ኢዜማ በሽመልስ አብዲሳ የአደባባይ ዝልፊያ ላይ ነገ መግለጫ እንደሚሰጥ አንዷለም አራጌ ገለጹ
ሠሞኑን በተነሱት ግጭቶች እና የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር በሰጡት ኹከት ቀስቃሽ ዙሪያ የዜግነት ፖለቲካንየሚያራምደው እና በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ኢዜማ ነገ ጋዜጣዊ መግለጫ መግለጫ እንደሚሰጥ ኢትዮጵያ ነገ አረጋግጣለች::
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣውን የጽንፈኝነት ፖለቲካን እንዲሁም በአማራ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶችን አለመቆጣጠሩን ተከትሎ ከተለያዮ ወገኖች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግፊት እየደረገበት መሆኑ ይታወቃል::
በዚህ መሠረት ከቅማንት ህዝብ ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ቀውስ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በመስቀል አደባባይ ላደረጉት ንግግር በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ኢዜማ በነገው እለት መግለጫ እንደሚሰጥ ሪፖርተራችን ዘግቧል::
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የአማራን ሕዝብ ነፍጠኛ ብለው የተሳደቡበት እና የአዲስ አበባን ባለቤትነት ወደ ኦሮሚያ ያሻገሩበት ግጭት ፈጣሪ ንግግር የኢዜማ አመራሮችን በእጅጉ ያስቆጣ መሆኑን የገለጸው ሪፖርተራችን በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ለሥራ ጉዳይ የሚገኙት የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አንዱአለም አራጌ በጉዳዮ ላይ ፓርቲያቸው አቋሙን ለመንግሥት እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በነገው ዕለት ለማሳወቅ መወሰኑን መናገራቸውን ታማኝ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል::
የሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካ ስንብት ሲካሄድ የሙያ አጋሮቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተሳናቸው
የሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካ የስንብት መርሃ ግብር በዛሬው እለት በብሄራዊ ቴአትር ተካሂዷል፡፡ ቀብሩም በጴጥሮስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል:: በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተርም የተለያዮ የሙያ አጋሮቹን አነጋግሮ መረጃውን አድርሶናል::
በመርሃ ግብሩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዩን ጨምሮ ቤተሰቦቹ ፣ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተካሂዷል ። የሙዚቃ ፈርጡ ኤልያስ መልካ ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 24 2012 ዓ.ም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።
የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት የሆነው ኤልያስ መልካ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያኖረ አርቲስት መሆኑ አይዘነጋም::ኤልያስ መልካ የስኳር እና ኩላሊት ህመም ገጥሞት ህክምናውን ሲከታተል ቆይቷል።
እስከ መስከረም 17 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ኤልያስ መልካ በፋና ላምሮት የድምጻውያን ተስጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግልም ነበር:: ኤልያስ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ ጊታሪስት፣ ፒያኒስት ሲሆን አዳዲስ ሙዚቀኞችን ለሀገራችን በማስተዋወቅና ችሎታቸውን ለይቶ ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግም ይታወቃል ።
ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቼሎ የሙዚቃ መሳሪያን ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ከመምህሩ አክሊሉ ዘውዴ፣ ከዕዝራ አባተ፣ ከያሬድ ተፈራና ከሌሎችም ጋር በመሆን በመዲና ባንድ ውስጥ ሰርቷል።
በቀጣይነትም ከዜማ ላስታስና ከአፍሮ ሳውንድ ባንዶች ጋር የሰራበት ጊዜም ነበር ። ከ30 በላይ ሙሉ አልበሞችን ልዩ አድርጎ በማቀናበር የሠራላቸው ድምጻዊያን በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ስኬታማ መሆን እንዲሆኑ አድርጓል::
ከመሃሙድ አህመድ፣ ከፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ ከአለማየሁ እሸቴ ጋር የሠራ ሲሆን ቴዲ አፍሮ፣ አለማየሁ ሄርጶ ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ ፣ ትዕግስት በቀለ ፣ አብነት አጎናፍር ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ ፣ ሄኖክ አበበ ፣እዮብ መኮንን፣ ሚካኤልበላይነህ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ልኡል ኃይሉ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ ሚካያ በሃይሉ፣ ትግስት በቀለ፣ ቤሪ፣ ዳን አድማሱ ጥቂቶቹ ናቸው። “ሙዚቃ በኤልያስ መልካ ከነሙሉ ክብሯ ታልፋለች”ይላሉ ብዙ ድምጻዊያን::
ሕይወቱን ፈጽሞ አላባከነውም ለሚወደው ሙያ ኢንቨስት አድርጎታል በማለት የሙያ አጋሮቹ የሚገልጹት ተወዳጁ ኤልያስ መልካ ዛሬ በቅዱስ ወ ጳውሎስ የቀብር ስነ ስርዓቱ ተፈጽሟል::
በሽኝት ፕሮግራሙና በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር የተለያዮ አርቲስቶችን ለማነጋገር ሞክሯል:: በኤልያስ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው የነገረን የረዥም ዓመት ጓደኛውና ዜማ ላስታስንአብሮት የመሠረተው ሳክስፎን ተጫዋቹ ሚካኤል ኃይሉ ኤልያስ ለሙዚቃ የተፈጠረ ዕድሜውንም ለሙያው ክብር የሰጠ በሳል ሙያተኛ ነበር ሲል ይገልጸዋል::
“ከሞቱ አራት ቀን በፊት ስልክ ደውዬለት ሳናግረው ጤንነቴ ቆንጆ ነው አይዞህ አታስብ” ብሎኝ ነበር ሲል ለሪፖርተራችን የገለጸው ዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራ ሸዋ የኤልያስ መልካ የሙዚቃ ተሰጥኦ እና ችሎታ በምንም መስፈርት ሊለካ የማይችል መሆኑን መስክሯል::
በተወለደ በ42 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሳቂታው ኤልያስ በረዥም ዘመናት ውስጥ የሚፈነጥቅ የሙዚቃ ብርሃን ነውበማለት የነገሩን ተወዳጆቹ ድምጻውያን ዘሪቱ ከበደና ጎሳዬ ተስፋዬ በተለያዮ አጋጣሚዎች ከሕዝብ ዘንድ ያደረሷቸው ጣዕመ ዜማዎች የኤልያስ ድንቅ ፈጠራ አሻራ ያረፉባቸው እንደሆኑ አረጋግጠዋል::
“ኤልያስ መልካ ከዕድሜው በላይ የገዘፈ ተጨልፎ የማያልቅ የዕውቀት ጸጋን የታደለ ነው” ያለው የሙዚቃ ባለሙያ እና በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ም/ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬ ስብሓት ኤልያስ ከጎበዝ ሚዚቀኝነቱ በሻገር የሙያው ስነምግባር በትክክል የገባው ትልቅ ሙዚቀኛ እንደሆነና በግለ ባህሪውም ቅን ለሰዎች ሩህሩህና አዛኝ እንደነበር ለኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ይፋአድርጓል::
በኤልያስ መልካ የሽኝት ፕሮግራም ላይ በርካታ የሙያ አጋሮቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በዕንባ ሲታጠቡ ተመልክተናል:: “እሱ ሙዚቃን ማቀናበር ከጀመረ በኋላ ሙዚቃ ሥሠራ የሆነ ሰው ከጀርባዬ ቆሞ የሚያየኝ ያለ እስኪመስል ድረስ የበለጠ ትኩረት ሰጥቼ እንድሠራ ተፅዕኖ አድርጎብኛል” በማለት የወጣቱን የሙዚቃ ባለሙያ ችሎታ ከ15 ዓመት በፊት በተደረገለት አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ የመሠከረለት አበጋዝ ክብረዎርቅ ሺዎታ ኤልያስ መልካ ዛሬ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ ነገ በኤልያስ መልካ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን::
ሐረር ቢራ ፋብሪካ በአርሶ አደሮችና በወጣቶች ውሃ በመከልከሉ ምርቱ አሽቆለቆለ
በዓለም አቀፉ ግዙፍ ቢራ አምራች ካምፓኒ ባለቤትነት የሚተዳደረው ሐረር ቢራ ፋብሪካ ለውሃ አቅርቦት የሚጠቀምበትን በሐረሪ ክልል ፍንቅሌ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የውሃ መሳቢያ መስመሮቹን እና ጀኔተሮቹን እንዳይጠቀም ላለፉት ሁለት ዓመታት በአርሶ አደሮችና በወጣቶች በመከልከሉ ምክንያት ምርቱ እንዳሽቆለቆለ ታወቀ::
ካምፓኒው 200 ሚሊዮን ብር አውጥቶ የገዛቸው ጀኔተሮችና ሌሎች መሣሪያዎችም አገልግሎት መስጠት አቁመው በፈሳሽ ማመላለሻ መኪና ውሃ ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት የቢራ ምርቱን ቀጥሎ ነበር::
ሐረር ቢራ ከ19 70ዎቹ ጀምሮ የሚጠቀመው የውሃ መስመር ከዚሁ ከፍንቅሌ ወረዳ ነበር:: ሄኒከን ፋብሪካውን ገዝቶ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በአካባቢው በተነሳው ችግር ወጣቶቹና አርሶ አደሮቹ መጠቀም አትችሉም በሚል አገልግሎቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል::
ጉዳዮን በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከአቶ ለማ መገርሳ ጀምሮ አሁን ስልጣን ላይ እስካሉት አካላት ድረስ እንዲያውቁት ቢደረግም ከማኅበረሰቡ ጋር ተነጋግረን እንዲፈታ እናደርጋለን ከማለት ውጪ ምንም የተሠራ ነገር አለመኖሩን የፋብሪካው ሓላፊዎች ይናገራሉ:: በወረዳውከሚገኙ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ጋር ለበርካታ ጊዜያት ውይይት ቢያደርጉም ፍላጎታቸውን ፈጽሞ ማወቅ እንዳልቻሉ የሚያስረዱት አመራሮች ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ዘመናዊ የመስኖ እርሻ ስርዓት ለመዘርጋት በቢራ ፋብሪካው ሃሳብ አቅርቦ እንደነበርም ይጠቁማሉ::
ለሐረር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚቀርበው ከድሬደዋ 75 ኪሎ ሜትር አቆራርጦ እና አዶሌ አዎዳይንና ሃረማያን አቋርጦና አዳርሶ የተረፈውን ውሃ በመሆኑ በክልሉ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳለ ይታወሳል:: ይሄንን የውሃ መስመር ሃረማያ ላይ በመዝጋት 10 ሚሊየን ብር ወደ አካውንታችን ካላስገባችሁ ውሃውን አንለቅም የሚሉ ግለሰቦች ውዝግብ ፈጥረው እንደነበርም ይታወቃል::
የሐረር ቢራ ውሃ የሚጠቀምበትን የውሃ መሳቢያ ከዚህ ቀደም በተቆረጠበት ወቅት የክልሉ መንግሥት ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር ተደራድሮ 20 ሚሊየን ብር መክፈሉን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቧ አይዘነጋም::
የዮንቨርስቲ ተማሪዎች ሃይማኖትና ባህልን መሠረት ያደረገ አለባበስ እንዲጠቀሙ ሕግ ወጣ
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአለባበስ የስነ ምግባር ደንብን ለመወሰን በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስቴር የተጠናው ጥናት ተጠናቆ በጥር ወር ይፋ እንደሚደረግ ተሰማ::
ለአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመደበኛነት እንዲያገለግል ተብሎ በጥናት ይረጋገጣል የተባለው አለባበስ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ አለባበሶችን እንደሚደነግግም ከወዲሁ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: መመሪያው እስካሁን ድረስ በየዮንቨርስቲው ተበታትኖ የሚገኘውን የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ይተካል ተብሎ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ታምኖበታል::
በርካታ ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎደለው አለባበስ በመጠቀም መማር ማስተማሩን ሲያውኩ ነበር የሚል ዕምነት ያለው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተለይም ፀጉራቸውን አንጨባረው የሚመጡ ተማሪዎች በዮንቨርስቲው በስፋት መመልከት የተለመደ ክስተት መሆኑን አስታውቋል::
በአዲሱ መመሪያ መሠረት የፓርቲ አርማ ያለበት ልብስ እና ለግጭት የሚዳርጉ የተለያዪ አለባበሶችን መጠቀም የሚከለክል ነው:: ተማሪዎች በመማሪያ ክፍሎች በመጻሕፍት በምግብ በመኝታ በመዝናኛ እና በጤና አገልግሎት መስጫዎች በጋራ እንደመገልገላቸው የግልም ሆነ የጋራ ባህርያትና በመማር ማስተማር ሂደት እንዲሁም በማህበራዊ ደህንነት ላይ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ተብሏል።
ያልታወቁ ታጣቂዎች በአርማጭሆ 1500 ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ
በማዕከላዊ ጎንደር ታች አርማጭሆ የሚገኙ ነዋሪዎች ማንነታቸው ያልታወቁ ኃይሎች ድንገት ወደ አካባቢው እየመጡ በሚያደርሱት ጥቃት መኖሪያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::
የተደራጀ ቡድኑ በሚያካሂደው ዘረፋ አማካኝነት ከአንድ ሺኅ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን በመተው ተፈናቅለዋል:: የአርማጭሆ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የአርሶ አደሮች ንብረት ሙሉ ለሙሉ እየተዘረፈ ሲሆን አራት የተለያዮ ሰብሎችን የያዙ መኪኖችም በታጣቂዎቹ ተዘርፈዋል::
ይህ ዘረፋ ከፍ ብሎ በመኖሪያ ቤቶች ላይ በሚደርስ ጥቃት የሰው ሕይወት መጥፋት በመጀመሩ ያለን አማራጭ መሰደድ ብቻ ነው ያሉት አማራዎች ችግሩ ከወረዳው የጸጥታው ኃይሎች በላይ መሆኑ ደግሞ ስጋታቸውን እንደጨመረው ገልጸዋል::
ባለፈው ዓመት መጋቢት 2011 ዓ.ም ላይ በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ጨምሮ በዞኑ 50 ሺኅ ተፈናቃዮች እንደነበሩ አይዘነጋም:: ከጳጉሜ 3/2011 ዓ.ም ጀምሮ በስፍራው እንደገና ባገረሸው ግጭት ሳቢያ በታች አርማጭሆ ወረዳ መፈናቀሉ ተከስቷል:: በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተመሳሳይ የፀጥታ ችግር ያለባቸው ምሥራቅ ደንቢያ ፣ ምዕራብ ደንቢያ፣ ጭልጋ ቁጥር አንድ፣ ጭልጋ ቁጥር ሁለት አይከልና አርማጭሆ አካባቢዎች መሆናቸውም ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል።
“የሰው ዘር መገኛ” የተሰኘ አዲስ ሙዚየም በሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው
የቅርጽ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሰው ዘር ቅሪት አካሎች ለዕይታ የሚቀርቡበት አዲስ ሙዚየም በዋና ከተማዋ አምስት ኪሎ አካባቢ ሊያስገነባ መሆኑን አስታውቋል::
በአውሮፓ ሕብረት ሙሉ ድጋፍ ከሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዲዛይን እና ተያያዥ ሥራዎችን ማካሄድ የተጀመረ ሲሆን ጠቅላላ ወጪውም ከሰባት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተነግሯል::
ከአንድ ዓመት በኋላ የሙዚየሙ ግንባታ የሚጀመር ሲሆን በውስጡ የሰው ዘር ቅሪተ አካሎችን በመያዝ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ጎብኚዎችን ለመሳብ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግም ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል::
አዲስ የሚገነባው ሙዚየም የሰው ዘር ቅሪተ አካላትን ጨምሮ የተለያዮ ቅርሶች ለዕይታ ከሚቀርቡበት ብሔራዊ ሙዚየም ተለይቶ የሚወጣ እንደሆነም ተነግሯል:: ኢትዮጵያን የሚያቋርጠው የምሥራቅ አፍሪካ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ በርካታ የሰው ልጅ እና የእንስሳት ቅሪት አካላት የሚገኙበት አካባቢ ነው::
የሰው ዘር መገኛ በሚል ስያሜ የሚገነባው ሙዚየም ለመገንባት የሚወጣውን ወጪ መንግሥት እንዲሁም በውጪና በሀገር ውስጥ ለጋሽ ድርጅቶች እና ተመራማሪዎች የሚደገፍ መሆኑ ታውቋል::
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ፊት ለፊት በ4 ሺኅ 451 ካ.ሜ ቦታ ላይ ለሚገነባው ሙዚየም በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች ለማስነሳት 9 ሚሊየን 166 ሺኅ ብር የካሳ ክፍያ ተፈጽሞ መጠናቀቁንም ሰምተናል:: በዓለም ላይ ከተገኙ 23 የቅድመ ሰው ዝርያዎች መካከል አስራ ሦስቱ በኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው::