ከ21 ዓመት በኋላ በኔዘርላንድ የተገኘው የጨለንቆ ስላሴ ዘውድ 55 ሺኅ ዶላር ተገመተ

ከ21 ዓመት በኋላ በኔዘርላንድ የተገኘው የጨለንቆ ስላሴ ዘውድ 55 ሺኅ ዶላር ተገመተ

ለ21 ዓመታት ተደብቆ የኖረ ዘውድ በኔዘርላንድስ መገኘቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ መሠንበቱ ይታወሳል:: ለ41 ዓመታት በኔዘርላንድ የኖሩት አቶ ሲራክ አስፋው ዘውዱ ቤታቸው የገባው በአጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ። የጥገኝነት ጥያቄና ሌላም ጉዳያቸው ተጠናቆ ወደ ሌላ ቦታ እስኪሄዱ ድረስ የግል ሰነዶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም ዕቃዎች አቶ ሲራክ ቤት በአደራ የሚያስቀምጡ ሰዎች ከአራት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ አቶ ሲራክ ቤት ይመላለሱ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ትተውት እንደሄዱም ለቢቢሲ ገልጸዋል::

ዘውዱ የማን ነው? መቼ የነበረ ዘውድ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ዜናውን ተከትለው  በስፋት እየተሰሙ ናቸው። አንዳንዶች በላሊበላ እንዲሁም በፋሲለደስ ወቅት የነበረ ነው ቢሉም፤ ኒው ዮርክ ታይምስ ያናገረው በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረገው ጃኮፖ ጊንስቺ፤ ዘውዱ ከሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን በ1990ዎቹ የተሰረቀ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆነው ጃኮፓ እንደሚለው፤ ዘውዱ ከመጥፋቱ በፊት በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቄስ ዘውዱን ራሳቸው ላይ ጭነው ፎቶ ተነስተዋል። ዘውዱ በአይነቱ የተለየ እንደሆነ የሚናገረው ተመራማሪው፤ ዋጋውንም 55 ሺህ ዶላር ያወጣል ሲል ገምቶታል::

ከመቐለ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስትያን ውስጥ በርካታ ንዋየ ቅድሳት እንዳሉ ይነገራል። በተለይም ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስትያኑ እልፍ ንዋየ ቅዱሳን ማበርከታቸውን ቤተ ክርስትያኑ ግቢ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ አባቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ለአሥራ ስድስት ዓመታት መንነው በቤተ ክርስቲያኗ የሚኖሩት የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አባ ገብረሥላሴ፤ ሦስት ዘውዶችን ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስቲያኗ መስጠታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ1745-1865 በወቅቱ የእንደርታ ዙሪያ የሚባለውን ሰፊ ግዛት ያስተዳደሩት ራስ ወልደሥላሴ በአራት ቦታዎች ማለትም በጨለቆት፣ በአንጣሎ፣ በፈለግዳሮና በመቐለ ቤተ መንግሥቶችን ገንብተዋል በአንድ ወቅትም ጨለቆትን ዋና ከተማቸው አድርገዋትም ነበር።

ራስ ወልደሥላሴ ካበረከቷቸው ዘውዶች መካከል አሁን በኔዘርላንድ የተገኘው ዘውድ አንዱ ሲሆን፤ ከ24 ዓመታት በፊት መሰረቁንና ከዚያም መሰወሩን ዘውዱን በመስረቅ የተጠረጠረው የቤተ ክርስቲያኑ አቃቤ ነዋይ (ጠባቂ)፤ ከአምስት ዓመታት ዕስር በኋላ ቅርሱ ሳይገኝ መለቀቁን ገልጸው “መንግሥት ሓላፊነቱን አልተወጣም” በማለት የትግራይ አስተዳደር ላይ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ከሰሞኑ የዘውዱን መገኘት ዜና የሰሙት አባ ገብረሥላሴ፤ ምንም እንኳን ጥልቅ ደስታቸውን ቢገልፁም “እንዴት ተወሰዶ፣ እንዴትስ ነው እየተመለሰ ያለው የሚል ጥያቄ በውል መመለስ ይኖርበታል” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል::ከኢትዮጵያ ተሰርቆ የተወሰደ አንድ ዘውድ ኔዘርላንድ ውስጥ መገኘቱንና በቅርቡ ወደ አገሩ እንደሚመለስ የሰማው የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘውዱ የሥላሴ ጨለቆት ስለመሆኑ ቅንጣት ታህል አይጠረጠርም ሲሉም ተናግረዋል።

