ይህን መጽሐፍ የማዘጋጀት ሐሳብ ውስጤ የተከሰተው በነሐሴ 2004 ነበር፡፡ በወቅቱ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰርኩ በኋላ ጫና፣ እንግልትና ስቃይ ከሞላበት ምርመራ ወደ ቀዝቃዛ የእስረኛ ማረፊያ ክፍል ስመለስ ጽናት አገኝ ዘንድ ቁርኣንን ማንበብ አዘወትር ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ አንዳንድ የቁርኣን አንቀፆች ጽናት እየለገሱኝ፤ ሌሎች ደግሞ እንዳስተነትን እየገፋፉኝ ከፊሎቹ ከዚያ በፊት ያላነብኳቸው ይመስል እያስገረሙኝ ቆየሁ፡፡ በተለይ የአምባገነኑን ፊርዐውን ታሪክ የሚያወሱ ኣያዎችን (አንቀጾችን) ሳነብ ደግሞ አምባገነኖች ሙሉ ሥዕላቸው ውስጤ ይፈጠር ጀመር፡፡ በዚህን ጊዜ
ስለ ፊርዐውንና አምባገነኖች የመጻፉ ሐሳብ በውስጤ ተፈጠረ፡፡ በማዕከላዊ እስር ቤት በተለይ ደግሞ በእስረኞች ላይ በሮቹ ለ24 ሰዓት ዝግ የሚሆንበት የሳይቤሪያ (በተለምዶ) እና ድቅድቅ የጨለማ ክፍል (ስምንት ቁጥር) ብዕርም ሆነ ወረቀት ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ማዘጋጀት ቀርቶ ማስታወሻ መያዝ የማይቻል ነበር፡፡ የነበረኝ ብቸኛው አማራጭ የቁርኣን አንቀጾችን እየደጋገሙ በማንበብና በማስተንተን ከአዕምሮ ጓዳ ላይ ለማስቀረት መሞከር ብቻ ነበር፡፡ በዚሁ ሁኔታ ላይ ሳለሁ አንድ ዕለት የማዕከላዊ አመራሮች ወደቢሯቸው ጠሩኝ፡፡ እንደገባሁም፦ ‹‹በሙስሊሞችና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ በምን መልኩ ሊፈታ እንደሚችል የችግሩን መነሻ እና የመፍትሔ ሐሳብ እንድትጽፍ መንግሥት ይፈልጋል፡፡›› ተባልኩ፡፡ ብዕርና ወረቀትም ሰጡኝ፡፡
ለሁለት ቀናት ጉዳዩን በጥልቀት ሳስብና ሳሰላስል ቆየሁ፡፡
የነበርኩበት ድቅድቅ ጨለማ፣ ጠባብና ቀዝቃዛ ክፍል ለመፃፍ የማይሞከርበት በመሆኑ በመጠኑ የተሻለ ብርሃን ወዳለው ክፍል ቀየሩኝ፡፡ እኔም ነፃ ሆኜ የችግሩን ምንጭ እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በዝርዝር ጻፍኩኝ፡፡ ጽሑፉን በዚያው ዕለት በነሐሴ 14/2004 ምሽት ላይ ለኮማንደር ተክላይ አስረከብኩ፡፡ የፃፍኩትን የመፍትሔ ሐሳብ አልተደሰቱበትም ነበርና አንዷም ነጥብ በተግባር ላይ ሳትውል ቀረች፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በእጄ ላይ የገባች ብዕር ኋላ ላይም በፍተሻ እስክትወሰድ ድረስ አብራኝ ቆየች፡፡ ቁርኣንን በማንበብም በርካታ አንቀጾች ላይ ምልክት ማድረግ ቻልኩ፡፡ ከፊርዐውንም ባሻገር ስለ ኒፋቅ፣ ጽናት እና ስኬት የመጻፍ ሐሳብ ሰንቄ ነበርና ለዚህ ተግባር የሚያግዙኝን አንቀጾች በውስጤ ማንሸራሸር ጀመርኩ፡፡ በተለይ ደግሞ ከመስከረም 2005 ጀምሮ የነበረው ጊዜ ምርመራው ተጠናቆ ታሳሪው በጫና የማያምነበት ላይ ፈርሞ ስለነበር ብዙ ጊዜ ነበረው፡፡ የማዕከላዊ ቆይታችንን ጨርሰን በጥቅምት 19/2005 ‹‹ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል መናድ›› የሚል እና ‹‹የሽብር ተግባር መፈጸም›› የሚሉ ሁለት ክሶች ተመሠረቱብን፡፡ በዚያው ዕለትም ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወረድን፡፡
ተከሰን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መውረዳችን ለብዙዎቻችን የተፈታን ያክል ነፃነት ተሰማን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መገላገላችን ነበር፡፡ ቃሊቲ ስንደርስም በማዕከላዊ ስናነባቸው የነበሩት መጻሕፍት በሙሉ ‹‹ይመረመራሉ›› በሚል ሰበብ ተወሰዱብን፡፡ ምልክት ሳደርግባት የነበረችው ቁርኣንም በዚህ ጊዜ አብራ ተወሰደች፡፡ ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ መጋቢት 2005 ‹‹ተመርምረው መግባት የተፈቀደላቸው›› ተብለው ጥቂት መጻሕፍት በእጃችን ገቡ፡፡ በዚህን ጊዜ ምልክት ሳደርግባት ከነበርኩበት ቁርኣን ጋር ዳግም ተገናኘን፡፡ እስከዚያ ድረስ ከሌሎች እስረኞች እዋሳቸው ከነበሩት መጻሕፍት ሌላ ቃሊቲ ዞን ሁለት በነበርኩበት ጊዜ በዞኑ ቤተመጻሕፍት ውስጥ ያገኘኋቸውን ጥቂት መጻሕፍት አነብ ነበር፡፡ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከማዕከላዊ በተለየ ሁኔታ ወረቀቶች፣ ደብተር እና ብዕር መግባት ይችሉ ነበር፡፡ (ከፍርድ ቤት ጉዳይ ውጭ እንዳይወጣ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል) እስረኛው የራሱን ጉዳይ መከታተልና ማስፈፀም እንዲችል በየዞኑ በሚገኙት ሱቆች ውስጥ በሽያጭ ይቀርቡለትም ነበር፡፡
በሚያዚያ 2005 የአማርኛውን ቁርኣን ሙሉ ትርጉም ማግኘት በመቻሌ በማዕከላዊ ምልክት ያደረኩባቸውን አንቀጾች የአማርኛ ትርጉማቸውን ወደ ማስታወሻ ደብተሬ መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡ በግንቦት 2005 በቃሊቲ ማረምያ ቤት የነበርን የቀጠሮ እስረኞች በሙሉ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተዘዋወርን፡፡ እዚያም ስንደርስ ከፍተኛ ፍተሻ ተደረገብንና በየዞኑ ተደለደልን፡፡ ማስታወሻ ደብተሮቼ ይወሰዳሉ የሚል ስጋት አድሮብኝ የነበረ ቢሆንም ከመወሰድ ተረፉ፡፡ ቂሊንጦ ስንደርስ እኔና አባሪዎቼ በሙሉ በዞን አንድ ተመደብን፡፡ ከሌሎች ታሳሪዎች በተለየ ከቤተሰብና ጠያቂ ጋር የምንገናኘው ከሰኞ እስከ አርብ ከ6፡00-6፡30 ለሰላሳ ደቂቃ፣ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ እስከ ሰባት ሰዓት ተደረገ፡፡ ሌሎች እስረኞች ጠዋት 3፡00-6፡00 ከሰዓት ደግሞ 8፡00-10፡00 በቤተሰብና ወዳጆቻቸው ሲጠየቁ የኛ ጊዜ ማጠሩ በአንድ በኩል አድሎ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ጊዜ እንድናገኝ ረዳን፡፡ ሰኔ 20 ቀን 2005 ላይ መጽሐፍ የማዘጋጀቱን ሥራ ጀመርኩ፡፡ (በእርግጥ ከዚያ በፊት የፃፍኳቸው የመጽሐፉ ጅምሮች ነበሩ፡፡) በመስከረም 18 ቀን 2006 እኔና በድሩ ሑሴን ሌሎች አባሪዎቻችንን ተከትለን ከነበርንበት ወደዞን ሦስት ተዛወርን፡፡ ቀደም ብሎ በአንድ ዞን የነበርነው ወደሦስቱም ዞኖች ተበታተንን፡፡ ይህ የተደረገው ከቤተሰብ ጋር የምንገናኝበት ሁኔታ እንደሌሎች እስረኞች እንዲሆን ተብሎ እንደሆነ ተነግሮን ነበር፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በውስን ዘመዶችና ጠባብ ጊዜ የመጠየቁ ሂደት ቀርቶ እንደማንኛውም እስረኛ ሆነ፡፡ ይህም ከሕዝቡ ጋር ለመገናኘት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረ፡፡ አብዛኛውን ጊዜያችንንም ጠያቂዎችን በማስተናገድ ወደማዋሉ ገባን፡፡ የጀመርኳቸው መጻሕፍት የመጨረሱ ሂደት ጊዜ ሊወስድ ግድ ሆነ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ከመስከረም 2006 ጀምሮ እንደ ሌሎች እስረኞች መጻሕፍት ሳንሱር እየተደረገ ማስገባት ተፈቀደልን፡፡ በእርግጥ የሚገቡት መጻሕፍት ማረሚያ ቤቱ እንድናነባቸው ወሰነልንና እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ከቁርኣን ባሻገር ሌሎች መጻሕፍትን ከታሳሪው እየተዋስኩ፣ ቤተመጻሕፍቱ የሚገኙትንና ተፈቅዶልኝ የሚገቡትን መጻሕፍት ማንበቡን ተያያዝኩት፡፡
ቂሊንጦ የቀጠሮ እስረኞች ማረፊያ ቤት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመጠኑ ይሻላል፡፡ ቃሊቲ ዞን 2 በነበርኩበት ጊዜ የቆየሁበት 4ኛ ቤት ከሦስት መቶ በላይ እስረኞች ያድሩበት ነበር፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሰው ተፋፍጎ መሬት ላይ በደቦቃ ይተኛ ነበር፡፡ ቤቱ ከቆርቆሮ የተሠራ በመሆኑ የሰው ትንፋሽ በሚፈጥረው ሙቀት የእስረኛው ላብ ጣሪያ ላይ ተጠራቅሞ እንደ ዝናብ በሰው ላይ ይጠባጠብ ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ማንበብና መጻፍ አስቸጋሪ ቢሆንም በወቅቱ ለአርባ ቀናት ያክል ደቦቃ በተኛሁበት ጊዜም ይሁን አልጋ ካገኘሁ ቡኋላ ለማንበብና ለመፃፍ ሙከራ አድርጌ ነበር፡፡ ምን እንደማነብና ምን እንደምጽፍ ለማወቅ ይጣጣሩ የነበሩት ‹‹እስረኞች›› በሌሊት ጭምር ይከታተሉኝ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ከነአባሪዎቼ በጠባቧ ዞን-3 ስድስተኛ ቤት በተሰባሰብንበት ጊዜ የቤቱ ሁኔታ የተሻለ ቢሆንም ክትትሉ ግን አልቀረም ነበር፡፡
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእያንዳንዱ ቤት ከ100-120 እስረኛ ይታሰራሉ፡፡ ቤቶቹም ከድንጋይና ብሎኬት የተሠሩ ሲሆኑ ከቃሊቲ ጋር ሲነጻጸር ሙቀቱም ቢሆን ምቹ ነው፡፡ ለጠያቂዎች እጅግ መራቁ እንጂ ለእስረኞች ከቃሊቲ የተሻለ ሊባል የሚችል ነው፡፡ቂሊንጦ ከሁኔታው ጋር ራስን አላምዶ ማንበብበና መጻፍ ግድ ይላል፡፡ ያለበለዚያ በየቤቱ የሚገኙት 2 ጥጋቸውን ይዘው የሚገኙት ቴሌቭዥኖች