት ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም “ልሙጥ ባንዲራ መያዝ ትችላላችሁ፣ አትችሉም” የሚለው ውይይት ላይ የሌሎች እምነት ተከታይ ሓላፊዎች መሳተፋቸው ግን አስቀድሞም ቢሆን እንዳልጣማቸው ለቢቢሲ አስታውቀዋል::

ከስብሰባው በኋላ የከተማው ከንቲባ ጠርተዋቸው ይቅርታ እንደጠየቋቸው፣ በሰንደቅ አ ዓላማ ጉዳይ ተነጋግረው፤ ልሙጥ (ኮከብ የሌለው) ባንዲራ መያዝ በሕግ ስለማይፈቀድ፤ ይዘው መውጣት እንደሌለባቸው መስማማታቸውን እንዲሁም የበዓል ማድመቂያ ሪቫኖችን ግን በአደባባይ ላይ አስረው በዓሉ በድምቀት እንዲከበር እንደተስማሙ አረጋግጠዋል::

መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል በቢሾፍቱ የደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሲሆኑ፤ የመስቀል በዓልን ለማክበር በቢሾፍቱ የሚገኙ አድባራት በአጠቃላይ ወደ መስቀል አደባባይ እንደሚወጡ አስታውሰው፤ ሁሉም ቤተክርስቲያናት በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ወደ መስቀል አደባባይ መምጣታቸውንም ይፋ አድርገዋል:: ሆኖም የደብረ መፅሔት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያንን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የለበሱት ልብስ ላይ “ልሙጥ ባንዲራ አለበት” ያሉ የአካባቢው ወጣቶች፤ ዝማሬ የሚያሰሙትን የዕምነቱን ተከታዮች አታልፉም ብለው እንደከለከሏቸውና ወደ መስቀል አደባባይ መሄድ አንዳልቻሉ መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል ይናገራሉ።

ምዕመናኑ እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ተነስተው ወደ ቢሾፍቱ መስቀል አደባባይ መሄድ የጀመሩት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር:: በግምት ከቤተክርስቲያኒቱ 500 ሜትር እንደራቁ ግን ከኅብረተሰቡ የተነጠሉና ራሳቸውን ቄሮ ብለው የጠሩ ወጣቶች “የለበሳችሁት ባንዲራ የተከለከለው ነው” በሚል ሕዝቡን በኃይል አስቁመዋል::

“በመጀመሪያ እነዚህን ወጣቶች እየዘመርን አልፈናቸው ነበር” ያለው የሰንበት ትምህርት ቤቱ አገልጋይ፤ በኋላ ግን የቀበሌ 5 አስተዳደር ፖሊስ ይዘው ሄደው መንገዱን እንደዘጉትና ለሰዓታት ስላስቆሟቸው ፤ “የለበስነው የመዘምራን ልብስ ድሮም እንጠቀምበት የነበረ፣ ቆቡም ድግድጋቱም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው። ይህንን ካላወለቃችሁ አታልፉም አሉን” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል::

“ይህ ምልክት የቀስተ ደመና ምልክት፣ ከመስቀሉ በፊት ነበረ፣ የኖህ ቃል ኪዳን የዳግመኛ አለመጥፋት ምልክት ነው” የሚሉት ደግሞ የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሐፊ ፤ አትሄዱም ብለው ያስቆሟቸው የጸጥታ አካላት እና ቄሮዎች፤ ሰንደቅ ዓላማውን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማዛመድ “የአብን ነው፣ የኢዜማ ነው” ብለው ስላንገላቷቸው የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም አናወልቅም በማለት መስቀል አደባባይ መሄዳቸውን ትተው ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን መመለሳቸውን ገልጸዋል::

የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን መዘምራንና ምዕመናን አለመምጣታቸውን ያስተዋሉ ወደ መስቀል አዳባባይ የሄዱት ሰዎች፤ “አንድ ደብር ጎሎ ደመራ አናበራም” ብለው ወደ ኪዳነ ምሕረት እንደሄዱ የተናገሩት መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል ናበዚህም የተነሳ በቢሾፍቱ መስቀል አደባባይ ደመራውን ሳያበሩ መቅረታቸውን ጠቁመው የፖሊስ ሓላፊውን አናግረው “ምዕመኑ ይመጣሉ” መባላቸውን እና ሳይመጡ ሲቀሩ ግን የተወሰኑ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከመስቀል አደባባይ ተነስተው ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ምዕመናኑን ለማምጣት ማምራታቸውን ይናገራሉ::

የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች የኪዳነ ምሕረት ምዕመናንን አሳምነውም ወደ መስቀል አደባባይ ለመውሰድና ደመራው እንዲበራ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ስላልተሳካ፤ ወደ መስቀል አደባባይ በመመለስ ትምህርተ ወንጌል ተሰብኮ፣ ጸሎት ተደርጎ፣ ወደ ቡራኬ ሊኬድ በሚባልበት ሰዓት፤ በመስቀል አደባባይ የተገኘው ምዕመን “ኪዳነ ምሕረቶች ሳይመጡ ዳመራው አይለኮስም” በማለቱ ምክንያት ጸሎት ተደርጎ፣ ደመራው ሳይለኮስ ትተው እንደሄዱ የዓደአ ወረዳ የቤተክህነት ጸሀፊ እና የደብረ ገነት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ለቢቢሲ አስረድተዋል::

” ጠዋት እንዳየነው ግን ደመራው ተቃጥሏል፤ ማን እንዳደረገው አናውቅም” ያሉት የወረዳው የቤተክህነት ጸሐፊ በበዐሉ እንዲህ አይነት ችግር የታየው በኪዳነ ምሕርት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ቢሾፍቱ አፋፍ ደብረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲይን ጭምር ነው ብለዋል::

የቢሾፍቱ የምንጣፍ አንጣፊ ማኅበራት፤ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ላይ የሥላሴና የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ያለበት ካናቴራ እንዲያወልቁ ተደርገዋል::  ቲሸርቱን አምና ወጣቶቹ ለጥምቀት በዓልም ተጠቅመውበታል የነበረ ቢሆንም ለደመራው በዓል ግን በጸጥታ አካላት በመከልከላቸው ነጠላ ለብሰው ወደ መስቀል አደባባይ ለመምጣት ተገደዋል::

ዛሬ  በበርሊን ማራቶን ያሸነፈው ቀነኒሳ በቀለ ከሞት ተነስቼያለሁ አለ

ከሩጫው መድረክ ጠፍቶ የከረመው የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ ዛሬ በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ላይ ለውድድሩ ክብረወሰን ሁለት ሰከንዶች የቀሩት ውጤት በማስመዝገብ አሸንፏል::

ከማራቶን ክብረ ወሰን ቀጥሎ ሁለተኛው ምርጥ ሰዓት ነው በተባለ 2 ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከአርባ አንድ ሰከንድ በማስመዝገብ ነው ቀኒሳ በርሊን ላይ ድል መቀዳጀት የቻለው::

የዚህን ውድድር ውጤት ከሞት እንደመነሳት ነው የምመለከተው በማለት ከአሸናፊነቱ በኋላ የተናገረው ቀነኒሳ ፤ ለረጅም ጊዜ በህመም ምክንያት ከሩጫ ውድድር እርቆ መቆየቱ እሱንም ሆነ ኢትዮጵያውያንን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከትቶ እንደነበር አስታውሷል::

ወደፊትም በጤናው ላይ ምንም ችግር ካላጋጠመው የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን ለመስበር ተግቶ እንደሚሠራ ያሳወቀው ቀነኒሳ በቀለ ፤ “ህመም ላይ ስለነበርኩ ክብረወሰኑን ለመስበር የሚያስችል በቂ ልምምድ  አላደረግኩም ነገር ግን ጠንክሬ ከሠራሁ በቅርቡ የማራቶን ክብረ ወሰን ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል” ብሏል::

