ሽመልስ አብዲሳ አማራን ነፍጠኛ በማለት ጽንፈኛ ብሔርተኛ መሆናቸውን በአደባባይ አሳዮ
የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በመስቀል አደባባይ የኢሬቻን በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት አማራውን ነፍጠኛ በሚል በይፋ ዘልፈዋል::
ፕሬዝዳንቱ ጃዋር መሐመድና አክራሪ ብሔርተኞች የሚያስተጋቡትን የግጭት እና የጥላቻ ንግግር በማሰማት የተረኛነት ፖለቲካ አራማጅነታቸውን አሳይተዋል::
የአማራ ሕዝብን ነፍጠኛ ብለው የተቹትና አዲስ አበባ የኦሮሞ መሆኗን ያመላከተ ንግግር ያሰሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለውጡ ላይ ተስፋ ባደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የስጋት ውሃ ደፍተውበታል:: አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት ንግግር ምን ይዘት እንዳለው ሕዝብ እንዲረዳ ወደ አማርኛ ተርጉመን በዚህ መልክ አቅርበነዋል::
“ይኸው ለዚህ በቃን
የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብ፣
የተከበራችሁ የገዳ አባቶች፣
የሲቄ እናቶች ፣
ቄሮ እና ቀሬ ፣ የህዝባችን ጋሻዎች፣
እንኳን ድል አደረግን ፣ እንኳንም እዚህ ደረስን ፣
የተከበራችሁ ሚኒስቴሮች ፣ አምባሳደሮች ፣ በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ እዚህ የተገኛችሁ አካላት ፣ ብሔር ብሄረሰቦች ፣ ከሁሉም በላይ የደቡብ ህዝቦች ክልል መንግስት ፣ የጋምቤላ መንግስት ፣ ቤንሻንጉል ፣ አፋር ፣ የሶማሌ መንግስት ፣ የአማራ ክልል መንግስት ፣ እዚህ የተገኛችሁ ብሔር ብሄረሰቦች ፣ ይህ በዓል በዓላችን ነው ብላችሁ እዚህ ስለተገኛችሁ ታላቅ ምስጋና ላቅርብላችሁ ፣ ክቡር ሁኑ ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እዚህ ነበር የተሰበረው፤ እዚህ ነበር መዋረድ የጀመረው፤ እዚህ ነበር ቅስሙ የተሰበረው፡፡ ቱፋ ሙናን፣ የዚያን ዘመን ታጋዮች የነፍጠኛ ስርዓት እዚህ ነበር የሰበራቸው፡፡ ዛሬ የሰበረንን ሰብረን፣ ከመሰረቱ ነቅለን፣ ከመሰረቱ ነቅለን ኦሮሞ በተዋረደበት ቦታ ተከብሮ ይገኛል፡፡
ኦሮሞ እንኳን ድል አደረክ፡፡ የ150 ዓመት ትግል ፣ ሃይለማርያም ገመዳ ፣ ዋቆ ጉቱ፣ ታደሰ ብሩ ፣ የኦሮሞ ታጋዮች በሙሉ የተሰበሩበት፣ በእልህ የታገሉለት፣ ሌት ተቀን የለፉለት ፣ ኦሮሞነት (ኦሮሙማ) ወደቦታው እንዲመለስ የደከሙት፣ ዛሬ የኦሮሞ ታላላቆች በከፈሉት መስዋእትነት፣ በተለይም ቄሮ እና ቀሬ ስናይፐር ፊት ቆመው ታግለው ኦሮሞን ዛሬ የድል ባለቤት አድርገዉት ይገኛሉ፡፡ ይህ ድል የግለሰቦች አይደለም ፣ይህ ድል የተወሰኑ ቡድኖች አይደለም፤ ይህ ድል የኦሮሞ ሕዝብ ድል ነው፡፡ ኦሮሞ እንኳን ድል አደረክ፡፡ ያለፉት ስርዓቶች የኦሮሞ ማንነት እና ምንነት እንዲሰበር፣ የኦሮሞ ማንነት በነበረበት ቦታ ላይ ሌላ ነገር ገነቡ፡፡ የኦሮሞ ምልክት በነበረበት ሌላ ነገር አስቀመጡ፣ ሌላ ስም አወጡለት፡፡ ሆኖም ሊቀብሩት አልቻሉም፤ ሆኖም ሊቀብሩት አልቻሉም፤ ሆኖም ሊያስቀሩት አልቻሉም፡፡ የኦሮሞ እዉነት ተነስቶ ተናገረ፤ የኦሮሞ እዉነት ተነስቶ ቆመ፡፡
እንኳን ድል አደረግን!”
