‹‹ምንም እንኳን ጉዳዩ በሒደት ያለና ያልተቋጨ በመሆኑ በዚህ ወቅት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሚወጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል እምነት ጉዳዩን በዝምታ ለማለፍ የተሞከረ ቢሆንም፣ የተሳሳቱ መረጃዎች ተደጋግመው ሲመጡ ችላ ማለት ደግሞ ሕዝቡ ውስጥ መደናገርን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሕዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኗል፡፡›› ይህ አንቀጽ የተወሰደው ዓርብ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ሕወሓት ውህድ ፓርቲን አስመልክቶ ላወጣው መግለጫ፣ በኢሕአዴግ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በአገሪቱ ከተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፊት ሲመጡ፣ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በርካታ የማሻሻያ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ቃል ገብተው ነበር፡፡
በወቅቱ የተገቡ ቃሎችንና ዕቅዶችን ተፈጻሚ ለማድረግም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲሠለፉ ጥሪ ከማስተላለፍ ባለፈ፣ የግንባሩ አባል ድርጅቶችም በአንድነት ሆነው የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ ተግተው እንዲሠሩም ማሳሰቢያ አዘል ጥሪም አድርገው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሊገጥማቸው የሚችለውን ፈተና አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ በግንባሩ ውስጥ ያሉትን ድርጅቶች አስማምቶ ለአንድ ዓላማ ማሠለፍ አንዱና ዋነኛው ሊሆን እንደሚችል የገመቱ በርካቶች ነበሩ፡፡
በግንባሩ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በመታዘብ ይህንን ልዩነት ወደ አንድ ማምጣት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል የሚል ግምታዊ አስተያየት ሲሰጡ የነበሩ የፖለቲካ ተንታኞችና ፖለቲከኞች ዋነኛ ምክንያታቸው ደግሞ፣ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የመሀል አገር ፖለቲካን ትቶ ወደ ትግራይ መግባቱን በመጥቀስ ነው፡፡ እንዲሁም በሌሎች የግንባሩ ድርጅቶች ውስጥም ቢሆን በአንድነት የመቆምና የመታገል እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን በማውሳት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ታዋቂው ፖለቲከኛና የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ከወራት በፊት በሰጡት አስተያየት፣ ለአዲሱ አስተዳደር ከፍተኛ ፈተና የሚሆነው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን አስተባብሮ መምራት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
እንዲህ ያሉ በርካታ አስተያየቶች ሲደመጡ የነበረው ደግሞ በግንባሩ ድርጅቶች መሀል ከፍተኛ መጠራጠር በመፈጠሩና አመራሮቹም ያለውን ልዩነት በንግግርና በውይይት ከመፍታት ይልቅ፣ በተናጠል የሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችና አስተያየቶች እየተካረሩ በመሄዳቸው ነው፡፡
ምንም እንኳን በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የአቋም ልዩነት በተለይ ከሕወሓት በኩል የሚሰጠው የፌዴራል ሥርዓቱን ለማፍረስ እየተሠራ ነው የሚለው ወቀሳና ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱን መቼ ተንከባክባችሁ ታውቁና?›› የሚለው ምላሽ፣ ከፍተኛ የልዩነት ነጥብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር፡፡
እንዲህ ያሉ አስተያየቶች በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ አልፎ አልፎ እየተሰጡ የቆዩ ቢሆንም፣ በተለይ ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ በኋላ ግን የግንባሩ ፓርቲዎች የሚነጋገሩት በመግለጫ ሆኗል፡፡
ሰኔ 15 ቀን በባህር ዳርና በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግድያ ተከትሎ ሕወሓት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) በስም በመጥቀስ የአማራ ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ በመግለጫ የጠየቀ ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን ከአዴፓ ጋር መሥራት እንደሚያስቸግረው አስታውቆ ነበር፡፡ ይህን መግለጫ ተከትሎም አዴፓ የመልስ ምት በመስጠትና ሕወሓትን በመውቀስ የራሱ ሥራ እንዲሠራ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው የግንባሩ ድርጀቶች የእርስ በርስ መወነጃጀልና መቋሰል፣ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ደግሞ ዳግም ተቀስቅሶ ነበር፡፡ በወቅቱ የአዴፓ አመራሮች ሕወሓትን በስም በመጥቀስ ከቅማንት የማንነት አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጀርባ በመሆን፣ በአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ እንዳይሰፍን እየሠራ እንደሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ሕወሓትም በበኩሉ አፀፋዊ ምላሽ በመስጠት የአዴፓን አመራሮች፣ ‹‹የራሳችሁ ችግር ወደ ሌላ ሦስተኛ ወገን አታስተላልፉ፣ የሚገባችሁን የቤት ሥራ ሥሩ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡
ይህ በሁለቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሲካሄድ የቆየው እንካ ሰላንትያ ባለፈው ሳምንት ደግሞ አገራዊ ቅርፅ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለተከታታይ ሰባት ቀናት መደበኛ ጉባዔውን በመቀሌ ከተማ ሲያደርግ የነበረው ሕወሓት፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በክልሉ ስለተከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ላይ ዝርዝር ግምገማ ማካሄዱን ያስታወቀ ቢሆንም፣ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሳበው ግን ኢሕአዴግን አንድ ውህድ ፓርቲ ለማድረግ እየተሠራ ያለውን እንቅስቃሴ በመቃወም ያራመደው አቋም ነው፡፡
ሕወሓት በዚህ አቋሙ፣ ‹‹ኢሕአዴግን አፍርሶ አንድ ፓርቲ ለመመሥረት የሚደረገው ጥረት ኢሕአዴግን ብቻ ሳይሆን አገር ሊበትን ይችላል፤›› በማለት አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን ሕወሓት በመግለጫው ይህን ቢልም፣ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዓርብ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ደግሞ በመግለጫው የተሰነዘረውን ሐሳብ በማጣጣል፣ ‹‹ኢሕአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ኅብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም. ከተካሄደው አምስተኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ፣ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል፤›› በማለት ያጣጣለው ሲሆን፣ በተለይም ባለፈው ዓመት በሐዋሳ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የጥናት ሥራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው፣ አንድ ጠንካራ አገራዊ ፓርቲ እንዲመሠረት ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል፡፡
ይህ የኢሕአዴግ አቋም በርካታ ትችቶች እየተሰነዘሩበት የሚገኝ ቢሆንም፣ የመንግሥትና የፓርቲ አለመለያየት አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ነው በማለት ፓርቲው መታመሙ አገር ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በማለት ሐሳቡን የሚጋሩም አሉ፡፡
‹‹የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በስፋት ካያቸው ጉዳዮች አንዱ በአገራችን እየታየ ያለው ፈጣን አደጋና ወደፊትም ሊኖረው የሚችል አጠቃላይ ሁኔታ›› የሚመለከት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ይህ ችግርም እየተባባሰ የመጣውና ከዕለት ወደ ዕለት መጠኑና ስፋቱ እንዲጨምር ያደረገውም ‹‹የፓርቲ ውህደት ለመፈጸም እየተደረገ ያለው የችኮላ እንቅስቃሴ ነው፤›› በማለት አስታውቋል፡፡
‹‹በደፈረሰ አመለካከትና በአንድነት ሊሰምሩ በማይችሉ እሳትና ጭድ አስተሳሰቦችን በተሸከመ ኢሕአዴግ አይደለም ውህደት ቀርቶ፣ በግንባርነት ለመቀጠል የማይችል የተበተነ ድርጅት ነው አሁን ያለው፡፡ እንደዚህ ያለ የተበተነ ድርጅት ወደ አንድ ፓርቲ ውህደት ይመጣል ብሎ ማሰብ በራሱ ድርጅቱን ከመበተን አልፎ አገርን የሚበትን ተግባር ነው ሊሆን የሚችለው፤›› በማለት፣ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ታቃውሟል፡፡
ከዚህ አንፃር በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ አብዛኞቹ በማኅበራዊ የመገናኛ ትስስሮች የተሰጡ አስተያየቶች የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች ያልተመቻቸው ነገር በተፈጠረ ቁጥር በውይይትና በድርድር ለምፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ አገር ትበተናለች የሚለው አስተያየታቸው በራሱ በታኝ ነው በማለት የተቃውሞ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ችግራቸውን በአስቸኳይ መፍታት ካልቻሉ፣ የአገር ህልውና ላይ አደጋ መደቀኑ አይቀሬ እንደሆነ የሚገልጹ ድምፆችም አሉ፡፡
የኢሕአዴግ ምክር ቤት በበኩሉ፣ ‹‹እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ሕወሓት፣ በአሁኑ ወቅት ውህደቱን በተመለከተ አሉታዊ ገጽታ ያላቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል፤›› በማለት በመውቀስ፣ ከዚህም አንፃር ሕወሓት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ የሚሰጡ መግለጫዎች ሁለት መሠረታዊ ስህተት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡ እነዚህም ስህተቶች ከድርጅት አሠራርና ዲስፒሊን ጋር የተያያዙና በይዘቱ በማለት ገልጿቸዋል፡፡
‹‹የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ባልተገጸበት ሁኔታ ሕወሓት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅት አሠራርና ዲሲፕሊንን የጣሰ፣ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ መታረም ያለበት ነው፤›› በማለት ምክር ቤቱ ከዲስፒሊን አንፃር ያለው ስህተት ገልጿል፡፡
ከይዘት ጋር በተገናኘ ደግሞ ሕወሓት በተለያዩ መድረኮች አሀዳዊ ሥርዓት ለመመሥረት የታቀደ አስመስሎ የሚያቀርበውን ወቀሳ የተመለከተ ሲሆን፣ ‹‹የኢሕአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውኃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም፤›› በማለት ወቀሳውን አጣጥሎታል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር አቶ ትዕግሥቱ አወሉ አጠቃላይ የመግለጫውን ይዘት ሕወሓት አሁን ካለበት የፖለቲካ ዓውድ አንፃር መመልከት እንደሚገባ ገልጸው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ እንደተገፋ የሚያምነው ሕወሓት ከራሱ ዕይታ አንፃር እንዲህ ዓይነት አቋም ቢያራምድ አይገርምም፤›› በማለት፣ የሕወሓት ከመሀል አገር ፖለቲካ መገፋት የፈጠረው ስሜት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን፣ ‹‹በዚህ አገር የመንግሥትና የፓርቲ ድንበር አለመኖር የፓርቲውን ሕመም የአገሪቱ ሊያደርገው ይችላል፤›› ሲሉም፣ አጠቃላይ በሕወሓት የቀረበው ተቃውሞ ከዚህ አንፃር ሊታይ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን ውህድ ፓርቲ በመመሥረቱ አገሪቱን ይበትናል የሚለው አገላለጽ በመርህ ደረጃ ተገቢ ባይሆንም፣ ነገር ግን በበርካታ የአፍሪካ አገሮች እንደተመለከተው እንኳን ድርጅት አምባገነን መሪዎች ሥልጣናቸውን በተለያየ መንገድ ሲለቁ የተፈጠሩ ብዙ ውጥንቅጦች አሉ፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የኢሕአዴግ መፍረስ ችግር አለው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ማለት አይደለም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
እንዲህ ያለውን ትርክት የሚቃወሙ በርካቶች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ቡድን በላይ ስለሆነች፣ የእነዚህ ቡድኖችና ድርጅቶች መክሰም፣ መፍረስ ወይም መዋሀድ አገሪቷን የመፍረስ አደጋ ውስጥ አይከታትም በማለት ይሟገታሉ፡፡
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበር አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የሕወሓት አመራሮች ከዚህ ውህደት ከሚለው ሐሳብ ጋር እያራመዱት ያለው አቋም ጭራሽ እንደተምታታባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዓመታት ውህደት እንዲካሄድ ጥረት እየተጠና ነው ሲሉ ከርመው፣ አሁን የውህደት ነገር እየቀረበ ሲመጣ እንዲህ ማለታቸው አሳፋሪ ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የኢሕአዴግ ምክር ቤት በበኩሉ፣ ‹‹የሕወሓት መግለጫ ችግር የውህደት አጀንዳውን አሁን ያለው የለውጥ አመራር በድንገት ያመጣው በሚያስመስል መልኩ ማቅረቡ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹አሁን ያለው የለውጥ አመራር የሠራው ነገር ቢኖር ለረዥም ዓመታት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሲጓተት የቆየውን ጥናት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለውሳኔ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ማድረሱ ብቻ ነው፤›› ብሏል፡፡ እንዲህ ያሉ አስተያየቶችም ተቀባይነት እንደሌላቸው ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከመግለጫው አቋም ጋር የሚስማማ ሐሳብ ያላቸው አረጋዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ሕወሓት በዚህ ሰዓት እየሰጠው ያለው አስተያየት ለአገር ወይም ለሕዝብ ከመቆርቆር የመጣ አይደለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጡት ለድርጅቱና ለአመራሩ ልዕልና መሆኑን የሚያሳይ ነው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡
‹‹እንዲህ ያሉ መግለጫዎች የሚወጡት ሕዝብና አገርን አስቀድመው ቢሆን ኖሮ በጉዳዩ ላይ መግባባት አያዳግትም፡፡ ነገር ግን አሁን ችግር እየፈጠረ ያለው የራስ ወደድነት ስሜት በማየሉ ነው፤›› በማለት፣ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ለአገር ህልውና ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡
በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ቁርጠኛ ሆነው በልዩነትና በሚያግባባቸው ጉዳዮች ላይ ለመሥራት የቁርጠኝነት ችግር እንዳለ ሲገለጽ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን አገርን የመምራት ያህል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ድርጅት አባሎች በመግለጫ የሚነጋገሩት እስከ መቼ ነው? ልዩነቶችን ፈትቶ ወደ ውህደት የሚደረገው ጉዞ ከውስጡ የሚገጥመውን ችግር መክቶ የምር ተዋህዶ የገባውን ቃል ለመፈጸም ምን ያህል ዝግጁ ነው? እንዲሁም ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚለውን ትርክት ሊያከስምና ሟርት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ድርጅት የሚፈጠረው መቼ ይሆን? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሲሆን፣ አስቸኳይ ምላሽ የሚሻ ዓብይ ጉዳይ መሆን እንዳለበት የሚያሳስቡም በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢሕአዴግ ወደ ውህደት የሚያደረገው ጉዞ መበታተን አስቀርቶ ብልፅግናን ይዞ ይመጣል? ወይስ አደጋው ያይላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የብዙዎች ጉጉት ነው፡፡
|| ምንጩ ሪፖርተር ነው ||