ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ባለችው የህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሰሞኑን የተካረረ ዲፕሎማሲያዊ እስጣ እገባ ውስጥ የገቡት የግብጽ እና የኢትዮጵያ መንግስታት የጦርነትን፣የድርድርን እና የገለልተኛ አገርን አማራጭነት እየጠቃቀሱ ይገኛሉ።
ታይምስ ኦፍ እስራኤል የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ “የግብጽ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ይወሰድ” ሲል አንድ አፍቃሪ መንግስት የሆነ የግብጽ ሚዲያ የጦርነት ጥሪ አድርጓል ሲል አስነብቧል።እብደላህ ኤል ሳናዋይ የተባለ ታዋቂ የግብጽ አምደኛ በእለታዊው ኤል ሸሩኩ ጋዜጣ ላይ ባቀረበው የእሁድ እለት መጣጥፉ ላይ “ግብጽ ትንሽ አገር አይደለችም፣ ብቸኛው መፍትሔ በአለም አቀፍ ሸምጋዮች መዳኘት አሊያም የወታደራዊ እርምጃን መጠቀም ብቻ ነው” ሲል ለግብጻዊያን አንባቢዎቹ የክተት ሰራዊት ጥሪ፣ የጥቁር አባይ ዋንኛ ምንጭ ለሆኑት ለኢትዮጵያኖች ደግሞ “የወየውላችሁ!ብታርፉ ይሻላል!” መልእክቱን አስተላልፏል ።
ሌላኛውም ግብጻዊው የቀድሞው የአል መስሪይ አልዬም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ግብጽ ከእስራኤል ጋር እኤአ ከጥቅምት 6-25 1973 ያካሄደችው (የአረቦች እና የእስራኤል ጦርነት )ተብሎ የሚጠራው የስዊዝ ካንል እና ሰናዬ በረሐ ፍጥጫን በማውሳት “ትላንት የሰናይ በረሀን ነጻ ለማድረግ ያካሔድነው ውጊያ ተጠየቃዊ (ሎጂካል) ነበር፣ዛሬም ለውጥ የምናደርገው ፍልሚያ ፍትሐዊ ነው፣ሁለቱም አደጋቸው ተመሳሳይነት አለው፣ ጦርነት የመጨረሻው መፍትሔ ነው” ሲል በ ፌስ ቡክ የወዳጆች መረብ ገጹ ላይ አስነብቧል።
እንደ እነዚህ ታዋቂ የግብጽ የሚዲያ ዘዋሪዎች እይታ ከሆነ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በአምስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እየገነባችው የሚገኘው የህዳሴው ግድብ “ለግብጽ ብሔራዊ ደህንነት አደገኛ በመሆኑ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጽም የግድ ይላታል” የሚል አመለካከትን እያንጸባረቁ ይገኛል።
አሶሴትድ ፕሬስ በቅርቡ ያነጋገራቸው አንድ የግብጽ ባለስልጣን “በኢትዮጵያ ግትር አቋም ተስፋ ቆርጠናል፣ ውጤት በሌለው ድርድር ህይወታችንን አናጠፋም፣ ከዚህ በሁዋላ ሁሉንም አማራጮችን ለመጠቀም ዝግጁ ነን፣ነገር ግን ቅድሚያ ለዲፕሎማሲ እና ለውይይት እድል እንስጠው።” በማለት አስጠንቀው ነበር። ግብጽ ዲፕሎማሲ ላለቸው መንገድ የሩሲያ፣ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የአለም ባንክ ደጆችን እንኳኩታለች። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በኩል በሶስቱ ተደራዳሪ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን) የተጀመረው ድርድር በግብጽ ታክቲካዊ አካሄድ እና የሀያኛው ክፍለ ዘመን አቋም የተነሳ መቋጫ ሳያገኝ የአራተኛ ወገን ሸምጋይነትን ፍለጋ መማሰኑ ብዙም ውጤት አያስገኝም በማለት ተቃውማዋለች።
ማክሰኞ እለት ወደ ሩሲያ ለመጀመሪያው የአፍሪካ እና የሩሲያ የጋራ መድረክ ለስብሰባ ከመሄዳቸው ቀደም ብለው ከተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው” ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከተፈለገ ብቸኛው መፍትሄ ድርድር ብቻ ነው ከዚህ ውጪ ጦርነት ውስጥ እንግባ ከተባለ ሚሊዮኖችን ማስታጠቅ ይችላል፣ አንዱ ሚሳየልን ሲያስወነጭፍ ሌላኛው ወገን ቦምብ ይወረውራል። ጦርነት ለማንኛችንም አይጠቅምም “የማለታቸውን ተከትሎ የግብጽ መንግስት ባወጣው መግለጫው” እኛ ስለ ድርድር እያወራን በዶ/ር አብይ በኩል ስለ ጦርነት መነገሩ እጅግ እስደንግጦናል፣ የተጠቀሙት ቃለት ተገቢ አልነበረም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የግብጹ ፕ/ት አልሲሲ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብን በተመለከተ ቀደም ሲል ካይሮ ላይ ለወጣቶቻቸው በሰጡት ምክር አዘል መልእክታቸው ላይ “ጠንካሮች ካልሆናችሁ ግብዞች ዳቦዎችሁን ይነጥቋችሁዋል ” ማለታቸው አይዘነጋም ሊገባደድ 70% የቀረው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከጅማሮው የካይሮ እና የአዲስ አበባ ገዢዎችን ለዲፕሎማሲያዊ ጦርነት እንደጋበዘ ይገኛል። ምክንያቱም ውሃ ለግብጾች ህይወት እንደመሆኑ ሁሉ ከጨለማ መውጣትም ለአብዛኛው ኢትዮጵያኖች የህይወት ጉዳይ በመሆኑ ነው።