የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም

ኦዴፓ የሽመልስ አብዲሳን የጥፋት ንግግር በመግለጫ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከሩ ተገለጸ 

ከቀናት በፊት  አዲስ አበባ ላይ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት ንግግር ለማብራራት  የሚሞክር መግለጫ ፓርቲያቸው ኦዴፓ ዛሬ  በይፋ አውጥቷል።

ቅዳሜ ዕለት በበዓሉ ዋዜማ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አደረጉት የተባለው ንግግር በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ በተለይ አንዳንድ የአዴፓና የኦዲፒ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ በማህበራዊ መድረኮች ላይ ሲወዛገቡና ጠንከር ያሉ ቃላትን ሲለዋወጡ ሰንብተዋል።

ትናንት በፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዷለም አራጌ የሚመራው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰኘው ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ላይ ጉዳዩን በማንሳት ትችትን ሰንዝሯል። ኢዜማ በጉዳዮ ላይ በፍጥነት መግለጫ ማውጣቱ ደግሞ ነገሩን እንደ አዲስ አክርሮታል::

የነገሩ ጡዘት ድንጋጤ ውስጥ የከተተው ኦዴፓ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ በበኩሉ የምክትል ፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ የተከሰተውን ውዝግብ ለማጥራት የሰጠው መግለጫ መሆኑን  በግልጽ ባያሰፍርም ያነሳቸው ነጥቦች ግን ንግግራቸውን የተመለከቱ እንደሆነ መረዳት ይቻላል::

ኢዜማ በአቶ ሽመልስ ንግግርና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ “የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት ነው” ብሏል።

ኢዜማ በመግለጫው ላይ እንዲህ ዓይነቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም በመጠየቅ፤ “የአገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ሓላፊነት መሆኑን እናሳስባለን” ሲልም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ህዝብ የተለያዩ አፈናዎችና ትንኮሳ እየደረሰበት እንደሆነና “የከተማ ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም” ያለው ኢዜማ ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እንደሚደግፍ በመግለጫው አረጋግጧል።

ኦዴፓ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶች ለማሟላት ከእህት ድርጅቶችና ከአጋሮቹ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሲታገል፣ በጋራ መሥዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱንና አሁንም እየታገለ መሆኑን  ድርጅቱገልጿል። አክሎም “በታሪክ ውስጥ የተሠሩ ስህተቶችን በጋራ ነቅሶ ማረም፣ እንዲሁም ካለፈው ትምህርት ወስዶ ተጨማሪ ስህተቶችን ባለመድገም፣ ብሎም የነበሩንን ድሎች አስፍቶና አጠናክሮ በማስቀጠል የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት” ዋነኛ አላማው እንደሆነም አመልክቷል::

“ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር አልነበረም። ሕዝቦች ሲጨቆኑ እንጂ ሲጨቁኑ አልኖሩም። ከየትኛውም ወገን የመጡ ጨቋኝ ገዥዎች ጥቅማቸውን እንጂ የመጡበትን ወገን እንደማይወክሉ በጽኑ ያምናል” ያለው የዶክተር ዐቢይ ኦዴፓ ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፈዉ ታሪካቻው ከተፈጸሙ ስህተቶች ይልቅ በአንድነት የሚያስተሳስሯቸው መልካም ነገሮች በርካታ እንደሆኑ ጠቅሶ “ከመጣንበት መንገድ በላይ ወደፊት አብረን የምንጓዘዉ ረጅም ጉዞ እንደሚረዝም “ይረዳል” ብሏል።

መግለጫው በኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች መካከል ያለው የወንድማማችነት ትስስር በቀላሉ የሚበጠስ እንዳልሆነ በማንሳት “የአዴፓና የኦዴፓ የዓላማ እና የተግባር አንድነት ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ፈተናዎች እንዳለፈ ሁሉ ወደፊትም መሰናክሎቹን ሁሉ እየተሻገረ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲያችን በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ደግመን ለማረጋገጥ እንወዳለን” ሲል ያስረዳል::

ሓላፊነት በጎደለው መልኩ ግጭት ቀስቃሽ ሆኖ የቀረበው የሽመልስ አብዲሳን ንግግር ምላሽ አድበስብሶ በሚሰጥ መልኩ የቀረበው የኦዴፓ መግለጫ ድርጅቱ የተሠራውን ታላቅ ስህተት አምኖ ይቅርታ ማስጠየቅ እና ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው ሸፋፍኖ ለማለፍ መሞከሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመናቅ ተለይቶ አይታይም ሲሉ የተለያዮ የፖለቲካ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል::

ዶ/ር ዐቢይ የኖቤል ሽልማቱን የማግኘት ዕድላቸው 80 ፐርሰንት መሆኑ ተገለጸ 

በመጪው አርብ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሚዘጋጀው የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ታይም መጽሔት ዘገበ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ፍጥጫ እልባት በመስጠት፤ ሰላም በማምጣት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እንዲሁም ሌሎች ባመጧቸውም መሻሻሎች ሽልማቱን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ በእንግሊዝ የተለያዩ ፖለቲካዊ ትንበያዎችን በመስጠት የሚወራረደው ላድብሮክ አሳውቋል።

ይህ ድርጅት 80% (4/1) ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምቱን ከወዲሁ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ አስቀምጧል። ዓመታዊው ሽልማት በዓለም ውስጥ ለሰላም አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን እውቅና  ይሰጣል::

አምና የኮንጎ ዜግነት ያለው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጋና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ናዲያ ሙራድ ወሲባዊ ጥቃትን ለጦርነት መሳሪያነት መጠቀሚያነት ለማቆም በሠሩት አመርቂ ሥራ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል::

በዘንድሮው ሽልማት 301 ዕጩዎች ያሉ ሲሆን፤ 223 ግለሰቦች እንዲሁም 78 ድርጅቶች መሆናቸውንም የኖቤል ተቋም አስታውቋል። ምንም እንኳን እነማን ዕጩዎች እንደሆኑ ባይታወቁም የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ግምቶቻቸውን እያስቀመጡ ነው። በዚህም መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግና የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ተጠባቂ ሆነዋል::

ከ21 ዓመት በኋላ በኔዘርላንድ የተገኘው የጨለንቆ ስላሴ ዘውድ እያነጋገረ ነው 

ለ21 ዓመታት ተደብቆ የኖረ ዘውድ በኔዘርላንድስ መገኘቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ መሠንበቱ ይታወሳል:: ለ41 ዓመታት በኔዘርላንድ የኖሩት አቶ ሲራክ አስፋው ዘውዱ ቤታቸው የገባው በአጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ። የጥገኝነት ጥያቄና ሌላም ጉዳያቸው ተጠናቆ ወደ ሌላ ቦታ እስኪሄዱ ድረስ የግል ሰነዶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም ዕቃዎች አቶ ሲራክ ቤት በአደራ የሚያስቀምጡ ሰዎች ከአራት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ አቶ ሲራክ ቤት ይመላለሱ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ትተውት እንደሄዱም ለቢቢሲ ገልጸዋል::

ዘውዱ የማን ነው? መቼ የነበረ ዘውድ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ዜናውን ተከትለው  በስፋት እየተሰሙ ናቸው። አንዳንዶች በላሊበላ እንዲሁም በፋሲለደስ ወቅት የነበረ ነው ቢሉም፤ ኒው ዮርክ ታይምስ ያናገረው በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረገው ጃኮፖ ጊንስቺ፤ ዘውዱ ከሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን በ1990ዎቹ የተሰረቀ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆነው ጃኮፓ እንደሚለው፤ ዘውዱ ከመጥፋቱ በፊት በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቄስ ዘውዱን ራሳቸው ላይ ጭነው ፎቶ ተነስተዋል። ዘውዱ በአይነቱ የተለየ እንደሆነ የሚናገረው ተመራማሪው፤ ዋጋውንም 55 ሺህ ዶላር ያወጣል ሲል ገምቶታል::

ከመቐለ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስትያን ውስጥ በርካታ ንዋየ ቅድሳት እንዳሉ ይነገራል። በተለይም ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስትያኑ እልፍ ንዋየ ቅዱሳን ማበርከታቸውን ቤተ ክርስትያኑ ግቢ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ አባቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ለአሥራ ስድስት ዓመታት መንነው በቤተ ክርስቲያኗ የሚኖሩት የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አባ ገብረሥላሴ፤ ሦስት ዘውዶችን ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስቲያኗ መስጠታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ1745-1865 በወቅቱ የእንደርታ ዙሪያ የሚባለውን ሰፊ ግዛት ያስተዳደሩት ራስ ወልደሥላሴ በአራት ቦታዎች ማለትም በጨለቆት፣ በአንጣሎ፣ በፈለግዳሮና በመቐለ ቤተ መንግሥቶችን ገንብተዋልበአንድ ወቅትም ጨለቆትን ዋና ከተማቸውአድርገዋትም ነበር።

ራስ ወልደሥላሴ ካበረከቷቸው ዘውዶች መካከል አሁን በኔዘርላንድ የተገኘው ዘውድ አንዱ ሲሆን፤ ከ24 ዓመታት በፊት መሰረቁንና ከዚያም መሰወሩን ዘውዱን በመስረቅ የተጠረጠረው የቤተ ክርስቲያኑ አቃቤ ነዋይ (ጠባቂ)፤ ከአምስት ዓመታት ዕስር በኋላ ቅርሱ ሳይገኝ መለቀቁን ገልጸው “መንግሥት ሓላፊነቱን አልተወጣም” በማለት የትግራይ አስተዳደር ላይ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ከሰሞኑ የዘውዱን መገኘት ዜና የሰሙት አባ ገብረሥላሴ፤ ምንም እንኳን ጥልቅ ደስታቸውን ቢገልፁም “እንዴት ተወሰዶ፣ እንዴትስ ነው እየተመለሰ ያለው የሚል ጥያቄ በውል መመለስ ይኖርበታል” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል::ከኢትዮጵያ ተሰርቆ የተወሰደ አንድ ዘውድ ኔዘርላንድ ውስጥ መገኘቱንና በቅርቡ ወደ አገሩ እንደሚመለስ የሰማው የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘውዱ የሥላሴ ጨለቆት ስለመሆኑ ቅንጣት ታህል አይጠረጠርም ሲሉም ተናግረዋል።

ቄስ ንጉሠ ሀጎስ ላለፉት ሦስት ዓመታት የቤተ ክርስትያኑ ዓቃቤ ነዋይ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። “ሥላሴ ጨለቆት ውስጥ ሦስት ዘውድ ነበር፤ የተሰረቀው አንድ ነው። ሦስቱም የወርቅ ቅብ ሳይሆኑ ከተጣራ ወርቅ የተሠሩ ናቸው። የጠፋው ዘውድ ከወርቅ መሠራቱን ለማወቅ ያሉትን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል” ሲሉ ስለ ነዋየ ቅድሳኑ ጥራት ይመሰክራሉ።

ሌላው የመቐለ ከተማ ኗሪ አቶ ብስራት መስፍን፤ በ1987 ዓ. ም. (ከ24 ዓመታት በፊት) የቀይ መስቀል ሠራተኛ በመሆን ወደ ትግራይ ከመጣው እንግሊዛዊ ዴቪድ ስቴብልስ ጋር ይተዋወቃል። ዴቪድ ብስራትን ይዞ አካባቢውን ለማስጎብኘት ወደ ሥላሴ ጨለቆት ይሄዳል። ብስራት ቤተ ክርስትያኑን መጎብኘቱንና እዛው ከነበሩት ዘውድና የወርቅ ፅዋ ጋር ፎቶ መነሳቱን ያስታውሳል።

“ዘውዱ መሰረቁን ሰምቼ ስለነበረ ሰሞኑን ዳግም መገኙቱን ስሰማ ያንን ፎቶ ስፈልግ ነበር ያደርኩት። መጨረሻ ላይ ተሳክቶልኛል” ሲል በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ ይዞ ቀርቧል። አቶ ብስራት መስፍን በአሁኑ ሰዓት ራሱ ያቋቋመውን ‘ትምህርታዊ ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች’ የተሰኘውን ምግባረ ሰናይ ድርጅት በመምራት ላይ ነው::

የዘውዱ መገኘት ከተሰማ በኋላ ከዴቪድ ጋር በኢንተርኔት መጻጻፉንም ተናግሯል:: “ወደ ሥላሴ ጨለቆት በሄድንበት ወቅት ከዘውድ በተጨማሪ ወርቃማ ዋንጫ እንዲሁም ስድስት በወርቅ የተዋበ መጽሐፍ ቅዱስ አይተናል። የሚያሳዝነው ግን በጣም ጥቂቶች ብቻ የሚያውቁት በጣም ብዙ ታሪክ ነው ያላችሁ”

የዘውዱን መገኘት በሚመለከት የትግራይ የባህልና ቱሪዝም ቢሮም መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ሓላፊት ወ/ሮ ብርኽቲ ገብረመድህን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጉዳዩን በቅርብ ርቀት እየተከታተሉት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ምን ዓይነት ቅርስ ነበር የጠፋው? ምን ያህል ሕጋዊ ማስረጃስ ይኖራል? አሁን ተገኝቷል የተባለው ቅርስስ ምን ይመስላል? የሚለውን በሚገባ አጥንተን ሕጋዊነት ባለው መንገድ ለመሄድ እየሠራን ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ቢሮው ከሚመለከተው የፌደራል መንግሥታዊ አካል ጋርም በስልክ ተገናኝቶ ስለ ጉዳዩ በዝርዝር መወያየቱን አሳውቋል።

የሚመለከተው አካል ስለ ጉዳዩ መረጃ ማግኘቱንና እየተከታተለው ሲሆን ዘውዱ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  በቅድሚያ ይረከበዋል ተብሎ ይጠበቃል::

በ40ኛው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ጉባዔ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሰነድ ተቀባይ ሆነ

በካናዳ ሞንትሪያል ሲካሄድ በቆየው 40ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሰነድ ተቀባይነት ማግኘቱ ተነገረ::

በኢትዮጵያ የቀረበው ሰነድ በአቪዬሽን ሴክተሩ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ፣ በተለይም በስልጠናና በአቅም ግንባታ ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል::

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዓለም የሚያውቀው ንጹህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ሰንደቅ ዓላማችን በጉልህ የተንጸባረቀበት የሀገር ባህል ልብሳችን ተውበው በታደሙበት ጉባዔ ላይ ፤ ጠቅላላ ጉባዔው ሰነዱን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ  መተግበሪያ የአሠራር አቅጣጫዎችን አመላክቷል።

ዓለም አቀፋ ጉባኤ አባል አገራቱን ለማጠናከር ስልጠናዎችን በፋይናንስ የሚደግፉ ሀገራትንና ኢንተርናሽናል ተቋማትን ማስተባበር ፣ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአባል ሀገራቱን የስልጠና እና አቅም ግንባታ ፍላጎት በመለየት አቅማቸውን ለማጎልበት መስራት እንደሚኖርበት አሳስቧል።

ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ሥልጠና በፈረንጆቹ 2015 ያጸደቀውን የአቪዬሽን ሥልጠና እንዲሁም አቅም ግንባታ ፍኖተ ካርታ እንዲተገበር እገዛ ማድረግ እንደሚገባም ወስኗል። ሀገራት የየራሳቸውን የስልጠና ማእከላት በማደራጀትና በማጠናከር ስልጠና በመስጠት የአቅም ክፍተታቸውን እንዲሞሉ ማበረታታ እንደሚያስፈልግም በጉባዔው ላይ ከመግባባት ተደርሷል::

የአዲስ አበባን ታክሲዎች ሙሉ ለሙሉ እቀይራለሁ ያሉት ታከለ ኡማ  ከማህበራት ጋር ተወያዮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የታክሲ አገልግሎት (ኤታስ) ከሚሰጡ 13 ተቋማት ጋር ተወያዮ::

የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የኤታስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲከተሉት ባወጣው መመሪያ ዙሪያ እና የትራንስፖርት ሴክተሩን በዘላቂነት ዘመናዊ ለማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ከኤታስ እና ሶፍትዌር ማበልፀጊያ ተቋማት ጋርም እንዲሁ ምክክር ተደርጓል፡፡

የኤታስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በከተማ አስተዳደሩ ረቅቆ በቅርቡ ይፋ የሆነው መመሪያ ቴክኖሎጂው ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደሌለው ጠቁመው ህጉን እንደማይቃወሙ እና ለተፈጻሚነቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል::

ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አሰጣጥ በከተማዋ ውስጥ እንዲስፋፋ ፍላጎቱ መሆኑን ገልጿል::

በከተማዋ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ ሌሎች ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን ለሚያመጡ በራቸው ክፍት መሆኑን የገለጹት ም/ከንቲባው ፤-በቀጣይነትም የከተማ አስተዳደሩ የተቀላጠፈ እና ህዝቡን የሚጠቅም መመሪያ ቀርጾ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ይሠራል ብለዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎች ያረጁ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ተሽከርካሪዎቹን በአዲስ በመተካቱ ሂደት ከጎናቸው እንዲቆም  የኤታስ ድርጅቶቹ ጥሪ  አቅርበዋል::

ፌደራል ፖሊስ ከ2012 ዓ.ም ዋዜማ አንስቶ የተበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በሠላም ተከብረዋል አለ

በኦዴፓ የበላይነትና በኦሮሚያ ልጆች እየተዘወረ ነው ተብሎ የሚታማው ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከዘመን መለወጫው 2012 ዓ.ም ዋዜማ አንሰቶ የተከናወኑ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቀዋል አለ::የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እስካሁን የተከበሩ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው ይህንን የሰማነው::

በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ሓላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ የአዲስ ዓመት ዋዜማን ጨምሮ የመስቀል ደመራ በዓል እና እሬቻ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቀዋል ሲሉ ተሰምተዋል:: ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቁም ህዝቡ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ ሠርቷልብለዋል::

ምክትል ኮሚሽነሩ  ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላቱ ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ ለሰራው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል። በተለይ በእሬቻ እና የደመራ በዓል ምክንያት ለነበረው የመንገድ መዘጋጋት የአዲስ አበባ ህዝብ ላሳየው ትእግስት እና ትብብር ምስጋና ሊቸረው ይገባል ሲሉ ያልተለመደ መግለጫ ሰጥተዋል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡ በመሰል ሀገራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ይህን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ያቀረቡት ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ፣ የፌደራል፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ፖሊስ በመናበብ እና በመተባበር ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና ይቸራቸዋል ማለታቸውን አድምጠናል::

LEAVE A REPLY