የሠላምና ፍቅር ነው በተባለው ኢሬቻ በዓል ላይ ቄሮ ሜንጫና ገጀራ ይዞ ወጣ
ሠሞኑን ከመጠን በላይ አከባበሩ የተካበደው እና ፖለቲካዊ ይዘትን የተላበሰው ኢሬቻ በርካታ አወዛጋቢና ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ክስተቶች እያሳየ ይገኛል::
ከ150 ዓመት በኋላ በፊንፊኔ በዓሉን ልናከብር ነው በሚል የተዛባ ትርክት የተቃኘው ኢሬቻ ከባህላዊ ዕምነቱ ባፈነገጠ መልኩ ይልቅ በጽንፈኛ ብሔርተኖች ፖለቲካ አጀንዳ ተጠልፎ ሲወድቅ ታይቷል::
የበዓሉ ብቸኛ ምንጭ የሆነው የኦሮሞ ማኀበረሰብን የሚወክለው እና የማዕከላዊ መንግሥቱን በበላይነት ጨብጧል ተብሎ የሚታማው የጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኦዴፓም ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በማኅበረሰቡ ላይ የሚስተዋለው የተረኝነት ስሜት እሬቻ ላይ እንዲፀባረቅ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል እየተባለ ነው::
ሰሞኑን በአዲስ አበባ እንደታየው ብዛት ያላቸው ቄሮዎች የተከለከለውን የኦነግ አርማ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መታየቱን ተከትሎ በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ሕዝብ እያለ ነው በማለት ሥርዓቱን ተቃውመዋል::
ዛሬ እንደታየው ደግሞ ጥቂት ቄሮዎች የአዲስ አበባን ለፀብ የሚጋብዝ ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽመዋል:: በተለያየ ግሩፕ ውስጥ ሆነው የሚጨፍሩ ወጣቶች የኦነግ አርማን በተለያዮ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ከመቀባታቸው ባሻገር ሜንጫ እና ገጀራ ይዘው በመውጣት የሌላውን ኅብረተሰብ ስብዕና የሚነካ ዜማ ሲያሰሙ ታዝበናል::
ኢሬቻ የፍቅር እና የሰላም በዓል መሆኑ እየታወቀ ወጣቶቹ በዛ መንፈስ ጸብ ቀስቃሽ መሣሪያዎችን ይዘው ሲወጡ የጸጥታ ኃይሎች ድርጊቱን ለማስቆም አለመሞከራቸው እንቅስቃሴው በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ እንዲፀባረቅ አካል ድጋፍ አለ የሚል ጥርጣሬንም ፈጥሯል:: በተለይም የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ ከኦሮሚያ ክልል በመጡ ሰዎች በብዛት እንዲዋቀሩ መደረጉ የአሠራር ዝርክርክነት እንዲታይ አድርጓል::
600 ነጥብ ያመጡ የአማራ ክልል ተማሪዎች ገንዘብና ላፕቶፕ ተሸለሙ
በአማራ ክልል በ2011ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው 600 እና ከዛ በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች በባህር ዳር ከተማ ሽልማት ተሰጣቸው::
በሽልማት ስነ-ስርዓቱ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በክልሉ በመደበኛ እና በማታው መርሃ ግብር የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ 92 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 55 ሺህ 158 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣታቸውን ይፋ አድርገዋል::
በ2010 ዓ.ም 12 ተማሪዎች 600 እና ከዛ በላይ ነጥብ ማስመዝገባቸውን ያስታወሱት ሓላፊው በ2011ዓ.ም ደግሞ 51 ተማሪዎች 600 እና ከዛ በላይ ነጥብ ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከ600 በላይ ነጥብ ላስመዘገቡ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው የ5 ሺህ ብር ሽልማትና በውጤት ቅደም ተከተላቸው በጣም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 23 ተማሪዎች ደግሞ የላፕቶፕ ኮምፒውተር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል::
በሀገር አቀፍ ደረጃ 645 በማምጣት 1ኛ የወጣው ተማሪ ብሩክ ዘውዱ እና 631 ነጥብ በማስመዝገብ በክልሉ ከሴቶች 1ኛ የሆነችው ተማሪ ዳግማዊት በድሉ ሽልማቱ የበለጠ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው እና በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንደሚማሩ ገልጸዋል:: ሽልማቱ በክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ በአማራ ክልል የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም እና በአስራት የትምህርት ሽልማት አማካኝነት የተዘጋጀ ነው::
አመለ ሸጋው የሙዚቃ ፈርጥ ኤልያስ መልካ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
ዝነኛው የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት ኤልያስ መልካ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ተወዳጁሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ የስኳር እና ኩላሊት ህመም ገጥሞት ህክምናውን ሲከታተል ለረዥም ጊዜ ቆይቶ ነበር::
በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ አብነት ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር የተወለደው ኤልያስ መልካ በልጅነቱ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ:: በለጋ ዕድሜያቸው አብረው የሰንበት ትምህርት በወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን እየተማሩ ማደጋቸውን የሚናገረው ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ፣ ፒያኖ እና ጊታር ቤታቸው እየመጣ ይጫወት እንደነበር ትውስታውን ባጋራበት አጋጣሚ ገልጿል::
ኤሊያስ መልካ በአዲስ ከተማ ገነት ወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል እንደነበር ፣ በጣም ተጫዋች፣ የዋህና ቅን እንደነበርም ተናግሯል::
ኤሊያስ መልካ ዕድሜው የአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ኃይሉ ተስፋዬ የሚባል ትምህርት ቤት ከዚያም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ከፍተኛ 7 ትምህርት ቤት ተምሯል። ኤልያስ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በ1987 ዓ.ም ገብቶ የተማረ ሲሆን በዋናነት ቼሎ አጥንቷል። ኤሊያስ ሙዚቃን ማቀናበር የጀመረው በገና ስቱዲዩን ያቋቋመ ሲሆን በሙያው ታታሪና ጎበዝ እንደነበር አብረውት የሠሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አመለ ሸጋው ሙዚቀኛ በዋናነት ሊድ ጊታር ከመጫወት ባለፈ የሙዚቃና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ነበር።በመዲና፣ ዜማ ላስታስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ውስጥምተጫውቷል:: ኤሊያስ መልካ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ በኦሮምኛ ሙዚቃ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የድምፅና የቅኝት አደራደሮች ላይ የሠራው አነስተኛ ጥናት በዘርፉ ተጠቃሽ መሆኑን መምህራኖቹ ይመሰክራሉ::
በቅርቡም ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን አውታር የተሰኘ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ ሠርቶ ማስተዋወቁ ይታወሳል።ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎችና ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ያረጋገጡለት ከያኒ ነበር።