ጩኸት በተለይ ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጫወታ ባለ ቀን ከተመልካቹ ጩኸት ጋር ጆሮ ያደነቁራሉ፡፡ እስኪለምዱት አልፎ አልፎም ቢሆን የትኋን ትንኮሳም በራሱ ሐሳብ ይሠርቃል፡፡ እነዚህን ከሌላው እስረኛ ጋር የምንጋራቸው ቅጣቶች ሳያንስ የሕዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትንና አባሪዎቻችንን ለረዥም ጊዜ በልዩ ጥበቃ የማየት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ምን እንደምናወራ፣ ምን እንደምንጽፍና እንደምናስብ ለማወቅ እኛን እንዲከታተሉ ሥራ የተሰጣቸው ‹‹ታሳሪዎች›› ነበሩ፡፡ የሚረብሹኝን ነገሮችና ሰዎችን ለመሸሽ ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ የዒሻ ሰላቴን እንደሰገድኩ ከነጫጫታው የመተኛት ልምድ አዳበርኩ፡፡ ሰው ሁሉ ወደመኝታው ካቀናና ፀጥታ ከሠፈነ በኃላ ከለሊቱ 6 ሰዓት ላይ ከእንቅልፌ በመንቃት እስከንጋት ማንበብና መጻፍም ጀመርኩ፡፡ ይህ መጽሐፍም የተጻፈው በዚህ መልኩ ነበር፡፡
እስር ቤት ብዙ ድንገተኛ ፍተሻዎች ተደርገው የታሳሪዎች የግል ማስታወሻዎች ይወሰዳሉ፡፡ በመሆኑም እስረኛው የፃፋቸው ጽሑፎች እንዳይወሰድበት ይጠነቀቃል፡፡ ብዙ ታሳሪዎች የፃፏቸውን ጽሑፎች ሲቀሙ ዳግም የመጻፍ ሞራል በቀላሉ አይመጣላቸውም፡፡ ቃሊቲም ሆነ ቂሊንጦ እስር ቤቶች ከኔም ሆነ ከአባሪዎቼ በተለያየ ጊዜ በርካታ ማስታወሻ ደብተሮች በፍተሻ ተወስደዋል፡፡ ለምሳሌ እኔ በማረሚያ ቤቶቹ በነበረኝ የሁለት ዓመት ከወራት ቆይታ ውስጥ በአጠቃላይ አስራ ሁለት ማስታወሻ ደብተሮች ተወስዶብኛል፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ድርጊት ማሰልቸቱና በመጠኑም ቢሆን ተስፋ ማስቆረጡ እንዳይፈጠር ራስን ማፅናናትና የሞራል ከፍታ ላይ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ በሚወሰድብኝ ሰዓት ሁሉ ይህ ድርጊታቸው ከመጻፍ እንዳያግደኝ ራሴን አሳምኛለሁ፡፡ በወረቀቱ ላይ የሰፈረውን እንጅ ከሰው አዕምሮ ያለውን መውሰድ አይቻል?
ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ ፍተሻ ከሚያደርግባቸው እስረኞችም አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ፍተሻ ሲኖር በርከት ያሉ ፖሊሶች ወደየመኝታ ክፍሉ በድንገት ይገባሉ፡፡ እስረኛውን ወደውጭ በማስወጣትና በር በመዝጋት ብርበራ ያካሂዳሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለፍተሻ የሚመጡት እስረኛው መኝታ ላይ በሆነበት ለሊት ከ11፡00 እስከ 11፡30 ባለው ጊዜ ሲሆን አንዳንዴ ፍተሻ በቀን የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ በተለይ የእኔን መኝታ ቦታ ብቻ ትኩረት አድርገው ለመፈተሽ በድንገት ይመጡ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት (መጋቢት ወር 2006) ውስጥ እንደተለመደው ሌሊት 11፡25 ላይ ተቀምጬ እየፃፍኩ ነበር፡፡ ያለሁበት መኝታ ቤት ከውጭ የተቆለፈብንን ቁልፍ የመከፈት ድምፅ ተሰማኝ፡፡ አመጣጣቸው ለፍተሻ መሆኑ ገባኝ፡፡ ዝግጁ ሆኜ ጠበቅሁ፡፡ ወዲያው በሩ ተከፈተና በርከት ያሉ ፖሊሶች ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ እስረኛውን ለመቀስቀስ የፊሽካ ድምጽ አሰሙ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቅስቀሳውን ለማጀብ በእጃቸው አጨበጨቡ፡፡ ሰዉ ከሞቀ እንቅልፉ መነሳት ጀመረ፡፡ በዕለቱ በዋናነት የእኔ መኝታ ስፍራ እንዲያስፈተሽ ታዞ የመጣው የፖሊሶች ኃላፊ ‹‹አሕመዲን ጀበል ማን ነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ጊዜው የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ ማዘጋጀት የጀመርኩበት ወቅት ነበር፡፡ ከነበርኩበት ስፍራ በመነሳት ወደ አልጋዬ ተጠግቼ ‹‹እኔ ነኝ›› አልኩ፡፡ ኃላፊውም አብረውት ለመጡት ፖሊሶች ‹‹የርሱን ቦታ በደንብ ፈትሹ›› በማለት ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡ ለአራት ሆነው የእኔን ዕቃዎችና መኝታ አገላብጠው ፈተሹ፡፡
የፍርድ ቤት ማስታወሻ ደብተሬን ጨምሮ ያገኙትን ጹሑፍ ወሰዱ፡፡ ግና የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ ሳይወስዱት ቀሩ፡፡ ፍተሻው ካበቃና ፖሊሶች ከሄዱ በኋላ እስረኛው በመናደድ ስሜት ‹‹የፃፍከውን ሁሉ ወሰዱ? ምን ወሰዱብህ? አይዞህ!… ወዘተ›› በማለት የማጽናናት ሚናውን ተወጣ፡፡ ሌሎች የእስር ጓደኞቼ ደግሞ ፖሊሶች አመሰቃቅለው የሄዱትን ዕቃዎችን በማስካከል አብሮነታቸውን አሳዩኝ፡፡ በሌላ ጊዜ ከቀኑ 7፡30፣ 10፡00 እና 11፡30 ላይ ፍተሻ የተካሄደበት ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ፡ አንድ ቀን የእኔን ስፍራ በተደጋጋሚ እንዲፈትሽ ሲላክ የነበረ አንድ የሺፍት መሪ እንደተለመደው ስድስት ፖሊሶችን አስከትሎ በቀን ወደ መኝታዬ መጣ፡፡ በጋራ ሆነው ፍተሻ አካሄዱ፡፡ ይዘውት የሚሄዱት ማስታወሻ ደብተር ሲያጡ ማረሚያ ቤቱ ራሱ አጣርቶ ያስገባልኝን መጻሕፍት ይዘው ሄዱ፡፡ ሲሄዱም ፖሊሱ ‹‹ለምንድነው አንተ ሁሌ የምትጽፈው? ሂዱና የእርሱን ቦታ ፈትሹ እየተባልን እኛም እኮ ደከመን፡፡ መጻፍሕን ለምን አትተውም?›› ብሎ ምክሩን ለገሰኝ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ማዕከላዊ ሆኜ ሐሳቡ የተጠነሰሰው ‹‹ኒፋቅና ሙናፊቆች ድብቁ የማንነት ጭንብል ሲገለጥ›› የሚለው መጽሐፌ ታህሳስ 02/2006 ተጠናቆ በሰኔ 2006 ለሕትመት በቃ፡፡
ለሕትመት ከመብቃቱ በፊትም መጽሐፉ ሌላ መሰናክል ማለፍ ነበረበት፡፡ ክስተቱ እንዲህ ነበር፡፡ መጽሐፉ ተጠናቆ ከእጄ ከወጣ በኃላ በኮምፒውተር የተተየበ አንድ ገጽ በአጋጣሚ ከአባሪዬ ከኡስታዝ ሰዒድ አሊ ወንድም በሑሴን አሊ እጅ ይገባል፡፡ ወደ ማረሚያ ቤቱ ወንድሙን ለመጠየቅ ለመግባት ሲፈተሸ አንድ ገጽ የመጽሐፉ ክፍል በፖሊሶች እጅ ይገባል፡፡ ፖሊሶችም ወዲያውኑ ስልክ ይደውላሉ፡፡ ከማዕከላዊ ፖሊሶች መጥተው ሑሴንን ወደ ማዕከላዊ ይወስዱታል፡፡ በዚሁ ሰበብ ምርምራ ሲደረግበትና ‹‹በሽብር ወንጀል ተጠርጥሯል›› እየተባለ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅበት ለአራት ወራት በማዕከላዊ ታስሮ ቆየ፡፡ በመጨረሻም ተለቀቀ፡፡ እርሱ በተያዘበት ማግስት በኔ መኝታ ቦታ ላይ ድገተኛ ፍተሻ ቢደረግም ምንም ሊገኝ አልቻለም፡፡ መጽሐፉ ታትሞ መሰራጨት እንደጀመረም የታተመው ቀሪ መጽሐፍ ሊጠረዝ ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት ተወስዶ ነበር፡፡ ተጠርዞ ከዚያ ከወጣ ከኋላ በወቅቱ መጽሔቶችን በሚያትሙ ማተሚያ ቤቶች ላይ አሰሳ ሲደረግ የተበላሹ ጥቂት የመጽሐፉ ኮፒዎች በአሳሽ ካድሬዎች እጅ ገቡ፡፡ በአጋጣሚ የመጽሐፉን የተበላሹ ኮፒዎች ያገኙት ካድሬዎች ቀሪ መጽሐፍቱንና የሕትመቱን ፕሌት ለመውሰድ ባለማተሚያውን አጨናነቁ፡፡ ሆኖም እዚያ ባለመታተሙ ምንም ሊያገኙ ሳይችሉ ቀረ፡፡ ይህ ሂደት በመጽሐፉ ስርጭት ላይ ጥቂት መሰናክል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በአላህ እርዳታ መጽሐፉ ለሁለተኛ ጊዜ ሊታተም በቅቷል፡፡
ይህ በእጅዎ የሚገኘው መጽሐፍም በተመሳሳይ መሰናክል ውስጥ አልፏል፡፡ መጽሐፉ አልቆ ከእጄ ከወጣ በኋላ በኮምፒውተር ይተየባል፡፡ ቀጥሎም አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ለወንድሞች ለማድረስ ፎቶ ኮፒ እየተደረገ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ኮፒ አስደራጊው ከፎቶ ኮፒ ቤቷ ይዞ ሊወጣ ሲል ፖሊሶች ከዚያው ደረሱ፡፡ የሚበተኑ በራሪ ወረቀቶችን ያገኙ መስሏቸው ልጁን ይይዙታል፡፡ ይዘውት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊሄዱ ይፈልጋሉ፡፡ መጽሐፍ መሆኑን ሲያረጋግጡ ‹‹የመጽሐፉን ደራሲ ደውልና ጥራው›› በማለት ያፋጥጡታል፡፡ በወቅቱ መጽሐፉ ርዕስና የኔ ስም አልነበረውም ነበር፡፡ በመጨረሻም ፖሊሶቹ ልጁንም ሆነ መጽሐፉን ወደ ጣቢያ ሳይወስዱ ትተው ይሄዳሉ፡፡ የአላህ እርዳታ ታክሎበት እነዚህንና ሌሎችን ውጣውረዶችን አልፎ መጽሐፉ በእጅዎ ሊገባ ችሏል፡፡ መጽሐፉን ከማዘጋጀቱ ጀምሮ ያለፈበትን ሂደት ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ ሂደቱን ሳስብ ቀጣዩ የበዕውቀቱ ስዩም ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ በዕውቀቱ ‹‹ፍኖተ ነፃነት›› የሚል ርዕስ የሰጠው ግጥሙ እነሆ፦
ክቡር መንፈሴ ሆይ!
አንተው ሕግ አርቃቂ
አንተው ፍርድ አጽዳቂ
የወህኒው ባለቤት የወህኒ ጠባቂ
ደካማው ሰለባህ በኃይልህ ስር ታስሮ
ያመልጥ ይሆን ሰብሮ
ይበቀለኝ ዞሮ
ምን ያስብ ምን ያቅድ?
