በ400 ሚሊዮን ብር ዕዳ 200 የኢትዮጵያ ባቡር ፉርጎዎች በቻይና ተይዘዋል ተባለ
ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት እንዲሰጡ የዕቃ እና የመንገደኞች ማጓጓዣ ሁለት መቶ የባቡር ፉርጎዎች ዕዳቸው ባለመከፈሉ በቻይና መንግሥት ተይዘው እንደሚገኙ ታወቀ::
የባቡር ፉርጎዎቹ 14ሚሊዮን ዶላር ወይም 400 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ክፍያ ባለመፈጸሙ ከቻይናው የባቡር አምራች ኩባንያ ፉርጎዎችን መረከብ እንዳልተቻለ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት::
መንግሥት የባቡር ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ወቅት 65 በመቶ የሚሆነው የባቡሩ ክፍል በውጭ ባለሙያዎች እንዲገጣጠም ቀሪው 35 ፐርሰንት ደግሞ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲሠጥ መመሪያ ያስቀመጠ በመሆኑ የ35 በመቶውን የባቡር መገጣጠም ሥራ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውል ፈጽሞ ወስዶ ነበር::
ሆኖም ሜቴክ የመገጣጠሙን ሥራ አሳልፎ ለአንድ ቻይና ኩባንያ በመስጠት ሥራውን ሲያከናውን ከመቆየቱ ባሻገር በሜቴክ ትዕዛዝ ሲገጣጠሙ የነበሩት ባቡሮች ከግማሽ በላይ ገብተው ሁለት መቶ የሚሆኑ ፉርጎዎች ማለትም አራት ሙሉ ባቡሮች (አራት ትሬን ሴት) ቀሪ ክፍያ ባለመፈጸሙ የተነሳ የቻይናው ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግሥት የክፍያ ማረጋገጫ ካልተሰጠው በስተቀር እንደማያስረክብ አስታውቋል::
የምድር ባቡር አመራሮች ጉዳዮን ለሜቴክ ቢያሳውቁም ተቋሙ ውስጥ በተካሄደው ከፍተኛ ሪፎርም ምክንያት የባቡሩን ጉዳይ የሚመለከተውን ሰው ለማግኘት እንደተቸገሩ የደረሰን ዜና ያስረዳል::
ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አሁን ካሉት ባቡሮች ተጨማሪ አራት ባቡሮችን ለመጨመር ፍላጎት እንዳለውም ሰምተናል::
የመብራት ኃይል ሠራተኞች የተደረገላቸው የ18 በመቶ ደምዎዝ ጭማሪ ተቃውሞ አስነሳ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከ22 ሺኅ በላይ ለሚሆኑት ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞቹ የደምዎዛቸውን እስከ 18 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ቢያደርግም የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ያላገናዘበ ነው ሲሉ የድርጅቱ ሠራተኞች ተቃወሙ::
ከሐምሌ 1ቀን 2010 ጀምሮ እስከ ሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ውስጥ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ተቀጥረው እየሠሩ ላሉ ሠራተኞች እና የሥራ ሓላፊዎች ጭማሪው የተደረገ ሲሆን በደረጃ አራት እርከን ወይም የደምዎዛቸውን 18 በመቶ በመጨመር ከሐምሌ 1ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ነው የተነገረው::
በዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤታቸው ከ60 በመቶ በታች የሆኑ ሠራተኞች እና የሥራ አፈጻጸም ምዝና ውጤታቸው ከ65 በመቶ በታች የሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ከዓመታዊ የደምዎዝ ጭማሪው ውስጥ አይካተቱም ተብሏል:: በሥራ ደረጃቸው ከደሞዝ እርከን ጣሪያ በላይ የሆኑና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ ሠራተኞች እንዲሁም የሥራ ሓላፊዎች የደምዎዛቸውን 11 በመቶ እንዲያገኙ ተደርጓል::
የተቋሙ ሠራተኞች የሥራው ባህርይ አድካሚ መሆኑን በማንሳት ክፍያው የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ አለመሆኑን በመግለጽ የደምዎዝ እርከን ማሻሻያ እንዲያደርግ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ሲያነሱ ነበር ከዚህ ቀደም ተገልጿል:: አሁን የተደረገውም ጭማሪ አብዛኛውን ሠራተኛ ያላስደሰተ እና በየዓመቱ ከትርፍ ላይ የሚደረግ አነስተኛ ጭማሪ መሆኑን ይናገራሉ ሠራተኞቹ::
የደምዎዝ እርከንና ዕድገት ጥያቄውን ለሚመለከተው ክፍል በተደጋጋሚ ቢቀርብም “እየታየ ነው” የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስታወሱት ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 18 በመቶ የደረሰ ሲሆን የምግብ ዋጋ ግሽበት 23 በመቶ በመድረሱ በድህነት አረንቋ ለተዘፈቀው ሕዝብ ጭማሪው የሚፈይደው ነገር እንደሌለ በሠራተኛ ማህበራቸው አማካይነት ባወጡት መግለጫ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል::
አዳዲስ መኪኖች ላይ አበረታች የሆነ የቀረጥ ማሻሻያ ተደረገ
የገንዘብ ሚኒስቴር አዳዲስ መኪኖች ላይ የአምስት በመቶ የቀረጥ ቅናሽ ማድረጉ ታወቀ:: ዓለም ዐቀፉ የጉምሩክ ድርጅት በየአምስት ዓመቱ የሚያሻሽለውን የታሪፍ መጽሐፍ መሠረት በማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት ተከልሶ መጠናቀቅ ይገባው የነበረውን የታሪፍ መጽሐፍ በማዘጋጀት ነው የታሪፍ ማሻሻያው የተደረገው::
መጽሐፉ ለተሽከርካሪ ምርቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና ከዚህ ቀደም ከሦስት ገፅ በላይ ከፍ በማድረግ አሻሽሏል:: የገንዘብ ሚኒስቴር የገቢዎች ሚኒስቴር እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የትራንስፖርት ባለሥልጣን በጋራ በመሆን ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ጊዜ ባካሄዱት ጥናት መሠረት የታሪፍ መጽሐፉ በዝርዝር መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል::
ከተደረጉት ማስተካከያዎች መሀል ከአስር ዓመት በላይ እና በታች የሆኑትን ተሽከርካሪዎች በመለየት ለሁለት በመክፈል የተሠራው ሥራ ነው:: ከአንድ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ተመሳሳይ 35 በመቶ ቀረጥ ቢጣልባቸውም ወደፊት በሚወጡ ሕጎች መሠረት ሕግ አውጪው የተለያዮ ቅጣቶችን ሊጥል እንደሚችልም ተጠቁሟል::
በተለይም ሙሉ በሙሉ ተበትነው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነጻ የተደረገ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ መኪናን በዝርዝር ውስጥ በማካተት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ ፈቅዷል:: የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ ኃይል ቀላቅለው የሚጠቀሙ መኪኖችም በመጽሐፉ የተካተቱ ሲሆን የተጣለባቸውም ቀረጥ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ታውቋል::
የተደረገው የቀረጥ ቅናሽ በተለይም ሙሉ በሙሉ ያልተገጣጠመ መኪና ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች አበረታች እንደሆነ ቢነገርም አሁን ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያሉ ገጣጣሚዎች በከፊል የተገጣጠመ መኪና የሚያመርቱ መሆኑ አይዘነጋም::
የገቢዎች ሚኒስቴር በሩብ ዓመት በታሪክ ትልቁን ግብር መሰብሰቡን አሳወቀ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም የንግድ መቀዛቀዝ ቢቀጥልም የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዮ ምንጮች የሰበሰበው ግብር የ3 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳሳየ ታወቀ::
በ2011 በጀት ዓመት 56 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው ሚኒስቴሩ 57 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 102 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቋል:: ለተገኘው ጭማሪ ዋነኛ ምክንያቶች ግብር ከፋዮችን በማስተማር በተሠራው ሥራ እንዲሁም በተወሰዱ ሕግ የማስከበር ዕርምጃዎችና ሠራተኞች በትጋትና በቁርጠኝነት የሥራ ድርሻቸውን በመወጣታቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል::
ባለፉት ሦስት ወራት የግብር አፈፃፀም በወራት ሲከፋፈል በሐምሌ ወር 18 ቢሊዮን ብር ሲሰበሰብ በነሐሴ ወር 20 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም መስከረም ላይ 19 ነጥብ 1ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል:: ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም የንግድ መቀዛቀዝ ቢቀጥልም የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዮ ምንጮች የሰበሰበው ግብር የ13 ቢሊዮን ብር የሰበሰበው ሚኒስቴሩ በሩብ ዓመቱ ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ መሆን ችሏል::
በሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ስም በአምቦ ዮንቨርስቲ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመረቀ
በሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ስም የተሰየመው የባህል ጥናትና ምርመር ማዕከል በአምቦ ዮንቨርስቲ ተመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ያስገነባው ማዕከል በሃገሪቱ የሚገኙ የብሄር እና ብሄረሰቦች ባህል ላይ ጥናት ለማድረግ እና ለማስተማር ያቀደ ነው። በሎሬቱ ስም በተሰየመው በዚህ ማዕከል ውስጥ ቤተ-መጽሃፍት እና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይገኛሉ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ታደሰ ቀነዓ (ዶ/ር) ማዕከሉ የተቋቋመው ለሁለት ዓላማ መሆኑን ጠቁመው”የመጀመሪያው አዲሱ ትውልድ ታላላቆቹን አውቆ እንዲዘክር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ ሎሬት ጸጋዬ አይነት ትውልድ ለመፍጠር ነው” ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልል እንደሚመጡ ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ ተማሪዎች ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት እና የሚማማሩበት ማዕክል እንደሚሆንም አስረድተዋል።
የማዕከሉ ምረቃ ላይ የተገኙት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ሚንሰትር ዴኤታ የሆኑት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ከሎሬት ጸጋዬ በላይ ለፑሽኪን እውቅና የምትሰጥ ሃገር ውስጥ ነው ያለነው” ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ያላትን ሃብት ዘንግታ እና ምሁሮቿ የሚገባቸውን ክብር ተነፍገው ኖረናል ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህን መሰል ማዕከላት ማቋቋም የሃገርን አንድነት ከማጠናከር በተጨማሪ ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠት አርአያነት ያለው ተግባርም ነው ብለዋል። 1970 ላይ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተዋወቁ የሚናገሩት አርቲስት እና የሕግ ባለሙያው አበበ ባልቻ፤ ሎሬት ጸጋዬ በአራት ቋንቋዎች ድንቅ አድርጎ ይጽፍ የነበረ ሰው ነው ብለዋል።
“ጸጋዬ የአርት ሰው ነው። ታሪክም ይጽፋል። የሃገራችንን እና የአፍሪካን ታሪክ ለዓለም ያስተዋወቀ ሰው ነው። ሎሬት ጸጋዬ ሲከፋው እና ቅር ሲለው አምቦ መምጣት ይወድ ነበር” ያለው አንጋፋው አርቲስት እና የሕግ ባለሙያው አበበ ባልቻ፤ ዩኒቨርሲቲው የሚፈቅድ ከሆነ በቅጥር ግቢው ውስጥ የሎሬቱን ሃውልት ማቆም እንሻለን ብሏል።
ከሎሬት ጸጋዬ ጋር የስጋ ዝምድና እንዳለው የሚናገረው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በበኩሉ፤ “ጸጋዬ የእኔ ዘመድ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዘመድ ጭምር ነው ፤ ለሎሬት ጸጋዬ የመታሰቢያ ሃውልት በአምቦ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም ሊቆምላቸው ይገባል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል::
ሎሬት ጸጋዬ ምዕራብ ሸዋ አምቦ አካባቢ 1928 ዓ.ም. ነበር የተወለዱት። ለስነ-ጽሁፍ ፍላጎት ማሳየት የጀመሩት ደግሞ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ ነበር :: በ16 ዓመታቸው ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤትን ከተቀላቀሉ በኋላ በይበልጥ የስነ-ጽሁፍ ችሎታቸውን አዳብረዋል። 1959 ዓ.ም. ላይ ሕግ ለማጥናት ወደ አሜሪካ ቺካኮ ማቅናታቸውንም የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ። ከአሜሪካ መልስ የብሔራዊ ቲያትር ሓላፊ በመሆን ሠርተዋል።