አፍቃሪ ጁዋሮች መደመር መጽሐፍን አቃጠሉ፣ ህይወት ጠፋ… || በታምሩ ገዳ

አፍቃሪ ጁዋሮች መደመር መጽሐፍን አቃጠሉ፣ ህይወት ጠፋ… || በታምሩ ገዳ

የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ባለቤት እና የኦሮሞ ፈርስት አክቲቪስት የሆነው ጁዋር መሐመድ ከመንግስት ይደረግለት የነበረው የጥበቃ እና የፕሮቶኮል አቅርቦት ሊቋረጥ ነው የሚል መረጃ ደርሶኛል በማለት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የለጠፈውን መረጃን ተከትሎ የጅዋር ደጋፊዎች በመዲናይቱ አዲስ አበባ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ መዝጋት፣ የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ የእንደመር መጽሐፍን ማቃጠላቸው፣ የሰዎች ህይወትም መጥፋቱ ተዘገበ።

ተደርጓል በተባለው የስልክ ልውውጥ ላይ በአገሪቱ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ በመምጣቱ ላለፉት አስራ ስድስት ወራት ለፖለቲከኞች እና ለአክቲቪስቶች ከግብር ከፋዩ ህዝብ ኪስ ይወጣ የነበረው የገንዘብ ወጪ ይቋረጣል የሚል ነው ተብሏል።

ምንም እንኳን ለአክቲቪስት ጅዋር የሚደረገው የደህንነት እና የጥበቃ ወጪ በማን ትእዛዝ ፣ከየትኛው መንግስታዊ ካዝና እና እስከመቼ እንደሚዘልቅ በውል ባይታወቅም ከወራት በፊት ወደአገር ቤት የሄዱ አንዳንድ ዲያስፖራ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች “የሆቴል እና የጥበቃ ወጪያችሁ ጊዜው ተጠናቋል “ተብለው በሰላም ሻንጣቸውን ሸንክፈው ዜግነት ወደሰጧቸው አገራት ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ እንደሚገኙ ከቅርብ ምንጮች ለማወቅ ተችላል።

የኬኒያው ዘ ስታር ጋዜጣ ቢቢሲን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በደደር አካባቢ ለጀዋር ድጋፍ ለመስጠት ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች ባለፈው ጥቅምት 11/ 2019 እኤአ የአለም የሰላም ኖቤል ሽልማትን አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ ያሳተሙት እና ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መደመር የተሰኘው መጽሐፍን ወጣቶቹ ከእየስፍራው በመሰብሰብ በአደባባይ ሲያቃጥሉ፣ የዶ/ር አብይ አህመድ ስብእናን ሲያንቋሽሹ፣ በተቃራኒው ለጅዋር መሐመድ ያላቸው ታማኝነትን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

የፖሊስ ኮሚሽነር ጄ/ል እንደው ታሰው ለቪኦኤ በሰጡት አስተያየት” ጁዋር ጥቃት ስለሚደርስብኝ ጥበቃዬ እንዳይስተጓጎልብኝ የሚለው ግምቱ የተሳሳተ ነው። የጥበቃ እና የደህንነት ሽፋናቸው የተነሳባቸው ሰዎች ቀደም ሲል አሉ ፣ወደፊትም ቢሆን እንደ አስፈላጊነቱ የጥበቃ አገልግሎቱ ይነሳል” በማለት ጁዋር የመጀመሪያውም ወይም የመጨረሻው ሰው እንደማይሆን ተናግረዋል።

እንደ ዜና አገልግሎት ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ዶ/ር አብይ አህመድ ከፍተኛ ደጋፊ እና ተቀባይነት አላቸው ተብሎ በሚገመተው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይህንን አይነቱን ተቃውሞ መቀስቀስ እና ማደራጀት በጠ/ሚ/ሩ ተወዳጅነት ላይ አሉታዊ ገጽታ ሊፈጥር ይችላል ሲል ገምቷል።

በአምቦ፣ በአዳማ፣ በጅማ፣በሻሸመኔ፣በምስራቅ ሀረርጌ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች የታየው ተቃውሞ በሰው ህይወት ላይ ከአራት በላይ የሞት፣
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የፌስ ቡክ ተከታይ (ሰራዊት) እንዳለው የሚነገርለት አክቲቪስት ጁዋር መሐመድ ቀደም ሲል ስለአገሪቱ ስላለው አስተዳደር ተጠይቆ ሲመልስ” አገሪቱን እያድተዳደሯት ያሉት የአብይ አስተዳደር እና የቄሮዎዎች አስተዳደር ናቸው “ማለቱ አይዘነጋም።

በአገሪቱ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በረባው ባረባው፣ በሀሰት መረጃ እየተገፋፉ አውራ ጎዳናዎችን መዝጋት፣ በማንነታቸው ብቻ የሰላማዊ ዜጎችን ጉዞ እና ጊዜዎችን የማሰናከል ኃላቀር ታክቲክን የሚዘውሩ ኃይሎች ግድብ እንዲገዙ ያለመደረጉ፣ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጻሚዎችን ህጋዊ ሽፋን ከመስጠት እንደሚቆጠር እንዲሁም አገሪቱንም እና ዜጎችን ወደ ማይወጡት አዘቅት እንዳይከታቸው ስጋቶች አሉ።

LEAVE A REPLY