ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጃዋር መሐመድ እና አባሪዎቹን አስጠነቀቁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ስለ ምርጫ፣ ስለ ፌዴራል ሥርዓቱ፣ ሙስና፣ ሚዲያ፣ ፀጥታና ደህንነት፣ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ ቀርቦላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምርጫን በተመለከተ “በዘንድሮም ምርጫ ይሁን በሚቀጥለው ምርጫ ተግዳሮት የሌለው ምርጫ ማድረግ አይቻልም” በማለት ምርጫው ይራዘም የሚለው አስተያየት እንደማያዋጣ አስረድተዋል::
መንግሥት በቂ በጀት ለምርጫ ቦርድ መመደቡን እንዲሁም የቦርዱ አባላትም ከማንኛውም ጊዜ የተሻለ ነፃ ነው የሚያስብል እንደሆነም በመጥቀስ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ምርጫ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል። “የመንግሥት ፍላጎትም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ዝግጁነትም ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።መንግሥት፣ ሕዝብ እና ምርጫ ቦርድ ተባብረው የተሻለ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ዕምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።
በምርጫ ሕጉ ላይ ቅሬታ ያላቸው ፓርቲዎች ያቀረቡት ቅሬታ አግባብ እንዳልሆነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰብሰብ ማለት ለሁላችንም ያስፈልጋል፤ ምርጫውን ማድረግ በብዙ መልኩ ይጠቅመናል፤ ፈተና አልባ ምርጫ ባይሆንም የተሳካ ምርጫ ማድረግ ይቻላል” ሲሉ አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ፤ ኢሕአዴግ የኢትዮጵ ያአባት አይደለም፤ እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚል አስተሳሰብ ትክክል ያልሆነ ነው” በማለት በኢሕአዴግ ውስጥ ስላለው መከፋፈል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢህአዴግ ውስጥ ላለፉት 5 እና 10 ዓመታት ውህደቱ ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን አስታውሰው፤ ውህደት እንዲፈፀም በሀዋሳው ጉባኤ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን መሠረት ባደረገ መልኩ “እየተወያየን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “ውህደቱ ጊዜው አሁን አይደለም” የሚሉ ፓርቲዎችና አባላት ቢኖሩም እስካሁን ግን ውህደቱ አያስፈልግም ያለ አካል ሰምተው እንደማያውቁ በይፋ አረጋግጠዋል።
በክልሎች መካከል ያለውን ፀጥታ በተመለከተም፤ የትጥቅና የቃላት ፉክክር እንደሚታይ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የውጊያ ቀስቃሾች ሁል ጊዜም አንድ ዓይነት ናቸው” በማለት በየጊዜው ግጭት እየቀሰቀሱ በዚያ ውስጥ መኖር የሚፈልጉ አሉ በማለት ወጣቶች እንዲነቁ መክረዋል።
የትግራይ ክልልን እየመሩ ያሉ አመራሮች የክልሉን ችግር መፍታት እንጂ ከአማራ ክልል ጋር መዋጋት አይፈልጉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በመካከል የድራማው አካል የሆኑትን የመለየት ችግር ነው ያለው” ብለዋል። የክልሎች ትጥቅ በሀገር ደረጃ የሚያሰጋ አይደለም በማለት ክልሎች መዘጋጀት ያለባቸው የራሳቸውን የክልል ውስጥ ደህንነት ለመጠበቅ እንጂ ከሌሎች ክልሎች ጋር ለመጋጨት መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት የሚችለውን እያደረገ እንደሚሄድ ጠቅሰው በአማራና ቅማንት፣ በሶማሌና በአፋር መካከል የሦስት ቀበሌ ችግር ነው ያለው በሚል ችግሩን የፈጠሩት ሌሎች ናቸው ማለት የሚለው ስለማያዋጣ ሓላፊነት ወስዶ መሥራት ይጠይቃል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “መንገድ መዝጋት የኋላ ቀር ፖለቲካ ውጤት ነው።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረው ነገር የማስተካከያ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