ምን ይክብ ምን ይንድ
ብለህ በማውጠንጠን ዕረፍት ከምታጣ
ምርኮኛህን ፈተህ አንተው ነፃ አውጣ፡፡(በዕውቀቱ ስዩም፣ ስብስብ ግጥሞች፣ 2001፣ ገጽ 61)
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኜም ቢሆን ይህንን መጽሐፍ በማዘጋጀት ወደ እርስዎ በማድረስ ሚናዬን ተወጥቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኸው ዛሬ መጽሐፉ በእጅዎ ላይ ይገኛል፡፡ የቀረው የእርስዎ ሚና ነው፡፡ መግዛት፤ ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስተዋወቅና ማሰራጨት!
ለተለያዩ ወንድሞች ምስጋናዬን ላቀርብ ወደድኩ፡፡ ማረሚያ ቤት ሆኜ የፃፍኩትን ‹‹ኒፋቅና ሙናፊቆች…›› የተሰኘውን መጽሐፌን በማንበብ፣ በማስተዋወቅ እንዲሁም በአሜሪካ (ዋሽንግተን ዲሲ)፣ ደቡብ አፍሪካ (ጆሃንስበርግና ፕሪቶሪያ) እና ሳውዲ ዐረቢያ (ጅዳና ሪያድ) መጽሐፉን በማሳተም ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እንዲዳረስ የበኩላችሁን ለተወጣችሁ ወንድሞቼ ምስጋናዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡ አላህ ጥረታችሁን ከመልካም ሥራችሁ ሚዛን ላይ ያድርግላችሁ፡፡ በተመሳሳይም ለዚህ መጽሐፍ ስርጭትም ሁላችሁም የየበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
በመጨረሻም በተለያየ መልኩ በርካታ ሙስሊምና ክርስቲያን ወንድሞቼ ለዚህ መጽሐፍ ስኬት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ሁላችሁንም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡ ሙዲ፣ ዑመር፣ ዘላለም፣ ሐምዱ፣ ኻሊድ፣ ሀብታሙ፣ ዘይኑ፣ ኢብራሂም፣ ሙሐመድ፣ አይዳ፣ ተመስገን፣ ዘቢብ፣ ሰላሐዲን፣ ወንድሙ፣ ሙባረክ፣ ሚፍታህ፣ ኡሙ ሙሐመድ ቢንት ሙሐመድ፣ የሕያ፣ ሐይደር፣ ሳዲቅ፣ ሰሚር፣ ሳሙኤል፣ ተማም፣ ሰዒድ፣ አብድልቃድር፣ ባሕሩ፣ ሰሎሞን፣ ኢብራሂም እና አለማየሁ ናቸው፡፡ ሌሎችም በበፊቱ መጽሐፌም ሆነ በዚህኛው የየበኩላችሁን አስተዋጽኦ በተለያየ መንገድ ለተወጣችሁና ለምትወጡ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
***********
ይህ መጽሐፍም በ2007 በታተመበት ጊዜ መጽሐፉን ሲሸጡ የተገኙ 10 የሚሆኑ መጽሐፍት አዟሪዎች በፖሊስ ለቀናት ታስረው ‹‹ሕዝብን በመንግስት ላይ የሚያነሳሳ መጽሐፍ ሲሸጡ ተገኙ›› ተብለው ፍ/ቤት ቀርበው ነበር፡፡ በኋላ ፍ/ቤቱ እያንዳንዳቸው በሁለት ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወሰነ፡፡ ይህም ሌሎች መጽሐፍ አዟሪዎች መጽሐፉን በድፍረት እንዳያዞሩ እንቅፋት ቢሆንባቸውም በድፍረት የሸጡም ነበሩ፡፡ ቀሪ የታተመ መጽሐፍ እርሱ ዘንድ የቀረው ማተሚያ ቤትም ኃላ ላይ በመኪና ጭነው ከኔ ቤት ጎረቤት አራግፈው እስከ መሄድ ደርሰው ነበር፡፡ ለማንኛውም መጽሐፉን የት እንደምታገኙ ለጠየቃችሁኝ መጽሐፉ በአሁኑ ሰዓት በየመጽሐፍት ቤቱ ይገኛል፡፡ በተለይም ጃዕፈር መጽሐፍት ቤት፣ ነጃሺ፣ በመስጊድ ደጃፍና ሌሎች መጽሐፍት ቤት ያገኙታል፡፡
መልካም ንባብ!