የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል ዮንቨርስቲዎች አልክም አለ

የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል ዮንቨርስቲዎች አልክም አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሕወሓት መራሹ የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አልልክም ብሏል::

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ሓላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው" የሚል አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል።

"አማራ ክልል የተመደቡት 600 ተማሪዎች እንደማይሄዱ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥት አሳውቀናል። ይህ የክልሉ አቋም ነው" ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሓላፊው በመናገር ድርጅታቸው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብና የአማራን ሕዝብ ለማጋጨት ያለውን ጥልቅ ፍላጎት ያሳዮበትን ሀሳብ ይፋ አውጥተዋል::

ዘንድሮ በትግራይ ክልል የዩኒቨሲቲ መግብያ ፈተና ወስደው ማለፍ የቻሉ የተማሪዎች ቁጥር ከ9000 በላይ መሆኑን የጠቀሱ ባለሥልጣን፤ ወደ አማራ ክልል ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ከ2000 በላይ እንደነበረ እና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉንም ጠቁመዋል።

"ከአንድ ወር ተኩል በላይ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲወያይ ቆይቷል። የተቀሩ 600 ተማሪዎችን ሌላ ቦታ እንዲመደቡ ይሠራል፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የትግራይ ክልል ሌላ አማራጭ ይፈልጋል እንጂ ተማሪዎቹን ወደዛ አይልክም" በማለት ሠፊውን የአማራ ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀዋል።

ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ አመዳደብ ስርዓት መሰረት ከአንድ ክልል አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በክልላቸው የተቀሩት 60 በመቶ ደግሞ ሌላ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይመደቡ እንደነበረ የሚያስታውሱት ሓላፊው፤ "ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በበዙበት ወቅት ይህ ተቀይሮ 10 በመቶ በክልላቸው 90 በመቶ ደግሞ ወደ ሌላ ክልል እንዲላኩ መደረጉ አግባብ አይደለም" ሲሉ የክልሉን መንግሥት አቋም አስታውቀዋል።

ይህ እንዲስተካከል ከፌደራል እና ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት መደረጉን እና 20 በመቶ በክልላቸው 80 በመቶ ደግሞ ከክልል ውጪ እንዲመደቡ መወሰኑንም አስረድተዋል።

የትምህርት ቢሮው ሓላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ትግራይ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎች "ምንም አይነት የደህንነት ችግር አይገጥማቸውም" ሲሉም ተደምጠዋል። የትምህርት ቢሮ ሓላፊው ሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ተማሪዎች ጉዳይ ዙሪያ ግን ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

LEAVE A REPLY