“የሚያባሉን እድሜ ጠገብ ሰዎች ናቸው” ያሉት የለውጡ ፊት አውራሪ ባይሎጂም [ሥነ ሕይወትም] ከዚህ አንጻር የራሱ መፍትሔ ስላለው ሰላም ማደፍረሱ እንደማይቀጥል አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሥፍራዎች በግላቸው በመንቀሳቀስ በርካቶችን ያነጋገሩት ሰላም ለኢትዮጵያ ቀዳሚ ስለሆነ ነው በሚል መርህን በመከተል እንደሆነና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ፣ በብሔሮች መካከል እርቅ እንዲፈጠር የእርቅ ኮሚሽን እንዲቋቋም የተሠራው የውስጥ ሰላም ወሳኝ ስለሆነ መሆኑን አመላክተዋል።
“50 ሺህ ተፈናቃይ አለብን ያሉ 1ሺህ ተፈናቃይ ማቅረብ አልቻሉም፤ ማፈናቀልና ተፈናቃይ መቀበል ንግድ ነው የሆነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ “በጌዲዮ የተፈናቀለው በሚሊየን ተጠርቶ ስንመልስ ግን አነስተኛ ቁጥር ብቻ እንዳላቸው ተረድተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥታቸው ለውስጥ ሰላም አበክሮ እየሰራ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የምንታገሰው የነበረውን ነገር ላለመድገም ነው” ሲሉ አስረድተዋል። የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ ጠንከር ያለውን የግብፅ አቋም አስመልክቶ ሲጠየቁም” የማንንም ፍላጎት ለመጉዳት የጀመርነው ፕሮጀክት አይደለም” በማለት በመግባባትና የግብፅን ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንቀጥላለን ብለዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ከግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“ቁጭ ብለን እናወራለን፤ ማንም ይህንን ግንባታ ማስቆም አይችልም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል” በማለት ጦርነት እንከፍታለን የሚሉ አስተያየቶቸን አስመልክተው “ማንንም አይጠቅምም ብለን እናምናለን” ብለዋል። “ጦርነትም ከሆነ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ አላት፤ በሚሊዮን ማሰለፍ እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
“በቀድሞ መሪዎች የተፈጠሩ ስህተቶችን እናስተካክላለን እንጂ የተጀመሩ ምርጥ ስራዎችን አናቋርጥም፤ እንዲህ አይነት ምርጥ ስራዎችን በማቋረጥ አገር አትገነባም” ሲሉም መክረዋል::
የኑሮ ውድነቱን ካመጡ ነገሮች መካከል አንዱ የቤት ኪራይ ውድነት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛው የምግብ ዋጋ መናር እንዲሁም ሥራ አጥነትና የሚመረተው ምርት በገበያ ከሚፈለገው ያነሰ መሆን ነው ብለዋል አንደኛውን ነጥሎ በመፍታት ለሁሉም መፍትሄ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት በሚመለከት እስካሁን ከተገነቡት ቤቶች በእጥፍ የሚልቅ በመንግሥትም በግል ባለሃብቶችም ለመገንባት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ግንባታ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጪም የሚካሄድ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታው በጥምረት ወይንም በሙሉ ኢንቨስትመንት እንደሚሆን አብራርተዋል። ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የለገሃሩን ፕሮጀክትንም በማስታወስ ሌላ ጎተራ አካባቢ በተመሳሳይ ለባለሃብቶና ዲፕሎማቶች የቤት ፍላጎት የሚሆን አዲስ ቱሞሮ የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከቻይና መንግሥት ኩባንያ ጋር ሊፈራረሙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ሌላው የግል ባለሀብቶች መካከለኛ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች የሚሰሯቸው ቤቶች ችግሩን እንደሚያስተነፍሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ እንደራሴዎቹ አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለት ወር ውስጥ እስከ 4ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚሆን የቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው ብለዋል። እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መጠለያ በመስጠት የተለያዩ ሥራዎች ላይ ለማሰማራት ሁሉንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑንም መስክረዋል።
በሁለት ወር ውስጥ የሚጠናቀቀው በቀን 1 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርተው ከግለሰቦች ጋር በመነጋገር እየተገነባ ያለው ፋብሪካ ቢያንስ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች በቅናሽ ዳቦ ለማቅረብ እንደሚያስችል በመግለጽ በምግብ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህ ዓመት የበጀት ዓመት መጠናቀቂያ ድረስ የሚጠናቀቀውና ግዙፍ የሆነው ሌላ የዳቦ ፋብሪካ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ንጉስ በሰጡት ርዳታ በቀን ከ10 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት ፋብሪካ መሆኑንም ገልፀዋል። ይህ ፋብሪካ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ ዜጎችም የዳቦ አቅርቦት ይኖረዋል ተብሏል።
የከተማ እርሻ ላይ በመሰማራት የስራ ፈጠራና የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ይሰራል ሲሉም አክለዋል። የመገናኛ ብዙኃንን አስመልክቶ ጠቅላዩ በተናገሩት ንግግር ሚዲያው ላይ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት ሚዲያ ነፃ እንዲሆን በተደጋጋሚ መጠያቃቸውን አውስተዋል።
“መቻል ላይ ግን ችግር አለ፤ ሚዲያ የዘር፣ የብሔር፣ የነጋዴዎች መቀለጃ ሆኗል።” በማለት ኢትዮጵያዊያን መረጃዎችን እያጣሩ እንዲሰሙና ኃላፊነት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የሌላ አገር ፓስፖርት ኖሯቸው የሚዲያ ባለቤት የሆኑ ሰዎችን በሚመለከትም “ትዕግሥት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው እርምጃዎችን መውሰዳችን አይቀርም” በማለት “ሁለት ቤት መጫወት አይቻልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጃዋር መሐመድ “መኖሪያዬም ሆነ መሞቻዬ በኦሮሚያና ፊንፊኔ ነው” በማለት ለዶ/ር ዐቢይ ምላሽ ሰጠ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በፓርላማው ባደረጉት ንግግርና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ስሙን ባይጠቅሱም ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉለት አወዛጋቢው አክቲቪስት እና የፖለቲካ ተንታኝ ለዶክተር ዐቢይ አስተያየት ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል::
በርካታ አስተያየት ሰጪዎችና የፖለቲካ ሰዎች ግለሰቡ ራሱን ይፋ ባደረገ መልኩ የሰጠውን እንካ ሰላንቲያ የንቀትና የማን አለብኝነት ስሜት የተንጸባረቀበት ተራ ድርጊት ነው ሲሉ በይፋ እየተቹት ይገኛሉ::
ጃዋር መሐመድ ለዓመታት በተጠቀመበትና አሁንም በሚገለገልበት የፌስ ቡክ ገጹ የውጭ ፖስፖርት ቢኖረውም አሁንም ለኦሮሞ ሕዝብ ከመታገል ወደ ኋላ የሚጎትተው ነገር እንደሌለ በአማርኛና በኦሮምኛ ባሠፈረው ጽሑፉ ላይ ገልጿል::
በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ጃዋር መሐመድ ለተከታዩቹ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮምኛ ካሰፈረው ጽሑፍ መሐል ወሳኝ ነጥቦቹን ወደ አማርኛ በመቀየር በዚህ መልክ አድርሶናል::
“ትናንትም ለትምህርት እንጂ ሀገር ጥለን አልወጣንም:: የውጭ ሀገር ዜግነትንም ተገደን እንጂ ወደን እንዳልወሰድን ያውቃሉ::…ሚኒሶታም ሆነ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ በተገናኘን ጊዜ ከዚህ በኋላ መኖሪያዬም ሆነ ሞቴ በኦሮሚያና ፊንፊኔ እንዲሆን ነግሬዎት ነበር::… ሀገር ቤት የገባነው ጭቆና ሲመጣ ለመሸሽ አይደለም::…ደስታውንም ሆነ መከራውን አብረን ለመቅመስ ወስነን እንጂ:: ዋሳችን የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ ፓስፖርትም አይደለም:: እግዚአብሔር (ፈጣሪ) እና የኦሮሞ ሕዝብ ነው”
በዋግ ኽምራ 126 ሺኅ ሕዝብ በድርቅ የተነሳ ለከፍተኛ ርሃብ መጋለጡ ታወቀ
በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በተከሰተው ድርቅ 126ሺ ዘጠና ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ። በ2011 ዓ.ም በነበረው ዝቅተኛ ዝናብ ምክንያት ድርቅ በመከሰቱ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ መልካሙ ደስታ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ አስታውቀዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ምንም ዓይነት ዝናብ ያልጣለ ሲሆን፣ ክረምት ዘግይቶ የገባባቸው እንዲሁም የመጠን እና የሥርጭት ጉድለት የታየባቸው አካባቢዎች ለድርቅ እንደተዳረጉ እና ምንም እንኳን የዝናብ እጥረቱ የዋግ ኽምራ አብዛኛው ወረዳዎች ላይ ቢከሰትም በተለየ ሁኔታ ግን ሰሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ እንዲሁም ከፊል ሰቆጣ ዙሪያ ለከፍተኛ ችግር ተከስቷል። ይህን ተከትሎም በዞኑ ከሚገኙ ስድስት መቶ ሺ ነዋሪዎች መካከል 126 ሺ ዘጠና የሚሆን ሰው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
“ዝናብ ባለመጣሉ ችግር የገጠማቸው ወረዳዎች የሰብል ግምገማ ተደርጎ ምላሽ ይሰጣል ከማለት ቀድሞ ለነዚህ ሰዎች መድረስ አለብን፤ አሁን ባለው ሁኔታ 126ሺህ ሰዎች በአፋጣኝ ልንደርስላቸው ይገባል” ሲሉ የተናገሩት አቶ መልካሙ በማኅበረሰቡ መካከል ያለው የመረዳዳት እና ያለውን የመካፈል ባህል እስካሁን ቢያቆየውም መንግሥት በአፋጣኝ ካልደረሰ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ስጋታቸውን አጋርተዋል።
“ድርቅ ረሀብ መሆን አይገባውም” ሲሉም ድርቁ አሁን ካለበት ደረጃ የከፋ ሆኖ ወደ ረሀብ ሳይሸጋገር በፊት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት፤ ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ለክልል እና ለፌደራል መንግሥት ያሳወቁት ከሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ እንደሆነም አልሸሸጉም። መረጃ በወቅቱ ለማጥራት ባለመቻላቸው ሂደቱ ቢዘገይም ክልሉ ጉዳዩን ለፌደራል መንግሥት እንዳሳወቀና ከዛ በኋላ የጨረታ፣ የሎጂስቲክ ችግር ገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም አሁን የከፋ ችግር ውስጥ ያሉት ተለይተው እርዳታ ማጓጓዝ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል።
126ሺህ ለሚሆኑት ሰዎች ከፌደራል የተደረገው እርዳታ ከመንግሥት መጠባበቂያ የተገኘ ሲሆን፤ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ እርዳታ ጎን ለጎን እንደሚሰጥም ይሰጣል የሚሉት ከፍተኛ አመራር ፤ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ወደ አካባቢው ገብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ (የፊታችን እሮብ ጥቅምት 12 ድረስ) ወደማከፋፈል እንደሚሄዱም አረጋግጠዋል።
“አሁን የገጠመን ችግር የመንገድ ነው። እሱን ኀብረተሰቡን በማሰማራት መሠራት ያለበት ሥራ መሠራት አለበት። በዚህ ወር ውስጥ መድረስ ካልተቻለ የሰው ሕይወት ሊያልፍ ይችላል ብለን እንፈራለን” ሲሉም ተደምጠዋል::
