የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም

ለኢሬቻ የተዘጋጀውን ግዙፍ ጭኮ ወጪ መንግሥት ካልሸፈነ ለሕዝቡ በቅናሽ እንደሚሸጡ ባለ ሀብቱ ገለፁ

በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ እና የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ኦሮሞዎችን የሚያገናኘው የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ፤ እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው:: የኢሬቻ ክብረ በዓል በኦሮሞዎች ዘንድ ከሚከበሩ የተለያዩ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በትውልዶች መካከል ሲወርድ እንደመጣም ይነገራል፡፡

በዚህ አመት በአዲስ አበባ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የኢሬፈና (ምስጋና የማቅረብ ሥነ ሥርዓት) ስፍራ በፍልውሃ አካባቢ እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ አካባቢውን የማስተካከል ሥራ ተከናውኗል። በዚህ በዓል ላይ ለመታደም ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከአፋር፣ ከሱማሌ፣ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ሌሎች ክልሎች የሚመጡ ተሳታፊዎች ይታደሙታል ተብሏል::

ዛሬ መስከረም 23 የተከናወነውን የዋዜማ ፕሮግራም ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሎም ይጠበቃል:: ከእነዚህ መካከል አራት ሺህ ሜትር የሚረዝም ጭኮ፣ የሙዚቃ ድግሶች በሚሌኒየም አዳራሽና በስታዲየም፣ እንዲሁም የሲዳማ የቄጠላ ባህል (ባህላዊ ጭፈራ)  ትዕይንት ዋነኞቹ ናቸው::

በመስቀል አደባባይ የጭኮ ዐውደ ርዕይ፣ የቄጠላ ጭፈራ፣ የፈረስ ጉግስ እንዲሁም ሌሎች የባሕላዊ ምግቦችና አልባሳት ትርዒት ይካሄዳል:: ክብረ በዓሉ ላይ ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ተሳፈታፊዎች ወደ አዲስ አበባ መጓዝ የጀመሩት ከቀናት በፊት መሆኑን ሲሆን በአጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል::

በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከ15 እስከ 20 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች [ፎሌዎች] እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን የሰላም ማስከበሩን ሥራ በሓላፊነት የሚሰራ ኮሚቴም ተዋቅሯል ተብሏል። በትናንትናው ዕለትም የኢሬቻ በዓልን ምንነት ማስረዳት ላይ ያተኮረ ፎረም በሸራተን አዲስ ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ምሁራንና አባገዳዎች ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር የታደሙ ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር የሆኑት ሒሩት ካሳው ባደረጉት ንግግርም “የብሔር ብሔረሰቦች ባህል ከሌለ የኢትዮጵያ ባህል የምንለው አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም የሕዝቦችን መቀራረብ ለማጠናከርና የሀገሪቱን ቱሪዝም ለማበረታታት ይህንን መሰሉ ባህላዊ ፌስቲቫሎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ተናግረዋል::

አባ ገዳዎችና አደ ሲንቄዎች የኢሬቻ ባህልን ጠብቀው ወደዚህ ትውልድ በማስተላለፋቸው አመስግነው፤ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

4000 ሜትር የሚረዝም ጭኮ የኦዳራ ኢንተርናሽናል ካፌ ባለቤት የሆኑት አቶ ድንቡ አብደላ፤ የኢሬቻ ክብረ በዓል ወደ አዲስ አበባ መመለሱን አስመልክተው አበርክተዋል:: “የድርሻዬን ልወጣ ብዬ ነው” ያሉት ባለሀብት እስካሁን ‘ረዥሙ ነው’ የተባለውን ጭኮ ለማዘጋጀት በዚህ መንፈስ መነሳታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ጭኮን ለምን እንደመረጡ ሲያስረዱም “ይህ ትልቅ ሕዝብ ምን ባህላዊ ምግብ አለው? በምን ይታወቃል? ብለን አምስት ባህላዊ ምግቦችን ከዘረዘርን በኋላ ጭኮ በድሮ ጊዜ በጦርነት ወቅት እንደ ስንቅ ተይዞ የሚኬድ ስለነበር፣ ከዚያ አንጻር መርጠነዋል” ብለዋል።

ይህን 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ጭኮ ለማዘጋጀት 49 ኩንታል ገብስ፣ 3538 ኪሎ ግራም ቅቤ ጥቅም ላይ መዋሉን የጠቆሙት አቶ ድንቡ፣ በቀን 300 ሜትር ያህል ጭኮ ሲሰራ መሰንበቱን፤ በሥራው 18 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ሥራውም 29 ቀናት ፈጅቷል ብለዋል::

ይህንን ረዥም ጭኮ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ መታሰቡንም የሚናገሩት አቶ ድንቡ፤ ይህን ጭኮ መንግሥት ወጪውን ሸፍኖ ለተሳታፊዎች በነፃ የማያቀርብ ከሆነ እነርሱ በተመጣጣኝ ዋጋ በእለቱ ለመሸጥ ማሰባቸውን ገልጸዋል።ይህንን ጭኮ ለማዘጋጀት ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ግን ባለሀብቱ አልተናገሩም።

አሜሪካ በአባይ ጉዳይ ምክንያት የሌለው መግለጫ አወጣች

በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የመሙላት ሂደትንና አጠቃቀም ላይ ትብብር፣ ዘላቂነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን በተመለከተ እየተደረገ ያለውን ድርድር አሜሪካ እደግፋለሁ አለች:: ከኋይት የፕሬስ ጽህፈት ቤት ሐውስ በወጣና ዝርዝር ጉዳዮችን በማይጠቅሰው አጭር መግለጫ ላይ ነው ይህ የተባለው::

 “ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት በምጣኔ ሃብት የመልማትና የመበልጸግ መብት አላቸው ፤ አስተዳደሩ [የአሜሪካ] ሁሉም አገራት እነዚህን መብቶች ሊያስከብር የሚችልና የእያንዳንዳቸውን የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያስከብር በጎ ፈቃደኝነትን የተላበሰ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ያቀርባል” ይላል መግለጫው::

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ክፍል ይህንን መግለጫ ከምን ተነስቶ እንዳወጣ የገለጸው ነገር የሌለ ሲሆን ተጨማሪ የሰጠው ማብራሪያም የለም። ይህ መግለጫ ምናልባትም ዛሬና ነገ ካርቱም ውስጥ የሦስቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያደርጉታል ተብሎ ከሚጠበቀው ቀጣይ የሦስትዮሽ ውይይት ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይገመታል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኒውዮርክ ላይ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችውን ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር ውጤት ላይ አለመድረሱ በአካባቢው ላይ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚያው መድረክ ላይ ለግብጹ ፕሬዝዳንት ንግግር ምላሽ በሚመስል ሁኔታ “የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም” በማለት ሃገራቱ የወንዙን ውሃ በጋራ መጠቀም አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል:: ፕሬዝዳንቷ አክለውም የተፋሰሱ ሃገራት “የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ” በንግግራቸው ላይ አንስተዋል።

ባለፈው መስከረም 3 እና 4/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ባለስልጣናት ካይሮ ላይ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ በተከታታይ እያደረጉት ያለው የሦስትዮሽ ውይይት መካከል አንዱ የሆነው ካይሮ ላይ የተካሄደ ቢሆንም ያለስምምነት ተጠናቋል:: የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከካይሮው ድርድር በኋላ አዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ አዲስ ሃሳብ እንዳቀረበችና ኢትዮጵያ ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገች ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ግብጽ ያቀረበችው ሃሰብ፤ የግድቡ የውሃ የሚሞላው በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያም ይህ የግብጽ ሃሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ ዋነኛ የተፋሰሱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ወንዝ ውሃን አጠቃቀም የተመለከተውን “የመርህ ስምምነት የጣሰና ጎጂ ግዴታን የሚያስቀምጥ ነው” በማለት እንደማትቀበለው አሳውቃለች። ሚኒስትሩ በተጨማሪም ይህ የቀረበው ሃሳብ “ግብጽ የወንዙ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 40 ቢልየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለችውም” ብለዋል።

በግድቡ የውሃ አሞላልና የመልቀቅ ሂደት ዙሪያ ያሉትን ሁኔታዎች እንዲያጠና የተቋቋመው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን 5ኛ ስብስባውን ካርቱም ሱዳን ውስጥ ሰኞ እለት አካሂዶ የነበረ ሲሆን፤ ቡድኑ ዛሬ መስከረም 23 እና 24/2012 ዓ.ም እዚያው ካርቱም በሚካሄደው የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል

የኦነግ ባንዲራ ይዘው የሚጨፍሩ ቄሮዎች በአዲስ አበባ በግልጽ ታዮ

በአዲስ አበባም ሆነ በቢሾፍቱ በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከአባ ገዳ ባንዲራ ውጪ የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እንዳይያዝ ተወስኗል ቢባልም ዛሬ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ከአዲስ አበባ በተለያዮ ቴሌቪዥን ቻናሎች ላይ በርከት አርማዎች ታይተዋል::

በተለይ የፋና ቴሌቪዥን ላይ በመስቀል አደባባይ ላይ ወጣቶች የኦነግ ባንዲራን ይዘው ሲጨፍሩ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ በተደጋጋሚ ታዝበናል :: ሁኔታው ያበሳጫቸው ኢትዮጵያውያንም እየተከበረ ያለውን ፖለቲካዊ ድባብ የታቀፈው ኢሬቻና ኦነግን የሚያረጋግጡ የፍቶ ማስረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየለቀቁ ይገኛሉ::

በአንድ ሀገር ሁለት ሕዝብ ያለ ይመስል የመስቀል በዓል ላይ በተለይም ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ልሙጡ የኢትዮጵያ ባንዲራ እንዳይውለበለብ ያገደው መንግሥት የኦነግ አርማን ለይምሰል አግጃለሁ ቢልም በፋና ቴሌቪዥን ላይ ግን አርማው እየተጨፈረበት በግልጽ ሲውለበለብ መላው ሕዝብ ተመልክቷል::

በአዲስ አበባ እና በደብረ ዘይት የሚከበረው የኢሬቻ በዓልአስተባባሪ ኮሚቴ እና የቱለማ አባ ገዳ የሆኑት ጎበና ሆላ   የኦነግ ባንዲራ በከተሞቹ ላይ እንዳይታይ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረው ነበር:: ባንዲራው የግጭት መንስዔ እንዳይሆንና ኢሬቻ ከፖለቲካ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ስለሆነ እንዳይቀላቀል ሲሉ ውሳኔውን ማሳለፋቸውን አባገዳው መግለጻቸው ይታወሳል::

ቀደም  ሲል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ባንዲራ የኦሮሞ ሕዝብ የትግል ዓርማ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ በፊትም ቢሾፍቱ ላይ ሲካሄድ በነበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ክልክል ሆኖ ይዞ የተገኘ ግለሰብ በሕግ ይጠየቅ እንደነበር አይዘነጋም::ይታወሳል።

LEAVE A REPLY