“የሕዝብ ድምጽ ይሰማ” የጥቅምት 2ቱን ሠልፍ አስመልክቶ ባላአደራው ነገ መግለጫ ይሰጣል
በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው የባለአደራው ም/ቤት (ባልደራስ) እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በዋና መዲናዋ መስቀል አደባባይ ጠርቷል::
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ እየተንሰራፋ የመጣውን የኦሮሞ ጽንፈኛነት ፖለቲካን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የእሬቻ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተከብሯል:: በዚህ ፖለቲካ ዕሳቤ የተጠለፈው የእሬቻ በዓል ላይ የተረኝነት ፖለቲካን ከመስበክ ባሻገር የአማራን ሕዝብ በይፋ ነፍጠኛ በማለት የተቹት አቶ ሽመልስ አብዲሳ መተቸታቸው ይታወሳል::
በከተማዋ ሕዝብ ላይ የእሬቻን በዓል ተከትሎ ከየት እንደመጡ በማይታወቁ እና አማርኛ ፈጽሞ በማይችሉ ፎሌዎች አማካይነት እንዲጉላላ ያደረገው የታከለ ኡማ አስተዳደር እና ኦዴፓ በከተማይቱ ላይ ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት ገሀድ አውጥተውት ታይተዋል እየተባሉ በሚተቹበት ወቅት ሠልፉ መጠራቱ በከፍተኛ ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ድጋፍ አግኝቷል::
“ከአንድ ዓመት በፊት የነበረው የለውጥ ተስፋ ደብዝዟል::ዴሞክራሲ እና ሰላም ከዚህች ሀገር እየራቁ በአንጻሩ የአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኝነት በአመራሮች ደረጃ ጭምር እየተሰበከ ነው ” የሚለው እስክንድር ነጋ “ወደ ነበርንበት የለውጥ ተስፋ እንድንመለስ እንፈልጋለን:: ሀገሪቱም ወደ ተረጋጋ ሠላሟና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሻገር ጭምር” ሲል ሰልፉን አስመልክቶ ላነጋገረው የአዲስ አበባ ሪፖርተራችን ገልጿል::
በዚህ ወቅት የተለያዮ ግጭቶች በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰታቸውን ተከትሎ ፣ ብዛት ያላቸው የህሊና ዕስረኞችም በተጨማሪነት በግፍ እየተሰቃዮ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የእሁዱ ሰልፍ ሀገራዊ አጀንዳን እንደሚያራምድ የሚናገረው እስክንድር ነጋ አጠቃላይ ሕጋዊውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ነገ አርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለኢትዮጵያ ነገ አስታውቋል::
ግብፅ በአባይ ላይ ያለኝን መብት መከላከል የሚያስችል ኃይልና ቁርጠኝነት አለኝ አለች
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹኩሪ ትናንት ፓርላማ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ የውሃ ሙሌቱን መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል።
“ኢትዮጵያ በኦፕሬሽኑ ቀጥላለች፤ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም። ይህ ተግባር የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ እና በቀጠናው ላይ አለመረጋጋትን በመፍጠር አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ሁሉንም አካላት የሚያስማማ መፍትሄ በማፍለቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ማለታቸውን ከሮይተርስ ዜና ሰምተናል::
የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ መስከረም 23 እና 24 በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የተደረገውን የሦስትዮሽ ምክክር ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርባ ነበር። ኢትዮጵያ በበኩሏ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አልቀበልም ማለቷ ይታወሳል: :