“ሙዚቃ ከነሙሉ ክብሯ በኤሊያስ በኩል ታልፋለች” ሲሉ የሚመሰክሩለት ባለሙያዎች፣ የድምጻዊ ቴዲ አፍሮን “አቦጊዳ” ፤ የሚካኤል በላይነህን በ”አንተ ጎዳና” የዘሪቱ ከበደን የሙዚቃ ሰንዱቆች ያቀናበረው ኤሊያስ መልካ ነው።
የሚኪያ በኃይሉን “ሸማመተው” የእዮብ መኮንንን “እንደ ቃል”፣ የጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኃይሌ ሩት፣ አረጋኽኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤን፣ ትዕግስት በቀለ፣ የትግርኛ ዘፋኝዋ ማህሌት ገብረ ጊዮርጊስ፣ ጌቴ አንለይ፣ ቼሊና ኤሊያስ የጥበብ አሻራ ካረፈባቸው ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ኤሊያስ መልካ በተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሕብረ ዝማሬዎችን ያቀናበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል መላ መላ፣ ማለባበስ ይቅር፣ ለአፍሪካ ሕብረት፣ በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮሩት ሙዚቃዎች ዋነኞቹ ናቸው።
ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያው ኤሊያስ መልካ ትዳር ያልመሰረተ ሲሆን፣ በተለያዩ ሥራዎቹ የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናን ከተለያዩ ወገኖች አግኝቷል። እስከ ባለፈው ቅዳሜ ድረስ በፋና የድምፃውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል ቆይቷል::
የዮንቨርስቲ ምደባ በመጠናቀቁ ተማሪዎች ዮንቨርስቲዎቻቸውን ማወቅ ይችላሉ ተባለ
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በሙሉ የዩኒቨርሲቲ ምደባ በመጠናቀቁ ከአሁንጀምሮ መመልከት ይቻላል ተባለ::
ተማሪዎች በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ዌብ ሳይት www.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉ ነው የተነገረው፡፡ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ2012 የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብን ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም::
በያዝነው ዓመት በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ የሚያገኙ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ 46 ሺህ 416፣ ሴት 32 ሺህ 865 በድምሩ 79 ሺህ 281 ሲሆኑ ፥ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ወንድ 34 ሺህ 838 ሴት 28 ሺህ 702 በድምሩ 63 ሺህ 540 መሆናቸው ታውቋል::
ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገቡ ተማሪዎች 55 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ፥ 44 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ ወደ መንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር 142 ሺህ 821 ነው።
የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች መግቢያ አራት መሰረታዊ የትምህርት አይነቶችን ውጤት መሠረት አድርጎ እንደሚወሰን መገለጹ ይታወሳል።የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥቡ የሚቆረጠው በእንግሊዝኛ፣ በሂሳብ፣ የስኮላስቲክስ አፕቲቲዩድ፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ በፊዚክስ፣ ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ በጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነቶች ነው።
የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በአራት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ እንዲወሰን የተደረገው የጋሸበና የተጋነነ የፈተና ውጤት በመታየቱ መሆኑን የትምህርት ሚስቴርና የክልል የትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል::
ለቤተ መንግሥቱ የዕድሳት ባለሙያዎች ምንም ዓይነት ክፍያ አልተፈጸመም
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከገቧቸው ቃልኪዳኖች መካከል አንዱ ታላቁን ቤተ መንግሥት አድሰው ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነበር። በዚህ መሠረትም በቅርቡ የተለያዩ ግንባታዎች እና ዕድሳት የተካሄደበትን ቤተ መንግሥት የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ ሲያስጎበኙ በመገናኛ ብዙኃን መታየታቸውም ይታወሳል::
ከመስከረም 30 ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል በተባለው በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የዕድሳት እና የአረንጓዴ መናፈሻውን ሥራ ከሚሠሩት ባለሙያዎች መካከል የቅሪተ አካል ተመራማሪዋ መስከረም አሰግድና በሥነ ጥበብ ባለሙያው ኤሊያስ ስሜ የሚመራው ቡድን ዋነኛው ነው::
የዞማ ቤተ መዘክርን ሃሳብ የጠነሰሱት መስከረም አሰግድ፤ ከሥራ ባልደረባቸው ኤሊያስ ስሜ ጋር በመሆን በርካቶችን ያስደመመውን የቅርጻ ቅርጽና የዞማ አፀድ ሠርተው ለሕዝብ ዕይታ አብቅተዋል:: በአሁኑ ወቅት እሱን የማጠናከር አላማ እንዳላቸው እና ቤተ መዘክሩ “በቅቶታል” የሚባል ደረጃ አለመድረሱን ያስረዳሉ::
እነዚህ የጥበብ እጆች ታዲያ በዚያው ተወስነው ብቻ አልቀሩም። አሻራቸውን ለማሳረፍ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጥሪ ቤተ መንግሥትም ጎራ ብለዋል::
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጉብኝት ወደ ዞማ ቤተ መዘክር ጎራ ባሉበት ጊዜ በሥራው ከመደመማቸው የተነሳ የአዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤትን ገጽታ እንዲለውጡላቸው ጥያቄ አቅርበው ሊያሳዩዋቸው ይዘዋቸው መሄዳቸውን የምታስታውሰው መስከረም ፤ እነሱም ሥራቸውን ወዲያው እንደጀመሩና እሱን በመሥራት ላይ ሳሉ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሥራ እንዲሻገሩ በድጋሚ መጠየቃቸውን ገልጻለች::
የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀ የምትናገረው መስከረም “እሱን ካሳመርን በኋላ በቀጥታ ቤተ መንግሥቱን እንድናስውብ ጠየቁን፤ እናም በማግስቱ ወደ ሥራው ገባን” በማለት አጋጣሚውን ለቢቢሲ አብራርታለች:: ቤተ መንግሥቱ ካረፈበት 40 ሺህ ካሬ ሜትር፤ 15 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆነው የግቢውን አካል እነ መስከረም እየተጠበቡበት ናቸው::
መስከረም ለቤተ መንግሥቱ እንግዳ አይደ፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ በአውሮፓ ኅብረትአማካኝነት ከሌሎች አምባሳደሮች ጋር ለእራት ግብዣ ወደ ቤተ መንግሥት አቅንተው ነበር። ይሁን እንጅ የሄዱት በምሽት ስለነበር ግቢው ምን እንደሚመስል የማየት እድሉን አላገኙም። “ቀጥታ ወደ እራት ግብዣው ከዚያም ወደ መኪና ነበር” ያመራሁት ትላለች:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ግን ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ተጋብዘው፤ ግቢውን በሙሉ ዞረው ጎብኝተዋል፤ ጠቅላይ ሚንስትሩም ከባለሙያዎቹ አስተያየት እየጠየቁ ሲወያዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።
