የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም

በአ/አ ጀሞ አደባባይ የጃዋር ደጋፊዎች መንገድ ዘግተው ጎማ ሲያቃጥሉ ዋሉ

ሞቴም ሆነ ኑሮዬ በኦሮሚያና በፊንፊኔ ነው ያለው የአክቲቪስት ጃዋር ደጋፊዎች ዛሬ ጽንፈኛ ብሔርተኞችና አለቃቸው በሚቋምጥላት አዲስ አበባ ጀሞ አደባባይ አካባቢ ወጥተው ሲረብሹ ታይተዋል::

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ ሁከትና ግርግር ናፋቂ ቄሮዎች ሌሊቱን በሙሉ ሲጠራሩ እና ሲሰባሰቡ ቆይተው ረፋዱ ላይ ጀሞ አካባቢ መንገድ በመዝጋት ለጃዋር የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ በመቃወም ስርዓቱን በአመጽና በብጥብጥ ለመበታተን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል::

አመጸኞቹ ወደ ተለያየ ስፍራ የሚንቀሳቀሰውን ሕዝብ መንገድ በመዝጋት ሠርቶ የመኖር ተፈጥሮአዊ መብቱን ከሠገደባቸው ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች ለጸብ የሚጋብዙ እና አግላይነትን የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበር ወደ ስፍራው የተጓዘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ካደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል::

” ፊንፊኔ ኬኛ ፣ የአዲስ አበባ ወጣት ዱርዬ፣ ነፍጠኛው ገደል ግባ” የሚሉ ግጭት ቀስቃሽ መፈክሮችን በአማርኛና በኦሮምኛ ሲያሰሙ የነበሩት የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች ብዛት ያላቸው ጎማዎችን በማቃጠል አካባቢውን በጭስ ሲያጥኑት አርፍደዋል::

ከአዲስ አበባ ወጣቶች እና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ለመፍጠር ሆን ብለው ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉት ቄሮዎች ቀስ በቀስ ወደ ዋና ከተማዋ ሜክሲኮ አካባቢ ለመጠጋት የነበራቸው ፍላጎት ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የጸጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ በመፍራት አስቀድመው በተሰባሰቡበት ቦታ ሊቀጭ መቻሉን አላስፈላጊውን ረብሻ በቦታው ተገኝቶ ከተከታተለው ሪፖርተራችን ዘገባ መረዳት ችለናል::

በአምቦ ከተማ በተቀሰቀሰው አመጽ አምስት ወጣቶች በጥይት ተመቱ

ዛሬ በአምቦ በተቀሰቀሰው የጃዋር ደጋፊዎች ረብሻና ግጭት አምስት ሰዎች በጥይት መመታታቸውን ለኢትዮጵያ ነገ የደረሰው ዜና ያስረዳል ።

አክቲቪስቱ ድረሱልኝ በሚል ያስተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ ከፍተኛ ደጋፊ እንዳለው በሚነገርለት በአምቦ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ነዋሪዎች አምስት ሰዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ከማገኙ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ደጋፊዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች በድንጋይ እና በፌሮ ከባድ የመፈንከት አደጋ እንደደረሰባቸው መረጃዎቹን በትክክል ከመዘገቡ ታማኝ ምንጮቻችን ለማወቅ ችለናል::

ሌሊቱን በአክቲቪስት ጀዋር መሃመድ መኖሪያ ቤት ተፈጸመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡት የአምቦ ቄሮ ነን ባይ የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች፤ በአምቦ ግጭት መፍጠራቸውን ተከትሎ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን እና ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ ዝግ እንደሆነ ተረጋግጧል::

ለተቃውሞ የወጡትን ሰዎች ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ከተኮሱ በኋላ ተቃዋሚዎች ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወር እንደጀመሩ እና አመጹ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተባባሰ የጠቆሙት የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ፤ ከነዋሪዎች መሀል አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው አምቦ ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል::

በአምቦ የሚገኙ ምንጮቻችን ባደረጉልን ከፍተኛ ትብብር ባገኘነው የአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል ድንገተኛ የሕክምና ክፍል ስልክ ቁጥር ደውለን ባገኘነው መረጃ መሠረት እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በጥይት የተመቱና በተለያዮ የብረት ቁሳቁሶችና በድንጋይ ተመትተው የክፉኛ የቆሰሉ ዘጠኝ ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተገንዝበናል::

