የአዲስ አበቤን ዲሞክራሲያዊ መብት የነፈጉት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በኦሮሚያ አደባባዮች ሲወደሱ ዋሉ
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን የኖቤል ሽልማት በማስመልከት በተለያዮ ከተሞች የደስታ መግለጫ ሰልፎች ተካሄዱ። ጠቅላይ ሚንስትሩ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከ20 በማያንሱ የኦሮሚያ ከተሞች የደስታ መግለጫ ሰልፎች በኦዴፓ እና የኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት ተከናውነዋል።
በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንዲሁም በድሬ-ደዋ ከተማ አስተዳደር የደስታ መግለጫ ሰልፎች መካሄዳቸው ተሰምቷል::
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ግልጽ በሆነ የኦሮሞ ብሔርተኝነት በገነነባት ሀገር ላይ ሰልፎቹ በነጻነት መካሄዳቸውን የሚያረጋግጡ በ19 ከተሞች የተደረጉ ሰልፎችን የሚያሳይ ምስል መለጠፋቸውንም ታዝበናል።
የደስታ መግለጫ ሰልፎች ከተካሄዱባቸው ከተሞች መካከል፤ ወሊሶ፣ ጅማ፣ አጋሮ፣ በደሌ፣ መቱ፣ ጊንጪ፣ አምቦ፣ ነቀምቴ፣ አዳማ፣ ዱከም፣ ባቱ፣ ሻሸመኔ፡ ጉጂ፣ ነገሌ ቦረ፣ ቡሌ ሆራ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ፊቼ እንዲሁም በምዕራብ እና ምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ከተሞች በዋናነት ይጠቀሳሉ::
አርብ ዕለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንዳሸነፉ ከተሰማ በኋላ ለድጋፍ ሰልፎቹ በማህብራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥሪ ሲደረጉ ቆይተው 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምባገነኑ ኦዴፓ በኦሮሚያ ከተሞች እሁድ የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ በማስታወቅ ባለ ጊዜው የነጻነት ተቋዳሽ የኦሮሚያ ሕዝብ ብቻ መሆኑን ባረጋገጠ መልኩ የአዲስ አበባን ሕዝብ ድምጽ እንዲታፈን ስውር ትዕዛዝ ማስተላለፉን በርካታ ፖሐቲከኞች እየገለጹ ነው::
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውልድ ስፍራ ጅማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ ወጣቶች”የደስታ ሰልፍ የተከናወነባት ጅማ ከተማ ልዩ የሆነ ስሜት ውስጥ ነው የምትገኘው” ካሉ በኋላ የጅማ ዩኒቨርሲቲባዘጋጀው አውቶቢስ ሕዝቡ ወደ ስታዲየም መምጣቱን እና የዐቢይ ሽልማት የእኛም ሽልማት ጭምር ነው በማለት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሻሸመኔ በተካሄደው የድስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲእንደተናገሩት፤ ሰልፈኞቹ ደስታቸውን ከመግለጻቸው በተጨማሪ በወለጋና በጉጂ አካባቢዎች መንግሥት ጸጥታ እንዲያሰከብር ድምጻቸውን እግረመንገድ ማሰማታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰሞኑን ከተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች የመጡ ሰዎች እንደልብ በሩጫ እና በኢሬቻ በዓል ላይ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በማራገብ እንደፈለጉ በፈነጩባት አዲስ አበባ ላይ የከተማዋ ነዋሪ ለሚያነሳቸው ሀገራዊ ጥያቄዎች ዲሞክራሲያዊ መብቱን ነፍገው የኦሮሚያ ወጣቶች በመንገድ መዝጋት አስነዋሪ ተግባር ውስጥና በድጋፍ ሰልፍ እንዳሻቸው እንዲሆኑ ማድረጋቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል::
