በእነ ጀነራል ተፈራ ማሞ ላይ ጥቅምት 12 ክስ እንዲመሠረት ዛሬ ተወሰነ
በግፍ ታስረው የሚገኙት የእነ ጀነራል ተፈራ ማሞን ጉዳይ የሚከታተለው ባህር ዳር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ በሰበር አቤቱታ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ ማድረጉ ተሰማ።
ፍርድ ቤቱ መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ሰበር ችሎት ዓቃቤ ህግ በሰበር አቤቱታ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ዝርዝር ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ተከትሎ የተጠርጣሪ ቤተሰቦችና መላው የአማራ ሕዝብ ውሳኔውን በጉጉት ሲጠብቅ ነበር::
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ሰበር ችሎትም መዝገቡ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የማያሰጥ መሆኑን በመግለፅ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ አድርጓል:: ወትሮውንም በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች የተላለፈውን ውሳኔ አስቀድመው ገምተውት እንደነበር ለኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ተናግረዋል::
ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ይግባኝ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ተጠርጣሪዎቹ ለ64 ቀናት በማረፊያ ቤት የቆዩ መሆናቸውን በመግለፅ፥ መርማሪ ቡድኑ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ መረጃ ሲያጣራ በመቆየቱ እንዲሁም ቀሪ ምስክሮች ጥቂት መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ክስ እንዲመሠረት ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል።
ውሳኔውን ተከትሎ በርካታ የአማራ ተወላጆች ክልሉን በሚያስተዳድረው አዴፓና በፌደራል መንግሥቱ ላይ ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ይገኛሉ::
አስቻለው ደሴ በእናቱ ቤት ተከቦ ተገደለ
ከሰኔ አስራ አምስቱ የአማራ ክልል መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር ንክኪ አለው የተባለው አስቻለው ደሴ ዛሬ መገደሉ እየተነገረ ነው::
የብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ቀኝ እጅ ናቸው በሚል ከሚጠረጠሩ እና አክራሪ የአማራ ብሔርተኝኘትን በማራመድ ከሚወነጀሉ ጥቂት ሰዎች መሀል አንዱ የሆነው ሻለቃ አስቻለው ደሴ ከአራት ወር በፊት ከተፈጠረው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች እየተፈለገ መሆኑን ኢትዮጵያ ነገ ከሦስት ወር በፊት ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል::
የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተር የአማራው አርበኛን አሟሟት በተመለከተ የቅርብ ቤተሰቦቹን አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሠረት አስቻለው በምዕራብ ጎንደር የማገኘው በእናቱ መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደተገደለ አረጋግጧል::
በአማራነቱ ብቻ ቀደም ሲል ሥልጣን ላይ በነበረው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ተይዞ ዘግናኝ ግፎች ሲፈጸምበት ቆይቷል:: በቅርብ የሚያውቁት ደፋርነቱንና ጀግንነቱን ይመሰክሩለታል::በአስፈሪው ጨለማ ዘመን ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ በመቃወም ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ የነበረው አስቻለው ደሴ በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት ቡድን ተይዞ ዘግናኝ ግፍ ተፈጽሞበታል::
በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እና በተለያዮ ስውር የደህንነት ማሰቃያዎች ውስጥ ለበርካታ ወራት የተሰቃየው አስቻለው ደሴ ከጀርባ እና ውስጥ እግር ቶርቸሮች ባሻገር የእግሮቹን ጥፍሮች ሙሉ ለሙሉ እስከመነቃቀል ያሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥቃቶች ተፈጽመውበት ለአመታት ታስሯል::
በሀገሪቱ መጣ የተባለውን ለውጥ ተከትሎ ከዕስር የተፈታው አስቻለው የአማራን ሕዝብ መብት ለማስጠበቅ ይረዳሉ ባላቸው መንገዶች ትግል ሲያደርግም ነበር:: በተለይም በምድረ ገነት የኦነግ ጦርን መክቶ በመመለስ ረገድ የአማራ ሕዝብ ባለውለታ መሆኑ ይነገርለታል::
በጀነራል አሳምነው ጽጌ የተመራው ማስረሻ ሰጤ እና ዘመነ ማስረሻን ያካተተው የቤኒሻንጉል ታጣቂ ኃይሎች ላይ ለተወሰደው የአጸፋ ዕርምጃ የአስቻለው ደሴ ሚና ከፍተኛ እንደነበር የቅርብ ሰዎቹ ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል::
በዚህ መልክ ለአማራ ሕዝብ ባለውለታ የነበረው አስቻለው ደሴ የወላጅ እናቱ መኖሪያ ቤት በታጣቂዎች ከተከበበ በኋላ እጅ እንዲሰጥ የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ መገደሉ ተረጋግጧል:: በርካታ የአማራ ተወላጆች ሥርዓቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ግልጽ በደል እየፈጸመ ነው ሲሉ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል::
በ”ተጠለፈ ትግል” መጽሐፍ የተነሳ አዟሪዎችበአዲስ አበበባ በአሸባሪነት ተፈርጀው ታሰሩ
ሰሞኑን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች “የተጠለፈው ትግል በሚል ርዕስ በመድህን ሲራጅ ሐምሌ 2011 ዓ.ም ላንባቢያን የቀረበውን መጽሐፍ አትማችኋል፣የመጽሐፉን የፊት ሽፋን ዲዛይን ሰርታችኋል፣መጽሀፉን አከፋፍላችኋል፣አዙራችሁ እና በመደብራችሁ ሽጣችኋል” በማለት አዟሪዎችን እያሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ያነጋገራቸው መጽሐፍ አዟሪዎች ገለጹ::
እስካሁን ድረስ ስድስት ሰዎች በ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙ ሲሆን ፖሊስም በሽብር ወንጀል እንደከሰሳቸው ሪፖርተራችን አረጋግጧል::
በአገሪቷ ህግ በይፋ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ የፖለቲካ ቡድን በሌለበት እና ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት ተከሰው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ምህረት ተደርጎላቸው በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ እነዚህ ግለሰቦች ግን ሽኔ ከሚባል ጽንፈኛ የአሸባሪ ቡድን ጋር አብራችኋል የሚል ክስ እንደተመሰረተባቸውና ፍ/ቤት ቀርበውም የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
በዚህም የተነሳ በአዲስ መልክ ከተያዙት ባሻገር ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ የቆዩ ግለሰቦችም አሉበት።ለዚህ ማሳያም መጽሐፉን አከፋፍለሀል በማለት በእስር ላይ የሚገኘው እና የኤዞፕ መጽሀፍት መደብር ባለቤቱ መሳይ ማሩ በዋነኝነት እንደሚጠቀስ ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ አስታውቋል::
መጽሀፉ በፒዲኤፍ ጭምር ይለ ገደብ ተሰራጭቶ እየተነበበ መሆኑን የገለጡ ምንጮች በአንድ መቶ ሀምሳ ብር ይሸጥ የነበረው በዚህ ምክንያት ፍላጎት በመጨመሩ ዋጋው ተሰቅሎ በድብቅ እስከ ሁለት ሺህ እየተሸጠ መሆኑንም ይናገራሉ። የመጻፍና ሀሳብን የመግለጥ መብቶች እየተከበሩባት ነው በምትባለው አገር ይህ አይነቱ እርምጃ ለብዙዎች ያልተጠበቀ ሆኗል:: በኢህአዴግ/ህወሓት የስልጣን ዘመን በመሰል ሁኔታ ደህንነቱና የጽጸጥታ ክፍሉ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ብዙዎች ለመሰል እስራቶች ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል።
ለክልሎች ፌደራል መንግሥት የሚያደርገው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ለ2 ዓመት ተራዘመ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚያደረገው የድጎማ በጀት የማከፋፈያ ቀመርን ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ወሰነ:: የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ጉዳዮችን ተመልክቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ከተመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚያደረገው የድጎማ በጀት የማከፋፈያ ቀመር አንዱ ሲሆን ይህ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን ቀመር ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ ለሶሰት ዓመታት እስከ 2012 በስራ ላይ እንዲወል መወሰኑ አይዘነጋም።
በድጎማ በጀት ክፍፍል ቀመር ላይ የሚነሱ የፍትሃዊነት ጥያቄን ለመመለስ ከህዝብና ቤት ቆጠራ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወቅታዊ መረጃዎችን በመተንተን አዲስ ቀመር በ2013 በጀት ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ነበር።ሀሆኖም የህዝብና ቤት ቆጠራ በመራዘሙ እና ቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት በመሆኑ አዲሱን ቀመር የፌዴራልና የክልል አመራሮችን አግኝቶ ቀመሩን አሳታፊ በሆነ መንገድ ለማዘጋጀት አስቸጋሪ መሆኑ ተጠቅሷል።
ሀ በስራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት ቀመር ለሁለት አመት እንዲራዘምና ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅት ከተያዘው ዓመት አንስቶ እንዲጀመር የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት የድጎማ ማከፋፋያ ቀመሩ ለማራዘም የቀረቡ ምክንያቶች ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን ያነሱ ሲሆን፥ የጋራ ገቢና የድጎማ በጀት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባለት ደግሞ ቀመሩን ለሁለት ዓመት ማራዘም ያስገደደውን መንስኤ አስረድተዋል።
ይህን ተንተርሶም ምክር ቤቱ በስራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት ማከፋፈያ ቀመሩ ለሁለት ዓመት እንዲራዘም በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል:: ምክር ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በቀረቡለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት 8 ማመልከቻዎች ቀርበውለት ጉዳዮቹን ከመረመረ በኋላ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ምክር ቤቱም የቀረቡት ስምንት ማመልከቻዎች ውስጥ ስድስቱ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ያለ ሲሆን፥ ቀሪ ሁለቱ ማመልከቻዎች ደግሞ የህገ መንግስት ትርጉም እንደማያስፈልጋቸው ውሳኔ አስተላልፏል::