የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከለማ መገርሳና ሞፈሪያት ካሚል ጋር ተወያዮ

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ዛሬ ሊወያዩ ቀጠሮ መያዙን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ጉዳይ አስፈፃሚ መላከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሠይፈ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር። ሁለቱ ወገኖች በተያዘው ቀጠሮ መሠረት ተገናኝተው ስለመወያየታቸውና ስለደረሱበት ስምምነት ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ምሽት 12 ሰዓት ድረስ ግን ይፋ የሆነ አንዳችም ነገር የለም::

የተጀመረውን የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተከትሎ የዕምነቱ ተከታዮችና ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ስፍራዎች እየገጠሟቸው ናቸው ባሏቸው ጥቃቶችና ችግሮች ዙሪያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲያናግሯቸው የቤተክርስቲያኗ አባቶች በጠየቁት መሰረት ነው ውይይቱ የተከናወነው።

የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዛሬ አርብ ከሰዓት በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳና ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ከሰዓት በኋላ መነጋገራቸውን ለቤተ ክህነት ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል::

በሁለቱ ቀናት ኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በነበሩት የተቃውሞ ሠልፎች ላይ ክርስትያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት ደርሶባቸዋል ያሉት መላከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ፤ “ተቃውሞው የፌደራል መንግሥቱ ላይ ይምሰል እንጂ ጥቃት የደረሰው በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖችና ቤተ ክርስቲያናት ላይ ነው” በማለት ሀቁን አጋልጠዋል።

ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተሰባሰቡ ከ60 በላይ ሊቃነ ጳጰሳት ለስብሰባ ተቀምጠው የነበሩ ሲሆን በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ አካባቢ፣ ዶዶላ፣ አርሲ ነገሌ፣ ኮፈሌ አካባቢ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን እንደሰሙ ተደናግጠው ከሰዓት በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሲወያዩ መቆየታቸውንም የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች አስታውቀዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁኔታው እጅግ ከማዘናቸው የተነሳ “ስብሰባውን በትነን ወደ ሚመለከተው አካል ሄደን ከልጆቻችን ጋር ሰማዕትነትን እንቀበላለን” እስከማለት እንደደረሱና ትናንት ከሰዓት በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን እንዲሁም ግጭቶቹ በተነሱባቸው አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊት መላኩ ከተነገራቸው በኋላ መረጋጋታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

ግጭቶች በተነሱባቸው አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ጥቃቱን በመሸሽ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ መጠለላቸውን የተናገሩት መላከ ሕይወት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተለየ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት እየደረሰባት በመሆኑ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

“ለቤተክርስትያን የሕግ ከላ እንዲደረግ፣ መንግሥት በእምነታቸው ብቻ የሚሳደዱ ምዕመናን ጉዳይ አሳስቦት የመኖርና የማምለክ መብታቸው እየተገፋ በመሆኑ እንዲያስቆምልን እንጠይቃለን” ያሉት የሃይማኖት አባት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጠብቁ፣ መንግሥት ጥፋተኞች ላይ እርምጃ እንዲወስድና ከለላ እንዲሰጥ እንደሚያሳስቡም ገልጸዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ትናንት ከተጀመረ በኋላ በመሃል በአገሪቱ እያጋጠመ ያለውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ ለቤተክርስቲያኗ ምዕመናንና ለመላው ህዝብ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የጸሎትና የምሕላ ዐዋጅ ማወጁን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ አይዘነጋም::

በተለያዩ ቦታዎች ባለው አለመረጋጋት ሳቢያ መደበኛ ጉባኤውን በማቋረጥ በምዕመናንና በአብያተ ክርስትያናት ላይ ደረሱ በተባሉ “ጉዳቶችና ባሉ ስጋቶች” ላይ በመወያየት መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክር ማምሸቱን ያስታወሱት ምንጮች ፤ ሲኖዶሱ ያቀረበው የሰላም ጥሪ በዋናነት “መስመር እየለቀቀ የመጣውን በምዕመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን የማያባራ ጥፋት ማስቆምን” የሚመለከት እንደሆነም ነግረውናል።

“እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን ችግሩ ቀጥሎ በዚህ ሳምንትም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች እየተከሰተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል::

በኦሮሚያ ከተሞች ዛሬን ጨምሮ የሞቱት ሰዎች 31 መድረሱ ተረጋገጠ

አወዛጋቢው እና ሁከት ናፋቂው አክቲቪስት ጃዋር ሞሐመድ መኖሪያ ቤት አጋጠመ የተባለውን ክስተት እና በፍርሃት ተሸብቦ ያቀረበውን የድረሱልኝ  ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና በአንዳንድ ስፍራዎች ረቡዕ እና ሐሙስ ሲካሄዱ ከቆዩት የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር 31 መድረሱ ተሰማ።

ዛሬ በሐረር፣ ድሬደዋ፣ አዳማ ፣ባሌ፣ አምቦ ፣ ሻሸመኔ እና ቢሾፍቱ ያለው ድባብ ምን እንደሚመስል ወደ ስፍራው ስልክ የደወለው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ እግረ መንገድ በግጭቶቹ የሞቱትን ሰዎች አሃዝ ለመሰብሰብ ሞክሯል:: በዚህም መሠረት እስካሁን ድረስ በመላው ኦሮሚያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 31 መድረሱን አረጋግጧል::

የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎባቸው ሰው ከሞተባቸው አከባቢዎች መካከል አምቦ፣ ድሬዳዋ ዶዶላ እና ባሌ ሮቤ ከተማ በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ዛሬ በአብዛኞቹ ከተሞች መከላከያ ሠራዊት መግባቱን ተከትሎ መጠነኛ የሆነ መረጋጋት እንዳለ ምንጮቻችን ገልጸውልናል:: ቢቢሲ በበኩሉ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 27 እንደደረሰ አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን ከታማኝ የዜና ምንጮቻችን የደረሱ የከሰዓት በኋላ ጥቆማዎች በዶዶላና አምቦ ከተሞች ቆስለው ሕክምና ላይ ከነበሩ ሰዎች መሀል አራት ሰዎች ዛሬ ረፈድ ላይ ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል::

በታማኝ ምንጮቻችን መረጃ መሠረት ረቡዕ በአምቦ ከተማ ከተገደሉት ሦስት ሰዎች በተጨማሪ ሐሙስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ዛሬ በጥይት ከተገደሉት መካከል የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ሞሮዳ ሞሳ የሚባሉ  ሰው አንዱ ሲሆኑ ፤ አቶ ሞረዳ ልጃቸውን ፍለጋ በወጡበት ወቅት ከጸጥታ አስከባሪ ኃይል በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን በቅርብ ርቀት ሆነው ክስተቱን የተመለከቱ ሰዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል::

በአምቦ  ከተማ ደግሞ ሐሙስ ከተገደሉት ሁለት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎቸ በጥይት መመታታቸውን ከደረሰን ዜና ተገንዝበናል።

“14 ሰዎች በጥይት ተመተው እኛ ጋር መጥተዋል። ሁለቱ ህይታቸው አልፏል። 9 ሰዎች ደግሞ ተኝተው እየታከሙ ሲሆን የተቀሩት ቀላል ህክምና ተደርጎላቸው ወደየቤታቸው ተመልሰዋል” በማለት ለቢቢሲ የአምቦ ሆስፒታል ዳይሬክተር ትናንት መናገራቸው እንዳለ ሆኖ፤ ወደ ሆስፒታሉ የሄዱትሰዎች በሙሉ ወንዶች እንደሆኑና ረቡዕ 3፤ ሐሙስ 2 በድምሩ የሟቾች ቁጥር 5 ደርሶ እንደነበር እና ዛሬ ደግሞ አንድ ሰው በተጨማሪ መሞቱን የዜና ምንጮቻችን አስታውቀዋል::

በተያያዘ ዜና ሁለቱ ቀናት በምስራቅ ሐረርጌ በተካሄዱት ሰልፎች የሟቾች ቁጥር ሰባት መድረሱን ወደ ከተማዋ ስልክ ደውሎ መረጃ የሰበሰበው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አረጋግጧል:: በምስራቅ ሐረርጌ በሚገኙ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው እንደነበር እና፤ በሁለት ከተሞች በተፈጠረው ግጭት የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎች ጠቁመዋል::

ስድስቱ ሰዎች የተገደሉት ትናንት ጉሮ ጉቱ በምትባል ከተማ ወደ ብሄር እና ሃይማኖታዊ ጥቃትና ግጭት ነው ያሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች “አንድ ባለሃብት የደህንነት ስጋት ተሰምቶት ሁለት ሰዎችን በጥይት መትቶ  በመግደሉ፣ በመቀጠልም በቂም በቀል ግለሰቡ እና ሁለት የቤተሰብ አባላቱ ሊገደሉ ችለዋል” ሲሉ የአደጋውን መጠን ገልጸው ፤ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት ሲገደል በተመሳሳይ ሁኔታ የቆሰለ ሌላ አንድ ወጣት ደግሞ ዛሬ ሐረር ከተማ ሆስፒታል በሕክምና ላይ ሆኖ ሕይወቱ አልፏል ብለዋል::

በሌላ በኩል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ረቡዕና ሐሙስ በነበሩ ግጭቶች በጠቅላላው 6 ሰዎች መገደላቸውን ታውቋል። ሐሙስ በነበረ ግጭት 4 ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ረቡዕ ደግሞ ሁለት ሰዎች የተገደሉ መሆኑ ይታወሳል:: በከተማው ከጠዋት ጀምሮ የተካሄደው ሰልፍ ከሰዓት በኋላ ግን ይህ ሠልፍ መልኩን በመቀየሩ፤ ለሕይወታቸው የሰጉ ሰዎች በአካባቢው በምትገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው አንደሚገኙም ከደረሰን ዜና መረዳት ይቻላል።

በሐረር ከተማ ረቡዕ 3 ሰዎች መገደላቸውን ከነዋሪዎች ዛሬ ያረጋገጥን ከመሆኑ ባሻገር፤ በድሬዳዋ ከተማም ረቡዕ 1 ሰው የተገደለ ሲሆን ዛሬ ደግሞ 5 ሰዎች እንደተገደሉም ሰምተናል:: የድል ጮራ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አብዱራሃማን አቡበከር ሐሙስ ሰባት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታላቸው እንደመጡ ለመገናኛ ብዙሃን  ሲናገሩ ተሰምቷል::

ለህክምና ከመጡት ሰዎች መካከል 4ቱ ህይወታቸው አልፏል:: ሰዎቹ በጥይት እና በሌሎች ነገሮች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የመጡት አሁንም በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጠናል።

ረቡዕ በአዳማ ከተማ የተከሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ባህርያቸውን በመቀየር በሁለት ጎራ በተከፈሉ ሰዎች መካከል ግጭት ተከስቶ በሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ለጃዋር መሐመድ ድጋፍ ለማሳየት በወጡ ወጣቶች እና እነሱን በሚቃወሙ መካከል ግጭት መፈጠሩ አይዘነጋም::

 በከተማዋ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ዱቄት ፋብሪካ የጥበቃ ሠራተኛ  ለዘረፋ የመጡ የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች ላይ ጥይት ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ መንጋዎች በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖችን እንዳቃጠሉ መረጃውን ያደረሱን የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች፣ ሐሙስ ዕለትም  አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ከ20 በላይ የንግድ ሱቆች በተቃዋሚዎቹ በተፈጸመባቸው ጥቃት በእሳት ተቃጥለው መውደማቸውንም አስታውቀዋል::

መከላከያ ሠራዊት ግጭት ወደ ተከሰተባቸው የኦሮሚያ ከተሞች ገባ

ረቡዕና ሐሙስ ዕለት ከፍተኛ ተቃውሞ ሠልፍ ከተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ተነገረ:: የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡበት ወቅት ችግሮቹ ደረሱበት በተባለው ቦታ ደርሰው እንቅስቃሴውን መቆጣጠር ችለዋል ሲሉ ተደምጠዋል ።

መከላከያ ሠራዊቱ ከተሠማራባቸው ከተሞች መካከል አምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቤ፣ አዳማ፣ ሞጆ እንዲሁም በድሬዳዋ እና ሐረር መሆናቸውም በከፍተኛ አመራሩ ተገልጿል። ሠራዊቱ ወደ ስፍራው የገባው የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት መሆኑን ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ አስታውቀዋል።

እስካሁን በተሰራው ሥራ ተጨማሪ የሰው ህይወት እና ንብረትን ከጥፋት ማትረፍ የተቻለ ቢሆንም፤ መከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ጉዳት ማጋጠሙን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አልሸሸጉም። ሠራዊቱ በእነዚህ አካባቢዎች ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከወጣቶች እና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን እና የተዘጉ መንገዶችንና የንግድ ተቋማትን ማስከፈት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል። የፀጥታ መደፍረስ ያጋጠማቸው አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢዎቹን የማረጋጋቱን ይቀጥላል ብለዋል::

አዲስ አበባ ላይ የመሬት ወረራ በዘመቻ መልክ ተፈጸመ

በአዲስ አበባ በተለያዮ አካባቢዎች የህገ ወጥ መሬት ወረራ በዘመቻ መልክ እየተፈጸመ መሆኑ ተሰማ:: አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች የመሬት ወረራው የተደረገባቸው ክ/ከተሞች ናቸው::

በተለይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የተከሰተው የመሬት ወረራ እጅግ የከፋ መሆኑንም ከነዋሪዎቹ መረዳት ችለናል:: በእነዚህ የተጠቀሱት አራቱም ክፍለ ከተማዎች የመሬት ወረራን ሲፈጽሙ የነበሩት ወጣቶች ለጊዜው በውል ካልታወቁ አካባቢዎች በአይሱዙ ተጭነው የመጡ መሆናቸውን በቦታዎቹ ላይ ተዘዋውሮ ዘገባውን ያጠናቀረው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተራችን ያስረዳል::

