ኮ/ል ከማል ገልቹ እና ዳውድ ኢብሳ በጃዋር መኖሪያ ቤት መግለጫ ሰጡ
በኦሮሚያ የተለያዮ ከተሞች ውስጥ የተቀሰቀሰው አመጽ እንዳይበርድና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረቡለትን ጥያቄዎች እስኪመልስ ድረስ ረብሻው እንዳይስተጓጎል የሚያነሳሳ መልዕክት ያዘለ መግለጫ አንጋፋዎቹ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በይፋ ሰጥተዋል::
ዛሬ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተዘጋጀውና በኦ ኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ስርጭት አየር ላይ በዋለው ወቅታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳና ኮ/ል ከማል ገልቹን ጨምሮ የተለያዮ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና የብሔሩ ጽንፈኛ ልሂቃኖች ተገኝተዋል::
አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ክፉኛ የኮነነው ጃዋር መሐመድ የለውጡ ቡድን የኦሮሞን ሕዝብ መብት አሳልፎ የሚሰጥ እንጂ የሚያስጠብቅ አይደለም ብሎ ከመተቸቱ ባሻገር የኦሮሞ ወጣቶች እያደረጉት ያለውን አመጽና ሁከት እንደ ትክክለኛ እንቅስቃሴ በመቁጠር አበረታቷል::
ለውጡን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙትና በተከተሉት ጽንፈኛ ፖለቲካ እንቅስቃሴ አማካይነት ከወራት በኋላ ከሓላፊነታቸው የተነሱት ኮ/ል ከማል ገልቹ በየቦታው እየታየ ያለውን የኦሮሞ ወጣቶች ረብሻ በማበረታታት አሁን ላይ በተለያዮ ስፍራዎች እየሞቱ ያሉትን ወጣቶች የሚገድለው የኦሮሞ ሕዝብ ሳይሆን ኦሮምኛ የሚናገሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው በማለት ለሁለት የተከፈለውን የኦሮሞ ሕዝብ ግጭት ሸፋፍነው ለማለፍ ሞክረዋል::
ኦሮሞን ኦሮሞ አይገድልም በሚል ሰበብ የአመጹን አቅጣጫ በመቀየር በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች በሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ መግለጫ የሰጡት የቀድሞው የኦነግ አባልና አመራር ከማል ገልቹ የተቀጣጣለው አመጽ እንዲበርድ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን የሚያሳዮ ተደጋጋሚ አስተያየቶችንም ሲሰጡ ተደምጠዋል::
በተመሳሳይ የኦነግ ሊቀመንበር በሁሉም ረገድ ከጃዋር መሐመድ ጎን መሆናቸውን በመግለጽ ቄሮ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በመግለጽ ለሚደርሰው ውድመትና የሰው ሕይወት መጥፋት መንግሥት ተጠያቂ ነው ሲሉ ተናግረዋል::
ጃዋር መሐመድ የግድያ ሙከራ እንደተካሄደብኝ የሚያሳይ መረጃ ደርሶኛል አለ
ራሱን የኦሮሚያ ሕዝብ መሪ አድርጎ የሾመው ጀዋር መሐመድ ማክሰኞ እኩለ ለሊት ላይ በመኖሪያ ቤቱ ተፈጽሟል ስላለው ጉዳይ እና የኦሮሚያ ከተሞች አመጽ ጉዳይ ከቢቢሲ ጋር መጠነኛ ቆይታ አድርጓል።
“ተኝቼ ነበር፤ በፌደራል ፖሊስ ተመድበውልኝ የነበሩት ጠባቂዎች በአስቸኳይ መሳሪያችሁን ይዛችሁ ውጡ ተባሉ። ይህ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ፤ አንደኛ እኩለ ለሊት ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ ጀዋር ሳይሰማ ውጡ ነው የተባሉት። በዚያ ላይ የሚተኩ ጠባቂዎች የሉም ነበር” በማለት በውድቅት ሌሊት የነበረውን ሁኔታ ያስታወሰው ጀዋር፤ በሁኔታው የተደናገጡት ጠባቂዎች የተፈጠረውን ለእርሱ እንደነገሩትና እሱም በስም የጠቀሳቸውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰብ ጋር ስልክ ቢደውልም፣ “ጌታዬ እኔ ደሃ ነኝ። የተሰጠኝ ትዕዛዝ ልጆቹን አስወጣቸው ነው እንጂ ማን ይተካ? ምን ይሁን የተባለ ነገር የለም” የሚል ምላሽ እንደሰጡት አስታውቋል።
“የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር ስልክ ደወልኩ፣ አያነሱም። ምክትላቸውም ጋር ደወልኩ፤ እሳቸውም ስልክ አያነሱም። ከዚያ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን ጋር ደውዬ ምክትል ኮሚሽነሩ ስልክ እንዲያነሱ አስደረኩ። ምክትል ኮሚሽነሩ ትዕዛዙ ትክክለኛ መሆኑን ሲናገሩ በጣም ተገርምኩ” በማለት ለቢቢሲ የተናገረው ጃዋር መሐመድ
ከዚህ የስልክ ጥሪ በኋላ በሦስት ፓትሮል መኪና ተጨማሪ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል መምጣቱን እና ሁኔታው በእሱ ጠባቂዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን በመፍጠሩና ፍጥጫም ስለነገሠ፣ የተፈጠረውን ውጥረት ሊያረጋጋ የሚችል እና ሓላፊነት የሚወስድ የመንግሥት ባለስልጣን ማግኘት ስላልቻልኩ ይህን ጉዳይ ህዝብ ማወቅ አለበት ብዬ ለማስተዋወቅ ተገድጃለሁ በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ እየሆነ ያለውን ለማሳወቅ የጻፈበትን አጋጠሚም በቆይታው አስረድቷል::
“ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የደህንነት ኃይሎች በአጽንኦት የተናገሩት ‘ብዙ ባላንጣዎች ስላለህ ጥቃት ቢሰነዘርብህ በሃገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ስለዚህ የደህንነት ጥበቃ ሊኖርህ ይገባል’ ነው የተባልኩት።
እኔ ወደ የግል ሴኪዩሪቲ መግባት ፈልጌ ነበር ግን ግዴታ የመንግሥት ጥበቃ ያስፈልግሃል ተባልኩ” በማለት መጀመሪያ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ ጠባቂዎች በመንግሥት የተመደቡለትን ሂደት የሚያስታውሰው አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ፤ “እኔን ማሰር ከተፈለገ በፈለጋቸው ጊዜ ቢጠሩኝ የምገኝላቸው ሰው ነኝ። ‘ና ታሰር’ ቢሉኝ እንኳ ክሱ አሳማኝ እስከሆነ ድረስ እምቢ የምልበት ምክያት የለም።” በማለት በእሱ ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ አጣጥሏል::
“በውድቅት ለሊት በጣም አጣራጣሪ በሆነ መልኩ የተሞከረው ምን እንደሆነ አልገባኝም። የእስርም አይመስለኝም። ከውስጥ እንደምሰማው ሰሞኑን የነበረን ክርክር እየጦፈ ስለመጣ ጥበቃዎችን በማስነሳት እንዲፈራ እና እንዲሸማቀቅ እናደርጋለን’ የሚል የውስጥ ንግግር እንደነበረ፤ ከዚያም በገፋ መልኩ በዱርዬዎች ቤቴ ላይ ጥቃት በማድረስ ለማሳበብ እንደታሰበ ነው ያሉኝ መረጃዎች የሚያሰዩት” የሚለው ጃዋር “በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ወይ አንድ አደገኛ ሴራ አለ ወይም የሚያሳፍር ልፍስፍስነት አለ። ኮሚሽነሩ የተናገረው ነገር ከአንድ ከፍተኛ የደህንነት ሓላፊነት ካለበት የፖሊስ መሪ የማይጠበቅ እና አሳፋሪ ነው። ሴራ ያለበት ኦፕሬሽን ሞክረው ስለከሸፈባቸው ነው። ምንም አልተሞከረም የሚለው ነገር ነጭ ውሸት ነው። ይህም ሊታረም ይገባል” ብሏል::
”ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅርበት ነው የምሰራው። እዚህ አገር የመጣሁት ባለኝ ልምድ እና ዕውቀት ልረዳቸው ነው። ከፖለቲካል ማኔጅመንት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥራን ነው የምሰራው። ችግር በተፈጠረ ቁጥር ይጠይቁኛል ተንቀሳቅሼ አረጋጋለሁ። ከአንዳቸውም ጋር የግል ቁርሾ የለኝም፤ አዎ እተቻለሁ። አሁን ያለው አያያዝ ወደ አህዳዊ ሥርዓት እየተቀየረ ስለሆነ፣ የሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በጣም ያሳሰበኝ ድርጅቶቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ አባላት በፕሮጀክቱ እንደማያምኑ በግል እየገለጹልኝ፤ ነገር ግን ደግሞ ካላቸው ፍራቻ የተነሳ የሚደግፉበት ሂደት ስላለው ይህ መተቸት አለበት።” በማለት ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር ስላለው ግንኙነት አወዛጋቢ የሆነ አስተያየት ሰጥቷል::
“የእኔ ጽሁፍ እና ትችት ትናንት ለተፈጸመው የግድያ ሙከራ የሚጋብዝ አይደለም” የሚለው ጃዋር መሐመድ ትናንት በመኖሪያ ቤቱ ተፈጸመ ስላለው ክስተት፣ እስካሁን ያለው መረጃ የሚጠቁመው በእርሱ ላይ የተደረገ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ ሲል ተደምጧል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለ20 ዓመት ሲሳተፍ እንደቆየ የሚናገረው ጃዋር፤ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅምን እንደገነባ ይናገራል። “እኔ በተለያዩ የዓለም አገራት ፖለቲካን ተምሬና ብዙ ጽሑፍ ጽፌ፤ ወጣቶችን አሰልጥኜ የዚህ ለውጥ ዋና ቀያሽ ሆኜ ስሰራ ነበር” ይላል።
“እውቀቴንና ጉልበቴን ለእዚች አገር ለግሼ መንግሥት ሳይናድ ሃገር ሳይፈርስ ለውጥ እንዲመጣ ረዳሁ። ይህም ተዋቂ እና ተጽእኖ ፈጣሪ እንድሆን ረድቶኛል።” “ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው ሰው ስልጣን አካፍሉኝ ማለት እችል ነበር። እኔ ግን አልፈለኩም። እንደ ግለሰብ በደሎችን ሳይ ግፎችን ሳይ እናገራለሁ እጽፋለሁ። … ለዚች ሃገር በጎ እንጂ መጥፎ አላደረኩም” ሲል ይናገራል።
ጀዋር ለሁሉም ነገር እኔ ተጠያቂ የማድረግ አባዜ በዝቷል ያለ ሲሆን “… ባል እና ሚስት ከተጣሉ ተጠያቂው እኔ፣ ዝናብ ከጠፋ ተጠያቂው እኔ፤ እኔ ዲዛይን ያደረኩትና እኔ እስትራቴጂስት የሆንኩለት ንቅናቄ ጠቅላይ ሚንስትር እንደዛ አይነት ትችቶችን ፓርላማ ፊት ሲያቀርብ በጣም ነው ያሳዘነኝ” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
“ህዝቡ ሊረጋጋ ይገባል። ሰላማዊ ትግል ማድረግ አለበት። በንብረት ላይ ምንም አይነት ጥቃት ማድረስ የለበትም። ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሊተበበር እና ሊስማማ ይገባል” ያለ ሲሆን ጨምሮም “ሰዉ ህገ-መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድምጹን ማሰማቱ ትክክል ነው። መንግሥት እራሱን ከጸብ በመቆጠብ ነገሮችን ተረጋግቶ መፍታቱ ለመንግሥትም ለህዝብም ጠቃሚ ይመስለኛል” ብሏል።
ጃዋር ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ የጸጥታ ጥበቃው የሚመለከተው አካል ከሆነው ከፌደራል ፖሊስ በኩል ምላሽን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።
ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገሪቱ ጉዳይ ለሦስት ቀን ጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ አወጀ
ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ. ም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን የሀገሪቱን ጉዳይ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ለሦስት ቀን የሚቆይ የምሕላና የሰላም ጥሪ አቅርቧል።
በአገሪቷ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሳንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋታቸው እንዳሳሰበው የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ በይፋ ማወጁን ሰምተናል። ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጀምሮ ሁሉም አካላትና ዜጎች በየድርሻው ለአገራዊ ሰላም፣ አንድነት እና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል። ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች “ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች መነሻነት የተከሰቱ ናቸው” ሲልም አስታውቋል።
ከእውነታ የራቁ፣ የሕዝቡን የአንድነት እና የአብሮነት ባህል የሚጎዱ፣ ታሪክን የሚያፋልሱ ሐሰተኛ ትርክቶች ለግጭቶች መንስዔ ናቸው የሚለው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የብዙኃን መገናኛዎች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ምሁራንና የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት ተቆጥበው፤ ለአገራዊ አንድነትና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።
የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት ቀድሞ በመከላከል የሰው ሕይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን በማስቀረት የተጣለባቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ የጠየቀው ሲኖዶሱ፤ “እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን ችግሩ ቀጥሎ በዚህ ሳምንትም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየተከሰተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው” ብሏል::
ችግሩ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በሕብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል በመሆኑም ከሌሎች የመወያያ አጀንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት መወያየቱን ገልጿል።,”$ከውይይቱ በኋላም ባለ አስራ ሁለት ነጥብ የአቋም መግለጫ እና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል::
ማንኛውም የተለየ ሃሳብ ያለው ወገን በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ በውይይት ችግሮችን እንዲፈታ፣ የወደፊት የአገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ አገራቸውንን ከጥፋትና ካልተገባ ድርጊት እዲታደጉ መግለጫው ያስረዳል ።
ልዩ ልዩ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን በመገናኛ ብዙኃን አሊያም በማህበራዊ ሚዲያ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ተንታኞች እና አክቲቪስቶች ከስሜት፣ ከብሔር፣ ከቋንቋና ከኃይማኖት ልዩነት በጸዳ ሁኔታ ለሰላም የበኩላቸውን እንዲያደርጉ፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር ግጭትን ከሚፈጥሩ ነገሮችና ትንኮሳዎች እንዲቆጠቡና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዝቡ በማድረስ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቀው ቅዱስ ሲኖዶስ
ምሁራን ለአገር እድገት ያላቸውን ሚና የሚጠቅሰው መግለጫው አሁን አሁን ግን አንዳንድ ምሁራን የሚያስተላልፏቸው የኢትዮጵያን ታሪክ መሠረት ያላደረጉ ትርክቶች ለግጭትና ላለመግባባት መንስዔ ሲሆኑ እየተስተዋሉ ነው ብሏል::
በሮቤ ከተማ ሦስት ኦርቶዶክሶች የጃዋር ደጋፊ ነን ባሉ ሙስሊሞች ተገደሉ
የሽመልስ አብዲሳ በአደባባይ የሰበኩት የነፍጠኛ ፖለቲካና የሰባሪ ተሰባሪ ትርክት እንዲሁም የጃዋር የጽንፈኝነትና የሃይማኖት አጀንዳ ተጣምሮ ዛሬ በሮቤ ከተማ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ያለአግባብ እየቀጠፈ መሆኑ ተሰማ::
ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን ረፋድ ላይ ለኢትዮጵያ ነገ ከስፍራው የደረሰው የስልክ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ከሆነ ከትናንት በቀጠለው የጃዋር መሐመድ ጥሪ አመጽና ሁከት በከተማዋ የሚኖሩ ከእስልምና ዕምነት ተከታዮች ውጪ የሆኑ ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል:: ከትናንት ማታ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮችንና የአማራ ተወላጆችን ለማጥቃት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መቆየቱን ያመላከቱት የዜና ምንጮች ዛሬ ማለዳ ላይ ግን አጥፊዎቹ ያሰቡትን መተግበር እንደቻሉ ገልጸውልናል::
በሮቤ ከተማ ውስጥ የተቀጣጣለው አመጽ ሽመልስ አብዲሳ ወደአራገቡት የነፍጠኛ ፖለቲካ መሸጋገሩን የነገሩን ምንጮቻችን በር ዘግተው ከተቀመጡ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይች ውስጥ የተለያዮ ሰዎችን ቤት ሰብረው በመግባት በወንዶችና በሴቶች ላይ ከባድ ድብደባ ከመድረሱ ባሻገር ሦስት የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የጃዋር ደጋፊ በሆኑ ሙስሊሞች እየተጎተቱ ወጥተው በአደባባይ ተቀጥቅጠው ተገድለዋል::
በአሁኑ ሰዓት በሮቤ ከተማ የክርስቲያን እና የአማራ ተወላጅ ቤቶች እየተለዮ ምልክት እየተደረገባቸው መሆኑን ለኢትዮጵያ ነገ የገለጹ ነዋሪዎች መንግሥት በቀጣይ ከሚደርሰው ጥፋትና ዕልቂት እንዲታደጋቸው ጥሪ አቅርበዋል::
ዛሬ በባሌ ዶዶላ ከተማ አራት ሰዎች በዱላ ተቀጥቅጠው መሞታቸው ተረጋገጠ
አድማሱን እያሰፋ የሄደውና ከጅምሩ የተሳሳተ ዓላማ ያነገበው የኦሮሚያ ከተሞች አመጽ አቅጣጫውን ወደ ሃይማኖታዊ ግጭትና ጥቃት በመሸጋገሩ የጃዋር መሐመድን የአመጽ ጥሪ ተከትሎ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እየጨመረ መጥቷል::
ትናንት በባሌ ሮቤ እና ዶዶላ ከተሞች የተጀመረው አመጽ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በዶዶላ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ግጭት ቀስቅሶ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል:: ከሟቾቹ በተጨማሪ ቁጥራቸው 20 የሚደርስ የአካባቢው ነዋሪዎች ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲያጋጥማቸው በሕዝብና የመንግሥት ንብረቶች ላይም ከፍተኛ የሆነ ውድመት ደርሷል::
በሮቤና ዶዶላ ከተሞች በትናንትናው ዕለት የተጀመረው የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች አመጽ ከቀትር በኋላ አካሄዱን ቀይሮ ቤተ ክርስቲያናትን የማቃጠልና ካህናትን የማጥቃት ሙከራ የማሳደግ ፍላጎት በመታየቱ በከተሞቹ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች በየቤታቸው በራቸውን ዘግተው በመጸለይ ላይ መሆናቸውን ወደ ሁለቱ ከተሞች ስልክ ደውሎ ነዋሪዎችን ያነጋገረው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አስታውቋል::
ረቡዕ (ትናንት) ምሽት ላይ የተደራጁ የሮቤ ከተማና የዶዶላ ከተማ ሙስሊም ወጣቶች በየመንደሩ በመዘዋወር የክርሰስቲያን ቤቶችን አስከፍተውና ሰብረው በመግባት ጥቃት ለማድረስ ሞክረው የነበረ ቢሆንም የጥቃት ምልክቶቹ በታዩባቸው መንደሮች ውስጥ መከላከያና ፌደራል ፖሊሶች በፍጥነት በመድረሳቸው አክራሪ ሙስሊሞቹና ጽንፈኛ ብሔርተኞቹ ቦታውን ለቀው ለመሠወር ችለዋል::
ዛሬ በቀድሞወረ የባሌ ከተማ በአሁኑ አከላል የምዕራብ አሩሲ አካል በተደረገችው ዶዶላ ከተማ ከትናንቱ በቀጠለ አመጽ አደባባይ ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎችና በጸጥታ ኃይሎች መሀል ግጭት የተከሰተው የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አይወክለንም በሚል መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ብሔርና ሃይማኖት እየተለየ በእሳት እንዲጋዮ በመደረጋቸው እንደሆነ ለሪፖርተራችን አስተያየት ከሰጡ ነዋሪዎች መገንዘብ ችለናል::
ትናንት በዶዶላ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው የከተማዋ አጠቃላይ ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ቢደረግላቸውም ሕይወታቸው ማለፉን ከቤተሰቦቻቸው እንዳረጋገጡ የጠቆሙን የዜና ምንጮች፤ በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች ትናንት ማታ ወደ ሻሸመኔና ሀዋሳ ለተሻለ ሕክምና የተላኩ ሲሆን ከእነዚህ ቁስለኞች መሀል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ስተው እንደሚገኙ ከአስታማሚዎቻቸው በተገኘው ወቅታዊ መረጃ መሠረት ገልጸውልናል።
በተመሳሳይ ዛሬ ማለዳ በዶዶላ በተነሳው ግጭት አራት ሰዎች በዱላ ተደብድበው መሞታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል:: ዛሬ አመጹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሃይማኖት ጥቃት ተቀይሮ በዶዶላ ከተማ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች ዘግናኝ የሆነ ጥቃት ደርሶባቸዋል:: በዱላና ፌሮ እንዲሁም ሚስማር በተሰካበት አጠና ከተደበደቡት በርካታ ሰዎች መሀል አራቱ ሆስፒታል እንደደረሱ ሕይወታቸው ማለፉን በስልክ ወደ ከተማዋ ጤና ቢሮ ደውለን ማረጋገጥ ችለናል::
ዛሬ ለሰዓታት በዘለቀው ረበሻ ሰባት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲቃጠሉ፣ ከብቶች እና ሌሎች ንብረቶችም በስፋት እንደተዘረፉና የንግድ ሱቆች ጭምር በእሳት እንዲጋዮ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ይናገራሉ::
የዛሬው የዶዶላ ከተማ ግጭት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሳይሆን እርስ በእርስ የደረሰ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች በአካባቢው ያለው ችግር ከፖሊስ ቁጥጥር በላይ በመሆኑመከላከያ ገብቶ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ያለው ሁኔታ አስፈሪ በመሆኑ ለሕይወታቸው የሰጉ ሰዎች በአካባቢው በምትገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው አንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በቢሾፍቱ ጃዋርና ደጋፊዎቹን ተቃውመው የወጡ ወጣቶች በፖሊስ ተደበደቡ
ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ከትናንትና የቀጠለው ሰልፍ ዛሬ የተካሄደ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪ ለሁለት የተከፈለ መሆኑን ተከትሎ ፖሊሶች ለጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች ብቻ አደባባይ የመውጣቱን ዕድል ሰጥተው እነርሱን የሚቃወሙ የከተማዋ ነዋሪዎችን እያባረሩ ሲቀጠቅጡና መንገዶችን ሲዘጉ መታየታቸውን ካነጋገርናቸው የደብረ ዘይት ከተማ ነዋሪዎች መረዳት ችለናል::
በቅድሚያ ትናንትን የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ተጻርረው አጀባባይ የወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሚደግፉና ጃዋር መሐመድን ከሚቃወሙት ወጣቶች እንቅስቃሴ ሂደት ጋር በተያያዘ በመጀመሪያውኑም የከተማዋ ፖሊሶች ደስተኛ ባለመሆናቸው ዘግየት ብለው የተሰባሰቡትን የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎችን ማስቆም እየቻሉ ነጻነት በመስጠታቸውግጭት ሊከሰት ችሏል::
በሰልፉ ላይ አንድ ወገንን ነጥሎ የሚቃወሙ መፈክሮች መሰማታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪ ስለታማ ነገሮችና የጦር መሳሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰልፈኞችም በግልጽ ታይተዋል:: በከተማዋ ዛሬ ማለዳ ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ እንደነበር የጠቆሙት የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ትናንት ከባድ ጉዳት ባይደርስም ዛሬ ያለው ሁኔታ መልኩን ቀይሮ ወደ አስጊ ደረጃ እንደደረሰ አስታውቀውናል::
በተለይ ግጭቱ ማየሉን ተከትሎ የቢሾፍቱ ፖሊሶች ጃዋርን ተቃውመው አደባባይ የወጡትን ወጣቶች እያሳደደ በዱላ በመቀጥቀጥ በትኖ ለሁከት የወጡትን ቄሮዎች አደባባይ ላይ ሲጮሁ እንዲውሉ መፍቀዱ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል::
በሌላ በኩልበአዳማ ዛሬ ማለዳ ሰልፍ እና የጦር መሳሪያ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ጠቁመው ከጃዋር መሐመድ ጥበቃዎች መነሳት ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ትናንት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተካሄዱ ሰልፎችን ተከትሎ የዛሬን ሳይጨምር ስምንት ሰዎች እንደሞቱ የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡ ነው።