የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም

በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር የተፈጠረው ችግር ለመላ ሀገሪቱ ከባድ አደጋ መሆኑ ተነገረ

በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በጎንደር ከተማ እንዲሁም በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር “ማንነትን ሽፋን” በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት የጸጥታ መደፍረስ፣ የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት መከሰቱን የአማራ ክልል ደኀንነትና ጸጥታ ካውንስል ትናንትና ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል::

በክልሉ የማንነት ጥያቄዎችን ላነሱ ወገኖች ምላሽ መስጠቱን ያስታወሰው  መግለጫ ቅሬታ ያላቸው አካላት ጥያቄያቸውን አቅርበው መስተናገድ የሚችሉበት ዕድል እያለ በኃይል ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም መሞከራቸውን ጸረ ህገ መንግስትና የለየለት ጸረ ሰላም ተግባር ሲል ኮንኖታል።

“የቅማንት የራስ አስተዳደር ኮሚቴ የተከተለው አቅጣጫም ፍላጎትን በኃይል በብሔረሰቡና በክልሉ መንግሥት ላይ የመጫን “ኢ ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ” መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ካውንስሉ በመግለጫው ላይ እንደጠቀሰው “ኢ ሕገመንግሰታዊ ዕርምጃ ለመቀልበስ በተወሰደው ዕርምጃ” ግጭት መከሰቱንና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አንስቶ ክልሉና የፌደራል መንግሥት “በትዕግስትና በአርቆ አስተዋይነት” ችግሩን ለመፍታት ቢጥሩም ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን አብራርቷል።

በአካባቢው የተከሰተው ግጭት “አካባቢውን ወደ ተሟላ ትርምስ የሚያስገባና ለክልሉ ብሎም ለመላው ሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት” መሆኑንም የካውንስሉ መግለጫ አመልክቷል። የአካባቢው ሠላም መደፍረስ የገቢና የወጪ ንግድ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በዚህም የተነሳ የፌዴራል የፀጥታ ኃይል መከላከያን ጨምሮ ማንኛውም ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ መተላለፉ ተገልጿል።

የተላለፈውን መመሪያ በመከተል የክልሉ የፀጥታና ደኅንነት ካውንስል በማዕከላዊ፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር እና በጎንደር ከተማ ክልከላዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ መመሪያ መሰጠቱን አስቀምጧል።

ከመመሪያዎቹ መካከል ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴን የኃይል እርምጃ በመውሰድ መቆጣጠር የሚል የሚገኝበት ሲሆን ጥፋተኞችን ለመቆጣጠር ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃን በመውሰድ የኃይል ተግባርን ፍፁም እንዳይቀጥል ማድረግ የሚል ይገኝበታል። ካውንስሉ የሠላም አማራጮችን ለማስፋት በሚል በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግጭት የገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመመለስ ያሏቸውን ልዩነቶች እንዲፈቱ ጥሪም አስተላልፏል።

በግልፅ በታወቁ የፀጥታ ኃይሎች ከተያዙት ትጥቅና መሳሪያ ውጪ በተጠቀሱት የክልሉ ዞኖች ላልተወሰነ ጊዜ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሲንቀሳቀስ ይዞ የተገኘ ግለሰብ የሚወረስበት መሆኑ ተነግሯል።የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ህጋዊ ውሳኔ መሠረት በአፋጣኝ በሕዝብ ይሁንታ የሚደራጅ የራስ አስተዳድርን በማቋቋም ሁሉም አገልግሎት እንዲጀምር እንደሚያደርግም በመመሪያው ላይ ተካትቷል።

በአካባቢው ውስጥ በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ገብተው የነበሩ ኃይሎች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች እስከ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ የክልሉ መንግሥት በድጋሚ ይቅርታ ማድረጉም ታውቋል። ነገር ግን በሰው ግድያ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው በህግ አግባብ የሚታይ መሆኑ በመመሪያው ላይ ተካትቷል።

በየአካባቢው ለሚፈጠሩ “ወንጀሎች ፀረ-ሰላም ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች” ሁሉም አካላት የመቆጣጠር፣ የማሳወቅ፣ እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ ሓላፊነት አለባቸው ያለው መመሪያው፤ ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂነትን ከማስከተልም በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኘው ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተራግፎ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል ሲል አሳስቧል።

በኢ- መደበኛ አደረጃጀትና ባልተሠጠ ሓላፊነት ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ መከልከሉን ያስቀመጠው መመሪያው ተጠያቂነትም እንደሚያስከትል ገልጿል። ከጎንደር ወደ መተማ፣ ሁመራ፣ ባሕር ዳር፣ደባርቅ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶች በማንኛውም ጊዜ ነፃ ይሆናሉ ያለው መግለጫ ፣የሕዝብ በነፃነት የመንቀሳቀስን መብት ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል በማለት አሳስቧል::

በአካባቢው ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ክልል የፀጥታ ኃይል፣ በየደረጃው ያለው የክልሉ መስተዳድር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በጥምረት እንደሚሰሩ መመሪያው አስቀምጧል።

የፊታችን እሁድ በመቀሌ ሊካሄድ የነበረው ሠላማዊ ሰልፍ በሕወሓት ተከለከለ

ባለፈው ሳምንት በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን፤ ሕዝብና የመንግሥት አመራሮች ግምገማ ካደረጉ በኋላ ሦስት ሴቶች በአንድ የፖሊስ አባል ጥቃት ተፈፅሞብናል ሲሉ ተናግረዋል። የአዲ ዳዕሮ ከተማ ፖሊስ አባል የሆነው ተጠርጣሪ አንዲት ሴት በመድፈር ክስ የቀረበበት ሲሆን ፣ ሌሎች ሴቶችም በዚሁ የፖሊስ አባል ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ተከሳሹ ጉዳዩ እስከሚጣራ በሚል በስድስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር። ይህንን ተከትሎ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል አልታሰረም በሚል መስከረም 28 2012 ዓ.ም የከተማው ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ቁጣውን መግለፁም ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ መሆኑን በመግለፅ “ክስ ያቀረበችበት አንዲት ሴት ናት፤ የቀረበበት ክስም በሕጉ ዋስትና የሚያስከለክለው አይደለም ፤ በመሆኑም ግለሰቡ በዋስ ተለቆ ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛል” ሲልአስታውቆ ነበር።

ከዚህ በመነሳት ጉዳዮ ያልተዋጠላቸው ነዋሪዎች የፊታችን እሁድ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመቃወም በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማ አስተዳደሩ መከልከሉ ተሰምቷል።

የሠላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነችው ዶ/ር ሄለን ቴዎድሮስ “ማድረግ ያለብንን ሂደት ነው የተከተልነው፤ እኛ ያገባናል ብለን የተሰበሰብን ልጆች ፊርማችን ያለበት እና ለሰልፉ ሓላፊነት እንደምንወስድ ደብዳቤ ጽፈን ወደሚመለከተው አካል፤ መቀሌ ከተማ አስተዳደር ነው የሄድነው።” ስትል ሰልፉን ለማካሄድ ሕጋዊ አግባብን የተከተሉ መሆኑን አስታውቃለች።

አዘጋጆቹ ወደ መቀሌ ከተማ አስተዳደሬር ሄደው ባነጋገሯቸው ወቅት የመንግሥት አካል ካልሆነ በስተቀር በግለሰቦች ደረጃ ሠላማዊ ሰልፍ ሊደረግ እንደማይችል በመግለጽ እንደተከለከለ ተነግሯቸዋል። “ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ነው የሚሄደው፤ አዲ ዳዕሮ የተፈጠረውን ነገር ማንሳት ይቻላል” የምትለው ዶ/ር ሄለን ምንም እንኳን ግለሰቡን የተመለከተ የተለያዩ ወሬዎች ቢወሩም፤ አንዲትም ሴት ትሁን 50 ሴቶች መደፈራቸውን ሄደው መናገራቸውን ገልጻለች።

“ተጠርጣሪው ግለሰብ በ6 ሺህ ብር ዋስ ተለቋል፤ ለዚያውም የሕግ አስከባሪ የሆነ ፖሊስ። ይህም ትልቅ ነገር ነው የሚያሳየን። የብዙ ሴቶችን ታሪክ እናውቃለን፤ ተጠርጣሪዎቹ በትንሽ ብር ዋስ ነው የሚለቀቁት፤ ስለዚህ መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት እየሰጠው አይደለም” በማለትም ቅሬታዋን አቅርባለች::

በጉዳዩ ያገባናል የሚሉና ከተለያየ ሙያ የተውጣጡ ግለሰቦች ተሰባስበው ድርጊቱን በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተነሱት። መንግሥታዊ ክልከላውን አስመልክቶ የመቀሌ ከንቲባ ጽ/ቤት ሓላፊ የሆኑት አቶ ግርማይ ተስፋይ፤ “ሠልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ላቀረበ ሁሉ ማስተናገድ አይቻልም፤ዓላማው መታወቅ አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ግርማይ ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ላቀረቡት ግለሰቦች የሕጋዊ ድርጅት ማህተም ያለው የድጋፍ ደብዳቤ እንዲያመጡ ከመጠየቅ በዘለለ ሠልፉን ማካሄድ አትችሉም በሚል አልከለከልንም፣ ሲሉ ግለሰቦቹ ያቀረቡት ደብዳቤ ማህተም እንደሌለው አስታውቀው፣ ሠልፉን ለማካሄድ የሲቪክ ማህበረሰብም ይሁን የመንግሥት ድጋፍ ያለው ደብዳቤ ማቅረብ ግዴታ ነው ብለዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤታቸው በጎንደር ያስገነባውን የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መረቁ

የትምህርት ተቋማትና ከሴቶች ድጋፍ ጋር በተያያዙ ሀገራዊ ሥራዎች የተጠመደው ቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት  አዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገንብቶ ለምረቃ አብቅቷል::

በጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለቤት፣ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የሚመራው ጽሕፈት ቤት አማካይነትየተገነባው ሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል::

በዛሬው ዕለት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተመረቀው ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራውንም እንደጀመረ ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ዘገባ መረዳት ችለናል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም የትምህርት ቤቱን ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በቀዳማዊት ጽ/ቤት አማካይነት የተገነባው ትምህርት ቤትበጎንደር ከተማ ዙሪያ ከሚገኙ 5 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 4 ሺህ 840 ያህል ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል።

ግንባታው ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት በይፋ የተመረቀው ትምህርት ቤቱ፣ በጎንደር ከተማ የትምህርት ጥራት ችግር በመቅረፍ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።

ጽንስ በማቋረጥ አንድ ዓመት የተፈረደባት ሞሮኳዊቷ ጋዜጠኛ ከዕስር ተፈታች

ሞሮካዊቷ ጋዜጠኛ ከጋብቻ በፊት ወሲብ በመፈፀም፣ እንዲሁም በጽንስ ማቋረጥ የአንድ ዓመት ዕስር ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም የሞሮኮው ንጉሥ መሐመድ አራተኛ ምህረት እንዳደረጉላት የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የሃገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይየንጉሱ ጣልቃ መግባት “ርህራሄያቸውንና ምህረታቸውን የሚያሳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የ28 አመቷ ጋዜጠኛ ሃጃር ራይሱኒ በትናንትናው ዕለት ከእጮኛዋ ጋር ከዕስር ቤት ስትወጣ ጣቶቿን ከፍ አድርጋ፣የድል ምልክት አሳይታለች፣። በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠው እጮኛዋም ምህረት እንደተደረገላት አረጋግጧል:: በሞሮኮ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ወሲብ እንዲሁም ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል ነው።

የሞሮኮ መንግሥት ለዕስሯ የሰጠው ምክንያት የጽንስ ማቋረጥና ከጋብቻ በፊት የሚፈፀም ወሲብ ቢሆንም፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው በነፃ ጋዜጣ ላይ የተደረገ አፈና ነው ሲሉ በመከራከር ላይ ናቸው:: ወጣቷ ጋዜጠኛመንግሥትን በመተቸት በሚታወቀው “አክባር አል ያውም ” የተሰኘ ጋዜጣ ላይ ነው የምትሠራው።

በነሐሴ ወር ከሱዳናዊ እጮኛዋ ጋር ከማህጸን ክሊኒክ ስትወጣ የታየች ሲሆን፤ የጽንስ ማቋረጡን ክስም አልተቀበለችም። ወደ ክሊኒኩ የሄደችው ያጋጠማትን መድማት ለመታከም እንደሆነም በጊዜው ተናግራ ነበር።

ክሱንም ሆነ ውሳኔውን ፖለቲካዊ ፍርድ ነው ብላ ከማውገዟ ባሻገር ፣ መስከረም ወር ላይ አንድ ዓመት እንድትታሰር ተወስኖባት እንደነበር ይታወሳል:: ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ህግ በበበኩሉ የጋዜጠኛዋ ዕስር ከስራዋ ጋር እንደማይገናኝና የሄደችበት ክሊኒክም በህገወጥ ጽንስ ማቋረጥ ጥርጣሬ በፖሊስ ክትትል ሲደረግበት የነበረ ነው ብሏል።

በሕጉ መሠረት እጮኛዋም አንድ አመት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ በዶክተሩ ላይ ደግሞ ሁለት ዓመት ዕስር ተወስኖበታል። የዶክተሩ ረዳትና ነርሷ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙም የሙያ ፈቃዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በማገድ ብቻ ታልፈዋል።

በኮንዶም እጥረት ስትታመስ የቆየችው ታንዛኒያ 30 ሚሊዮን ኮንዶሞች ከውጭ አስገባች

ከወራት በፊት አንስቶ ከፍተኛ የሆነ የኮንዶም እጥረት እንዳጋጠመት የተገረላት ታንዛኒያ ሰሞኑን 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ኮንዶሞችን ከውጭ ማስገባቷ ታወቀ::

የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት እጥረቱን ለማቃለል 30 ሚሊዮን ኮንዶሞችን ለጊዜው ወደ አገሪቱ ያስገቡ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ ኮንዶሞችን ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በርካታ ታንዛኒያዊያን በመንግሥት የሚሠራጨው የኮንዶም አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ የኮንዶም መግዣ ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ጭማሪ እንዳሳሰባቸው ነው የተሰማው።

የታንዛኒያ ዋና ከተማና የቱሪስቶች መናኸሪያ በሆነችው ዳሬሰላም ውሰጥ ሚገኙ አንዳንድ የእንግዳ ማረፊያዎች እርግዝናንና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያገለግለውን ኮንዶም ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ካቆሙ ሰነባብተዋል።

“አንዳንድ መደብሮች እንደ የኮንዶሞቹ ዓይነት ከአንድ እስከ ሦስት ዶላር ከዛ በላይ ወጪን ስለሚጠይቁ፤ ይህን ያህል ወጪ አውጥተን ኮንዶም ማቅረብ ስለማንችል ፣ አሁን ደንበኞች ራሳቸው ይዘው መምጣት አለባቸው” ሲል አንድ የሆቴል ሠራተኛ ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።

የሀገሪቱ ረዳት የጤና ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ፋውስቲን ንዱጉሊል ፣ “አሁን የሚፈለገው የኮንዶም መጠን ቀርቧል፤ከ30 ሚሊዮን በላይ ኮንዶሞች አዝዘናል። አሁን የተቀየረው ኮንዶሞቹ የሚሰራጩበት መንገድ ነው፤ ቀደም ባለው ጊዜ ኮንዶሞችን የሚያሰራጩ ተቋማት ነበሩ። አሁን ግን የማሰራጨቱ ሓላፊነት የተሰጣቸው አዳዲስ ተቋማት አሉን።” ካሉ በኋላ “እኛ ማድረግ የፈለግነው አዲሱ አሠራራችን በተገቢው ሁኔታ መሥራቱን ማረጋገጥ ነው። በተጨማሪም ግንዛቤ ለመፍጠር እያደረግነው ያለው ዘመቻ ትኩረት ወደ አደረግንባቸው ሰዎች ሲደርስ ኮንዶም እንደተፈለገው ማግኘት ይቻላል” በማለት ዕቅዳቸውን አስቀምጠዋል።

LEAVE A REPLY