የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም

ሌሊሳ ዴሲሳ ከ18 ዓመት በኋላ የማራቶንን ክብር በወርቅ ሜዳሊያ  ወደ ኢትዮጵያ መለሰ

ኢትዮጵያ በአለም ሻምፒዮና የወንዶች የማራቶን ውድድር ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ በሌሊሳ ዴሲሳ አማካኝነት ወርቋን አገኘች:: በካታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ቅዳሜ እኩለ ሌሊት በተካሄደው የማራቶን ውድድር ሌሊሳ ዴሲሳ አንደኛ፤ ሞስነት ገረመው ደግሞ ሁለተኛ ሆነው ለኢትዮጵያ ወርቅና ብር አስገኝተዋል። ኢትዮጵያ በጎርጎሳውያኑ 2001 ካናዳ ኤድመንተን በተካሄደው የማራቶን ውድድር በገዛኸኝ አበራ ወርቅ ማግኘቷ ይታወሳል።

ሌሊሳ 2፡10፡40 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ያጠናቀቀ ሲሆን የራሱን የዓመቱን ምርጥ ውጤትም አስመዝግቧል። በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረገ የሚናገረው ሌሊሳ “ለአራት ወራት ያህል ራሴን ለውድድሩ ሳዘጋጅ ነበር፤ በተለይም አዳማን በመሳሰሉ ሞቃት ቦታዎች ልምምድ አድርጌያለሁ” ካለ በኋላ “ድሉ የኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ነው”ብሏል።

ሁለተኛ የወጣው ሞስነት ገረመው በአራት ሰከንዶች ተቀድሞ ነው ሁለተኛ የወጣው። ከውድድሩም በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃል ” ወርቅ አገኛለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን ከግማሽ ውድድር በኋላ ጎኔ ላይ ህመም እየተሰማኝ የነበረ ቢሆንም ሌሊሳን ብቻውን ላለመተው ስል ነው ውድድሩን ያጠናቀቅኩት ብሏል።

በውድድሩ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በከፍተኛ ሁኔታ በስሜት ተውጣ ታይታለች::

ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ የነሐስ ሜዳልያ አግኝቷል።ከኢትዮጵያዊያኖቹ በተጨማሪ ይህንን ውድድር በመፈራረቅ ሲመሩ የነበሩት ኤርትራዊው ዘረ ሰናይ ታደሰን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካዊ፣ ኬንያዊና እንግሊዛዊ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ አንዳቸው ወርቅ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር:: ዘረሰናይ ታደሰ ውድድሩን ስድስተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ሰባ ሦስት ሯጮች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር አስራ ስምንቶቹ አቋርጠው የወጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያዊው ሙሌ ዋሲሁን አንዱ ነው:: ምንም እንኳን ኳታር ውስጥ ያለው ሙቀት ከፍተኛ ቢሆንም የሙቀት መጠኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ውድድሮች የተሻለ መሆኑን በዶሃ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ታዝቧል።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተደረገው በዚህ ውድድር 29 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድና 48 በመቶ ወበቅ (ሂሚዩዲቲ) የነበረ ሲሆን የሴቶች ማራቶን ውድድር በተካሄደበት ወቅት 33 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀትና 80 በመቶ ወበቅ (ሂሚዩዲቲ) ደርሷል::

በዶሃ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የመጀመሪያ ቀናት ላይ በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጵያ ሴት ሯጮች በአስቸጋሪው የአየር ሁኔታ ምክንያት ውድድሩን ለማቋረጥ መገደዳችው የሚታወስ ነው።

ሌሊሳ ከአንድ ሳምንት በኋላ ኒውዮርክ በሚደረገው የማራቶን ውድድር እንደሚሳተፍ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ውድድር ማካሄድ ትችላለህ ወይ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ “ማገገም ከቻልኩ፤ አዎ እሳተፋለሁ” ብሏል። በዶሃ እየተደረገ ባለው የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ባገኘቻቸው የሜዳልያ ብዛቶች አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ጃማይካና ቻይናን ተከትላም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እስካሁን ባሉ ውድድሮችም ሁለት ወርቅ፣ አራት ብርና አንድ ነሃስ በማግኘት በአጠቃላይ ሰባት ሜዳልያዎችን አግኝታለች::

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2012  የሥራ ዘመኑን ነገ ይጀመራል

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ነገ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ይከፈታል::

በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የምክር ቤቶቹን መከፈት ካበሰሩ በኋላ የመንግስትን የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ የሚያመላክት ንግግር ያደርጋሉ::

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጽህፈት ቤት ሓላፊ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ከምክር ቤቶቹ አባላት በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እና ሌሎች እንግዶች በስነ ስርዓቱ  በእንግድነት ይታደማሉ ብለዋል። ከመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ በመቀጠል ሁለቱ ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ የጋራ መደበኛ ስብሰባቸውን ያካሂዳሉ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስራ ዘመኑ ከመደበኛ ስብሰባዎች በተጨማሪ የቋሚ ኮሜቴዎችና ሌሎች የምክር ቤቱን እንቅስቃሴዎች በመገናኛ ዘዴዎች በቀጥታ በማስተላለፍ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለማስፈን እንደሚሠራ ማሳወቁ አይዘነጋም::

ምክር ቤቱ በሥራ ዘመኑ ጥራትን፣ ተናባቢነትና ተፈፃሚነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ለውጡን ሊደግፉ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን ይሠራል ነው የተባለው::

በ2011 ዓ.ም በዋና ኦዲተር ከቀረበለት የሪፖርት ግኝት በመነሳትም የተጓደሉ አሠራሮችን ፈተሾ በማስተካከልና የሃብት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ላይ ምክር ቤቱ ያተኩራል።በሥራ ዘመኑ ሀገራዊ ምርጫና የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በተሣካ ሁኔታ እንዲከናወን የፀደቁ አዋጆችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተፈፃሚነታቸውን በጥልቀት ይከታተላል ተብሏል::

ዓላማውን የሳተው ሆራ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ አስገራሚ ትዕይንቶች ታዩበት

የሆራ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ በድምቀት ተከብሯል:: ትናንት በአዲስ አበባ ዛሬ ደግሞ በቢሾፍቱ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ለዘመናት በተከበረበት ቢሾፍቱም ባህላዊ አከባበሩ በፖለቲካዊ አጀንዳ ተጠልፎ ታይቷል::

በሆራ አርሰዴ ማለዳው ላይ በአባገዳዎች ምርቃት የምስጋና በዓሉ ተጀምሯል። ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፥ በበጋ ወቅት በከፍታ ቦታ ላይ የሚከበረው ወይም ኢሬቻ ቱሉ ሲሰኝ እንዲሁም በፀደይ ወቅት መግቢያ ላይ በወንዝ ዳር የሚከበረው ደግሞ ኢሬቻ መልካ በመባል ይታወቃል::

ዛሬ የተከበረው ኢሬቻ መልካ የኦሮሞ ህዝብ የክረምት ወቅት ማለፉንና የጸደይ ወቅት መምጣቱን አስመልክቶ ለታና አደይ አበባን በመያዝ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ባህላዊ በዓል ነው፡፡

ይህ ክብረ በዓል በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ሲሆን፣ የኦሮሞ ህዝብ የማንነቱ መገለጫ የሆነውን በዓል በአንድ ላይ ተሰብስቦ በየዓመቱ የመስቀል/ጉባ/ በዓልን ተከትሎ ባለው የመጀመሪያ እሁድ ቢሾፍቱ በሚገኘው ሆራ አርሰዲ ያከብራል፡፡

በዓሉን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተወላጆች በደማቅ ስነ ስርዓት ያከብሩታል:: ትናንትና በአዲስ አበባ በዓሉ በተመሳሳይ ሁኔታ በድምቀት ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል። ይሁንና በትናንትናው ዕለትም ሆነ ዛሬ በቢሾፍቱ በዓሉ ሲከበር ግልጽ የሆነ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ሲንፀባረቅ ታዝበናል::

ዛሬ በቢሾፍቱ ከተሞች በግልጽ እንደታየው ከኢሬቻ ምስጋና ይልቅ አማራን ነፍጠኛ እያሉ መሳደቡ በበርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ይመስላል:: በተለይ ትናንትና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት አማራን የሚዘልፍ ንግግር በዓሉን ለፖለቲካ ተልዕኮ መጠቀም ለሚፈልጉ ምቹ አጋጣሚን እንደፈጠረላቸው ታውቋል::

የመስቀል በዓል የደመራ ስነ ስርዓት ላይ የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የለበሱት ልብስ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም አለው በሚል የከተማዋ የመስቀል አደባባይ ፕሮግራም ያስተጓጎሉት ቄሮዎች የኦነግ አርማን በነጻነት ሲያውለበልቡ ታይቷል::

ወጣቶቹ በከተማዋ በሚገናኙ መዝናኛ ሥፍራዎችም ይህንን ለይስሙላ ተከልክሏል የተባለውን አርማ ይዘው ድርጅቱን በማወደስ ሲጨፍሩም አንዳች ከልካይ አለመኖሩን ታዝበናል::

ግብፅ በአባይ ጉዳይ አሜሪካና ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጠየቀች

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ለሁለት ቀናት ያህል መስከረም 23፣ 24 2012 ዓ.ም በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ያደረጉትን የሦስትዮሽ ምክክር ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲገቡ ጥሪ አቀረበች::