“አንድ መንግሥት ቤተ መንግሥት የሕዝብ ነው ብሎ ለመክፈት ማሰቡ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፤ ለዘመናት አጥሩን ነበር እኮ የምናየው” ሲሉ በወቅቱ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ። ወደ ሥራው በደስታ የገቡት ባለሙያዎቹ የተሰጣቸው ቦታ የሌሎች ግንባታዎች ትራፊ ቁሳቁሶች የሚጣልበት፤ ምንም ያልለማ ተዳፋት መሬት በመሆኑ የመጀመሪያ ሥራቸው ቦታውን ማፀዳት ነበር::
የመጀመሪያ ዲዛይናቸውን የሠሩትም በእነዚሁ ከሌሎች ግንባታዎች በተራረፉና በተጣሉ ድንጋዮች ነበር። ይሁን እንጅ የቦታው አቀማመጥ ተዳፋት በመሆኑና ወቅቱ ክረምት ስለነበር ሥራቸውን ፈታኝ አድርጎባቸው ነበር።ቦታው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ለሁሉም ምቹ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።
የውሃ ተፋሰሱንና መሬቱን ካስታካከሉ በኋላ ወደ ግንባታ የገቡት ባለሙያዎቹ፤ እያንዳንዱ ድንጋይ በተለያዩ አገር በቀል በሆኑ እፅዋቶች፤ አበባ፣ በቅጠላ ቅጠል እንዲሁም በተለያዩ ቅርፆች አምሳያ እየተጠረቡ እንደተሠሩ ይናገራሉ።በባለሙያው ኤሊያስ እየተሳሉ፣ በጠራቢዎች እየተጠረቡ ከአገር በቀል እፅዋቶች በተጨማሪ የድንጋይ ቅርጾቹ ግቢውን እንዲያስውቡት ተደርገዋል ብለዋል::
የድንጋዩ ንጣፍ እንዳይፈነቀልና ለዘመናት እንዲቆይ ድንጋዮቹ እየተበሱና ከሥራቸው በብረት እየተሳሰሩ የተሠሩ ናቸው።የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን የመጎብኘት እድል የነበራት መስከረም፤ “ሥራው ከዚህ የተቀዳ ነው፤ አልተቀዳም ብሎ መናገር አይቻልም ፤ ምናልባት ከአስተዳደጌም ሆነ ካየኋቸው መካከል የተከማቸ እውቀት ሊሆን ይችላል ፣ ዋናው የማምንበት ጉዳይ በጥራት በኩል ድርድር እንዳማይደረግ ነው። ለዘመናት የቆዩ እንደ ፋሲለደስ ያሉ ሃገራዊ ቅርሶችን በማንሳት ጥቃት ቢደርስባቸውም እስካሁን ድረስ ሊቆዩ የቻሉት ጥራት ስላላቸው ነው” ስትል ገልጻለች።
“ለነገ ተብለው ስለተሠሩ፤ ሲፈርሱ ቢውሉ ምልክታቸውን አልተውም” ስትል የሚሰሩት ሥራዎች ጥራት እንዲኖራቸው ያስገነዝባሉ። እንደ መስከረም አባባል አገር በቀል እጽዋቶች ስለተተከሉ፣ አረንጓዴ በመሆኑ፣ በእጅ መሠራቱ፣ በኢትዮጵያ ጥበብ መሠራቱ፣ ባለሙያዎቹ አገር ያፈራቸውና ከየገጠሩ የመጡ በመሆናቸው ሥራውን ለየት ያደርገዋል ።
“ያ እጅ የተረሳ እጅ ነው፤ ይህ ጥበብ እንዳለው ያልታወቀ ሕዝብ ነው። ወደታች ሲታዩ የነበሩ ጠበብቶች ናቸው የሠሩት፤ በእነርሱ መሠራቱም ልዩ ያደርገዋል” ትላለች። ቅማመ ቅመም፣ መድኃኒት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፤ እንደ ግራር፣ ወይራ እና የመሳሰሉት አገር በቀል ዛፎች መኖራቸውም ሌላው ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በየቀኑ እንደሚጎበኟቸው የሚናገሩት ባለሙያዎች “ፍቅር፣ ድጋፍ ነው የሚሰጡን፤ ባላቸው ደቂቃ ተሻምተው ብቅ ብለው ያዩናል፤ ሞራል ይሰጡናል። ‘እጃችሁ ይባርክ!’ እያሉ ነው የሚሄዱት፤ እኔ ስለ ፖለቲካ የማውቀው ነገር የለም፤ ግን እንደዚህ ዓይነት መሪ አለ እንዴ?” በማለትይጠይቃሉ።
ከዚህ የተነሳ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚሠሩት ሥራ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እንደሚተጉ ይናገራሉ። እነርሱ እንደሚሉት ስለ ክፍያ አስበውም፤ ተጨንቀውም አያውቁም “ጥሪ ሲቀርብልን እኔና ኤሊያስ ባንክ ያለንን ገንዘብ አይተን ብቻ ነው የገባነው” ይላሉ። “ስለ ገንዘቡ ጨርሶውኑ ማሰብ አልፈልግም፤ ሥራውን በጥራት ሠርተን ማስረከብ ብቻ ነው” ብለዋል።በሥራቸው ከ200- 250 ሠራተኞች እንዳሉ የገለጸችው መስከረም “ከመንግሥት ክፍያ የሚፈጸመው ለእነርሱ ደምወዝ እንጂ፤ እኛ ሙያችንን በነፃ ነው የሰጠናቸው” ሲሉ ለሙያቸው የሚከፈላቸው ክፍያ እንደሌለ ይፋ አድርገዋል::