በሴቶቹ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ያሸነፉ ሲሆን አሸቴ በከሬ እና ማሬ ዲባባ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል::

በወንዶቹ ከቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያኑ ብርሐኑ ለገሰ ሁለተኛ እንዲሁም ሲሳይ ለማ ሦስተኛ በመውጣት በሁለቱም ጾታዎች የበርሊን ማራቶን ውድድር በኢትዮጵያዊያን የበላይነት ተጠናቋል። የ37 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ ከዚህ በፊት በተካሄዱ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ክብረ ወሰኖችንም ያሻሻለ ኮከብ አትሌት መሆኑ አይዘነጋም::

በኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ የተያዘው የማራቶን ክብረወሰን ላይ ለመድረስ ሁለት ሰከንዶችን ዘግይቶ ውድድሩን የጨረሰው ቀነኒሳ “አዝናለሁ፤ እድለኛ አልነበርኩም። ነገር ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ ክብረ ወሰኑንም ለመስበር እችላለሁ” በማለት ህልሙን ተናግሯል::

ኹከት ውስጥ በከረመችው ድሬደዋ የዓለም የቱሪዝም ቀን እየተከበረ ነው

ሠሞኑን በተደራጁ ኃይሎች የመሬት ወረራ ስትናጥ በከረመችው ድሬደዋ ከተማ የዓለም የቱሪዝም ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል::

“ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት ”በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ40ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ ነው በዓሉ የከበረው::

ለአንድ ሣምንት በሚቆየው የዓለም የቱሪዝም ቀን የመክፈቻ ስነ ላይም ከፌደራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓል በውይይትና መስህቦችን በመጎብኘት እንደሚከበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል::

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር  በዓሉን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ “ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚከበረው የቱሪዝም ሣምንትም ዘርፉን ለማሳደግና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ለማቆራኘት በሚያግዙ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ይመክራል ብለዋል::

በተያዘው በጀት ዓመትም በቱሪዝም ዘርፍ ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ፤ በድሬዳዋና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙና አደባባይ ያልወጡ ባህላዊ ምግቦች የሚተዋወቁበት ሀገር አቀፍ ፌስቲቫልም በተያያዥነት እንደሚከናወን ሚኒስትሯ አመለክተዋል::

የግመል ሩጫ ውድድር እና የብስክሌት ውድድሮች፣ የኪነ ጥበባት ምሽትና የባህላዊ አልባሳት ምሽት ስነ ስርዓቶች የበዓሉ ማድመቂያ ናቸው:: በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ በህብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ለመስህቦችና መዳረሻዎች እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለዘርፉ እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋልም ተብሏል::

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባልተገለፀ ምክንያት በቁጥጥር ስር ዋሉ

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ሚዲያ ልማት ዋና መምሪያ ሓላፊ የሆኑት ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር ዋሉ:: ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቤተሰባቸው ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል::

የአማራ ክልል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ለሳምንታት በክልሉ ሥራ አመራር ተቋም ውስጥ በስልጠናና በግምገማ ላይ እንደቆዩ የተናገሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ ምናልባት እስሩ የተከሰተው ከዚሁ ስልጠናና ግምገማ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል::

 አሁን ላይ ኮሚሽነሩን ለእስር የዳረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ አንድ የቤተሰብ አባል የተናገሩ ሲሆን፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንዳንድ ሰዎች ግን ጉዳዩ ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ባህርዳር ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጋር የተያያዘ ንክኪ ሳይገኝባቸው አይቀርም ይላሉ::

ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ ከጥቂት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በተመለከተ ከአንድ የቤተሰብ አባላቸው ለማረጋገጥ ቢቻልም ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የጸጥታ ሓላፊዎች ግን እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም::

LEAVE A REPLY