እስካሁን የሞተ ሰው ባይኖርም ነገር ግን አፋጣኝ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ በቀጣይ ዐሥር ቀናት መድረስ ባለበት ቦታ ሁሉ መድረስ ይኖርባቸዋል ተብሏል። በዝቋላ ወረዳ በ01 ቀበሌ ነዋሪና የአራት ልጆች አባት አቶ በርሄ እያሱ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከተጎዱ አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው። “ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። ድሮ ዋግ ህምራ ወይም በዝቋላ ወረዳ ችግር ሲከሰት ወደ በለሳ፣ ደንቢያ ወይም ወደ ሱዳንም ይኬድ ነበር። አሁን ግን የተረጋጋ ስላልሆነ አልተቻለም” ሲሉ ዕውነታውን በግልጽ አስቀምጠዋል።
በቀበሌያቸው የክረምት ዝናብ ያገኙት ሐምሌ 29፣ 2011 ዓ.ም መሆኑን፣ ከዚያ በኋላ ግን ዝናብ የሚባል ነገር በቀበሌው እንደሌለና ድርቁ ሰዎችንም ብቻ ሳይሆን እንስሳትን እያጠቃ መሆኑንም አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ። “ኑሮ በጣም ከብዷል። የቀን ስራ እንዳንሰራም የምንሰራው ነገር ግራ አጋብቶናል። በግልም ያው ዕቃ የሚያሸክምም የለም። ያው ከእግዚአብሔር በታች ያለው መንግሥት ነው፤ የሚያደርገንን ለማየት በጉጉት እየጠበቅን ነው” ይላሉ።
ከእርሻቸው ውጭ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ በርሄ “ከተለያዩ ከተሞች ነጋዴ የሚያመጣው ቀይ ማሽላ አለ። ያው እሱን 15፣ 20 ኪሎ በብድር ሸምተን ነው የምንበላው፤ ያው የሰው ሕይወት በረሀብ ማለቅ ስለሌለበት” ይላሉ። የእሳቸው ቀበሌ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ቀበሌዎችም በድርቁ እንደተጠቁና በአካባቢውም ስር የሰደደ ድህነት እንዳለ ይናገራሉ።
ችግሩ የከፋ ከመሆኑ አንፃር ለመንግሥት ማሳወቃቸውን የሚገልፁት አቶ በርሄ “ዞሮ ዞሮ ተረጋጉ ሰው ወደ ስደት እንዳይሄድ አረጋጉት የሚል ነው ምላሽ የተሰጠን፤ ስደትስ ቢሆን የት ይሄዳል? አሁን ግን የተረጋጋ ሁኔታ ስለሌለ ወደየት እንሄዳለን?” በማለት ሕዝቡ በችግርና ግራ መጋባት ውስጥ መውደቁን አስረድተዋል
ሌላው በዝቋላ ወረዳ የሚኖሩት የሰባት ልጆች አባት የሆኑት የ40 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ አደሩ ወልዴም አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚሹ ይናገራሉ። ያጋጠማቸውንም ድርቅ በኢትዮጵያ ለብዙ ሰዎች እልቂት ካደረሰው ከ1977 ረኃብ ያላነሰ ድርቅ ነው ይላሉ።
“ህዝቡ በጣም ተቸግሮ ነው ያለው፤ እንሰሳትም እየሞቱብን ነው ያሉት። አሰቃቂ ሁኔታ ነው የገጠመን “በማለት አክለውም “ሳለ እግዚአብሔር የሞተ ሰው የለም፤ በቀጣይም እርዳታ ካልተደረገ የሰው ህይወት ሊጠፋ ይችላል” በማለት ይናገራሉ።
ከፌደራል መንግሥት ተወክለው የመጡ ሰዎችም በአካባቢው ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ። ከሰሞኑ እንዲሁም የቀበሌ አስተዳዳሪዎች ሲያወያዩዋቸው የነበረ መሆኑን ጠቅሰው “ሕዝቡ በአጠቃላይ የሚበላው የለም። ምን እናድርግ? ምን እንብላ” ብለው እንደጠየቁና ከአደጋና መከላከልና ምግብ ዋስትና መልስ ጠብቁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ወረዳው ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች የብር እርዳታ ቢያደርግላቸውም “ለሌላው ለተቸገረው ህዝብ ምንም አይነት እርዳታ አልደረሰውም” ይላሉ።
በቀድሞው ጊዜ እንዲህ አይነት ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት አርሶ አደሩ ወደሌላ አካባቢዎች ተሰዶ አጠራቅሞ የሚያመጣበት ሁኔታ ነበር አሁን ያ ሁኔታ በመቆሙ ለተደራረበ ችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።
“ቀድሞ ወደ ጎንደር፣ መተማ ይሰድድ ነበር። ባለው አለመረጋጋት ሁኔታ መሰደድ አልቻልንም። አርሶ አደሩ መሔጃ አጥቶ በጣም ተቸግሮ ነው ያለው” ይላሉ
የቀን ስራ በመፈለግም የዕለት ጉርስ ለማግኘትም እየታገሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አቶ መልካሙም በአርሶ አደሮቹ ሃሳብ ይስማማሉ “ከዚህ በኋላ ወር ወይም ሁለት ከዘገየ የከፋ ችግር ሊመጣ ይችላል” ይላሉ።
እንስሳትን በተመለከተ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መኖ በማቅረብና መስኖ ተከትሎ በመዝራት ለእንስሳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ያክላሉ። እንስሳት ወደ አጎራባች ቀበሌና ወረዳ እንዲሄዱ ቢደረግም ሌላ ቦታም እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ስጋት አላቸው። አሁን እየተደረገ ያለው የሰብል ግምገማ ውጤት ከ10 ቀን በኋላ እንደሚታወቅና ይፋ እንደሚደረግም ይገልጻሉ።
ከድርቁ ጋር በተያያዘ በሰዎች እና በእንስሳት ላይም በሽታ ሊከሰት ስለሚችል አስቀድሞ መከላከል አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል። ለእንስሳት መኖ ከመሰጠቱ በፊት ክትባት እንሚሰጣቸውም ይናገራሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዝናብ እጥረት ምክንያት በዞኑ አስቸኳይ ድጋፍ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እታገኘሁ አደመ እንደተናገሩት ድጋፍ የሚያስፈልገውን ህዝብ ችግር መንግሥት ሊፈታው የሚችል ነው ብለዋል።ችግሩን መጠን ለማጥናት የተለያዩ ባለሙያዎች ወደ አካባቢው በማቅናት ጥናት ማድረጉን አስታውቀዋል። በዚህ መሠረትም “የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለሚኖሩ የየዕለት ቀለብ ድጋፍ እንዲቀርብ ጠይቀን እየተጓጓዘ ይገኛል” ብለዋል።
“ከመስከረም ወር ጀምሮ ችግር ይኖራል በሚል እየተሠራ ነው” ያሉት ኮሚሽነሯ “ለ12 ወር የሚሆን ድጋፍ ለመጠየቅ ዕቅድ ተይዟል” ሲሉ ገልጸዋል። የተጠየቀው ድጋፍ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመው የሌሎች ድጋፍ በሚያስፈልግበት ወቅት በተቀናጀ መልኩ በቀጣይ ሊሠራ እንደሚችል አስረድተዋል።
በዞኑ የተሻለ ዝናብ ያገኙ አካባቢዎች በመኖራቸው ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ የሚፈልጉ አለመሆናቸው ታውቋል።
በሙስጠፌ መሐመድ የሚመራው ሶዴፓ አጋር ድርጅቶችን ያቀፈውን ውሕደት አበረታታ
ባለፉት 27 አመታት የበላይነት ይዘው የነበሩ የልዩነትና ጥላቻ ትርክቶችን፣ የብሔር ጽፈኝነትንና አጋር ድርጅቶችን አግላይ አካሄዶችን በሚፈታ መልኩ ኢህአዴግ የጀመራቸውን ለውጦች እንደሚያደንቅ በሙስጠፌ መሐመድ የሚመራው የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ሶዴፓ/ አስታወቀ።
ለውጡን ተከትሎ አምባገነኑና የወያኔ ቀኝ እጅ የነበሩት አብዲ ዒሌ ከሥልጣን ተወግደው አዲስ አስተዳደር የተሾመለት የሶማሌ ክልል መንግሥት (ሶዴፓ)፤ ኢህአዴግ ባለፉት አመታት የነበሩትን ስኬቶች ለማስቀጠል፣ የነበሩትን ስህተቶች ለማረምና አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ እራሱን ለመለወጥና አጋር ድርጅቶችንም ለማቀፍ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ፣ እራስን በራስ ከማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ስርዓትና ከምንከተለው የፌዴራል ስርዓት ጋር የማይቃረን፣ አሃዳዊ ስርዓት የመፍጠር ዓላማ የሌለውና ለሀገራችን ወቅታዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት መሆኑን አምናለሁ ብሏል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ያወጣው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት፤ በሶማሌና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አገራዊውን ለውጥ ለማዳናቀፍ ሌት ተቀን በሚጥሩ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ችግር በህገ-መንግስቱ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሶዴፓ ቁርጠኛ መሆኑን ይፋ አድርጓል።