ቄስ ንጉሠ ሀጎስ ላለፉት ሦስት ዓመታት የቤተ ክርስትያኑ ዓቃቤ ነዋይ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። “ሥላሴ ጨለቆት ውስጥ ሦስት ዘውድ ነበር፤ የተሰረቀው አንድ ነው። ሦስቱም የወርቅ ቅብ ሳይሆኑ ከተጣራ ወርቅ የተሠሩ ናቸው። የጠፋው ዘውድ ከወርቅ መሠራቱን ለማወቅ ያሉትን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል” ሲሉ ስለ ነዋየ ቅድሳኑ ጥራት ይመሰክራሉ።

ሌላው የመቐለ ከተማ ኗሪ አቶ ብስራት መስፍን፤ በ1987 ዓ. ም. (ከ24 ዓመታት በፊት) የቀይ መስቀል ሠራተኛ በመሆን ወደ ትግራይ ከመጣው እንግሊዛዊ ዴቪድ ስቴብልስ ጋር ይተዋወቃል። ዴቪድ ብስራትን ይዞ አካባቢውን ለማስጎብኘት ወደ ሥላሴ ጨለቆት ይሄዳል። ብስራት ቤተ ክርስትያኑን መጎብኘቱንና እዛው ከነበሩት ዘውድና የወርቅ ፅዋ ጋር ፎቶ መነሳቱን ያስታውሳል።

“ዘውዱ መሰረቁን ሰምቼ ስለነበረ ሰሞኑን ዳግም መገኙቱን ስሰማ ያንን ፎቶ ስፈልግ ነበር ያደርኩት። መጨረሻ ላይ ተሳክቶልኛል” ሲል በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ ይዞ ቀርቧል። አቶ ብስራት መስፍን በአሁኑ ሰዓት ራሱ ያቋቋመውን ‘ትምህርታዊ ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች’ የተሰኘውን ምግባረ ሰናይ ድርጅት በመምራት ላይ ነው::

የዘውዱ መገኘት ከተሰማ በኋላ ከዴቪድ ጋር በኢንተርኔት መጻጻፉንም ተናግሯል:: “ወደ ሥላሴ ጨለቆት በሄድንበት ወቅት ከዘውድ በተጨማሪ ወርቃማ ዋንጫ እንዲሁም ስድስት በወርቅ የተዋበ መጽሐፍ ቅዱስ አይተናል። የሚያሳዝነው ግን በጣም ጥቂቶች ብቻ የሚያውቁት በጣም ብዙ ታሪክ ነው ያላችሁ”

የዘውዱን መገኘት በሚመለከት የትግራይ የባህልና ቱሪዝም ቢሮም መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ሓላፊት ወ/ሮ ብርኽቲ ገብረመድህን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጉዳዩን በቅርብ ርቀት እየተከታተሉት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ምን ዓይነት ቅርስ ነበር የጠፋው? ምን ያህል ሕጋዊ ማስረጃስ ይኖራል? አሁን ተገኝቷል የተባለው ቅርስስ ምን ይመስላል? የሚለውን በሚገባ አጥንተን ሕጋዊነት ባለው መንገድ ለመሄድ እየሠራን ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ቢሮው ከሚመለከተው የፌደራል መንግሥታዊ አካል ጋርም በስልክ ተገናኝቶ ስለ ጉዳዩ በዝርዝር መወያየቱን አሳውቋል።

የሚመለከተው አካል ስለ ጉዳዩ መረጃ ማግኘቱንና እየተከታተለው ሲሆን ዘውዱ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  በቅድሚያ ይረከበዋል ተብሎ ይጠበቃል::

LEAVE A REPLY