ቱርክ የአሜሪካንን መውጣት ተከትላ ደቡብ ሶሪያን ወረረች። አሜሪካ ደግሞ “የኔ አገር አይደለም” ብላ ጥላ የወጣችው፣ አይሲስን ለመዋጋት በሄደች ጊዜ የጀርባ አጥንት ሆነው የረዷትን የሶሪያ ኩርዶች ክዳ ነው። እነዚያ የሶሪያ ኩርዶች ከ10ሺ በላይ ተዋጊዎቻቸውን አጥተዋል። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ አይ ሲስ በአሜሪካ ብቻ ተሸንፎ ከሶርያ ምድር አይወጣም ነበር።
አሁን አሜሪካ ኩርዶቹን “ሥራችሁ ያውጣችሁ” ብላ ከወጣች በኋላ ቱርክ ዘልላ ገብታ “ድንበሬን ላጽዳ” በሚል ምክንያት ስትገድል፣ ስታፈናቅልና በቦምብ ስትደበድብ ዓለም ኡ ኡ አለ። አውሮፓውያን ተቆጡ።
ትራምፕ ሰለ ዓለም የፖሊቲካ አካሄድ ያላቸው ዕውቀት የአንድ ተራ የከተማ ከንቲባ ያህል እንኳን ባለመሆኑ ያደረጉት ትልቅ ጥፋት አልታያቸውም። “እንዲሞቱ ፈርደው” ትተዋቸው የወጡት ኩርዶች በ እጃቸው ከ12ሺ የማያንሱ የአይ ሲስ ምርኮኛ አለ። ቱርክ ስታጠቃቸው፣ ምርኮኞቹን ትተው፣ እስር ቤቱን ከፍተው ለመዋጋት መሄዳቸው አይቀርም፣ ያን ጊዜ ያ ሁሉ የአይ ሲስ ወታደር ሾልኮ ወጥቶ አይ ሲስ እንደገና በሶሪያ ሌላ ግዛት እንደማይመሰረት ማንም ርግጠኛ አይደለም። በዚህ ላይ በክፉ ቀን የአሜሪካ ደጋፊ የነበሩትን መካድ ነገ ደጋፊ ማጣት ነው። አሜሪካ ያ ይጎዳታል።
ይህ የታያቸው የራሳቸው ፓርቲ ሰዎች ጭምር ትራምፕ ላይ ተንጫጩባቸው፣ ትራምፕ ደነገጡ። የሚናገሩትን እንኳን ማስተካከል አቅቷቸው፣ አንዴ ስለ ኩርዶቹ አያገባንም፣ አንዴ ደግሞ ቱርክን ከዚህ በላይ ሃይል ትጠቀሚና ዋ! ማለት ጀመሩ። የቱርኩ ኤድሮጋን አልሰማም አሉ። ትራምፕ ግፊትና ጫና ከቅርብ ሰዎቻቸው ጭምር መጣባቸው። ያን ጊዜ በአንድ በኩል ጦርነቱን ማቆም ባለመቻላቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኮንግረሱ እሳቸውን አልፎ ቱርክ ላይ ማዕቀብ ሊጥል መዘጋጀቱ ሌላ ጫና አመጣባቸው።
ከዚያ ምክትላቸውንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ቱርክ ላኩ። ማይክ ፔንስ እና ፖምፒዮም ሄደው ከቱርኩ መሪ ኤድሮጋን ጋር ተወያየን አሉ። ከዚያም “ስምምነት አደረግን የምስራች” ብለው የተስማሙበትን ይፋ አደረጉ።
የሚገርመው ግን ስምምነት ያሉት፣ ቱርክ ከፈለገችው በላይ የሰጣት፣ አሜሪካ ደግሞ ምንም ያላገኘችበት፣ ኩርዶች ጭራሽ የማይቀበሉት፣ ሶርያ የሌለችበት ስምምነት ነው።
ስምምነቱ ባጭሩ፣ “ቱርክ ክፍት እንዲሆን ከፈለገችው “የነጻ ቀጣና ዞን” ውስጥ ያሉ የኩርድ ተዋጊዎች እንዲወጡ የ5 ቀን ጊዜ ለመስጠት ያህል ተኩስ ለማቆም ተስማምታለች” የሚል ነው። ባጭሩ ኩርዶችና ሶርያውያንን የራሳችሁን መሬት ልቅቁና ውጡ ቱርክ ያለ ጦርነት ትያዘው ማለት ነው።
ሲጀመር፣ ይህ ቱርክ በጦርነት ልታገኝ ያሰበችውን ያለጦርነት እንቺ ውስጂው ማለት ነው።
ሲቀጥል፤ ኩርዶች አናስነካም ብለው እየተዋጉ ያለበትን መሬታቸውን ልቀቁና ለቱርክ ስጡ ማለት ነው።
ሲሰልስ፦ ቦታው የሶሪያ ክልል ሆኖ ሳለ፣ ያለ ሶርያ መንግስት ፈቃድና ይሁንታ የአንድ አገርን መሬት ቱርኮችን ውሰዱት ማለት ነው።
ይህ እንዴት ይሆናል?
ኤድሮጋን በጣም ብልጥ ናቸው። አንድም በጦርነት ሊይዙ ያሰቡትን ቦታ በነጻ ያለጦርነት ውሰዱ ተባሉ። ከዚያም ደግሞ አሜሪካ ልትጥል ካሰበችው ማዕቀብ “ይኸው ባልሺው ተስማምቻለሁ” ብለው ለማምለጥ ቻሉ – ለጊዜው። ትራምፕ በበኩላቸው “ተስማማን፣ በቃ፣ ይኸው ጦርነት የለም፣ ደምም አይፈስም ኤድሮጋንን አስቆምኩት” ብለው እንደተለመደው ጉራ ሊነዙ ይጀምራሉ።
በኔ ግምት ግን ኩርዶችም፣ ሶሪያም በዚህ አይስማሙም። ምናልባት የኮንግረስ አባላቱም በዚህ ላይስማሙ ይችላሉ። ቱርክም እስካሁን ለፈጠረችው ሞትና መፈናቀል ማንም ሳይጠይቃት ታመልጣለች ማለት አስቸጋሪ ነው።
የትራምፕና የቱርክ ስምምነት “ሌባው እየተኮሰ ቤትህ ከሚገባና ደም ከሚፈስ ፣ ውጣለትና ቤትህን ይውሰድ” እንደማለት ነው። ይህ ግን አገር ወይም መሬት እንጂ የቤት ዕቃ አይደለም። የማይረባ ስምምነት በመሆኑም የሚቆይ አይመስለኝም።