የአማራ ሕዝብ ተገፊነት፣ የአዴፓ ሥልጣን አልባነት የታየበት የባሕር ዳር መንገድ ተከፈተ
ከባህር ዳር አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ዓርብ መስከረም 30፣ 2012 ከረፋድ 5ሰዓት ጀምሮ ጎሃ ፅዮን ላይ ተዘግቶ ቆይቶ ትናንት ማታ መከፈቱን የአካባቢው ባለስልጣናት እና መንገደኞች ተናግረዋል።
የደጀን ወረዳ አስተዳዳርና ፀጥታ ሓላፊ አቶ ካሳሁን አስፋው “ቀድሞውኑ መንገዱ የተዘጋበት ምክንያት አግባብ አልነበረም። ለመንገዱ መዘጋትም ሆነ መከፈት የተነገረን ምክንያት የለም፤ ኦሮሚያ ላይ ያሉ ሰዎች ጋር ስንደውል መንገዱ አልተዘጋም ክፍት ነው ይሉናል፤ መኪኖችን ስንልክ ደግሞ ተመልሰው ይመጣሉ” በማለት ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
ከጎንደር ተነስታ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘች ያለችው ትዕግስት ደሴ፤ መንገዱ ተከፍቶ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ እያደረገች እንደሆነ ገልጻ ፣ አርብ ዕለት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢው አካባቢ መንገድ ተዘግቶ እንደነበረ እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተደርድረው እንደተመለከተችም አስታውሳለች።
“ዛሬ ጠዋ እሁድ ጥቅምት 2ቀን ከደጀን ተነስተን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እያደረግን ነው። አሁን ፍቼ አካባቢ ደርሰናል:ከትናንት ወዲያ አርብ ነው እዚህ የደረስኩት፣ ከዚያ ወደ ደጀን ተመልሰን። ዛሬ እንግዲህ መንገድ ተከፍቶ ጉዞ የጀመርነው” በማለት ለቢቢሲ በጠቆመችበት መግለጫ ለሦስት ቀናት በመንገድ ላይ መጉላሏቷን እና አብረዋት ያሉት አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎቹ ተማሪዎች እንደሆኑ ፣ትናንት ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር እንደተገደዱም ተናግራለች።
ደጀን ከተማ ተመላሽ ተሳፋሪዎችን በሙሉ የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ባለመኖራቸው አብዛኛው ሰው በቤተክርስቲያን፣ በሰው ቤት እና ደጅ ላይ ተጠልለው ነበር ያደሩት:: “አንድ ግዜ ከመኪና ወርደን ተፈትሸናል። መንገዱ ሰላም ነው” በማለት ዛሬ ላይ ያለውን ሁኔታ አስረድታለች። የደጀን ወረዳ አስተዳዳርና ፀጥታ ሓላፊ አቶ ካሳሁን መንገዱ ክፍት የሆነው ትናንት አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ነው ይላሉ። “አባይ በረሃ ላይ ብዙ መኪኖች በአንድ ጊዜ መተላለፍ ስለማይችሉ ቅድሚያ አባይ በረሃ ውስጥ ቆመው ለነበሩ መኪኖች ቅድሚያ በመስጠት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ቀርፈናል” ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ቢሮ ሓላፊ የሆኑት አቶ ለማ ሆርዶፋ ግን ቀድሞውንም ቢሆን መንገዱ አልተዘጋም በሚል አይን ያወጣ ውሸት ተናግረዋል::
አቶ ለማ ትናንት ቅዳሜ መኪኖች በሰላማዊ መልኩ እያለፉ እንደሆነ መረጃው አለኝ ሲሉ የሀሰት እና የንቀት አስተያየት መስጠታቸው አይዘነጋም:: ዛሬ እሁድ ጠዋትም ”መንገዱ ቀድሞም አልተዘጋም፤ ይኸው አሁን ፍቼ ከተማ ነው ያለኹት መኪኖች እያለፉ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል::
ዓለም አቀፍ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሪ በያዘችው ሀገር ለእሁድ ሰልፍ ወደ አዲስ አበባ እየሄዳችሁ ነው በሚል የሠንጋ ቡድን ኢትዮጵያውያን መንገድ ላይ ሁለት ቀን እንዲያድሩ ሲደረግ ምንም መፈየድ ያልቻለው የአማራ ክልል መንግሥት በአዴፓ የአዛዥነት ብልጫ እንደተወሰደበት ከማሳየቱ ባሻገር ሥልጣኑን በእጅ አዙር እየዘወረ ነው የሚባለው ጽንፈኛ ቡድን ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጥላቻና የማህበረሰቡን ተገፊነት ያሳየ ነው ተብሏል::
ፖሊስ የአዲስ አበባን ወጣቶች ያሰርኩት ለራሳቸው ደህንነት ነው አለ
በአዲስ አበባ የባላደራ ምክር ቤት ለጥቅምት 2 ይዞት የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ አባላቶቻቸው መታሰራቸውን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ለኢትዮጵያ ነገ ገልጿል። ሰልፉ በፖሊስ መሠረዙን ተከትሎ የአዲስ አበባ ነዋሪ ውሳኔውን ተቀብሎ ባለበት ሁኔታ ፖሊሶች ግን አሁንም ከየሰፈሩ ወጣቶችን በማሰር ላይ ናቸው ብሏል::
በትናንትናው ዕለት ለሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳ በወጡበት ወቅት “ሁከት ፈጥራችኋል” በሚል በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል በባላደራ ምክር ቤት የጉለሌ አስተባባሪ፣ እንዲሁም የሰልፉ አስተባባሪ የሆነው ናትናኤል ያለም ዘውድ አንዱነው።
ናትናኤል በቁጥጥር ስር የዋለው በትናንትናው ዕለት ጥዋት አራት ሰዓት ላይ ፒያሳ አካባቢ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም ከተለያዩ ስፍራዎች ተወስደው ለእስር ታደርገዋል።
በተያዙበትም ወቅት እንደሚፈለጉና ሕገ-ወጥ ቅስቀሳዎችን እያደረጉ በመሆናቸው ሓላፊውን ማናገር አለባችሁ ብለው ቢወስዷቸውም ጣቢያ ሲደርሱ ስልካቸውን እንደቀሟቸው ናትናኤል ይናገራል። “ሕጋዊ ሰልፍ ነው፤ መንግሥት እውቅና የሰጠው ሰልፍ ነው” ብለው ቢያስረዱም ተሰሚነትን እንዳላገኙ፣ ከላይ ትእዛዝም እስኪመጣ ጠብቁ መባላቸውን ገልጿል።
ናትናኤል የሰልፉ አስተባባሪ በመሆኑ ለብቻው ተለይቶ እንደተጠየቀና “አዲስ አበባ ፖሊስ ሰልፉን ከልክሎታል፤ ቅስቀሳ ማድረግ አትችልም መባሉን” እንዲሁም፤ አንደኛው መርማሪ “ለአንተ ደህንነት ነው ያሰርንህ፤ ከተለያዩ ቦታ የመጡ ሰዎች በናንተ ሰልፍ መጥራት ተናደው ጉዳት ሊያደርሱባችሁ ስላሰቡ ለእናንተ ደህንነት ነው” እንዳሏቸው ነግሮናል::
የፖሊሶቹ አስገራሚና ሰንካላ ምክንያት ያልተዋጠለት ወጣቱ ናትናኤል “መረጃው ካላችሁና ጉዳት ሊያደርሱ የመጡ ሰዎችን ማሰር አይቀልም ወይ” ብሎ ቢጠይቅም ከፖሊሶቹ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊያገኝ አለመቻሉን ለኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አስረድቷል።
አመሻሽ አራት ሰዓት ላይ “ሰልፍ የሚባል ነገር አለመኖሩንና አርፈው እንዲቀመጡ” ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን ጠቁሞ እሱ ታስሮበት በነበረው ጣይቱ ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሃያ የሚቆጠሩ የጃ ንሜዳ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ልጆች መታሰራቸውን፤ እንዲሁም መርካቶ ባሉት ፖሊስ ጣቢያዎች በቁጥር የማያውቃቸው ብዙ አባላቶቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።
ናትናኤልን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ትናንት ወደ አመሻሹ ላይ ቢፈቱም ዛሬ እሁድ ማለዳ ላይ ከየሰፈሩ በርካታ ወጣቶች ትፈለጋላችሁ በሚል በየቦታው ለዕስር መዳረጋቸውን ምንሊክ ሆስፒታል ፈረንሳይ ለጋሲዮን እና አውቶቢስ ተራ አካባቢ የተዘዋወረው ሪፖርተራችን ታዝቧል::
የባላደራ ምክር ቤቱ ህዝባዊ ሰልፉን ለመሰረዝ መገደዱንም ገልጿል። እስክንድር ነጋ በትናንትናው እለት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው ፖሊስ ባደረገው ክልከላ የተቃውሞ ሰልፉን መሰረዙን አስፍሯል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ የተፈቀደም ሰልፍ ይሁን በሰልፉ የሚዘጉ መንገዶች የሉም የሚለውን ክልከላ ተከትሎም ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ “ለሃገሪቱ ሰላምና ለህዝቧ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ሰልፉን ሰርዟል” ሲል አስታውቋል::
ትናንት ምሽት በፍልውሃ አካባቢ ፌደራል ፖሊሶች እርስ በርስ ተታኩሰው 2 አባላት ሲሞቱ 4ቱ ቆስለዋል
ትናንት አዲስ አበባ ከተማን በአስፈሪ ድባብ ተላብሰው ሲጠብቁ የነበሩ ፖሊሶች ማምሻውን እርስ በርሳቸው ተኩስ ከፍተው መገዳደላቸው ተሰማ::
በአዲስ አበባ በተለምዶ ፍልውሃ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 2 የፌደራል ፖሊስ አባላት ህይወታቸው ማለፉን የፌደራል ፖሊስ ኮምንኬሽን ለሸገር አረጋግጧል።
ፌደራል ፖሊሶቹ በከፈቱት የእርስ በርስ ተኩስ ልውወጥ ከሞቱት ሁለት አባላት በተጨማሪ 4 ፌደራል ፖሊሶችም መቁሰላቸውን ተሰምቷል።
ምክንያቱም ምን እንደሆነ የተጠየቁት የሥራ ሓላፊ የአንድ አባል ቀልድ መሳይ ብሽሽቅ ነው ሲሉ ተደምጠዋል:: በተጀመረው ብሽሽቅ አንደኛው አባል 2 ጓደኞቹን በእጁ በያዘው መሳሪያ ተኩሶ መግደሉን የፌደራል ፖሊስ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ህይወት ያጠፋው አባልም እንደቆሰለ እና ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሆነ ከዜናው መረዳት ችለናል። የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ፍልውሀ አካባቢ ምን ያደርጉ እንደነበር ለቀረበው ጥያቄ ፤ የኮሚንኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ጄላን አባሎቹ በአካባቢው የሚኖሩበት ቦታ አለ፣ በጥበቃም ሥራም የተሰየሙ ነበሩ የሚል ድፍንፍን ያለ ምላሽ ከመሥጠት ውጪ ብሽሽቁ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሁን አይሁን ግልጽ አላደረጉም።
የካቢኔ አባላት “እውነት ፍቅር ያሸንፋል” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ሐብል ዶ/ር ዐቢይን ሸለሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማግኘታቸው ተከትሎ የተለያዮ መንግሥታዊ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ናቸው::
በሀገር ውስጥም የደስታ መግለጫው ተጠናክሮ ቀጥሏል:: ዛሬ እሁድ ጥቅምት 2 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሾሟቸው የካቢኔ አባላት በጽሕፈት ቤታቸው በመገኘት ደስታቸውን እንደገለጹ ተሰምቷል::
የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም ለተገኘው ስኬት ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ የወርቅ ሐብል በስጦታ አበርክተዋል::
የካቢኔ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታሪካዊ ስኬት የደስታ መግለጫ በስጦታ ባበረከቱት የአንገት ሐብል ላይ “እውነት ፍቅር ያሸንፋል” የሚል ጽሑፍ እንደተቀረጸበት ታውቋል።