የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የህዳሴ ግድቡ የተርባይኖች መጠን መቀነስ ችግር እንደሌለው ሥራ አስኪያጁ አስታወቁ

በህዳሴ ግድቡ ላይ በቅርቡ ሊገጠሙ ከታቀዱት አስራ ስድስት ተርባይኖች መካከል ሦስቱ እንዲቀነሱ ምክረ ሃሳብ መቅረቡን የሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሃሮ ተናገሩ።

የተርባይኖች መጠን መቀነሱ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት ኢንጅነሩ፤ አንድ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ትልቅነት የሚለካው ጄነሬተሮች ወይም ተርባይኖችን በመደርደር አይደለም ብለዋል:: በተጨማሪምብዙ ተርባይኖችን መደርደር ሁልጊዜም አዋጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ለአንድ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ቁልፍ ከሆኑት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠንና ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ተወርውሮ ተርባይኑን ይመታል የሚሉት ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ከዝናብ መጠን ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን እና የውሃው የከፍታ መጠን ሊለያይ እንደሚችል በማስገንዘብ፤ የህዳሴ ግድቡ ያመነጫል ተብሎ የተሰላው በዓመት በአማካይ 15.760 ጊጋ ዋት ወይም አንድ ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሃዎር እንደሆነ ገልጸዋል።

“በዚህ የኢነርጂ (ኃይል) መጠን ላይ የተለወጠ ነገር የለም፤ አሁን ይህን ኢነርጂ (ኃይል) ለተጠቃሚው እንዴት ላድርስ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ጄነሬተሮች ይመጣሉ” በማለት የሚናገሩት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ጄነሬተሮች መካኒካል ኢነርጂን ወደ ኤሌክትሪካል ኢነርጂ እንደሚቀይሩ በመጠቆም “ጄነሬተር ወይም ተርባይን መደርደር በሚመነጨው የኢነርጂ (የኃይል) መጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም” ሲሉ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

የተርባይን እና ጄነሬተር ቁጥር የሚወሰነው፤ ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን፣ ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ላይ በምን ያክል ፍጥነት ተርባይኑን ይመታል፣ የኃይል ፍላጎት፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ እና የመሳሰሉት ላይ ነው ይላሉ። “10፣ 12፣ 20 ጄነሬተሮች ቢደረደሩ ተመሳሳይ የሆነ ኢነርጂ (ኃይል) ነው ማመንጨት የምንችለው” በማለትም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

“ተርባይን ተቀነሰ ብሎ ማውራቱ ትርጉም የለውም። ለአንድ የሃይድሮ ኃይል ማመንጫ ወሳኙ ኢነርጂ (ኃይል) ነው” የሚሉት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ጥቅም ላይ ይውላሉ ከተባሉት ከ16ቱ ተርባይኖች መካከል ሦስቱን ለመቀነስ የታሰበው ከዋጋና አዋጭነት አንፃር እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢንጂነር ክፍሌ ይህ ውሳኔ በምንም ዓይነት መልኩ ከግብጽ ፍላጎት ጋር የተገናኘ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ብቻ ያስገባ እንደሆነ ያስረዳሉ። “እንዳውም ብዙ ጀነሬተር ብንደርድር ብዙ ውሃ እንለቃለን ማለት ነው። ይህ ደግሞ የእነሱ ፍላጎት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 68.58 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። “ይህ የሲቪል፣ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የኃይድሮሊክስ ስትራክቸርን ጨምሮ ነው፤ በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2013 ዓ.ም. ላይ ኃይል ማመንጨት እና 2015 ደግሞ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ የተያዘ እቅድ ነው” ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ልዩነቶችን መፈጠሩ ይታወሳል። ከቀናት በፊት የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹኩሪ ለግብጽ የህዝብ እንደራሴዎች ባሰሙት ንግግር ግብጽ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው ጥቅም እና መብት አስከብራ ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱ እንዳላት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ያደረጉት የሦስትዮሽ ምክክር አለመሳካቱን ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል።

የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ አሜሪካ አደራዳሪ እንድትሆን ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም፤ ኢትዮጵያ ግን የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ይፋ አድርጋለች።

የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሩሲያ ተገናኘተው በጉዳዩ ላይ ለመምከር መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ፕሬዝደንቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን በሩሲያ መቼ እንደሚያገኙ ግልጽ ባያደርጉም ሩሲያ ጥቅምት 12 እና 13 ሩሲያ-አፍሪካ መድረክ የምታዘጋጅ መሆኑ ታውቋል።

“መደመር” የተሰኘው የዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ ቅዳሜ በ20 ከተሞች ይመረቃል

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈው “መደመር” መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል ተባለ።የመጽሐፉ ምረቃ አዲስ አበባን ጨምሮ በ20 ከተሞች በአንድ ቀን የሚከናወንም እንደሆነ ተነግሯል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ እና ሀረር ከተሞች በተገለጸው ቀን ይመረቃል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቶቹ ላይም የየከተሞቹ ነዋሪዎች፣ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በየአካባቢው ባህል መሰረት የምረቃ ሥነ ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን፥ ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ መረጃም ይሰጣል ተብሏል።

ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ቋንቋዎች ከመዘጋጀቱ ባሻገር 1 ሚሊየን ቅጂዎችም ታትመዋል። የመጽሐፉ ዋጋ 300 ብር ሲሆን፥ ገቢውም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት ይውላል ነው የተባለው።

የሀገር ውስጥ ምረቃው ከተጠናቀቀ በኋላ በውጭ ሀገራት በአሜሪካ እና ኬንያ፣ በተለይም በዋኝንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ እና ናይሮቢ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወን ይሆናል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሓላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ፥ መጽሐፉ በመደመር እሳቤ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ እና ኢንግሊዘኛ ቋንቋዎች ነው የተጻፈው። የኢንግሊዘኛው ቅጂ ግን ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ አዲስ ለምታስገነባው ፓርላማ ሕንጻ 370 ሚሊዮን ዶላር ሊሠጥ ነው

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥት ኢትዮጵያ ለምታስገነባው አዲስ የፓርላማ ህንጻ 370 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመስጠት ቃል መግባቱን አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለጹት ፤ የምክር ቤቱ ዲፕሎማሲ ሥራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማዕከል በማድረግ የመንግሥትን የልማት ግብ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው።

ከቀናት በፊት በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የልዑካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገው የሥራ ጉብኝትና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤታማ መሆኑን በዚህ ዕርዳታ ታይቷል ማለት ይቻላል። ሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ ደርሰው ሀገሪቱ ገንዘቡን ለመርዳት ቃል በመግባት በወዳጅነት መፈራረማቸው ዛሬ ተረጋግጧል::

የአዲሱ የፓርላማ ግንባታ ለምክር ቤቱ አባላት ጠቃሚ ሚና አለው ያሉት አቶ ተስፋዬ፥ ለአባላቱ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ምቹ ዐውድ እንደሚኖረውና ሥራቸውን በተሻለ መልኩ እንዲያከናውኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የልዑካን ቡድን ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት በፓርላማዎቻቸው መካከል የሚደረግ ትብብርን ለማሳደግና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግንኙነት በሁሉም አቅጣጫ እየተሻሻለ እና የልማት ትብብሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ ይገኛል። በአገልግሎት ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህንጻ አባላት እንዲሰበሰቡ እኤአ በ1930ዎቹ የተሠራ መሆኑ አይዘነጋም።

በኮንታ ልዮ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 21 ሰዎች ሞቱ

በደቡብ ክልል በኮንታ ልዩ ወረዳ ከባድ ዝናብን ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 21 ደርሷል።