ግብፅ ዓለም ባንክ ሦስተኛ ወገን ሆኖ ልዩነቶችን በመፍታት እንዲያደራድር ግብፅ ምክረ ሃሳብ እንደምታቀርብ የግብፁ አሀራም ኦንላይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዋቢ አድርጎ ሲዘግብ ፣ በትናንትናው ዕለት ሳሚህ ሽኩሪ “ግብፅ ከናይል ወንዝ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳልፋ አትሰጥም” ስለማለታቸው እንዲሁ አህራም የዜና ሽፋን ሰጥቶታል።
“ኢትዮጵያ 630 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የዝናብ ውሃ ታገኛለች፤ 10 ወንዞቿን ሳንጠቅስ ማለት ነው። ግብጽ ግን በውሃ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቃለች። የናይል ውሃ ጉዳይ ለግብጽ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው።” በማለትም ሚኒስትሩ ተናግረዋል::
አህራም እንዳስነበበው የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹኩሪ ሱዳን ከግብጽ ጋር ትብብር እንድታደርግም ጥሪ አቅርበዋል:: “ወንድማማች ህዝቦች ብቻ ስለሆንን ሳይሆን፤ የህዳሴ ግድቡ ግብጽን ብቻ ሳይሆን ሱዳንንም ይጎዳል” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የግብጽ ፓርላማ የህዳሴ ግድብ ግንባታን የሚከታተል ልዩ ጊዜያዊ ኮሚቴ ማቋቋም ተገልጿል። ኮሚቴው የግብጽን የናይል ውሃ የመጠቀም መብት ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንደሚያጠናም አህራም የግብጽ ፓርላማ አባላት የሃገሪቷ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ያስከተለውን ቀውስ ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ እጅግ ደካማ ነው ሲሉም ተችተዋል::
ሃጫሉ ሁንዴሳ በአ/አ ወጣቶች ተደበደበ የሚለው ወሬ ውሸት መሆኑን ድምጻዊው አረጋገጠ
አወዛጋቢው የኦሮምኛ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አበባ ውስጥ ተደበደበ በሚል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጨው ዘገባ ፈጽሞ ስህተት መሆኑን ድምጻዊው አረጋግጧል:: በወቅቱ ከሰዎቹ ጋር የቃላት ልውውጥ ከማድረግ ውጪ ምንም ዓይነት የድብደባ ጥቃት እንዳልተፈጸመበትም መስክሯል::
ሜክሲኮ አካባቢ በተለምዶው ኮሜርስ የተባለው ስፍራን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው እና በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ቪዲዮ ፣ አንዳንዶች ከሚናገሩት የድብደባ ጥቃት ጋር በማይገናኝ መልኩ ከሰዎች ጋር የቃላት ልውውጥ ሲያደርግና አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለመገለገል ጥረት ሲያደርጉ ያሣያል::
ሃጫሉ ከመኪናው ወርዶ በሚናገርበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ለመገላገል ሲሞክሩ ፣ ተጨማሪ ሰዎችም በስፍራው ሲሰበሰቡ እንዲሁም መኪናው የቆመው ሌሎች ተሽከርካሪዎች በሚያልፉበት ቦታ ላይ በመሆኑ መንገድ የተዘጋባቸው መኪኖች የጡሩምባ ድምጽ ሲያሰሙ በቪዲዮው ላይ ይታያል:: በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሃጫሉን ወደመኪናው እንዲሄድ ሲያግባቡት በንዴት “ዐቢይ ላይ ነው . . . ” የሚሉ ቃላትንም በቁጣ ስሜት ሲናገር ይደመጣል። ይህ ሁሉ የሆነው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን ከዛኑ ቀን ጀምሮ ሃጫሉ በአዲስ አበባ ተደበደበ የሚል የሀሰት ዜና ሲሠራጭ ቆይቷል::
ከአፍሪካ ኅብረት ጽህፈት ቤት ጀምረው ግለሰቦቹ እየተከታተሉ እስከሜክሲኮ ድረስ ሲሰድቡት እንደነበረ የተናገረው ሃጫሉ ሁንዴሳ ፣ “እኔ ሰውን አከብራለሁ ነገር ግን እንዲህ መብቴን የሚጥስ ነገር ሲገጥመኝ ከማንም ፈቃድ አልጠይቅም” በማለት የሰዎቹ ድርጊት እንዳስቆጣው ጠቁሞ ፣ ግለሰቦቹ ይሰንዝሯቸው የነበሩት ቃላት ስሜት ውስጥ የሚያስገቡ ስለነበሩ ሜክሲኮ አካባቢ መኪናውን አቁሞ “ሲከተሉኝ ነበር” ያላቸው አራት ሰዎች ወደነበሩበት ሊያናግራቸው መሄዱን ተከትሎ ሰዎች መሰባሰባቸውን ለቢቢሲ ገልጿል::
“የሰዎቹን ንግግር በዝምታ ማለፍ አስቸጋሪ ነበር ፣ ፍላጎታቸው በሚሰነዝሯቸው ቃላት ስሜታዊ በማድረግ አምባ ጓሮ ለመፍጠር ነበር” ሲል ክስተቱን የሚያስታውሰው ዝነኛው የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኙ ድምጻዊው ፤ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ እንደተደጋገመበት፣ በዚህ ወር ውስጥ ይህኛው ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተ ነው ብሏል:: እንዲህ አይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሥርዓት አልበኝነትን ለማስቆም የሚጠበቅበትን ማድረግ ይኖርበታልም ብሏል ድምጻዊዉ።
ውዝግቡ ከተከሰተ በኋላ ፖሊስ ከስፍራው በመድረስ እንደገላገላቸው፣ ለገሐር አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ግለሰቦቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን መለቀቃቸውን ያሳወቀው ሃጫሉ፤ ግለሰቦቹ ይሰነዝሩት የነበሩት ቃላት ከጥላቻ የመነጩና ስሜታዊ ያደርጉ ነበር ቢልም ከግለሰቦቹ ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከሄዱ በኋላ ነገሩ በቀላሉ ማብቃቱን ይፋ አድርጓል::
በ5 ቢሊዮን ብር በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ የተገነባው አንድነት ፓርክ ተመረቀ
በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት የተሠራው አንድነት ፓርክ ዛሬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል። ፓርኩን ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ እንደሆነም ሰምተናል::
ቤተ መንግሥቱ በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ አርፏል:: በውስጡ ሦስት ዋነኛ የቱሪስት መስህቦችንም ይዟል።ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ሲሆን፤ ከአፄ ምንሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው::
ከ1880ዎቹ ጀምሮ የተገነቡ የነገሥታት መኖሪያና ጽህፈት ቤቶች በዋናኝነት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህ ፕሮጀክት የነበሩበትን ይዞታ ሳይለቁ ዕድሳት ተደርጎላቸዋል:: ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የምንሊክ የግብር አዳራሽ ነው፤ ንጉሡ በዚህ አዳራሽ እንግዶቻቸውን ያስተናግዱም ነበር::
የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ሥራን ለመተግበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ታቅዶ በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር በማበርከት የእራት ድግስ የተካሄደበት ‘ገበታ ለሸገር’ መርሃ ግብር የተደረገውም በዚሁ በታደሰው አዳራሽ ውስጥ ነው::
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ልጅ የተዳረችውም በዚሁ አዳራሽ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ጋዜጠኞች ፓርኩን በጎበኙበት ወቅት ተገልጿል።
እኚህ የታሪክ ቅርሶች ሦስት ጊዜ እድሳት ተደርጎላቸዋል ፤ የመጀመሪያው በ1963ዓ.ም በኃይለ ሥላሴ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደርግ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ ሦስተኛው ደግሞ ቫርኔሮ በሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።
በዚህ ሥፍራ የፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) መኖሪያ ቤት በቀዳሚነት ይገኛል:: አባ መላ የአፄ ምንሊክ የጦር ሚንስትር ነበሩ:: ታላቁ የጦር ሠው ይኖሩበት የነበረ ትንሽ የእንጨት ቤት ከአፄ ምንሊክክ መኖሪያ ቤት ጎን ላይ ይገኛል። አፄ ምንሊክ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላም እንደ መኖሪያና ቢሮ አድርገው ሲጠቀሙበት ነበር። ቤቱ ፈርሶ የነበረ ሲሆን አሁን ሙሉ በሙሉ ታድሷል።
የአፄ ምንሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ናቸው:: በሚያምር መልኩ የአበባና የሐረግ ጌጥ የተፈለፈለበት ሆኖም ይታያል:: ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአፄ ምንሊክ የጸሎት ቤትና የሥዕል ቤት ሲሆን እንቁላል ቤት በመባል ይታወቃል:: አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር።
ወደ አጤ ሚኒሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ሲሆን በሚያምር መልኩ የአበባና የሐረግ ጌጥ የተፈለፈለበት ነው። ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአፄ ምንሊክ የጸሎት ቤትና የሥዕል ቤት ሲሆን እንቁላል ቤት በመባል ይጠራል። አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር። በሌላ አቅጣጫ ንጉሡ ከጦር መኮንኖቻቸው ጋር የሚገናኙበት ክፍል ይገኛል። በወቅቱ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ደግሞ ይህንን ክፍል እንደ ቢሮ ይጠቀሙበት ነበር።
ሌላው የዘውድ ቤት ነው፤ ይህ ሕንፃ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነገሥታትንና ዲፕሎማቶችን የተለያዩ ሀገራት ተቀብለው ያስተናግዱበት ነበር ተብሏል:: በህንፃው ከተስተናገዱ የውጪ ሀገራት እንግዶች መካከል በ1965 ንግሥት ኤልሳቤጥ 2ኛ፣ በ1966 የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ቻርልስ ደጋሌ እንዲሁም በ1956 የዩጎዝላቪያው ፕሬዝደንት ቲቶ ይገኙበታል።
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ የዚህን ህንፃ ምድር ቤት የአጼ ኃይለሥላሴን ባለስልጣናት አስሮ ለማሰቃየት ተጠቅመውበታል ተብሏል:: የጸሎት ቤቱና የሥዕል ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ነው። ሁለተኛው ፎቅ ላይ ከፍ ብላ የተሠራች በመስታወት የተሸፈነች ቤት አለች፤ ይህች ቤት ቴሌስኮፕ ያላት ሲሆን አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ ማየት ያስችላል::
በእንቁላል ቤት መገናኛው ድልድይ ጋ የመጀመሪያው ስልክ የገባበት ቤት ይገኛል። ቤቱ ከድንጋይና ከእንጨት የተገነባ ነው። አርክቴክት ዮሐንስ የኪነ ህንፃውን ጥበብ ሲገምቱ ከአርመኖችና ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሕንዶች ሳይሳተፉበት እንደማይቀሩ ይገምታሉ።ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የውይይት ክበብ በመሆን አገልግሏል።ሌላኛው ከአጤ ሚኒሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው። ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው።
በምድር ቤት የዙፋን ግብር ቤት ይገኛል። የነገሥታቱ መመገቢያ አዳራሽ ሲሆን ንጉሣዊ ቤተሰቦች ምግብ የሚመገቡበት ክፍል ነበር፤ ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የደርግ ምክር ቤት መሰብሰቢያ በመሆን አገልግሏል።
በፓርኩ ከተሰሩ መስህቦች መካከል የእንስሳት ማቆያና አኳሪየም (የውሃ አካል) አንደኛው ነው። በዚህም ውስጥ የጥቁር አንበሳ መኖሪያ፣ የዝንጀሮ መጠለያ፣ የአሳ ማርቢያ (አኳሪየም) ጨምሮ የ46 ዓይነት ዝርያ ያላቸው 300 ለሚሆኑ እንስሳት መጠለያ የሚሆን ስፍራም አለ። ለእንስሳቱ ምግብ የሚዘጋጅበትና ሕክምና የሚሰጥበት ሌላ ቦታ ላይ ተገንብቷል:: ይህ የእንስሳት መጠለያ ሕዳር 2012 ሥራ እንደሚጀምር ለማወተችሏል።ቅ በአንድነት ፓርክ ከተካተቱት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚንፀባረቅበት ነው።
ይህ ስፍራ የተገነባው በብሔር ብሔረሰቦች ቤት፣ ባህል፣ ምጣኔ ኃብትና የሕዝቦችን አኗኗር መሰረት በማድረግ እንደሆነና በዚህ ሕንፃ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያንፀባርቁ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በፓርኩ የጓሮ አትክልት፣ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አቀማመጥ በጠበቀ መልኩ ተሰርቷል። በዛሬው እለት የተመረቀው የአንድነት ፓርክ በነገው እለት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንደሚጎበኙት ለማወቅ ተችሏል።
ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ አዛውንቶች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ይጎበኛሉ ተብሏል። ሰኞ ማለትም ከጥቅምት 3 2012 ጅምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር እንዲሁም በቪአይፒ (VIP) 1 ሺህ ብር በመክፈል ቤተ መንግስቱን መጎብኘት ይችላል የተባለ ሲሆን 1000 ብር የሚከፍሉ ጎብኝዎች ታሪካዊ ቁሳቁስ የሚገኙበትንና ሌሎች እንግዶች እንዲያዩ ያልተፈቀደላቸው ስፍራ መጎብኘት ይችላሉ::
ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚካተቱበት የምገባ መርሀ ግብር በቀጣዮ ሳምንት ይተገበራል
ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚካተቱበት የዘንድሮው የምገባ መርሀ ግብር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ይለወጣል መባሉን ዛሬ ሰምተናል::
የሳምንቱ የከተማ መስተዳደሩ የሥራ ግምገማ ዛሬ ሲካሄድ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ ትኩረት የነበረ ሲሆን ለወጣቶች ስራ ፈጣራ የሚቀርቡ የፋይናንስና ሙያዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል ዋነኛ የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት እንደሆነ ነው የተነገረው::
ለመንግሥት ት/ቤት ተማሪዎች የተደረገው የዩኒፎርምና የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ስርጭቱ ስኬታማ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይም ወደ መማር ማስተማር እንደተገባ ያስታወሰው ግምገማ ፤ ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚካተቱበት የዘንድሮው የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብርም በአንዳንድ ት/ቤቶች የተጀመረ ሲሆን ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ በሥራ ላይ ይውላል ተብሏል::
ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆኑም በግምገማው ተነስቷል:: ኢ/ር ታከለ ኡማ በከተማ አስተዳደሩ የሚሰሩ ስራዎች ጠንካራዎቹን የበለጠ ማጠናከርና የሚታዩ ክፍቶችንም በፍጥነት በማስተካከል ለውጡን ማፋጠን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ፓርላማው 88 ዓመት የሞላቸው ሕንጻዎችን ለማፍረስ መወሰኑ አነጋጋሪ ሆነ
የኢትዮጵያ ፓርላማ በውስጡ ከያዛቸው ዕድሜ ጠገብ ከሆኑና ሙሉ ለሙሉ ከድንጋይ የተሠሩ ሕንጻዎች ክፍሎችን ለማፍረስ የፓርላማው ጽ/ቤት መወሰኑን ተከትሎ ቅሬታ ተነስቷል::
በውሳኔው ላይ ግልጽ ቅሬታ የተሰማቸው የአስተዳደር ሠራተኞች የበላይ አመራር አካላት በቂ ጥናትና ምርምር ሳያደርጉ ለጊዜው የተፈጠረውን የቢሮ ዕጥረት ለማስተካከል በሚል ዕሳቤ ከተገነቡ 88 ዓመት የሞላቸው የድንጋይ ቤቶችን በማፍረስ መወሰኑ ስህተት ነው ብለዋል::
ታሪካዊዎቹን የድንጋይ ቤቶች አፈራርሶ ባለ አራት ወለል ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችሉ የማሽነሪና የመሣሪያ አቅርቦት እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ረዥም ዘመናት ያስቆጠሩት ቤቶች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈርሱ ታውቋል::
ፓርላማው ከገጠመው የቢሮ ዕጥረት ጋር በተያያዘ ተቋሙ ከሚገኝበት ግቢ ውጪ በተለምዶ አሮጌ ቄራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የግለሰብ ሕንጻ በዓመት 18 ሚሊዮን ብር ክፍያ በኪራይ መቆየቱ ይታወሳል::
ይህን ችግር ለመቅረፍ ተብሎ ይገነባሉ የተባሉት ሕንጻዎች ማረፊያ እንዲሆኑ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ሁለት ሕንጻዎች ከመፍረሳቸው ባሻገር በተያያዥነት ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎችም የሚፈርሱ ይሆናል:: ለአብነት ያህል የኅትመት ቤት ሆኖ ሲያገለግል የቆየው መደበኛ ቢሮን ጨምሮ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ሦስት ቤቶች ፈራሽ መሆናቸው ተረጋግጧል::