ግብፅ የሦስትዮሽ ስምምነቶቹ ምንም ዓይነት ውጤት ባለማምጣታቸው ዓለም አቀፍ አደራዳሪ እንዲገባ ጥሪ ማድረጓን ተከትሎ ኢትዮጵያ በበኩሏ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበልም አስታውቃለች።

በሱዳን መዲና ካርቱም የተደረገውን የሦስትዮሽ ውይይት ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የግብፅ የሦስተኛ ወገን ጥሪ እስካሁን በሦስቱ አገራት ላይ የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጫማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል ብሏል::

የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በሱዳን በኩል ተቀባይነት የሌለውና በአገራቱ መካከል ያለውን ዘላቂ ትብብር የሚጎዳ፣ በአገራቱ መካከል የነበሩ ቴክኒካዊ ውይይቶችን ዕድል ቦታ ያልሰጠ እንዲሁም የነበረውን የውይይት መንፈስ የሚያጠለሽ ነው ሲል መግለጫው ያጣጥላል::

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ግብፅ ያቀረበችውን አደራዳሪ ሃሳብ እንደማይቀበሉት የገለፁ ሲሆን “ለምንድን ነው አዲስ አጋሮች የሚያስፈልገን? ስምምነቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ይፈለጋል ማለት ነው?” በማለት መናገራቸውም ተሰምቷል።

ግብፅ ማን አደራዳሪ ይሁን በሚለው ላይ ምንም ባትልም የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ፤ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የመሙላት ሂደትና አጠቃቀም ላይ ትብብር፣ ዘላቂነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን በተመለከተ እየተደረገ ያለውን ድርድር እንደምትደግፈው አሜሪካ ከውይይቱ በፊት መግለጫ ማውጣቷ አይዘነጋም::

ይህ የተገለጸው ከኋይት ሃውስ የፕሬስ ጽህፈት ቤት በወጣና ዝርዝር ጉዳዮችን በማይጠቅሰው አጭር መግለጫ ላይ ሲሆን፤ መግለጫው የወጣበት ምክንያትም አልተገለጸም።

በዚህ አጭር መግለጫ ላይ “ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት በምጣኔ ሃብት የመልማትና የመበልጸግ መብት አላቸው” ይልና ሲቀጥል “አስተዳደሩ [የአሜሪካ] ሁሉም አገራት እነዚህን መብቶች ሊያስከብር የሚችልና የእያንዳንዳቸውን የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያስከብር በጎ ፈቃደኝነትን የተላበሰ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ያቀርባል” ይላል።

ከውይይቱም በኋላ የግብፅ ፕሬዚዳንት ግብፅ በናይል ላይ ያላትን መብት ለማስጠበቅ ቁርጠኝነት እንዳላት አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ በፌስቡክ ገጸቸው ላይ እንዳሰፈሩት ” ግብፅ በናይል ላይ ያላትን መብት ለማስጠበቅ በፖለቲካዊ ምክክር እንደምትቀጥልና በዓለም አቀፉ ሕግጋት ማዕቀፍ ሥር አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጉዳይ ከግብፅ በኩል ለፖለቲካ ምክክር እንዲቀርብ ኃሳብ መቅረቡ የጉዳዩን መፍትሔ ያላገናዘበ፤ የሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ለመፍታት ቴክኒካዊ ምክክር አስፈላጊነቱን በተመለከተ የሰጡትን መምሪያ የጣሰና መፍትሔም እንደማያመጣ ኢትዮጵያ በምላሹ ገልፃለች።

ውይይቱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በትዊተርና ፌስቡክ ገፁ እንዳሰፈረው በህዳሴ ግድብ ሙሌትና መለቀቅ ላይ የሚደረጉ ስምምነቶችን ለማስቀጠል እንደሚፈልግና ከሁለቱም አገራት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

አስራ አንዱ የናይል ተፋሰስ አገራት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያለምንም ጉዳት የሚጠቀሙበትና ኢትዮጵያም ከውሃ ኃብቷ በመጠቀም ሕዝቦቿ የሚጠቀሙበትን መንገድ ለመቀየስ እንደምተሠራ ተገልጿል:: ኢትዮጵያ የትኛውንም ዓይነት ያለመስማማቶችም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በሦስትዮሽ ውይይቶች ለመፍታት እንደምትሠራ ብትናገርም ከግብፅ በኩል የሚሰሙት ውይይቶቹ ፍሬ አልባና ወደየትም የማያስኬዱ ናቸው የሚሉ ናቸው።

ባለፈው መስከረም 3 እና 4/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ባለሥልጣናት ካይሮ ላይ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ባደረጉት የሦስትዮሽ ውይይት፤ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ በተናጠል ያቀረበችው ሃሳብ በኢትዮጵያ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው።የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከካይሮው ድርድር በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ አዲስ ሃሳብ እንዳቀረበችና ኢትዮጵያ ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገች ተናግረዋል።

