ዌል እንግዲክ” እንዲል ኃይሌ፤ ነገሩን እናዋዛው ዘንድ ወደድን።
እናም ወደ ኮዬ ፈጬ ወረድን። በዚያ….
አንዱ ቄሮ ከመሰሎቹ ተነጥሎ ለብቻው ተቀምጧል። አዝኗል። በጣም ከፍቶታል።
“ምነው? ምን ሆነሀል?”
“ምን እባክህ፤ ቀረችኮ” አለ በዱላው መሬቱን እየተመተመ።
“ማ… ማናት የቀረችው?”
ነገረኝ፤ በለውጡ ሰሞን የጠበሳት “ፍቅረኛው” ናት የቀረችው። ለፍቅር ጉዳይ ቁርጥ ቀጠሮ ነበራቸው። እሷ ግን የውሃ ሽታ ሆነችበት። ከሌላ ሰውጋ ጀምራ ይሆናል እንጂ አትቀርም የሚል ክፉ ሀሳብ እያመነዠከ ት…ክ ..ዝ ብሏል። ያሳዝናል።
“በል አሁን ስሜቴን የምገልፅበት፣ አንድ ግጥም ፃፍልኝ፤ መቅረቷ እንዳበሸቀኝ የሚገልፅ…” አለኝ።
“ግጥምኮ እንደቀልድ የሚፃፍ አይደለም”
“ተው ባክህ፤ እዛ ፌስቡክ ላይ ዝም ብለህ ትቸከችክ የለ፤ ልትረዳኝ ስላልፈለግክ ነው አያቅትህም”
“ቄሮዬ …..”
አቋረጠኝ።
“እሺ፤ ከሆነ መፅሐፍም ቢሆን …ፈልግልኝ”
አንድ የሥነ ቃል ስብስብ መፅሐፍ ትዝ አለኝ።ከተሸከምኩት ቦርሳ ውስጥ አወጣሁት። “በቃ ከዚህ ውስጥ ስሜትህን የሚገልፅ ስንኝ ምረጥ” አልኩና መፅሐፉን ሰጠሁት። ገፆቹን እየገላለጠ አነበበና የመረጠውን “ግጥም” ጠቆመኝ። እንዲህ ይላል፦
.
“ትመጫለሽ ብዬ – ድንጋይ ስለቃቅም፤
ፍቅር ጣለሽ አሉ – ያንቺ ጉድ አያልቅም ”
.
አነበብኩና ፈገግ አልኩ።
“ምነው ሳቅህ?” አለኝ ኮስተር ብሎ።
“አይ…. የመረጥካቸው ስንኞች ከአንተ ሁኔታጋ አይሄዱም፤ ጥቂት ቃላቶች መሻሻል ቢደረግባቸው ጥሩ ነው”
“አሻሽልልኛ”
ባዶ ወረቀት አወጣሁና አሻሽዬ ፃፍኩለት። እንዲህ ብዬ፦
.
“ትመጫለሽ ብዬ – ዱላ ሳጠራቅም፤
ፍቅር ጣለሽ አሉ – ያንቺ ጉድ አያልቅም”
.
አነበበው። እና ትኩር ብሎ አየኝ። አየኝና ዱላውን ወዘወዘ።
.
“ሀጠ….ራ… ው!”
.
ዱላውን ከመሰንዘሩ በፊት ነቃሁ። ለካ የሆነው ሁሉ የሆነው፣ በህልሜ ነው