የነገው የአዲስ አበባ ሰልፍ ተከለከለ ያገደው ፖሊስ ምንም ምክንያት አላቀረበም
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ በማህበራዊ ሚዲያዎች እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ እንደሚደረግ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሰልፉ ምክንያት የሚዘጉ መንገዶች መኖራቸውን ገለፀ በሚል የኮሚሽኑን አርማና የሓላፊዎችን ስም በመጠቀም የተላለፈው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብለዋል።
በነገው ዕለት ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ስብሰባ በመስቀል አደባባይ የሌለና ምንም የሚዘጋ መንገድ አለመኖሩን አስረድተዋል:: የባላደራው ምክር ቤት ትናንት በሰጠው መግለጫ ላይ ሕጋዊ መስፈርቶችን አሟልተው ለአዲስ አበባ መስተዳደር ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል::
ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ቢያቀርቡም መከልከሉም ሆነ መፈቀዱ እንዳልተገለፀላቸው ተናግረው የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ነገር ግን ሕጉ እንደተፈቀደ ለማሳወቅ አያስገድድም በማለት ዝም በማለታቸው እንደተፈቀደልን ይቆጠራል ብለው ተናግረዋል:: የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው “ተስፋ የተጣለበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጅምር በመቀልበሱ ነው” በማለት ማስታወቁም አይዘነጋም።
ቀደም ሲል በተለያየ መንገድ ነገሮች እንዲስተካከሉ ድምፃቸውን ማሰማታቸውን፤ ነገር ግን ሰሚ በማጣታቸው ሁለተኛውን የሰላማዊ ትግል ስልት ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልፀው ፤ በዚህም መፍትሄ ካላገኘን በቀጣይ መንግሥትን ወደሚያስገድዱ የሥራ ማቆም እና ሌሎች የትግል ስልቶች ለመግባት እንደሚገደዱም በመግለጫቸው ላይ ጠቂመዋል።
ሰኔ 16 አንድም ድጋፍ ያላደረጉት የኦሮሚያ ከተሞች ፤ ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዶ/ር ዐቢይ ሰልፍ ይወጣሉ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሰላም የኖቤል ሽልማት በማስመልከት በነገው ዕለት በመላ ኦሮሚያ የደስታ መግለጫ ሰልፎች የሚደረጉ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች ከተለያየ አቅጣጫ እየተሰሙ ነው።
በአዲስ አበባ ነገ እሁድ የተጠራውን ሕዝባዊ ሰልፍ የከለከለው የታከለ ኡማ ኦዴፓ በሽመልስ አብዲሳ ፊታውራሪነት ነገ በመላ ኦሮሚያ የደስታ መግለጫ ሰልፍ እንደሚያካሂድ ገና ሽልማቱ ይፋ በሆነ 24 ሰዓት ይፋ ማድረጉ ኦዴፓ አፋኝ ከመሆን ባሻገር ለአዲስ አበቤ ልዮ ጥላቻ ያለው መሆኑን አረጋግጧል በሚል እየተተቸ ይገኛል::
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት እንኳን ደስ ያልዎት እንላለን ያሉት ኦዴፓና የኦሮሚያ ዞኖች ቀደም ሲል ለዐቢይ አሕመድ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሲሰጡ አለመታየታቸው ደግሞ የአሁኑን እሽኮለሌ ከልብ የመነጨ አይደለም የሚል አስብሏል:: በተለይም ሰኔ 16 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሲካሄድ በዛው ቀንና በሳምንቱ ባህርዳር ጎንደር ደሴ መላው የአማራ ክልል እንዲሁም የደቡብ ክልልና መላ ኢትዮጵያ የድጋፍ ሰልፎችን ሲያካሂድ ኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ አልተተገበረም ነበር::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ወጥተው በጊዜው ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳያገኙ የቀሩበትን ወሳኝ ወቅት ወደ ኋላ መለስ ብለው የሚያስታውሱ ሰዎች የነገው የድጋፍ ሰልፍ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሰላም የኖቤል ሽልማት በማስመልከት ነው ቢባልም ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር በተለይም ከአዲስ አበባ ጋር ብሽሽቅን ትኩረት ያደረገ ፖለቲካ ነው እየተባለ ነው::
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በሰጡት መግለጫ፤ ድሉ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ ድል ነው ካሉ በኋላ ይህ ትልቅ እውቅና የተገኘው ሕዝቡ አንድነቱን በማጠናከሩና በመደማመጡ የመጣ ትልቅ ድልም መሆኑን ተናግረዋል።
”ይህ የተገኘው ድል እጥፍ ክብርና ድል ነው” ያሉት አቶ ዴሬሳ የክልሉ ህዝብ ደስታው ከተነገረ ጀምሮ በተለያዩ መልኩ ስሜቱን እየገለጸ ይገኛል:: በተለይ ደግሞ የክልሉ ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ደስታውን ለመግለጽ በተለያየ መልኩ ጥያቄዎችን እያቀረበ ይገኛል ነው ያሉት። የክልሉ መንግስት ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሕዝቡ በተናበበና በተቀናጀ ሁኔታ ደስታውን እንዲገልፅ ይደረጋል” ብለዋል።
ለሰልፉ አስፋለጊው የፀጥታ ጥብቃ ተደርጎለት በቀጣይ እሁድ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚካሄድ ይሆናል ነው ያሉት አቶ ዴሬሳ ፤በቀጣይም የተሻለ ድል እና ውጤት ይገኝ ዘንድ ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ እንዲሄድም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ከባህር ዳር የመጡ መኪኖች ዛሬም በቄሮ እና ፖሊሶች መንገድ እንደተዘጋባቸው ቀርተዋል
ትናንት ከረፋድ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጎሃ ፂዮን አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ ተሽከርካሪዎች ማለፍ እንዳልቻሉና ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር መገደዳቸው ይታወሳል:: ይሄ መንገድ ትናንት ይከፈታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዛሬም አለመከፈቱ ታውቋል::
ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ከጎንደር የተሳፈረችው ትዕግስት ደሴ ትናንት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢው ላይ ሲደርሱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተደርድረው እንደተመለከተችና መንገድ መዘጋቱን እንደሰማች ተናግራለች።
ተሳፋሪዎቹ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር ተገደዋል። ደጀን ከተማ ተመላሽ ተሳፋሪዎችን በሙሉ የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ባለመኖራቸው አብዛኛው ሰው በቤተክርስቲያንና ሌሎች ቦታዎች ደጅ ላይ ተጠልለው በከተማው ሕዝብ ምግብና አንዳንድ እርዳታዎች ተደርጎላቸው ነው ያደሩት።
ዛሬ ጠዋት መንገዱ ይከፈት ይሆናል በሚል ተስፋ ደጀን ያደሩት ተሳፋሪዎቹ፤ መንገዱ ዛሬም ባለመከፈቱ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ።እንደውም ይባስ ብሎ ከአዲስ አበባ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎችም መንገዱ በመዘጋቱ ወደ መጡበት ለመመለስም የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ ታውቋል። ትናንት ከአዲስ አበባ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ማለፍ የሚችሉ ቢሆንም ይከፈታል በሚል ተስፋ ግን ከመመለስ ይልቅ መጠባበቁን እንደመረጡ ታውቋል።
“የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምዝገባ በጥቅምት አንድና ሁለት ነው፤ እኔ የተሳፈርኩበት አውቶብስ ውስጥ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ለምዝገባ ለመድረስ የተሳፈሩ ተማሪዎች ናቸው ፣ ትናንት በነበረው ሁኔታ የሕዝብ ማመላለሻዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዓይነት መኪና ማለፍ አይቻልም ” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች::
የደጀን ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ሓላፊ የሆኑት አቶ ካሳ አስፋውም በአሁኑ ሰዓት ኦሮሚያ ክልል ያለው ስላልተከፈተ ደጀን ከተማ ላይ በርካታ መኪኖችና መንገደኞች በከተማዋ እንዳሉና መንገዱ የተዘጋው ኦሮሚያ ክልል የአባይ በረሃ አፋፍን ወጣ እንዳሉ ወረ ጃርሶ ወረዳ ላይ መሆኑን ጠቁመው ስለምክንያቱ የምናውቀው የለም ሲሉ ተናግረዋል።
መንገዱ ከትናንት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በደጀን ከተማ ያለፉ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች መመለሳቸውን የሚናገሩት ሓላፊ ቀኑን ሙሉ ከኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረቦች ጋር ሲደዋወሉ እንደነበር እና እናጣራለን እንዳሏቸውም በማለታቸው መኪኖች መንቀሳቀስ ቢጀምሩም ፣ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ማለፍ ባለመቻላቸው በድጋሚ መመለሳቸውን አረጋግጠዋል።
ምመኪኖቹን የፀጥታ ኃይሎች ፈትሸው ቢያሳልፉም ወጣቶች እንደመለሷቸው ከመንገደኞቹ መስማታቸውን ይናገራሉ።በአንድ ቀን ሰባ፣ ሰማኒያ መኪና፣ በምሽት ደግሞ ከእጥፍ በላይ ከደጀን ወደ አዲስ አበባ መስመር የሚንቀሳቀሱ መኪኖች መኖራቸውን በመናገር ከተማዋ ላይ አሁን ከፍተኛ የመኪና ቁጥር መኖሩን አስረድተዋል።
በትናንትናው ዕለት በከተማዋ ከ200 በላይ መኪኖች ማደራቸውን ያደሩ ሲሆን፤ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ አዛውንቶች፣ ነፍሰጡሮች እንዳሉ፤ ተማሪዎቹም የመመዝገቢያ ቀን እንዳያልፍባቸው ስጋት እንደገባቸው እና ከትናንት ጀምሮ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች ማለፍ እንደማይችሉ ሌሎች ግን ማለፍ እንዳልተከለከሉ አቶ ካሳ ገልጸዋል።
ዛሬ ማለዳ ከኦሮሚያ ፖሊስ ምላሽ እንዳልተገኘም ሓላፊው ተናግረዋል።በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ኃላፊ አቶ ለማ ሆርዶፋ በበኩላቸው ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ የተዘጋበትን ምክንያት ለማጣራት አመራሮችን ወደ ሥፍራው እንደላኩ ጠቁመው፤ ዛሬ ጠዋትም በጉዳዩ ላይ ተነጋግረውበት አንድም መኪና መቆም እንደማይችል አቅጣጫ አስቀምጠው መኪና በሰላማዊ መልኩ እያለፈ እንደሆነ መረጃ አለኝ ብለዋል።
ተሳፋሪዎች ግን አሁንም መንገዱ እንደተዘጋ መናገራቸው የተገለጸላቸው ሓላፊ፤ “በአሁኑ ሰዓት ራሱ መኪና እያለፈ ነው፤ መንገድ ላይ ምንም ችግር እንደሌለ ተጨባጭ መረጃ አለኝ ” ሲሉ ድፍን ያለ ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
