የእነ ጀነራል ተፈራ ማሞን ከዕስር መፈታት ተከትሎ የባህርዳር ነዋሪ አደባባይ ወጣ
ዛሬ ከዕስር የተፈቱት የአማራ ክልል የፀጥታ አመራሮችን አስመልክቶ የባህር ዳር ነዋሪዎች ደስታቸውን አደባባይ ወጥተው እየገለጹ ናቸው:: ከተማዋም በተለየ ሁኔታ ተነቃቅታለች ውላለች።
ከሰኔ 15 ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በእስር ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ብርጋዴየር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረ እና ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተለቀዋል።
ጉዳያቸው እየተጣራ በዕስር የቆዩት ተጠርጣሪዎቹ ባለፈው ሐሙስ ዋስትና ጠይቀው ነበር፤ መዝገቡን ተመልከቶ ውሳኔ ለመስጠትም ለዛሬ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል። በቀጠሮው መሠረትም ዓቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ሰጥቷል።
ከምርመራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የተጣሩ መሆናቸውንና ሓላፊነታቸውን ተወጥተዋል ወይስ አልተወጡም የሚለው ጭብጥ ዋስትና የሚያስከለክል አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ መግለጹን የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቀቤ ሕግ የክልል ዓቃቤ ሕግ ኢዮብ ጌታቸው አስረድተዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ዋስ አቅርበው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል:: በዚህ መሠረትም ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና አቅርበው ከሰዓት በኋላ መውጣታቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል::
ኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ልዮ ዞን ሕዝብን እያሳመጸ ነው ተባለ
በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ኦነግ ሸኔ ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳመጽ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው:: በቅርቡ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ወረዳ ተከስቶ የነበረው ግጭትም መነሻው የታጣቂው ኦነግ ሸኔ ቅስቀሳ እንደሆነ ሰምተናል::
የኦነግ የጦር ክንፍ የነበረው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ በመግባት “አማራ ሃይማኖትህን ሊያስቀይርህ እና ሊወርህ ተዘጋጅቷል” በማለት ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል::
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የሸኔ ታጣቂ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር አድርጊያለሁ ሲል ከዚህ ቀደም ገልጾ የነበረ ቢሆንም ቡድኑ በአጣዬና ማጀቴ አካባቢ በአማራ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ከማድረሱ ባሻገር ወደኦሮሚያ ልዮ ዞን ዘልቆ በመግባት ሕዝቡ ለአመጽ እንዲነሳሳ ቅስቀሳውን በነጻነት እያካሄደ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸውልናል::
በአፋር ክልል 17 ሰዎች በታጣቂዎች በግፍ መገደላቸው ተረጋገጠ
በአፋር ክልል፣ አፋንቦ ወረዳ፣ ኦብኖ ቀበሌ ሳንጋ የሚባል ጣቢያ ላይ አርብቶ አደሮች በሰፈሩበት አካባቢ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታወቀ::
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አሊ ባሳለፍነው አርብ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ተፈፅሟል ባሉት ጥቃት፤ 17 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የስድስት ወር ህፃንን ጨምሮ ሴቶችና አረጋዊያን ይገኙበታል።
በ34 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። አራቱ ከ7 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲሆኑ፤ ዘጠኙ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል። የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው በአሳይታና በዱብቲ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተከታተሉ ሲሆን የከፋ ጉዳት ያጋጠማቸው ወደ መቀሌ ሆስፒታል መላካቸውን ሓላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የነዋሪዎቹ ንብረት የሆኑ በርካታ እንስሳትም ተገድለዋል፤ በንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል። የጥቃቱን ምክንያት በውል ባይታወቅም ከዚህ በፊት ከሚደርሱ አንዳንድ ግጭቶች በመነሳት የመሬት ወረራ ሊሆን እንደሚችል ቅድመ ግምታቸውን ያስቀመጡት አቶ ሁሴን አሊ ፤ “የመሬት ወረራ ነው፤ ወረዳው በሶማሌ ክልል ስር መሆን አለበት የሚሉ ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፤ ስለዚህ የመሬት ወረራ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለም ” ብለዋል።