አደጋው ከትናንት በስቲያ እሁድ ምሽት ከፍተኛ መጠን ያለውን ዝናብ  መዝነቡን ተከትሎ መድረሱን የኮንታ ልዩ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ይፋ አድርጓል።

የመሬት መንሸራተት አደጋው የተከሰተው በወረዳው አመያ 03 ቀበሌ ልዩ ስሙ ዱካ ዛሌ መዳኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን መሄጃ ላይ መሆኑ ታውቋል። በመሬት መንሸራተት አደጋውም በአካባቢው የነበሩ ቁጥራቸው አምስት የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች በናዳው ስር ተውጠዋል። በዚሀም በአደጋውም ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 21 መድረሱን ነው ጽሕፈት ቤቱ የገለጸው።

በአደጋው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከልም አንድ የፖሊስ አባል ከነ ሙሉ ቤተሰቦቹ እንዲሁም ሌሎችም ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው እንደሚገኙበት ከዜናው መረዳት ችለናል::

ሕወሓት ለቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የማዕካላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁ ተነገረ

ከ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት የተገፋው ሕወሓት ለቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የማዕካላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁ ተነገረ:: ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሳበው የ2011 ዓ.ም ቁልፍ እና ዐበይት ተግባራትን በዝርዝር ገምግሟል።

በተለይም መልካም አስተዳደርን በማስፈን እና ልማትን በማረጋገጥ በኩል ያሉትን አፈፃፀሞች ተመልክቷል ነው የተባለው::

ሕወሓት በ2011 ዓ.ም የነበሩ ሀገራዊ እና ዓለም ቀፋዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥንካሬዎችን እና ጉድለቶችን በዝርዝር በማየት ያሉትን ተግዳሮቶች ለመከላከል የሚያስችል አቅጣጫ በማስቀመጥ እና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቅቋል መባሉም ተሰምቷል::

በአብዛኛው ከማዕከላዊ መንግሥት እያፈነገጠ የሚገኘው ሕወሓት  በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ከእሱ ውጪ ምንም ዓይነት ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ ሕዝቡን ክፉኛ ጨቁኖ ይዞ እያሰቃየ መሆኑን ነባር የድርጅቱ ታጋይ አቶ ገብሩ አሥራት  መግለጻቸውን ኢትዮጵያ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን መዘገቡ ይታወሳል::

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ም/ቤት ስብሰባ ተጀመረ

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሽልማት መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤዋ፥ የሰላም ዋጋ ምን ያክል ውድ እና መተኪያ የሌለው ነው ብለዋል። የዚህ ባለቤቶችም እኛው ስለሆንን ለአፍታ ባለመዘናጋት የተገኘውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይገባናል ሲሉ ደስታቸውን አሰምተዋል።

አያይዘውም የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም መልካም ውጤቶችንና አዳዲስ ተስፋዎችን ጭምር በህዝቡ ውስጥ የፈጠረ መሆኑንም  አመላክተዋል። መንግሥት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያሳየው ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ፣ የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች እንዲደመጡ ለማስቻል እየተሠራ ያለው ሥራ የሀገራችንን መጻኢ ዕድል በዓለም አደባባይ እንዲታይ አስችሏልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በያዝነው በጀት ዓመት እንደ ምርጫና የህዝብና ቤት ቆጠራ ያሉ ትልልቅ ሃገራዊ ኩነቶች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል:: ምርጫውን ለማሳካት የመንግሥት ቁርጠኝነትና ዝግጅት ብቻውን በቂ ስለማይሆን ህዝብና የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2012 ዓ.ም ዕቅድ በምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መንግሥቱ ሻንካ በኩል መቅረቡን ከምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ምክር ቤቱ እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሚያካሂደው ስብሰባ በክልሉ መንግሥት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎችና በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም በ9ኛው ጉባኤ ባልታየው የ2012 ዓመት ዝርዝር የሥራ ዕቅድ ላይ በመወያየት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY