ከሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ከሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኖቤል ሰላም ሽልማት በማግኘታቸው የተሰማውን የላቀ ደስታ ሶዴፓ ይገልፃል።

የሶማሌ ክልል ህዝብ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ለዘመናት ለነፃነት፣ እኩልነትና በመፈቃቀድና መከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ጠንካራ ትግል ሲያደርግ የቆየ ከመሆኑም ባሻገር እንደ ሌሎች የአገራችን ህዝቦች ሁሉ በገዥ መደቦች ይደርስበት በነበረው በደልና ጭቆና ሳይንበረከክ ክብሩን ያላስደፈረና ለህልዉናው አደጋ የሆኑ ጉዳዮችን ሲመክት የቆየ ሀገር ወዳድ ህዝብ ነው። የሶማሌ ህዝብ በህገ መንግስቱ የተጎናፀፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲጠቀምና በሀገር ግንባታ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል መሪ ድርጅት በማስፈለጉ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከ21 ዓመታት በፊት ተመስረቶ የሶማሌ ህዝብን በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ዙሪያ ሲያታግል ቆይቷል።

ሶዴፓ በሶማሌ ክልል መሪ ፓርቲ ሆኖ በቆየባቸው ባለፉት 21 አመታት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰፋፊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አስመዝግቧል። ይሁንና ፓርቲው በራሱ የውስጥ ችግር እና በግል ጥቅማቸው የታወሩ የቀድሞ አመራሮች የመንግስትና የህዝብን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ያደርጓቸው በነበሩት ፀረ- ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ፌዴራላዊ ስርዓት አካሄድና ጣልቃ ገብነቶች ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ የፖለቲካ ፕሮግራሙን በነፃነት ተግባራዊ ባለማድረጉ ለህዝቡ ቃል በገባው ልክ ኃላፊነቱን መወጣት ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በሌላ በኩል ሶዴፓ ትክክለኛ አሰራሩን ተከትሎ በህገ-መንግስቱ መሰረት ክልሉ ወደ ዳበረ ዴሞክራሲና ብልጽግና እንዲመራ የሚታገሉ አመራሮችና አባላትም በግል ጥቅም የታወሩ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ጥቃትና እንግልት ሲደርስባቸው ቆይቷል። በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ህዝብ ህገ-መንግስታዊ የሆነው የፌዴራል ስርዓት በተሟላ መልኩ በተግባር እንዲከበር ባለፉት 27 አመታት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም እንደ ሀገር ለሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ትግል ምቹ ሁኔታ ሰላልነበር ጥረቱ የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል።

በመሆኑም ባለፉት 27 አመታት በሀገራችን ህገ-መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ በተገቢው መንገድ ሲተገበር እንዳልነበረ ይልቁንም ሶማሌ ክልልን ጨምሮ የተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በሞግዚትነት ሲተዳደሩ እንደነበሩ ሶዴፓ ያምናል። እነዚህ የሞግዚት አስተዳዳሪዎች ለግል ጥቅማቸው ማስፈፀሚያ የሚመቻቸውን አካል ለይስሙላ ከማስቀመጥ ባሻገር የክልሉን በጀትና መሬት በመቀራመት የክልሉን ህዝብ ለከፋ ጉዳት ዳርገዋል። በተጨማሪም በዘረፉት ሀብት አሁንም ድረስ አገርን ለማፍረስ እያዋሉት መሆኑ በእጅጉ ያሳዘነው ሶዴፓ እራሱን መለወጥና ያለፈውን መካስ እንዳለበት አምኖ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በዚሁ መሰረት እንደ ሀገር የተፈጠረውን ለውጥና የክልሉ ህዝብ በተጠናከረ መልኩ የጀመረውን ትግል እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከአንድ አመት በፊት ሶዴፓ እራሱን ለማደስና የተቋቋመለትን ዓላማ በነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ የጀመረው ትግል ፍሬ አፍርቶ እነሆ ዛሬ በክልሉ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከማስቻሉም በላይ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ከምንጊዜውም በላይ እየተፋጠኑ ይገኛሉ። የክልሉ ህዝብም ሶዴፓ ከበፊቱ በመማር የጀመረውን ለውጥ እያደነቀና ለውጤታማነቱም ከፓርቲው ጎን በመሆን ድጋፉን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

ሶዴፓም ውስጣዊ ጥንካሬውን በማጎልበትና እንደ ሃገር የተጀመረው ለውጥ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ህዝቡን ለመካስ የላቀ ጥረት እንዲሁም ከምንጊዜውም በላይ የራሱን ጉዳይ በራሱ እየወሰነ ስኬታማ እንቀስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

ይሁንና አንዳንድ በለውጡ ጥቅማቸውን ያጡ አካላት ከዚህ ቀደም በፓርቲያችንና በህዝባችን ላይ ሲያደርሱት በነበረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በደል ሳይፀፀቱ ዛሬም የእናውቅልሃለን አካሄድና የድሮውን ለመመለስ ተስፋቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ ይገኛል። እነዚህ አካላት ባለፉት 27 አመታት ክልላችንን ለችግር ዳርጎ የነበረው አካሄድ ዳግም እንዲመለስ ሶዴፓ መቼም እንደማይፈቅድ ግልፅ ሊሆንላቸው ይገባል። ለፓርቲያችንና ለህዝባችን የሚጠቅመውንም ጠንቅቀን የምናውቅና ቅንነት የጎደለው ምክር የምንሻ አለመሆናችንን ሊገነዘቡት ይገባል።

በተጨማሪም በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች አገራዊውን ለውጥ ለማዳናቀፍ ሌት ተቀን በሚጥሩ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ችግር በህገ-መንግስቱ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሶዴፓ ቁርጠኛ መሆኑን ይገልፃል።

በሌላ በኩል ባለፉት 27 አመታት የበላይነት ይዘው የነበሩ የልዩነትና ጥላቻ ትርክቶችን፣ የብሔር ፅንፈኝነትንና አጋር ድርጅቶችን አግላይ አካሄዶችን በሚፈታ መልኩ ኢህአዴግ የጀመራቸውን ለውጦች ሶዴፓ ያደንቃል። በተያያዘምኢህአዴግ ባለፉት አመታት የነበሩትን ስኬቶች ለማስቀጠል፣ የነበሩትን ስህተቶች ለማረምና አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ እራሱን ለመለወጥና አጋር ድርጅቶችንም ለማቀፍ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እራስን በራስ ከማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ስርዓትና ከምንከተለው የፌዴራል ስርዓት ጋር የማይቃረን፣ አሃዳዊ ስርዓት የመፍጠር ዓላማ የሌለውና ለሀገራችን ወቅታዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ሶዴፓ ያምናል።

በመሆኑም የበለፀገችና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ያረጋገጠች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ራዕይን ለማሳካት ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ተባብሮ መስራት፣ የህዝቡን የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ በቅንነት እየመለሱ መሄድና ሀገራዊውን ለውጥ በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር ወሳኝ መሆናቸውን በማመን የሶዴፓ ምርጫ የመተባበር፣ የመተጋገዝ፣ የመዋደድና የእውነተኛ ህገ-መንግስታዊና ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እንጂ ወደ ነበረው በደል፣ ግፍና ትርምስ የሚመልሰን ማንኛውም ህልም ሶዴፓ ዘንድ ቦታ የሌለው መሆኑን እንገልፃለን።

በህብረት የአገራችን መፃኢ እድል ብሩህ ነው!!!

ሶዴፓ ማዕከላዊ ጽ/ቤት

ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም

ጅግጅጋ

LEAVE A REPLY