መሬት ወረራ ለመሆኑ ምን ማስረጃ እንዳለቸው ለቀረበላቸው ጥያቄም ከአሁን በፊት የአርብቶ አደሮችን እንስሳት እየዘረፉና ግለሰቦችን እየገደሉ ይሄዱ እንደነበር ጠቅሰዋል። ታጣቂዎቹ በቁጥጥር ሥር አለማዋላቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው ካገኟቸው መታወቂያዎችና ሌሎች ማስረጃዎች ግን የጥቃት አድራሾቹን ማንነት መረዳት እንደቻሉ አብራርተዋል::
ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላም በአፋር ክልል በአብዛኛው የኢሳ ጎሳ አባላት ወደሰፈሩበት ‘ሃሪሶ’ የተባለ ቦታ ገብተዋል::”ጥቃት ፈፃሚዎቹ እንደ መትረየስ እና ቦምብ ያሉ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅመዋል” የሚሉት አመራር በጥቃቱ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን እና ወጣቶች ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።
በወቅቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን ለመከላከል ካደረጉት ጥረት ውጪ “ጥቃት አድራሾቹ ያሰቡትንከፈፀሙ በኋላ ወደ መጡበት ተመልሰዋል” በማለት የክልሉ መንግሥት የወሰደው እርምጃ እንደሌለ እና የክልሉ አመራሮች ወደ ሥፍራው አቅንተው የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በምሽት ወደ ሥፍራው በመሄድ እንስሳት መስረቅና አንዳንድ ሰዎችን ገድሎ መሄድ ካልሆነ በስተቀር እንደ አሁኑ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ተፈፅሞ እንደማያውቅም ሰምተናል። “በወረዳው 400 የሚጠጉ አርብቶ አደሮች ይኖራሉ” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ አሎ ያዩ በበኩላቸው፤ በርካታ አርብቶ አደሮች በሚገኙበት ኦብኖ ቀበሌ ጥቃት መፈፀሙን ይናገራሉ።
አስተዳዳሪው በጥቃቱ በሰው ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን የንብረት ውድመትም አስከትሏል። በአካባቢው በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት እንደሚደርስ ያስረዳሉ። አቶ አሎ ቦታው ድንበር በመሆኑ ከአዋሽ እስከ ጅቡቲ ያለው መንገድ ተመሳሳይ ጥቃቶችን እንደሚያስተናግድ ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም ነፍሰ ጡሮች ሳይቀሩ የተገደሉበት አጋጣሚ መኖሩን አስታውሰዋል።
የአፋር ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ አሕመድ ካሎይታ፤ በክልሉ ዞን አንድ፣ አፋንቦ ወረዳ ላይ በአርብቶ አደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን አመላክተው ፣ ጥቃቱም ከጅቡቲ በመጡ ከባድ መሳሪያ በታጠቁ ኃይሎች መፈፀሙን፣ በጥቃቱም ሴቶችና ህፃናትም ሰለባ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
“የደረሰው ጥቃት አሳዛኝና የሚያሳምም ነው” የሚሉት ሓላፊ አካባቢው ድንበር በመሆኑ ሕገ ወጥ ኮንትሮባንዲስቶች መንቀሳቀሻ መሆኑን አመልክተው፤ ታጣቂዎቹ ይህንን ሕገ ወጥ ድርጊት እንደልባቸው ለማንቀሳቀስ በማሰብ አርብቶ አደሮቹ ላይ ጥቃት እንደፈፀሙ እና በጥቃቱም ከጂቡቲ የገቡ እና የኢሳ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸውን ይናገራሉ።
“በዋናነት ሕፃናትና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው ነው ጥቃቱን የፈፀሙት” የሚሉት እኚህ ሓላፊ ሕይወታቸው ያለፉ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ላይ የሚገኙ እንዳሉ ተናግረዋል። “በአካባቢው ከክልሉ አልፎ ለአገር ስጋት የሆኑና ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ንግድ የሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦች አሉ፤ ብዙ ጊዜም ሕገ ወጥ መሣሪያዎች በአካባቢው ይያዛ፤ በመሆኑም የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሔ ሊወስድ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ ባለሥልጣናት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋጋጥ እየሠሩ መሆናቸውን ግን አልሸሸጉም::
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞቱ ሰዎች አስከሬን ከ7 ወር በኋላ ለቤተሰቦቻቸው መሰጠት ተጀመረ
ከወራት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ መሆኑ ተነገረ።
መጋቢት 1/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጠዋት ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ በጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው። ቦይንግ 737 ማክስ የተከሰከሰው ቢሾፍቱ አቅራቢያ ሲሆን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ ተሳፍረው የነበሩት 157 መንገደኞች ከሰላሳ አገራት የተውጣጡ ቢሆንም ከአደጋው የተረፈ ሰው አልነበረም። አደጋው በመላው ዓለም ድንጋጤን ፈጥሮም ነበር:: ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት 32 ኬንያውያን ሲሆኑ አስከሬናቸውም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ነው።
“በጣም የሚያሳዝነው ነገር እስካሁንም በጣም የተወሰኑትን የሰውነት ክፍሎች እንጂ ሙሉ የሰውነት ክፍል አላገኘንም፤ ይህ ደግሞ ለቀሪ ሥራዎችም ትልቅ ፈተና እንደሚሆንብን እንጠብቃለን፤ ለሃዘንተኛ ቤተሰቦችም ይህን ችግር እያሰረዳናቸው ነው” በማለት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከወራት በፊት መናገራቸው አይዘነጋም:::
የሟቾቹን አስከሬን ለመለየት የዲኤንኤ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ የሰባት ወራት ጊዜም ፈጅቷል። በቦሌ አየር ማረፊያ የቤተሰቦቻቸውን፣ የዘመድ ወዳጆቻቸውን አስከሬን ሊወስዱ የመጡ ግለሰቦች በሃዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ታይተዋል።
ከአደጋው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አስከሬናቸውን ማየት የቻሉት። በዛሬው ዕለትም በኬንያ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች የሃዘን ሥነ ሥርዓትም ይካሄዳል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለስልጣናት እንደተናገሩት መለየት ያልተቻለ አስከሬን እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች አደጋው በተከሰተበት አካባቢ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች በሚሠራው የማስታወሻ ስፍራ ይቀበራል::
የደሴና ኮምቦልቻ መንገድ በ13 ኪሎ ሜትር ሊያጥር መሆኑ ተሰማ
የደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ የሆነችውን የደሴ ከተማን ከኮምቦልቻ ከተማ ጋር የሚያገናኘው እና በተለምዶ ሃረጎ ተብሎ የሚጠራውን ጠመዝማዛ እና 20 ኪሎ ሜትር መንገድ ለማሳጠር መታሰቡ ተነገረ:: መንገዱ በዋሻ ውስጥ በሚዘረጋ 13 ኪሎ ሜትር የሚተካ መንገድ ለማሠራት ሥራ መጀመሩም ታውቋል::
ደሴ ከተማ በተለምዶ አሬራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን አዝዋ ገደል (ዶሮ መዝለያ) ዋሻ በመሥራት ሁለቱን ከተሞች ለማገናኘት የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ያፒ መርከዚ የተሰኘው ተቋራጭ ሥራውን እንዲሠራ ተመርጦ ሥራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል::
ኮምቦልቻ አየር ማረፊያን ጨምሮ የተለዮ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች የሚገኙ ሲሆን በዚህም ቀንድ ከብት ንግድን ጨምሮ የተለያዮ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደረግባት ከተማ ናት:: ደሰቅ ወደቡ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት መዳረሻ የሆነችው ከተማዋ ከጅቡቲ አፋር አድርጎ ወደ ኮምቦልቻ የሚደርስ መሆኑ ለመንገዱ ማጠር ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል::
የ15 ሺኅ ተማሪዎችን ዩኒፎርም ያላደረሱት የፍቅር ጋርመንት ባለቤት ታሰሩ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የደንብ ልብስ ለማሠራት ያወጣውን ጨረታ ካሸነፉት 18 ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የፍቅር ጋርመንት ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ነገ ባልደረባ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል::
ባለሀብቱ ከጥራት በታች የሆነ ጨርቅ ከውጪ አምጥተዋል በሚል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ ዉሉን በማቋረጥ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል:: ፍቅር ሌዘርና ጋርመንት ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር በጨረታው የቴክኒክ መስፈርት መሠረት ከተቀመጠው መመሪያ ውጪ ወደ ቻይና በመጓዝ ” ካሽሚር” የተባለ ጨርቅ ናሙና መላካቸውን ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ አድርሷቸው ነበር::
ሆኖም ማስጠንቀቂያውን ባለመቀበልና ማስተካከያ ባለማድረጋቸው ውሉን በማቋረጥ ገንዘቡን ድርጅቱ እንዲመልስ ከተማ አስተዳደሩ ክስ መስርቷል:: ሁለቱ ወገኖች አስቀድመው በፈጸሙት ውል መሠረት “ቲትረን 6000” በተባለ እና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በሚዘጋጅ ጨርቅ የደንብ ልብሱን ከዲዛይነሮቹ በቀረበላቸው መመሪያ ተሠርቶ ለመረካከብ ስምምነት ነበራቸው:: በግልጽ የታየው ግን ፍቅር ጋርመንት የቀረበላቸውን መመሪያ ወደ ጎን በመተው ያነሰ ጥራት ያለውን ጨርቅ ለመጠቀም ሞክረዋል ነው የተባለው::
የከተማ አስተዳደሩ የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ ለማግኘት ባለመቻሉ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ ድርጅቱ ድረስ በመሄድ ለጥፎ እንደነበር የአዲስ አበባ ሪፖርተራችን ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ ይናገራል:: ከሥራው አጣዳፊነት የተነሳ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘቱ ከተማ አስተዳደሩ ጉዳዮን ለፖሊስና ለዐቃቤ ሕግ አሳውቋል::
በቀጣይ የሚፈጠረው ችግር ክፉኛ ያሳሰባቸው የፍቅር ጋርመንት ባለቤት ለቅድሚያ ክፍያ የወሰዱትን 9 ሚሊዮን ብር ቢመልሱም ቅጣቱንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል::