ጠ/ሚ ዐብይ ለኖቤል ሽልማት በመታጨት ሁለተኛው የኢትዮጵያ መሪ እንደሆኑ ያውቃሉ? || ቢቢሲ

ጠ/ሚ ዐብይ ለኖቤል ሽልማት በመታጨት ሁለተኛው የኢትዮጵያ መሪ እንደሆኑ ያውቃሉ? || ቢቢሲ

የዘንድሮው የኖቤል የሠላም ሽልማት እጩ የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከአጼ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ ለሽልማቱ በመታጨት ሁለተኛው የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን ችለዋል።

በስፋት እንደሚነገረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ ዘንድሮ ለሽልማቱ በመታጨት ከቀረቡት ተፎካካሪዎች መካከል ለአሸናፊነት ተስፋ አላቸው ተብሎ ከሚጠበቁት ጥቂት እጩዎች አንዱ እንደሆኑም ተነግሯል።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው የነበሩት ከዛሬ 80 ዓመት በፊት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1938 ነበረ። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለኖቤል ሽልማት በመታጨት ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኖቤል የሠላም ሽልማት ታሪክ ውስጥ በዕጩነት ከቀረቡ ስድስት ንጉሣዊያን መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ከእርሳቸው ቀደም ብለው የሩሲያው ንጉሥ ዳግማዊ ኒኮላስ፣ የስዊዲኑ ልዑል ካርልና የቤልጂየሙ ንጉሥ ቀዳማዊ አልበርት ታጭተው የነበሩ ሲሆን ከእሳቸው በኋላ ደግሞ የግሪኩ ንጉሥ ቀዳማዊ ፖልና የኔዘርላንድስ ልዕልት ዊልሄልሚና ታጭተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩ የሆኑበት የዚህ ውድድር አሸናፊ ዛሬ ምሽት ኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ውስጥ በሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ ይደረጋል። የሌሎቹ የኖቤል ሽልማቶች ግን የሚሰጡት ስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ ነው።

በዚህ ዓመት በተለያዩ የኖቤል ሽልማት በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ የሚሆኑ ግለሰቦች ዘጠኝ ሚሊዮን የስዊዲን ክሮነር ወይም ከ900 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

አንዳንድ እውነታዎች ስለኖቤል የሠላም ሽልማት

በተለያዩ መስኮች ፍር ቀዳጅ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችንን ተቋማት በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

አልፍሬድ ኖቤል ኅዳር 18/1888 ዓ.ም በፈረመው ኑዛዜ ያለውን አብዛኛውን ሃብቱን የኖቤል ሽልማት ተብለው ለሚሰጡ ሽልማቶች እንዲውል ተናዟል።

በኑዛዜው ላይ እንደተገለጸው ከዚህም መካከል አንዱ የሠላም ሽልማት ሲሆን፤ ሽልማቱም “በመንግሥታት መካከል ወንድማማችነት እንዲሰፍን አብዝተው ወይም የተሻለ ሥራን ላከናወኑ፣ የጦር ሠራዊቶች ቅነሳና ለሠላም መስፋፋት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ይሰጥ” ይላል።

እስካሁን የተሰጡ የኖቤል የሰላም ሽልማቶች

ከአውሮፓዊያኑ 1901 ጀምሮ 99 የኖቤል የሠላም ሽልማቶች ተበርክተዋል። ሽልማቱ ከተጀመረ በኋላ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በተካሄዱባቸው ዓመታትና በሌሎችም ምክንያቶች ለ19 ጊዜያት ሳይሰጥ ቀርቷል።

የኖቤል የሽልማት ድርጅት እንደሚለው በመጀመሪያውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ወቅት ጥቂት የሠላም ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ በእጩነት የቀረቡት ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ለሽልማቱ የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦቸው የጎላ ነው ተብሎ ካልታሰበ ነው። በዚህም የሽልማቱ ገንዘብ በድርጅቱ እጅ ስር እንዲቆይ ይደረጋል።

ሽልማቱ በግልና በጋራ ይሰጣል

67 የሚሆኑ የኖቤል የሠላም ሽልማቶች በተናጠል ላሸነፉ ግለሰቦች የተሰጡ ሲሆኑ፤ 30ዎቹ ደግሞ ሁለት ግለሰቦች በጋራ የተሸለሟቸው ናቸው።

2 የሠላም ሽልማቶችን ሦስት ሦስት ሰዎች በቡድን አሸንፈዋል።

ለሦስት ሰዎች የተሰጡት ሽልማቶች በአውሮፓዊያኑ 1994 እና በ2011 ሲሆን የመጀመሪያውን የፍልስጥኤሙ መሪ ያሲር አራፋት እንዲሁም እስራኤላዊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሺሞን ፔሬዝና ይትዛክ ራቢን በጋራ ወስደዋል።

ሁለተኛውን ደግሞ አፍሪካዊቷ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰን፣ ላይቤሪያዊቷ የመብቶች ተሟጋች ሌይማህ ቦዊና የመናዊቷ ጋዜጠኛና የመብት ተከራካሪ ታዋኮል ካርማን ሽልማቱን ተጋርተውታል።

ሽልማቱ ከአንድ በላይ ለሆነ አሸናፊ የሚሰጥ ከሆነ የገንዘቡም መጠን ለአሸናፊዎቹ ይከፋፈላል። ሸላሚው ድርጅት ለአንድ ሽልማት ከሦስት በላይ አሸናፊዎች እንዳይኖሩ ይገድባል።

አጼ ኃይለ ሥላሴ እና ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛ ለንደን ውስጥImage copyrightGETTY IMAGES
አጭር የምስል መግለጫአጼ ኃይለ ሥላሴ እና ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛ ለንደን ውስጥ

የኖቤል የሠላም ሽልማት ለምን ያህል ጊዜ ተሰጠ?

የኖቤል የሠላም ሽልማት ለ133 ግለሰቦችና ተቋማት ተሰጥቷል። ከእነዚህ ውስጥም 106 ግለሰቦች ሲሆኑ 27ቱ ድርጅቶች ናቸው። ከተቋማቱ ውስጥ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ሦስት ጊዜ ሽልማቱን የወሰደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ደግሞ የኖቤል ሠላም ሽልማትን ሁለት ጊዜ ለማግኘት ችሏል።

በእድሜ ትንሿ የኖቤል ሠላም ሽልማት አሸናፊ

ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የምትጥረው ፓኪስታናዊቷ ማላላ ዩሳፍዛይ እንደ አውሮፓዊያኑ 2014 የተሰጠውን የኖቤል የሠላም ሽልማትን በ17 ዓመቷ በማግኘት በዕድሜ ትንሿ የሽልማቱ አሸናፊ ሆናለች።

አዛውንቱ የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ

በትውልድ ፖላንዳዊ በዜግነት እንግሊዛዊ የሆኑት ጆሴፍ ሮትብላት የኑክሌር ጦር መሳሪያ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንደ አውሮፓዊያኑ በ1995 የኖቤል የሠላም ሽልማትን ሲያገኙ እድሜያቸው 87 ነበረ። በዚህም በእድሜ የገፉ የሽልማቱ አሸናፊ ናቸው።

ሴት የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ

እስካሁን በግለሰብ ደረጃ ከተሰጡት 106 የኖቤል የሰላም ሽልማቶች ውስጥ ሴቶች ያገኙት 17ቱን ብቻ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማቱ የተሰጠው የኖቤል ሽልማት በተጀመረ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነበር። ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ 1905 የመጀመሪያዋ ሴት የሽልማቱ አሸናፊ የሆነችው በርታ ቮን ሰትነር ናት። ኦስትሪያዊቷ ሰትነር የረጅም ልቦለድ ጸሐፊና ስለ ሠላም ተከራካሪ ነበረች።

ከአንድ ጊዜ በላይ የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከየትኛው ተቋም በላይ በኖቤል ሠላም ሽልማት ዘርፍ እውቅናን አግኝቷል። ቀይ መስቀል ሦስት ጊዜ ሽልማቱን በመውሰድ ቀዳሚ ሲሆን መስራቹ ሄንሪ ዱና ደግሞ የመጀመሪያውን የኖቤል የሠላም ሽልማትን በመውሰድ ይታወቃል።

የሠላም ሽልማቱን አልቀበልም ያለው ግለሰብ

ቬትናማዊው ፖለቲከኛ ሊ ዱች ቶ በአውሮፓዊያኑ 1973 ከአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በጋራ የኖቤል የሠላም ሽልማትን ቢያሸንፉም ሽልማቱን አልቀበልም በማለት የመጀመሪያው ለመሆን በቅተዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች ለሽልማቱ የተመረጡት የቬትናም የሠላም ስምምነት እንዲደረስ ጉልህ ሚና በመጫወታቸው ነው። ሊ ዱች ቶ የኖቤል የሠላም ሽልማቱን አልቀበልም ያሉት በወቅቱ ቬትናም ውስጥ የነበረውን ሁኔታ እንደምክንያት ጠቅሰው ነው።

በእስር ላይ እያሉ የኖቤል የሠላም ሽልማትን ያሸነፉ

ሦስት ሰዎች እስር ቤት እያሉ የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል። እነርሱም ጀርመናዊው የሠላም ተሟጋችና ጋዜጠኛ ካርል ቮን ኦሲትዝኪ፣ የበርማ ፖለቲከኛዋ አንግ ሳን ሱ ኪ እና ቻይናዊው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሊዩ ዢኦቦ ናቸው።

ከሞቱ በኋላ የኖቤል የሠላም ሽልማትን ያገኙ

አንድ ግለሰብ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ የኖቤል የሠላም ሽልማትን አግኝተዋል። ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ 1961 የተሰጠ ሲሆን ተሸላሚውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊቀመንበር የነበሩት ዳግ ሐመርሾልድ ናቸው።

ከ1974 በኋላ የሽልማቱ ድርጅት ተሸላሚው ህይወቱ ያለፈው አሸናፊ መሆኑ ይፋ ከተደረገ በኋላ ካልሆነ በስተቀር በሞት ለተለዩ ሰዎች ሽልማቱ እንዳይበረከት ወስኗል።

LEAVE A REPLY