የሀገራችንን ሕዝቦች የእኩልነት፣ የፍትሕና እና የነጻነት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ብሎም የሕዝቦቻችንን የመልማትና የመበልጸግ ፍላጎት ከግብ ለማድረስ፣ ኦዲፒ ከእኅት ድርጅቶች እና ከአጋሮቹ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሲታገል፣ በጋራ መሥዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል፤ አሁንም በመታገል ላይ ይገኛል፡፡
ፓርቲያችን የትግል ሂደቶቹን በተመለከተ በሦስት መርሖች ይመራል፡፡ በታሪካችን ውስጥ የነበሩንን በጎ ዕሴቶችና ድሎች አክብሮና አጠናክሮ መቀጠል፤ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስሕተቶችን በጋራ ነቅሶ ማረም፣ እንዲሁም ካለፈው ትምህርት ወስዶ ተጨማሪ ስሕተቶችን ባለመድገም፣ ብሎም የነበሩንን ድሎች አስፍቶ እና አጠናክሮ በማስቀጠል የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ናቸው፡፡ እነዚህን የትግል መርሖች ለማሳካት ንግግሮቻችንና ተግባሮቻችን ሁሉ በሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም የሚያመጡ መሆን እንዳለባቸው ኦዴፓ በጽኑ ያምናል፤ ለስኬቱም በጽናት ይሠራል፡፡
ከየትኛውም ወገን የመጡ ጨቋኝ ገዥዎች ጥቅማቸውን እንጂ የመጡበትን ወገን እንደማይወክሉ በጽኑ እናምናለን፡፡ ባለፉት ዘመናት ስናደርግ የነበረው መራራ ትግል ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር አልነበረም፡፡ ሕዝቦች ሲጨቆኑ እንጂ ሲጨቁኑ አልኖሩምና፡፡ ከመጣንበት መንገድ በላይ ወደፊት አብረን የምንጓዘዉ ረጅም ጉዞ እንደሚረዝም እናውቃለን፡፡ ባለፈዉ ታሪካችን ከተፈጸሙት ስሕተቶች ይልቅ በአንድነት የሚያስተሣስሩን መልካም ነገሮቻችን ይበዛሉ፡፡ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች ዘመን ተሻጋሪ ወንድማማችነት የተገመደበት ገመድ በቀላሉ የሚፈታ ወይም የሚበጠስ አይደለም፡፡ የአዴፓ እና የኦዴፓ የዓላማ እና የተግባር አንድነት ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ፈተናዎች እንዳለፈ ሁሉ ወደፊትም መሰናክሎቹን ሁሉ እየተሻገረ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲያችን በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ደግመን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