ወጣቶቹ መሬት ወረራውን ከፈጸሙ በኋላ ይዘውት በመጡት መጋዝ እና ተጨማሪ የአናጢ ዕቃዎች እንጨት እየቆረጡ ቦታ ሸንሽነው ችካል በማኖር ልክ ፍቃድ እንዳለው  ሲከልሉ ታይተዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉዳዮ ላይ ከጸጥታ አካላት እና ከየክፍለ ከተማው አመራሮች፣ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ጋር በመሬት ወረራው ዙሪያ ባደረገው ግምገማ ድርጊቱ ፖለቲካዊ ዓላማ አለው ከሚል መደምደሚያ ላይ እንደደረሰም ለማወቅ ችለናል::

መሬት ወራሪዎቹን ከአዲስ አበባ ውጭ አደራጅቶ የሚልካቸው እንዳለና አዲስ አበባ ውስጥም የሚያስተባብራቸው ቡድን እንዳለ መስተዳደሩ ቢደርስበትም ይህን የሚያደርጉትን አካላት ከመንገር ግን ተቆጥቧል::

አሁን ባለን መረጃ መሠረት በተጠቀሱት ክፍለ ከተሞች ለአረንጓዴ ስፍራነት የተከለሉ ቦታዎች፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች በሊዝ የተያዙ የግለሰብ ይዞታዎችና የእርሻ ማሳዎች በማንአለብኝነትና በፊንፊኔ ኬኛ አስተሳሰብ መወረራቸውን በቦታው ተገኝተን ለመታዘብ ችለናል::

38 የህወሓት ምልምል ወታደርች ጎንደር ላይ መያዛቸው ተረጋገጠ

በጎንደር ወደ ትግራይ ሲገቡ የነበሩ ሰላሳ ስምንት የህወሓት ምልምል ወታደሮች ጎንደር ላይ እንደተያዙ ተሰማ:: በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም 38 የህወሓት ምልምል ወታደሮች መያዛቸውን የጎንደር ከተማ የጸጥታ ደህንነትና ሠላም ግንባታ ጽ/ ቤት አረጋግጧል::

ምልምል ወታደሮቹ የመከላከያን ኮማንድ ፖስት ሽፋንን በመጠቀም እና በሰሊጥ አጨዳ አሳበው በጎንደር በኩል ወደ ትግራይ ለውትድርና ስልጣን ሊሄዱ ሲሉ የተያዙት በቀበሌ 15 ወጣቶችና የፀጥታ አካላት አማካኝነት እንደሆነም ተረጋግጧል::

ምልምል ወታደሮቹ ሦስት ሲቪል የለበሱ የመከላከያ አባሎች እና አንድ ትግርኛ ተናጋሪ የሆነ የቡድን መሪው  34 ወጣቶችን በመመልመል በድምሩ 38 ሆነው በጉዞ ላይ ሆነው በተያዙበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ብር ተገኝቶባቸዋል:: በተጨማሪም በአንድ ግለሰብ ስም አራት መታወቂያ እና በሌላ አንድ ወጣት እጅ ደግሞ 7 የውጭ ሀገር ሲም ካርዶችን ይዘው መገኘታቸውን ከደረሰን ዜና ለመረዳት ችለናል::

ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 20 የሚደርሰው ወጣቶች  ወደ ጎንደር ያመጣቸውን ሰው እንደማያውቁት የተናገሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለሰሊጥ አጨዳና ለቀን ሥራ ነው ተብለው መምጣታቸውን ተናግረዋል:: ህወሓት ከአጋሮቹ ጋር በመመሳጠር የወታደርና የሰው ሃይል ለማሟላት ምንም የማያውቁትን የምስኪን አርሶ አደር ልጆች በከፍተኛ ዋጋ እየገዛ እንደሆነ የሚያሳዮ መረጃዎች አሉ የሚሉት የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታና ደህንነት ሓላፊዎች በአሁኑ ሰዓት የሰሊጥ አጨዳ ወቅት በማለፉ በዚህ ሰበብ ወጣቶች አይገባም ብለዋል::

ሰሊጥ ልምድ ባለው ገበሬ ነው የሚታጨደው የሚሉት የዜና ምንጮች የተያዙት ልጆች ግን አይደለም ሰሊጥ ሊያጭዱ ሰሊጥ በአይናቸው አይተው አያውቁም፤ ሰሊጥ የቱ ነው ብንላቸው  እንኳን ለይተው ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም ሲሉ ተናግረዋል::

LEAVE A REPLY