ኤልያስ መልካ ይቆጨኛል! || መስከረም አበራ

ኤልያስ መልካ ይቆጨኛል! || መስከረም አበራ

በሃገራችን የሙዚቃ ታሪክ “ወርቃማው ዘመን” የሚባለው ከሰባዎቹ መጀመሪያ እስከ ሰማኒያዎቹ ጅማሬ ያለው ዘመን እንደሆነ ሰርፀ ሲተነትን ሰምቻለሁ።

በዚህ ዘመን የወጡ ሙዚቃዎች መንገድ ላይ እየሄደ ለሚሰማቸው ከመንገድህ ቆም ብለህ አድምጣቸው የሚያሰኙ፣ ካፌ ውስጥ ሂሳብ ከፍሎ ሊነሳ ያለውን ሊያስቀምጡ የሚዳዳቸው፣ ስራየ ብሎ የከፈታቸውን “rewind” በተንን ደጋግመው የሚያስጭን አንዳች መስህብ ያላቸው ናቸው።

ከቅንብራቸው፣ዜማቸው፣ከዜማቸው የግጥማቸው መልዕክት ውበት፣ ጥልቀት፣ ምጥቀት አጃኢብ ነው! ከዚህ አጃኢብ ጀርባ አበበ መለሰ፣ ይልማ ገብረአብ፣ አለምፀሃይ ወዳጆ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ አድፍጠዋል!

የእነዚህ እንቁዎችን የጥበብ ዛር ሰብሰብ አድርጎ ያወረደበት፣ ተከታያቸው እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ብቃት የታደለው፣ እንቁው ኤልያስ መልካ ነበር። ኤልያስ ያቀናበረውሙዚቃ ከመግቢያው ጀምሮ ልብ የሚሰርቅ ነገር አለው፤ እስኪያልቅ ድረስ ወዴትም ሂዱ ሂዱ የማያስብል ሃያል መስህብ ጭምር።

ግጥሞቹ ሰም እናወርቅ ሳይባሉ ቅኔ ያዘሉ፣ ቁምነገር የተሞሉ፣ ራቅ ብለው የሄዱ፣ ሁልጊዜ የማይፃፉ የክት ናቸው። ዜማዎቹ ያሬድ ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ፣ ዜመኝነትም በዘር እንደሚሄድ ተጨማሪ ማመሳከሪያ ናቸው!

እንደው በጥቅሉ ኤልያስ መልካ ጥበብ ያዳላችለት፣ በርከክ ብላ እጅ የሰጠችው ሰው ነበረ!!! እንደፈለገ ይቀኝባታል፣ እንዳሻው ይነግስባታል፣ መልኳን በቀየረ ቁጥር ከነገሰባት በላይ ነግሶ፣ ከመጠቀው በልጦ ይመጥቅባታል።

ይህ ሁሉ የሚሆነው ለካ የሚወዳት ጥበብ አካሉን እየገዘገዘችው ነበር፣ አካሉን በልታ መንፈሱን የምታደምቀው! የአንዳንዴ የወደዱት ነገር በፍቅር ሸፍኖ ፍላፃውን ይልካል። የወደዱት በሽፍን ይገድላል!

ኤሊያስ ስቱዲዮ ቁጭ ብሎ ሌት እናቀን ተፈራርቀው፣ እሱ እዛ የጥበብ ገዳም ውስጥ እንደመሸገ ቀኖችም እንደሚሸኛኙ አንድ ወዳጁ የፃፈውን አነበብኩ። ይህን ሳነብ ባንፈልገውም የሰማነውን ሞቱን፣ በአፈር የሚያስረጀው ልክፍቱ መነሻው ይሄው ምስጠቱ ይሆን? አልኩኝ።

የነፍስ እርካታ ስጋን አይረዳም። እንቁው ልጅ ኤሊያስ ለነፍሱ ጥሪ እርካታ ረዥም ቀን እና ለሌሊት መቀመጡ በስተመጨረሻው አንጀት በሚበላ መልኩ ስጋውን ላከሳው ላገረጣው ህመም አሳልፎ ሰጥቶት ቢሆንስ?!! ስጋ የነፍስ ጥማት አይገባውም፤ ለነፍስ ጥሪ ሲጓዙ ስጋ ሊጎዳ ይችላ፣ ሊታመም ይችላል፣ በስተመጨረሻም ብዙ ይዞ ከነከባድ ይዘት ማንቀላፋት ይመጣል።

ኤልያስ ነገ የለም እንደተባለ ሁሉ ዛሬ የሰፈረበትን የጥበብ ሸክም ለማቃለል ሌት ተቀን በጥበብ ገዳም መንኖ፣ ውስጡ እየተበላ ውስጣችንን ያረሰረሰ ለጋስ ልጅ ነው! ዛሬ እንዲህ እሱን የማይመስል መልክ እስኪያመጣ በከባዱ ተይዞ ባለበት ሰዓት እንኳን ከጥበብ ማዕድ ላለመጉደል ህመሙን ንቆ ሲታገል አይቼ ፈጣሪ እንዲምረው ከልቤ ተመኝቼ ነበር። አልሆነም!

ኤልያስ እንደዚህ ጠቋቁሮ በቲቪ በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ሲታይ ነፍሱን ብቻ ለማርካት እስከመቃብር የሚጨክን ልጅ እንደሆነ ታዝቤያለሁ። ትናንት ደግሞ ሰርፀ በፋና ቲቪ ቀርቦ ጭራሽ የስቱዲዮ ቁሳቁሱን ቀይሮ በአዲስ መንፈስ ለስራ ሲታጠቅ እንደነበረ ሲናገር ስሰማ የመንፈስ ጥንካሬውን አድንቄያለሁ፣ ለመኖር ምኞት እንደነበረውም ተረድቼ ሃዘኔ ብሷል!

የሞት ቀይ መብራትን እያዩ ችላ ብሎ ለስራ መታጠቅ ነፍስን ብቻ ማድመጥን ይፈልጋል! ለመኖር እያለሙ ገና በጠዋቱ በሞት በደለኛ ሳያስቡት መታነቅ ምንኛ ክፉ ነው? ህመሙን ለብቻው ታሞ፣ ማንም ለብቻው የሚሞተውን ሞት መጎንጨቱም አሳዝኖኛል! ለምን አልተረባረብንለትም? የሚል ውለታቢስነትም ተሰምቶኛል፣ የዘመን ተጋሪ የሙያ አጋሮቹን መታዘቤንም አልደብቅም። አበበ መለሰን ለማዳን ቀደም ያለው ትውልድ አርቲስቶች እንዴት እንደተረባረቡ የሚታወቅ ነው። የሆነው ሆኖ የትውልዴን እዳ የሰረዘው ኤልያስ መልካ ይቆጨኛል!

LEAVE A REPLY