በጥይት ከተመቱት መሀል አንዱ ሆዱ ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የተነሳ  የቀዶ ህክምና የተደረገለት ፣ ሁለተኛው ብልቱ ወይም የዘር ፍሬው ላይ ጉዳት ደርሶበት በተመሳሳይ ሲሆን የቀዶ ህክምና ተካሂዶለታል :: ሦስተኛው ግለሰብ ትከሻው አካባቢ ወደ እጁ የሚዘልቅ ከባድ ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን የቀሪዎቹ ግን እንደ ሦስቱ ግለሰቦች ለሕይወታቸው የሚያሰጋ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ከሕክምና ባለሙያዎች መረጃ አግኝተናል::

በዛሬው የጃዋር መሐመድ የፍርሃት ጥሪና አመጽ በአምቦ ከተማ አንድ የፖሊስ መኪና ሙሉ ለሙሉ በቃጠሎ እንደወደመ ፣ ግጭቱን ተከትሎ በከተማው የንግድና ማንኛውም እንቅስቃሴ ከመቆሙ ባሻገር ከከተማዋ ለመውጣትም ሆነ ወደ ከተማዋ ለመግባት የሚያገለግለው መንገድ ሙሉ ለሙሉ መዘጋቱን ሪፖርተራችን በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪውች አስረድተዋል::

ሻሸመኔ ላይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ለተቃውሞ የወጡት ቄሮዎች ባንክ ለመዝረፍ ሞከሩ

በሻሸመኔ ከተማ የጃዋር መሐመድን ጠባቂዎች መነሣትና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግልጽ ተችትና ማስጠንቀቂያ የተንተራሰ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ወደ ስፍራው ስልክ ደውሎ አረጋግጧል።

የተቃውሞ ሰልፉ ከማለዳው ጀምሮ የተካሄደ ሲሆን እስከ ቀኑ አስረ አንድ ሰዓት ድረስ ከተማዋ በኹከት ስትናጥ እና ተቋማት ሲፈራርሱ ውለዋል:: በጀዋር መሃመድ ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ መቆም በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሚያወግዝ ረብሻ ሽብር ሲፈጥሩ የታዮት የጃዋር መሐመድ ጀሌና አምላኪዎች “የኦሮሞ ሕዝብ ብቸኛ መሪ ጃዋር ነው እያላችሁ ጨፍሩ” በማለት የ12 ዓመት ታዳጊ ሕጻናትን በዱላና በሜንጫ ሲያስፈራሩ እንደነበር ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል::

የተቃውሞ ሰልፉ ከሌሊቱ 10፡30 ጀምሮ እንዲካሄድ ስርዓት አልበኛ ቄሮዎች የሰው ቤት በር እና ጣሪያ ላይ ድንጋይ በመወርወር “ውጡ” እያሉ ሕዝቡን ክፉኛ ሲያስጨንቁ ነበር በማለት ያስታወሱት ምንጮቻችን ፤ ወደ ሻሸመኔ የሚያስገቡ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ቢገኙም፤ የተቃውሞ ሰልፉ እስከ ምሽት ድረስ መቀጠሉን በስልክ ለሪፖርተራችን አረጋግጠዋል::

ከዚህ ቀደም ለጃዋር መሐመድ በተደረገ አቀባበል ፕሮግራም ላይ ንጹህ ዜጋ ዘቅዝቀው የሰቀሉትና በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉት ጽንፈኞች ዛሬ ደግሞ በአንዳንድ የከተማዋ ባንኮች አካባቢ ኃይላቸውን በማሰባሰብ የዘረፋ ተግባር ለመፈጸም አቆብቁበው የነበረ ቢሆንም ፌደራል ፖሊስና መከላከያ አስቀድመው ተደራጅተው ጠንካራ ጥበቃ በማድረጋቸው ዕቅዳቸው ግቡን ሳይመታ መቅረቱን ሪፖርተራችን ካሰባሰበው አስተማማኝ መረጃ መገንዘብ ችሏል::

ሕግ አስከባሪ ባለበት ሀገር “ሕገ ወጥ ቄሮዎች “የጃዋር መሐድን መኖሪያ ቤት እየጠበቁ ነው

ላለፉት አስራ ሁለት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ በየቦታው የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን ሲያራምድ የቆየው ጃዋር መሐመድ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት የሚዲያ ማብራሪያ ላይ ተንተርሶ አላስፈላጊ ምለሽ በመስጠቱ መንግሥት መድቦለት የነበረው ጥበቃ እንዲነሳ ተዳርጓል::

ከኦሮሞ ሕዝብ ተሟጋችነቱ ይልቅ ኹከት ናፋቂነቱ ጎልቶ ይታያል የሚባለው ጃዋር መሐመድ በይፋ ያልተሾመ መንግሥት ይመስል የሀገሪቱን ፖለቲካ እሱ በሚፈልገው ቅኝት ውስጥ ሲያሽከረክረው ሰንብቷል:: ከፌደራል መንግሥቱ የጸጥታ ኃይል ይልቅ መንገድ በመዝጋት የሚታወቁትን ቄሮዎች እንደ ሕግ አስከባሪ የፈለጉትን እንዲያደርጉ ጉልበት ሰጪ ቅስቀሳ በማድረግ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ከፈጠረው ሽብርና ካደረሰው ጥቃት ባሻገር የደቡቧ ሃዋሳ ከተማ ድረስ በመጓዝ የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን መብቱን በኃይል እንዲያስከብር በይፋ የአመፅ ጥሪ አቅርቧል::

በተለይም ከኢሬቻ በዓል አከባበር ዋዜማ አንስቶ የኦዴፓ አመራሮችን ጭምር ለዓላማው ማስፈጸሚያ በመጠቀም የፊንፊኔ ኬኛ ፖለቲካን በይፋና ዙሩ በከረረ ፍጥነት ከማስተጋባቱ ባሻገር ሥልጣን ላይ ያሉትን ጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አሕመድና አጋሮቻቸውን በመተቸት የኦሮሞ ብሔረሰብን ጥቅምና መብት ሊያስከብሩ እንደማይችሉ ሲገልጽ መሰንበቱ ይታወሳል::

የኢሕአዴግ ውሕደትና ወደ አንድ ለገራዊ ፓርቲነት መምጣቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ተሰግስገዋል የሚባሉ አንዳንድ አፍቃሪ ኦነግ የሆኑ አክራሪ ብሔርተኛ የኦዴፓ አመራሮችን ቀጥተኛ አዛዥነትና ተሰሚነት እንደሚያሳጣው በመረዳቱ በእጅጉ ሲኮንንና ሲነቅፍ የሰነበተው ጃዋር መሐመድ ታሪካዊው  ቤተመንግሥት የኢትዮጵያን ታሪክ በጠበቀ መልኩ የተገነባው “አንድነት ፓርክ” በሚመረቅበት ዕለት ወደ አርሲ ተጉዞ በአኖሌ ወረዳ የሚገኘውን እና በሐሰተኛ ትርክት በ2005 ዓ.ም የታነጸውን አኖሌ ሐውልት ከሰባት ዓመት በኋላ እንደ አዲስ አስመርቋል::

በዚህን መሠሉ ለውጡን የመቀልበስና የሽብር ተግባር ውስጥ የሰነበተው ጃዋር መሐመድ ከተለያዮ ወገኖች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢገጥመውም እስካሁን ድረስ በመንግሥት ምንም ዓይነት ዕርምጃ ሳይወሰዱበት ቆይቶ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የተመደቡለት ጠባቂዎች እንዲነሱ ተደርጓል::

የጠባቂዎቹን መነሳት ተከትሎ “ሊያስሩኝ ነው፣ ሊገድሉኝ ነው” በሚል በፌስ ቡክ ጃዋር መሐመድ መልዕከት ማስተላለፉን የሰሙ ደጋፊዎቹ ዛሬ ማለዳ ላይ ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱን እንጠብቃለን ያሉ ቄሮዎች መኖሪያ ቤቱ የሚገኝበትን አካባቢ ወረውታል::

መንግሥትና ሕግ አስከባሪ ሕጋዊ ኃይል ባለባት ሀገር አንድ አክቲቪስትን እንጠብቀዋለን በማለት አደባባይ ላይና መኖሪያ ቤቱ አካባቢ የተከማቹት የኦሮሚያ ወጣቶች እየፈጸሙት ያለው ድርጊት ሕገ ወጥ መሆኑን ያውቁት እንደሆነ የጠየቃቸው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተርን አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ከማዋከባቸው ባሻገር “ሕገ ወጦቹ እኛና ጃዋር ሳንሆን የኦዴፓ አመራሮች ናቸው” በማለት ስርዓቱንና መሪዎቹን በይፋ ሲያንጓጥጡ ታይተዋል::

በጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ የሚስተዋሉት ቄሮዎች ጠዋት ላይ እንደፈለጉ ነዋሪውን እና በስፍራው የሚንቀሳቀሰውን ማንኛውም ሰው ሲፈትሹ የተመለከተው ዘጋቢያችን ወጣቶቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ጃዋር መኖሪያ ቤት የሚወስደውን መንገድ ለመዝጋት ሞክረው እንደነበር አስታውሶ ወጣቶቹ በማንአለብኝነት ድርጊቱን ሲፈጽሙ በቦታው የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ አባላት በዝምታ ሲያስተውሉ እንደነበር ትዝብቱን አጋርቷል::

LEAVE A REPLY