ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕወሓት ነባር ታጋዮችና ፈለጭ ቆራጮቹ የአባይ ጸሐዬና የስብሓት ነጋ መልዕክተኛና ታዛዥ እንጂ የመወሰን ሥልጣን የላቸውም በሚል የሚታሙት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት፣ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኢሕአዴግ ውሕደትን ድርጅታቸው አጥብቆ እንደሚኮንነው ገልጸዋል::
የትግራይ ክልል መንግሥት የኤርትራ እና የትግራይ ህዝቦች ዝምድና እንዲጠናከር፣ ግንኙነቱ ወደ ንግድና ትብብር እንዲሸጋገር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የጠቆሙት ም/ርዕሰ መስተዳደሩ “የፌደራል መንግሥት ያላደረገውን ነው እያደረግን ያለነው፤ የፌደራል መንግሥት ከሚሰራው ሥራ አንጻር ሲታይ እኛ እልፍ እየሰራን ነው” ካሉ በኋላ ፤ የተዘጉ የድንበር መተላለፊያዎችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ፕሬዝደንቱ በመኪና ነው ወይስ በአውሮፕላን የሚመጡት የሚለው ትተን፤ መንገዱ ሳይከፈት ግን እንዴት ነው የሚመጡት? ብለን እንጠይቅ። እኛ የተዘጋው መንገድ እንዲከፈት እንፈልጋለን፤ መጥተው ለማስተናገድም ዝግጁ ነን። ግን መንገድ ተከፍቶ በመኪና እንጂ በአውሮፕላን እንዲመጡ አንጠብቅም” በማለት የፕሬዝደንት ኢሳይያስን እና የዶ/ር ዐቢይን ወደ መቀለ መምጣት እንደሚደግፉትተናግረዋል::
የክልሉ መንግሥት ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ላለመመለስ የትግራይ ሕዝብ አደጋ ተደቅኖበታል የሚል ሰበብ እያቀረበ ነው የሚል ትችት እያቀረበ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ደብረፂዮን “ህዝቡ ላይ የተጋረጠ የህልውና አደጋ አለ፤ ለዚህ ነው አንድ እንሁን የምንለው። ህዝቡ በህልውናው የመጡበት ስጋቶች አሉ። የህዝብ ደህንነት ካልመልተጠበቀ የመልካም አስተዳደርና የመሬት ጥያቄዎች ትርጉም አይኖራቸውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በማንኛውም ጊዜ የትግራይ ህዝብ ሰለምና ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን፣ ቀደም ሲል ወደ መቀሌ የአየር ማረፊያ መጥተው የነበሩት የፌደራል ፖሊስ የጸረ ሽብር አባላትን ጉዳይ በማንሳት ድርጊቱን ጦርነት እንደታወጀብን ነው የምንቆጥረው በማለት “ቃታችንን ያልሳብነው እኛ እንጂ በእነሱማ ጦርነቱ ታውጆብን ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።
ህወሓት በውህደቱ ላይ የተለየ አቋም እንደሌለውና እንዲተገበር ፍላጎቱ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደብረፂዮን “የአራቱ ድርጅቶች የፖለቲካ ፕሮግራም አንድ አይነት ነበር፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነበር፤ አሁን ግን አንድ አይደለንም። ልዩነታችን አደባባይ ላይ ወጥቷል። ስማቸውን የቀየሩት ድርጅቶችም ፕሮግራማቸውን ለመቀየር አስበው ነበር፤ ከተቀየረው ፕሮግራማቸው ጋር ወደ ሃዋሳ ቢመጡ ኖሮ ያን ጊዜ እንለያይ ነበር” ሲሉ ውህደቱ በድርጅታቸው እንደማይደገፍ የሚያሳይና ከላይ ካነሱት ሀሳብ ጋር እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት ሰጥተዋል። አሁን ያለው ልዩነት የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት መሆኑን የጠቆሙት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር “ህወሓት ሳይሆን ቃሉን ያላከበረው፤ ከሃዋሳው ጉባኤ በኋላ ክዳችሁናል ነው እያልናቸው ያለነው” በማለት ኢህአዴግ ፕሮግራም የመቀየር ፍላጎት ካለው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ነበረበት ይላሉ።
ባለፈው ሳምንት ውስጥጧ ስለተከለከሉት የትግራይ ክልል ሁለት ሰልፎች ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ሰልፍ ይጠቅማል ወይ ካላችሁኝ? በእኔ እምነት አይጠቅምም፤ መዋቅራዊ ጽዳት ላይ ባለንበት ወቅት አይደለም ሰልፍ ወሬም አያስፈልግም። እንዴት ወደፊት እናምራ በሚለው ግን መነጋገር እንፈልጋለን:: መንግሥት በተግባር ሥራ በሚሰራበት ወቅት፤ መንግሥት ላይ ሰልፍ ማካሄድ አስፈላጊ አይደለም” ብለዋል።