ግብፅ በተናጠል ያቀረበችው የውሃ ሙሌቱን አለቃቅ ሰነድ ከአገራቱ ማዕቀፍ ትብብር ያፈነገጠና እየተካሄዱ ያሉ ስምምነቶችን የሚቃረን ነው ተብሏል። እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ግብጽ ያቀረበችው ሃሳብ የግድቡ የውሃ የሚሞላው በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያም ይህ የግብጽ ሃሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ ዋነኛ የተፋሰሱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ወንዝ ውሃን አጠቃቀም የተመለከተውን “የመርህ ስምምነት የጣሰና ጎጂ ግዴታን የሚያስቀምጥ ነው” በማለት እንደማትቀበለው አሳውቃለች። ሚኒስትሩ በተጨማሪም ይህ የቀረበው ሃሳብ “ግብጽ የወንዙ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 40 ቢልየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለችውም” ሲሉ ተናግረዋል::

ግድቦቹን ለመሙላት የሚያስፈልገው 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ብታስቀምጥም ግብፅ በበኩሏ የውሃ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጥ ጠይቃለች። ግብፅ የህዳሴ ግድብ መገንባት በየአመቱ የምታገኘውን 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሊቀንሰው እንደሚችል ስጋቷን ደጋግማ በመናገር ላይ ነች::

ሳዑዲ አረቢያ ጥንድ ፍቅረኞች ያለ ጋብቻ ወረቀት ሆቴል መከራየት እንዲችሉ ፈቀደች

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ወደ አገሪቷ የሚመጡና ያልተጋቡ የውጭ አገር ዜጋ ጥንዶች ሆቴል ተከራይተው አንድ ላይ ማሳለፍ እንደሚችሉ አስታወቀ::

በአገሪቷ የወጣውን አዲሱን የቪዛ ሕግ ተከትሎ ነው ፍቃዱ የተሰጠው:: ሕጉ የሳዑዲ አረቢያ ሴቶች በሆቴል ውስጥ ብቻቸውን ማሳለፍ እንደሚችሉም አረጋግጧል። ከዚህ ቀደም ጥንዶች በሆቴል ለማሳለፍ በጋብቻ የተሳሰሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸው ነበር በወግ አጥባቂዋ ሳዑዲ አረቢያ:: ሕጉ መሻሻል የአገሪቷ መንግሥት ጎብኝዎችን ለመሳብ የወሰደው እርምጃ እንደሆነ ነው የተነገረው::

ቀደም ሲል ጥንዶች በጋብቻ መተሳሰራቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ካላቀረቡ ሆቴል መከራየት እንደማይችሉ የሚከለክለው ሕግ አሁን ላይ ለውጭ አገር ዜጎችበሥራ ላይ ውሏል::

የአገሪቷ የቱሪዝምና ብሔራዊ ቅርስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ “ማንኛውም የሳዑዲ ዜጋ ሆቴል ለመከራየት የቤተሰብ መታወቂያ አሊያም የግንኙነታቸውን ሁኔታ ማረጋጋጫ እንዲያሳዩ ይጠየቃሉ” ሲል ያስረዳል:: ይሁን እንጂ ይህ ሕግ ከውጭ አገር ለሚመጡ ጎብኝዎች፣ የሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች መታወቂያ በማሳየት ብቻ ሆቴል መከራየትና በክፍሎቹ በነፃነት ማሳለፍ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል::

የተሻሻለው የቪዛ ሕግ እንደሚያትተው የውጭ አገር ሴት ጎብኝዎች በአለባበሳቸው ሙሉ በሙሉ እንዲሸፈኑ ባይገደዱም የሰውነት ክፍላቸውን የማያጋልጥ እንዲለብሱም አሳስቧል::

የአልኮል መጠጦች መጠጣት ግን የተከለከለ  መሆኑ ቀጥሏል:: በ’ኢንድፔንደንት’ ጋዜጣ ኤዲተር የሆኑት ሳይመን ካልደር የቪዛ የሕጉ መሻሻል ወደ አገሪቷ የሚገቡ ጎብኝዎችን ቁጥር ሊያሳድገው ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዓለማችን ሃብታም ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳዑዲ አገሪቷን ለጎብኝዎችና ለባለሃብቶች ምቹ ለማድረግ ሕጎቿን እያለዘበች ትገኛለች።

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በቅርቡ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩና ያለምንም ጠባቂ ሴቶች ከአገር ውጭ ጉዞ እንዲያደርጉ የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ በጣም የከረሩ ሕጎች ላይ የተወሰነ ማሻሻያ ቢያደርግም ሳዑዲ አረቢያ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጅ ግድያ ጋር በተገናኘ አሁንም በብዙ ሃገራት በመተቸት ላይ ነች::

LEAVE A REPLY