ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ሠፊ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየው ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ ትናንት ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም፣ ከስድስት ዓመት በፊት በተመሰረተበት የ”ፈጠራ ክስ” ጥፋተኛ ተብሎ ለዕሥር ተዳርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት፤ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለሕትመት የምትበቃው “ግዮን”መጽሔት አሣታሚ የሆነው ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ፣ ጥፋተኛ የተባለበት ክስ የተቀነባበረው የሕወሓት መራሹ መንግሥት ቁልፍ ሰው በነበሩት በአቶ በረከት ስምኦን መሆኑ ደግሞ በበርካታ ሙያተኞና ዜጎች ላይ ግርምትን ፈጥሯል፡፡
የወያኔ መንግሥት በ2ሺህ ዓመተ ምህረት አጋማሽ እንዲከስም ባደረገው ፕሬስ ውስጥ ሆነው፣ በከፍተኛ ሁኔታ የሚገዳደሩትን ጥቂት የነፃ ፕሬስ ውጤቶች፤ በዘመቻ መልክ ለማጥፋት ሲንቀሳቀስ፣ በ2006 ዓ.ም ወርሃ ነሀሴ በጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ ማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ለሕትመት ስትበቃ የቆየችው “ዕንቁ” መጽሔት በግፍ ከተዘጉት ስድስት ሚዲያዎች አንዷ ነበረች፡፡
በወቅቱ አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ የነበረው በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት ቡድንና የአቶ በረከት ስምኦን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፤ ሥርዓቱ ከመንግሥታዊ ባህሪይ ወደ ለየለት “የማፍያ ቡድን” በመሸጋገር፣ የተደራጁና የተቧደኑ የሕወሓት ሹማምንት ሀገሪቱን ክፉኛ እየቦጠቦጡ እንደሆነ በድፍረት መግለጻቸው በእጅጉ አስቆጥቶት፤ እራሱ ያፈራረሰውንና ያልተገበረውን ሕገ መንግሥት ተንተርሶ “ሕገ መንግሥቱን በሀይል ለመናድ” በሚል የፈጠራ ክስ፣ ስድስት ሚዲያዎች በሁለት ሣምንታት ውስጥ በሕግ እንደሚጠየቁ የሚገልፅ ዜና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማሰራጨቱ ይታወሳል፡፡
ከፍትህ ሚኒስቴር ተሰጠ የተባለው፣ ግን በቀጥታ “አይነኬ” ሹም ከነበሩት በረከት ስምዖን ቢሮ በቀጥታ እንደወጣ ከቅርብ ምንጮች ‹‹የተረጋገጠው መግለጫ መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡፡ ወትሮም ቢሆን ለነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ርህራሄ የሌለው ሕወሓት መራሹ መንግሥት፣ በትክክል እንዳለው ሚዲያዎቹ ጥፋቱን ፈጽመው ቢሆን ኖሮ ከቤትና ከቢሮአቸው ለቅሞ ማሠር የመጀመሪያ አማራጩ ነበር፡፡
ጋዜጠኞቹ በተሠራጨው መግለጫና በቀጣይ በሚሆነው የፈጠራ ክስ ተደናግጠው ከሀገር እንዲወጡ የሁለት ሣምንት ዕድሜ መስጠት ነበር የተፈለገው፡፡ ከመጀመሪያው ክስ በተጨማሪ ከአገር ውስጥ ገቢ ጋር በተያያዘ ተደራራቢ ሐሰተኛ ክስ መቅረቡ ደግሞ ጋዜጠኞቹ ‹‹ እምቢ ›› ብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢቀሩ እንኳን የሚሠሩበት የሚዲያ ተቋም እንደሚዘጋ የሚጠቁም እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በእነዚህ ሁለት የፈጠራ ክሶች ከሕትመት ውጪ እንድትሆን የተደረገችው የዕንቁ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ በጊዜው የሕወሓትን ውንጀላ ፈርተው አርባ ሁለት ጋዜጠኞች ሀገር ለቀው ወደ ኬንያ ሲሰደዱ፤ እርሱ ግን ‹‹ኢትዮጵያን ለቅቄ የሚያስኬድ ምንም ዓይነት ጥፋት አልሠራሁም፤ የሚመጣውን ነገር ሁሉ በፀጋ እቀበላለሁ” በማለት የቀረ ብቸኛ ጋዜጠኛ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት በ2006 ዓ.ም መጨረሻ ከተዘጉት ስድስት ሚዲያዎች ጋር አብራ በተጨፈለቀችው “ዕንቁ” መጽሔት ስም በ2007 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ክስ የተመሰረተበት፣ የአሁኗ “ግዮን” መጽሔት ባለቤት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ፤ ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጡት አንዳንድ ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን የተመሰረተበት የፈጠራ ክስ እንዲቋረጥ ለተለያዩ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በአካልና በጽሁፍ ቢጠይቅም አንዳችም ምላሽ ሣያገኝ ቆይቷል፡፡
በተለይም በአዴፓና ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የሥራ አስፈፃሚዎች፣ የመንግሥት ሹማምንት በድኅረ – ለውጡ ወቅት የጋዜጠኛው ክስ እንዲነሳ በሚነገራቸው ወቅት፤ እነበረከት ስምዖን ፕሬሱን ለማጥፋት የሄዱበትን ሀሰተኛ መንገድ እንደሚያውቁ በመግለጽ በዚህ ወቅት ይሄ የፈጠራ ክስ እንዴት ሊቋረጥ እንዳልቻለ በግርምት ከመጠየቃቸው ባሻገር፤ ክሱ ውድቅ መሆን አለበት የሚል ዕምነታቸው የፀና መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፁ እንደነበር፣ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ምንጮቹን በመጥቀስ ይናገራል፡፡
በሕወሓት መራሹ መንግሥት በግፍ የታሠሩ፣ በሀሰት የተፈረደባቸው ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ውሳኔው ተሽሮላቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል በቻሉበት ወቅት፤ ፍቃዱ ማ/ወርቅ ላይ በአምባገነኖች የተመሠረተው የፈጠራ ክስ ሳይቋረጥ መቅረቱ፣ አሁንም ድረስ ብዙዎችን ከሚነጋገሩ ባሻገር በፍትህ ስርዓቱ ላይ ብዙዎች ጥለውት የነበረውን ተስፋ እንዲያነሱ የሚያስገድድ በግልፅ የሚታይ ዕውነት ነውም ተብሏል፡፡
ዕንቁ መጽሔት፣ ሐምራዊ መጽሔት እና ሀበሻ ሪቪው የተሰኙ ሦስት የነፃ ፕሬስ ውጤቶች ቀደም ባለው የወያኔ ስርዓት ታግደውበት፣ በደህንነት ኃይሎችና በፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ክትትሎች እየተደረጉበት፣ ክሱን በሀገር ውስጥ ሆኖ ሲከታተል የቆየው ፍቃዱ ማ/ወርቅ ትናንት ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት፣ ጥፋተኛ እንደተባለበሥፍራው የተገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኛው ላይ ብይን ለመስጠት ከአንድ ሳምንት በኋላ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም በችሎቱ እስኪቀርብ ድረስ ታስሮ እንዲቆይ ፍ/ቤቱ መወሰኑን ተከትሎ፤ እስከዛው ድረስ በተለምዶ ጎማ ቁጠባ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በሚገኘው 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ዛሬ ማለዳ ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተጉዞ ዕሥረኛውን ጋዜጠኛ ያነጋገረው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ እንደገለጸው ከሆነ፤ ጋዜጠኛው በተለይም ካለፉት አስራ ስድስት ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ መጠነኛ ቢሆንም፣ የተሻለ የፍትህ ስርዓት ይኖራል ብሎ ከማመኑ አኳያ፤ እንዲሁም ከላይ እስከ ታች ባሉ ባለስልጣናት ክሱ በወያኔ የተፈጠረ የሀሰት ውንጀላ፣ በበረከት ስምዖን ጸሐፊነትና ዳይሬክተርነት ነጻ ፕሬስን ለማቀጨጭ የተዘጋጀ “ፊልም” መሆኑ ከመታወቁ ጋር ተያይዞ፤ እታሠራለሁ የሚል ዕምነት እንዳልነበረው ገልጾ የለውጡ ፍሬ የሆነችው ግዮን መጽሔትን በዚህ የሚጣረስ ዕውነታ ውስጥ ሆኖ ለማሳተም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ለመረዳትችለናል፡፡
በወያኔ የፈጠራ ክስ በዚህ ወቅት ጋዜጠኛው መታሰሩ አግባብ አለመሆኑን ያስታወሱ በሳል የሀገሪቱ ፖለቲከኞች፤ የለውጡ ቡድን ሕወሓት በክፋት ተግባሩ ጥሎት የሄደውን የቤት ሥራበማስፈፀም ታሪካዊ ስህተት ለመሥራት እየተንደረደረ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የተለያዩ የነፃው ፕሬስ አባላት፤በጋዜጠኛ ፍቃዱ ማ/ወርቅ ላይ የተወሰደው እርምጃ አስደንጋጭ የሚሆነው በዚህ ወቅት ጋዜጠኛው በመታሰሩ ሳይሆን፣ ክሱ በቀድሞው አምባገነኑ ስርዓት በፈጠራና ጋዜጠኞችን ከሀገር ለማሰደድ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ክስ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዕርምጃው ወደ ኋላ ተመልሶ የወያኔን ነፃውን ፕሬስ የማቀጨጭ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው የሚሉ ታዋቂ የነፃው ፕሬስ አባላትና የሕግ ባለሙያዎች በፍቃዱ ማ/ወርቅ ዕሥር ዙሪያ የሰጡንን አስተያየት ኢትዮጵያ ነገ በቅርቡ ይዛ ትቀርባለች፡፡