በየትኛውም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ መኪና በሠላም እየተንቀሳቀሰ እንዳለ እርግጠኛ እንደሆኑና ትናንት ጠዋት ላይ መንገድ መዘጋቱን አስታውሰው “ከምስራቅ ጎጃም ዞን የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረን፤ ወዲያውኑ አቅጣጫ አስቀምጠን ችግሩ ተፈቷል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ኃላፊው የሚያጣሩ ሁለት አመራሮችን ወደ ጎሃ ፅዮን መላካቸውን ከመግለፅ ባለፈ እስካሁን ምክንያቱ ተጣርቶ፤ በማንና ለምን እንደተዘጋ ግልፅ መረጃ እንደሌላቸው ነግረውናል።መንገዱ ስለመዘጋቱ የፀጥታ ኃይሉ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም መባሉንም ያነሳንላቸው ኃላፊ “ይህንን ኃላፊነት ወስጄ አጣራለሁ፤ ችግር የለውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር አጎራባች አካባቢዎችን በተመለከተ አዳማ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ የገለፁልን ኃላፊው አክለውም፤ በደብረ ብርሃን በኩልም ወደ አዲስ አበባ የሚያስገባው መንገድ ተዘግቷል መባሉንም “ውሸት ነው” በማለት ሰላም መሆኑን እንደሚያውቁ ገልፀውልናል።
ኦዴፓና አዲስ አበባ ፖሊስ የከተማዋን ወጣት በጅምላ እያፈሱ ነው
በፍርሐት እየራደ የሰነበተው የነጻነት ግንባር ቀደም ተፋላሚ የሆኑት የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጅምላ ማፈስ ጀመረ:: ትናንት የተደራጁ ጽንፈኛ የኦሮሞ ወጣቶች የባላደራውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማስተጓጎል ሲሞክሩ ግልጽ የሆነ ድጋፍ ሲያደርግ የታየው አዲስ አበባ ፖሊስ ከትናንት ምሽት ጀምሮ አፈሳ እያካሄደ ይገኛል::
የኣዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርሀት መግለጫ እንደሚያሳየው አዲስ አበባ ውስጥ የሚደረግ እንቅስቃሴን የሚገድብ ሰርኩላር አውጇል። መንግስት የባለ አደራው ምክር ቤት ሰልፍ መጥራት ለምን ሽብርና ፍርሀት እንደለቀቀበት በይፋ አልገለጸም። በተቀነባበሩ መልኩ ሰልፉን ለማደናቀፍ የሚሰራው ሴራ ግን አሁንም ቀጥሎ ዛሬ ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እያሠረ ነው::
ይህ ብቻ ሳይሆን ተረኞቹ ኦዴፓዎች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚያስገባውን መንገድ ዘግተውታል። መንገደኞች መንገድ ላይ ታግተው ያሉ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ የባለ አደራው ምክር ቤት የጠራው ሰልፍ ላይ ለመሳተፍ በመሄድ ላይ ናችሁ በሚል መሆኑ ታውቋል። ይህ የሚያመለክተው መንግስት በፍርሐት ሰንሰለት ከመታሰሩም አልፎ ለዜጎች መብት እንደማይጨነቅ ማሳያ ነው።ሕዝብን በማንገላታት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለነገ አደጋ እንዳለው በቅጡ መረዳት ያዳገታቸው ኦዴፓ እና በስሩ የተቋቋመው የይስሙላው የአዲስ አበባ ፖሊስ ወጣቶችን ከሕግ አግባብ ውጪ ማሰሩን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል::
ከትናንት ከሰዓት በጀመረው የአፈሳ ተግባር የፈረንሣይ ለጋሲዮን የ4 ኪሎ፣ የፒያሳ የልደታ፣ የአብነት፣ የአውቶቢስ ተራ፣ የጨርቆስ እና የሳሪስ ሰፈር ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባላደራውን ደግፋችሁ ሰልፍ ልትወጡ ነው በሚል በአምባገነኑ የኦዴፓ አመራሮች ልዮ ትዕዛዝ ለሕገ ወጥ ዕስር ተዳርገዋል::
ክልሎች በልዮ ኃይል ስም ማዕከላዊ መንግሥትን የሚገዳደር ጦር ፈጥረዋል ሲሉ ገብሩ አሥራት ተናገሩ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ያላቸው የአረና ትግራይ ፓርቲ አባልና ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አሥራት ክልሎች እያዋቀሯቸው ያሉት ልዮ ኃይሎች በከፍተኛ ሁኔታ ፌደራል መንግሥቱን የሚገዳደሩ ናቸው ሲሉ ተናገሩ::
የሕወሓት መሥራች እና የቀድሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራት ከ17 ዓመት በፊት በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ድርጅቱ ለሁለት ሲሰነጠቅ በአቶ መለስ ዜናዊና ስብሓት ነጋ ቡድን ተገፍተው ከድርጅቱ በግፍ መባረራቸው ይታወቃል::
የወያኔን ሥርዓት ጥለው ከወጡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመሠረቱት እና የአስራ ሁለት ዓመታት ዕድሜን ባስቆጠረው አረና ፓርቲ አማካይነት በሠላማዊ መንገድ ጭቆናን ለማስወገድ እየታገሉ ናቸው:: “ከእኛ በኋላ መጥተው አንዳንድ ፓርቲዎች ይሄን ሠራን እንዲህ አደረግን በእኛ ምክንያት ነው ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው ይላሉ:: ግን በጣም አስቸጋሪ በሆነው የሕወሓት አፈና ውስጥ የተንቀሳቀስንና የታገልን ፓርቲ እኛ አረናዎች ነን” የሚሉት አቶ ገብሩ አሥራት ፓርቲው ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን አራት አባላት ተገድለውበት የሞት መሰዋዕትነት በመክፈል ጭምር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሕወሓትን እየታገለ መሆኑን ለግዮን መጽሔት በሠጡት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል ታየፈድሰናል ቢባልም ሕወሓት እንኳን ሊታደስ ከእኔ ሌላ ፓርቲ ትግራይ ውስጥ መኖር የለበትም አቋም በማራመድ ላይ ነው በማለት የሚወቅሱት የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት በሌሎች ክልልሎች እንደሚታየው የገዢ ፓርቲውና የተቃዋሚዎች ውይይትን በትግራይ ለማምጣት በአረና በኩል ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ሕወሓት በቸልተኝነት መሰንበቱን አጋልጠዋል::
በአሁኑ ወቅት ሁሉም የኢሕአዴግ ፓርቲዎች አጋር የሚባሉትን ጨምሮ ሁሉም በየአካባቢያቸው ነገሥታት ናቸው በማለት “የእኔነት” ስሜት በግልጽ እየተስተዋለ መሆኑን የሚናገሩት ገብሩ አሥራት ” የልዮ ኃይል ሥልጣንና ገደብ በሕግ ያልተቀመጠ ነው:: ልዮ ኃይል ሲባል ስንትና ምን ያህል ነው? ክፍለ ጦር ማዘጋጀት አንድ ክልል ይችላል ወይ? የሚለው በሕግ ያለ አይመስለኝም” በማለት ጥርጣሬያቸውን በግልጽ ካስቀመጡ በኋለ “ክልሎች በልዮ ኃይል ስም ማዕከላዊ መንግሥትን የሚገዳደር ጦር እየፈጠሩ ነው” ሲሉ ሕገ ወጥ የጦር ግንባታውን ተችተዋል::
በቅርቡ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተናገሩት ዓይነት ንግግር የሁሉም የፓርቲና የክልል መሪዎች የተለመደ ጽንፈኛ አቋም የመያዝ ስሜት መሆኑን በግዮን መጽሔት ላይ ያመላከቱት ገብሩ አሥራት እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የፓርቲ አመራሮች ቁስል ከሚነካ እንዲህ ዓይነቱ ንግግር መቆጠብ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል::
ሕወሓትንም ሆነ ትግራይን ወክለው ብዙ ጊዜ መግለጫ የሚሰጡት ጌታቸው ረዳና ዶ/ር ደብረፂዮን ምንም ዓይነት ሥልጣን የሌላቸው ታዛዥ እና ተላላኪ ናቸው በማለት አሁንም የሕወሓት የበላይ አዛዦች ነባር ታጋዮች መሆናቸውን ባሳወቁበት ንግግር ” እንደ በፊቱም ባይሆን አልፎ አልፎ የትግል አጋሬ የነበሩ የሕወሓት ሰዎችን አገኛቸዋለሁ:: እነዚህ የሕወሓት ቀደምት ባለሥልጣናት አሁን በሚገኙበት ትግራይ ውስጥ መንግሥታዊ ሓላፊነት ባይኖራቸውም በጡረታ ቢገለሉም በሕወሓት ጉዳይም ሆነ ስለ ትግራይ ውሳኔ የሚሰጡት አዛዥ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው” ብለዋል::