የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም

የትግራይ ት/ቢሮ ተማሪዎቹን የመከልከል መብት እንደሌለው የሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር አሳወቀ

በትናንትናው ዕለት የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አዳዲስ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አልክም ማለቱን ተከትሎ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፤ ይህንን ለማለት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሥልጣን የለውም ሲል ገለጸ::

ተማሪዎችን የመደበው የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ነው ያሉት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ፣ ከመግለጫው በፊት በነበሩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ክልሉ ጥያቄውን ማቅረቡን አስታውሰዋል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ትናንት እንደተናገሩት “ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ሓላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው” ካሉ በኋላ ይህን ተከትሎም የክልሉ አቋም ነው ያሉትን አማራ ክልል የተመደቡ 600 የሚደርሱ ተማሪዎችን ወደዚያ እንደማይልኩ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥቱ አካል ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በተደጋጋሚ በዚህ ጉዳይ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን እና አሁን በክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያለው ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ ተማሪዎች ወደዚያው ሄደው እንዲማሩ እንደሚፈልጉ አቶ ደቻሳ ለቢቢሲ በተናገሩበት ወቅት አድምጠናል።

“ሁሉም ተማሪዎች ወደየተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ሄደው ይማራሉ የሚል እምነት ነው ያለን” ያሉት ሓላፊ፤ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥቱ በመሆኑ በየክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቢሮዎች ማዘዝ አይችሉም ሲሉ የትግራይ ትምህርት ቢሮ አቋምን አጣጥለዋል።

ከትግራይ ክልል የቀረበውን ተቃውሞም ተከትሎ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበዋል፤ እነሱም ወደ ተመደቡበት ተቋም ሄደው መማር ነውያለባቸው ሲል አሳስቧል።

አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንዳሉት “የስፖርትና የትምህርት ጉዳይ ሲነሳ በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዲህ አይነት ክፍተት አለ” በማለት ከትግራይ በኩል የቀረበውን ሃሳብም “አንተገብረውም፤ ሊሆንም አይችልም” ካሉ በኋላ ፤ በትግራይ ክልል ያሉም ሆኑ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ እነዚህን ልጆች ተቀብለው አያስተናግዱም ፣ የለባቸውምም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

 “ትግራይ ክልል ያሉትም ሆነ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች መቀበል በሚችሉት ልክ ተማሪ መድበናል” በማለት “ዩኒቨርስቲዎቹ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ተማሪ መቀበል አይችሉም፤ በጀትም የላቸውም” በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል።

በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላም እንዲኖር፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው ያሉት አቶ ደቻሳ፤ እስካሁን ድረስ ያለው ሁኔታ ጥሩ እንደሆነ ጠቁመው ፤ የተሻለ አቀባበል ለተማሪዎች እንዲደረግ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢዎቹ ማህበረሰብን አባላት የካተተበት ኮሚቴ በማቋቋም በቤተሰብ መንፈስ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን እየተቀበሉ ነው ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ታክስ የሚሠውሩ ፣ ደረሰኝ የሚያጭበረብሩ 166 ድርጅቶች ይፋ ተደረጉ

የገቢዎች ሚኒስቴር ታክስ የሚሰውሩ፣ ህገ ወጥ ደረሰኞችን የሚጠቀሙ እና የሚያትሙ 166 ድርጅቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ታክስ የሚሰውሩ፣ ህገ ወጥ ደረሰኞችን የሚጠቀሙና የሚያትሙ 166 ድርጅቶች መለየታቸውን ዛሬ በሰጡት መግለጫ  ላይ አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቶቹ ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ፣ ታክስን ለመሰወር እና ህገ ወጥ ተመላሽ ለመጠየቅ ፤ ህገ ወጥ ደረሰኞችን የሚጠቀሙ ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በነፍስ ወከፍ ከ51 ሚሊየን ብር በላይ ግብይት የነበራቸው ነገር ግን ባዶ፣ ኪሳራ እና ተመላሽ ከሚጠይቁ ደርጅቶች መካከል 16 ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በታማኝነት በወቅቱ ግብራቸውን ለሚከፍሉ ዜጎችም ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስተሯ ከ166 ድርጅቶች መካከል 136 ያህሉ ከ 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ማድርጋቸው በመረጃ ቋት ውስጥ ተገኝቷል:: ከብሄራዊ መረጃ እና ደህነት እንዲሁም ከፖሊስ ጋር በቅንጅት ህግ የማስከበሩን ሥራ እየተሠራ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

166 ድርጅቶች ምንም ዓይነት የሚሽጡት ዕቃም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት የሌላቸው ሲሆን በሀሰተኛ ፣ መታወቂያ እና አድራሻ ፈቃድ ሳይኖራቸው ደረሰኝ ያሳትሙ የነበሩ መሆናቸውን በመግለጫው ላይ ተሰምቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 57 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ማከናወኑንም አንስተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በሐምሌ ወር 18 ቢሊየን ብር፣ በነሀሴ ወር 20 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እና በመስከረም ወር 19 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል።

በ18 የገቢዎች ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችም ከሀገር ውስጥ ገቢ 31 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ ከውጪ የንግድ ቀረጥ እና ታክስ 24 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እና ከሎተሪ ሽያጭ 46 ነጥብ 1ሚሊየን ብር  ፤ እንዲሁም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች 21 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡም ታውቋል::

152 የመንግሥት መ/ቤቶች የኦንላይን አገልግሎት ሊጀምሩ ነው

በ2012 ዓ.ም ተጨማሪ 152 የመንግሥት አገልግሎቶች ባሉበት ግልጋሎት (የኦንላይን አገልግሎት) እንዲሰጡ ሊደረግ መሆኑ ታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፤ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን ባሉበት ግልጋሎት (የኦንላይን አገልግሎት) እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ቅድመ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ባዘጋጀበት ወቅት ሰምተናል።

በሚኒስቴር መ/ቤቱ ስር የተቋቋመው ብሔራዊ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መተግበሪያ ፕሮጀክት አሁን ያለበት ሁኔታ፣ ያጋጠሙ ችግሮች ፣ ዕቅዶች ቀርበውና ተገምግመው ወደ ፊት አገልግሎቱን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡ ነው የተገለጸው::

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ እስከአሁን በፕሮጀክቱ 126 አገልግሎቶች ለምተው በ34 ተቋማት ወደ ትግበራ መግባታቸውን ተናግረዋል።በያዝነው ዓመትም 152 አገልግሎቶችን እንዲለሙ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

የመብራት፣ የኢንተርኔትና የኔትወርክ ውስንነቶች፣ የተሟላና ወቅቱን የጠበቀ ግንዛቤ አለማግኘት፣ የመስሪያ ቤቶችና ደንበኞች ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የቁርጠኝነት አናሳ መሆን የአገልግሎቱ ተግዳሮቶች መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ባሉበት ግልጋሎት (የኦንላይን አገልግሎት) ፈጣን፣ ውጤታማና ዘመናዊ የሆነ አሰራር በመሆኑ ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን በእጅጉ ይቀንሳል የተባለ ሲሆን ፤ የተለያዩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በባሉበት ግልጋሎት (የኦንላይን አገልግሎት) እንዲሰጡ ለማድረግና ወደ ትግበራ እንዲገቡ የሚያስችላቸውን የስምምነት ፊርማ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል።

መድረኩ በዋናነት የተዘጋጀው አሠራሩን የሚጀምሩ አዳዲስ ተቋማት እውቀት ኖሯቸው አግልግሎቶቻውን እንዲያዘምኑና የተገልጋዮቻቸውን ፍላጎት ማርካት እንዲያስችላቸው መሆኑን ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል::

የኔዘርላንድስ መንግሥት ለአማራ ክልል 20 ሚሊዮን ዮሮ እረዳለሁ አለ

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ከኔዘርላንድስ አምባሳደር ቤንት ቫን ሎዝድሬኸት ጋር መወያየታቸው ተነገረ፡፡ አምስት የኔዘርላንድስ ባለሀብቶች በክልሉ ቁንዝላ በተባለ ቦታ በ500 ሄክታር መሬት ላይ በአበባ ልማት ላይ እንደሚሠማሩም በውይይቱ ላይ ተገልጿል ፡፡

በቁንዝላ ከሚካሄደው የአበባ ልማት ጎን ለጎንም የኔዘርላንድስ መንግሥት ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎች ተቋማትን ለአካባቢው ማኅበረሰብ መገንባት የሚያስችለው የድጋፍ ስምምነት ዕውን ሆኗል፡፡

ነዋሪዎቹም የአካባቢውን ውሃ ጥቅም ላይ በማዋል እንዲያመርቱ እና የግብርና ምርቶችን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ ነው አምባሳደሩ ዛሬ ያረጋገጡት፡፡ከኢንቨስትመንት ሥራው በተጨማሪ የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የኔዘርላንድስ መንግሥት 20 ሚሊየን ዩሮ እንደሚመድብም አብራርተዋል።በዚህም በአካባቢው የሚኖሩ 10 ሺኅየሚደርሱ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ስለ አበባ ልማቱ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱንና ከዚህ በፊት የነበሩ የአካባቢው ማህበራዊ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ የኔዘርላንድስ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደር ቤንት ቫን ሎዝድሬኸት ገልፀዋል፡፡

አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ክልሉ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆን ሠላምን በማረጋገጥ በኩል መንግሥት እየሠራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ሠላም በሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፍን ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::

ዶ/ር አቢይ  ቃል የገቡትን 25ሺህ ዩሮ ለፓስተር ዮናታን አስረከቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሄሰን የሰላም ሽልማት ያገኙትን 25 ሺህ ዩሮ ለመልካም ወጣት አገልግሎት ለመስጠት ቃል በገቡት መሰረት ፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ለፕሮጀክቱ መሪ አገልጋይ (ፓስተር) ዮናታን አክሊሉ አስረክበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወርሀ መስከረም አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለመደገፍ እየሠራ ላለው የላቀ ሥራ ይፋዊ ዕውቅና መስጠታቸው አይዘነጋም። 2009 ዓመተ ምህረት ላይ በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ የተጀመረው የመልካም ወጣት ፕሮጀክት በየክረምቱ ሲከናወን ቆይቷል።

የመልካም ወጣት ፕሮጀክቱ ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚወድ፣ ተግባቢ፣ ስደትን አማራጭ ያላደረገ፣ ከሱስ የነፃ እና የመፍትሄ አካል መሆን የሚስማማው ወጣትን መፍጠር ዓላማ ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ድጋፍን አግኝቷል።

LEAVE A REPLY