የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የተገዳደሉትን የኮሬ ብሔረሰብና የጉጂ ማኅበረሰብን አስታረቁ
በኮሬ ብሔረሰብ እና በጉጂ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በጋሞ ባይራ የሐገር ሽማግሌዎች በባህላዊ ዕርቅ ሥነ ሥርዓት መፈታቱ ተነገረ፡፡
በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረው ግጭት የበርካቶች ሕይወት በመጥፋቱ፣ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተከትሎ የኮሬ ብሔረሰብ የጋሞ ባይራ ሐገር ሽማግሌዎች እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ የሰላም ተምሳሌት የሆኑት ጋሞ ባይራ የሐገር ሽማግሌዎች ፣ የሰላሙን ጥሪ በመቀበል ወደ ግጭት የገቡትን ሁለቱን አካላት ከ6 ጊዜ በላይ ተመላልሶ በማወያየት እና በማደራደር ሰላም እንዲወርድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በዕርቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ሁለቱ አካላት ዳግም ወደ ግጭት እንዲገቡ የሚቀሰቅሱ አካላት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡
የጋሞ ባይራ የሀገር ሽማግሌዎች ረዥም እና አድካሚ የሆነ ጉዞን በተደጋጋሚ በማድረግ በኮሬ ብሔረሰብ እና በጉጂ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በማርገብ ሰላም እንዲሰፍን በማድረጋቸው ክብር ይገባቸዋል ሲሉ በዕርቁ ላይ የታደሙ የተለያዮ ወገኖች ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የሐገር ሽማግሌዎችም የጋሞ አባቶችን ፈለግ በመከተል በየአካባቢው የተፈጠሩ ችግሮች እንዲረግቡ የማድረግ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባም ሀሳብ ቀርቧል፡፡
በሰላም ማውረጃው የዕርቅ ፕሮግራም ላይ የጮዬ፣ የጋንታ፣ የሻራ፣ የዚጊቲ ባህላዊ መሪዎች/ካዎዎች/ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአባገዳዎች መማክርት ፕሬዚደንት እና የመንግሥት የሥራ አመራሮች መገኘታቸውን የዞኑ የህዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል::
በሁከቱ የተሳተፉ አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል ኢሰመጉ አሳሰበ
ሠሞኑን በኦሮሚያ የተለያዮ ከተሞች በተከሰተው ሁከት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመጉ) አሳሳበ።
ኮሚሽኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እና ተሃድሶ ዕርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስገኘው ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት መሆኑን አረጋግጧል።
በዋናነት ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰው ሁከት የተሞላ ነውጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን ጠቁሞ ግጭቱ የህግ የበላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ላይ የጣለ ክስተት መሆኑን አስታውቋል።
በዚህ ችግር ምክንያት እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 – 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና ከዚህ ውስጥ 10 ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ያመላከተው በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች በሁከቱ በተሳተፉ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ፣ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል ሲል ዕውነታውን አጋልጧል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው ፣ በሚሊየኖች የሚገመት የግለሰቦች፣ የሕዝብና የሃገር ንብረት መወደሙንም በመረጃ ላይ የተመሠረተው የኮሚሽኑ መግለጫ ያስረዳል።
የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት መዳረጋቸውን ያረጋገጠው የተቋሙ ጠንከር ያለ መግለጫአሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቅሬታ ወይም ጥያቄ ፣ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩንም አመላክቷል።
ድርጊቱ እና ያስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የሃገር ሰላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ማስከተሉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲልም አሳስቧል።
የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን፣ መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ሓላፊነት እና ግዴታ እንዳለባቸው ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ እንደሆነና ይህ የመንግስት ሓላፊነት እና ተግባር በሕጋዊ ሥርዓት ሊተገበር ይገባልም ሲልም አስጠንቅቋል።ኅብረተሰቡ ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ በመተባበር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ኮሚሽኑ ጥያቄ አቅርቧል።
በርካታ ሰዎች በተገደሉባት ሐረሪ ዶ/ር ዐቢይና ለማ መገርሳ እየመከሩ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ ከሐረሪ ክልል እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሐረሪ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ ፣ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና አቶ ለማ መገርሳ ከኅብረተሰቡ ለተነሳላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የሰላም ኮንፈረንስ በሀረሪ ከተማ በሚገኘው ጨለንቆ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በዛሬው ዕለት መካሄዱ ታውቋል፡፡
ሠሞኑን የጃዋር መሐመድን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ በተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች በተነሳው ግጭት በድሬደዋና በሐረር በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹን ዋቢ በማድረግ ኢትዮጵያ ነገ ከሁለት ቀን በፊት መዘገቡ ይታወሳል::
አብዲ ዒሌ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ዒሌ) ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ ማድረጉ ታወቀ። ተከሳሹ አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈፀሙና ጥፋተኛም እንዳልሆኑ አብራርተዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ የያዘው አቶ አብዲ ዒሌ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት እንደመሆኑ ፤ ፍርድ ቤቱ አቶ አብዲ ዒሌ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የዕምነት ክሕደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። ተከሳሹም የቀረበባቸውን ክስ “አልፈፀምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል።
“በክልሉ በተፈጸመው የቤተክርስቲያን ቃጠሎ እጄ የለበትም፤ በወቅቱ ከሶማሌ ብሔር ውጭ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ከክልሉ እንዲወጡ በማድረግ ረገድም አስተዋጽኦ የለኝም” ካሉ በኋላ ፤ ” ከቀረበው ክስ ውስጥ ሕገ-መንግሥቱ እንዲፈርስ አድርገሃል ተብሎ የቀረበብኝ ክስም እኔን አይመለከትም ፤ሕገመንግስቱን ሳስፈጽም ነው የኖርኩት ” ሲሉ ተደምጠዋል።
“400 የክልሉን ወጣቶች አስታጥቀሃል ተብሎ የቀረበብኝ ክስ መሰረተ ቢስ ነው፤ እኔን የሚመለከት አይደለም ” በማለትምተናግረዋል።
ክልሉን ለ10 ዓመታት በመሩበት ወቅት ሌሎች ብሔረሰቦች ፣በተለይም የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ይደርስባቸው የነበረ በደል እንዲቀር ሢሠሩ መቆየታቸውን የጠቆሙት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ፤ በእነዚህ ዓመታት በክልሉ የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንለፍርድ ቤቱ በንባብ አሰምተዋል።
በሀገሪቱ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን እየታየ ባለው የፖለቲካ ችግር በሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የመፈናቀልና ሌሎች ችግሮች እየተከሰቱ እኔ ብቻ ተጠያቂ መሆን የለብኝም አቋማቸውንም አሰምተዋል::
በዚህ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው 47 ሰዎች ሲሆኑ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት 16 ብቻ መሆናቸው፣ በዕስር ላይ ያሉ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት የሚጋፋ ነውሲሉም ጠበቆቻቸው ተከራክረዋል። ፖሊስ በተደጋጋሚ ተከሳሾችን በአድራሻቸው አላገኝሁም በማለት የሚያቀርበው ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነና ካልተቻለ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች ጉዳይ ተለይቶ እንዲታይም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ከዋሉ 15 ወራት መቆጠሩን በመገንዘብ በዚህ መዝግብ ተከሰው በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው ሰባት ሰዎች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ወስኗል።
በዚህ መዝግብ የተከሰሱ ሌሎች 10 ሰዎችን ፖሊስ በተደጋጋሚ ፈልጎ እንዲያቀረብ ትዕዛዝ ሲሰጥ የቆየው ፍርድ ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ ተከሳሾቹን በአድራሻቸው ፈልጎ እንዲያመጣ ዛሬም በተመሳሳይ ትዕዛዝ ሲሰጥ በችሎቱ ታዝበናል።
በሊቢያ የሽንት ቤት ውሃ ሲጠጡ የሰነበቱት፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከማጎሪያው ወጡ
ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በሊቢያ መንግሥት ይዞታ ስር ካለው የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል መውጣታቸው ተሰማ። ከስደተኞቹ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ናቸው ተብሏል።
በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ ከሚገኘው የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ለመውጣት የተገደዱበት ዋነኛው ምክንያት በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው እና ከሽንት ቤት ውሃ ለመጠጣት በመገደዳቸው መሆኑም ታውቋል።
ስደተኞቹ ለአንድ ዓመት ያህል በቂ ምግብ እና ውሃ ያላገኙ በመሆኑ ጉዳዮን ለሓላፊዎቹ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ::በትናንትናው ዕለትም ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም የማጎሪያው ጠባቂዎች “ከፈለጋችሁ መውጣት ትችላላችሁ ” ብለው በሩን እንደከፈቱላቸው ስደተኞቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል::
ቄስ ዮውሃንስ ጎበዛይና ተክለብርሃን ተክሉ በስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ለዓመት ያህል እንደቆዩና ስደተኞቹ በምግብ እጦት፣ በርሃብ ከመሰቃየታቸው ባሻገር በበሽታ ሲጠቁ መመልከታቸውን አስረድተዋል።
“ባለፉት ሳምንታት የሚጠጣ ውሃ አልነበረም እናም ከሽንት ቤት ውሃ እየጠጣን ነበር” ያሉትት ቄስ ዮሃንስ የታመሙ ሰዎችንም ከስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ተሸክመው ለሦስት ሰዓታት ያህል በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ትሪፖሊ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ማዕከል መድረሳቸውን አስታውቀዋል::
ሠላሟን ባጣችው ሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት ቢሮም ስደተኞቹ ማዕከላቸው መድረሳቸውን አረጋግጧል።በደቡባዊ ትሪፖሊ የሚገኘው የአቡ ሳሊም የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ከስምንት መቶ በላይ ስደተኞች ተጠልለውበታል ተብሎ ይታመናል።
በሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት እነዚህ የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከላት ለስደተኞቹ በቂ ባለመሆናቸው እንዲዘጉም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል::
በአዳማ እና በጅማ ከተሞች ሽመልስ አብዲሳና አደነች አበቤ ከሕዝብ ጋር ተወያዮ
የኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬ ለቀናት በአስፈሪ ግጭት ውስጥ በሰነበተችው አዳማ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ እያካሄዱ ነው። በኮንፈረንሱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳና ከበርካታየኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ካሉ ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳታፊ የሆኑበት የሰላም ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ በተመሳሳይ መልኩ በመካሄድ ላይ መሆኑን ሰምተናል። በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ ከጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦራ ዞን እና ባሌ ሮቤ ከተማ የተውጣጡ ከ1 ሺህ 600 የሚልቁ ነዋሪዎች፣ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች ጋር በመምከር ላይ ናቸው ተብሏል።
በውይይቱ ላይ የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንደተናገሩት በጥፋት ድርጊቶች ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን ያረጋገጣል።
ባሌ ሮቤ ላይ በተደረገው ውይይት የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ሰሞኑን የተፈጸመው ድርጊት ህብረተሰቡን አይወክልም ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ዋጋ መክፈል እንደማያስፈልግ የጠቀሱት ሚኒስትሯ ችግሮች ሲከሰቱ መመካከርና መደማመጥ አስፈላጊ ነው ሲሉ አስረድተዋል:: ውይይቱ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የታየውን የሰላም ዕጦት ችግር ከመሰረቱ ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል::
በአዲስ አበባ ተለይተው የተመረጡ መንገዶች ብቻ ጥገና እየተደረገላቸው ነው
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በአገልግሎት ቆይታ እና በሌሎች ምክንያቶች ለተጎዱ መንገዶች ጥገና እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
መ/ቤቱ በአገልግሎት ብዛት እና በክረምት ወራት በተፈጠረ ከባድ ዝናብ፣ እንዲሁም በከባድ ተሽከርካሪዎች ጫና ለተጎዱ መንገዶች ነው የመልሶ ግንባታ እና ቀላል የጥገና ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው።
ከላይ በተጠቀሱት የዕድሳት ነጥቦች መሠረት ከ4 ኪሎ እስከፒያሳ፣ ከመሳለሚያ እስከ ኮካ ኮላ፣ ከፒያሳ ከሊፋ ህንጻአካባቢ፣ ከእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን እስከ ሜታ ቢራ፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል እስከ አንበሳ ጋራዥ፣ ከጀርመን አደባባይ እስከ ቃሊቲ አደባባይ፣ ከእስጢፋኖስ እስከ ቦሌ መንገድ፣ ከራጉኤል ቤተክርስቲያን እስከ አቤት ሆስፒታል እና ቦሌ ሳይ ኬክ አካባቢ ባሉ መንገዶች የጥገና ሥራው በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ባለስልጣኑ የተጎዳ አስፓልትን በሚፈለገው ጥልቀትና መጠን ቆርጦ ማንሳት በሚያስችል አዲስ የሚሊንግ ማሽን በመታገዝ ጥገናውን እያከናወነ ነው ተብሎለታል:: በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም ከ75 ኪሎ ሜትር በላይ የግንባታና ጥገና ሥራዎች ያከናወነ አከናውኗል:: በቀጣይም 807 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል።
የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ “ፋውንዴሽን” በኢትዮጵያ ተቋቋመ
በኢትዮጵያ ቅርሶችን መጠበቅና መንከባከብን ዓላማው ያደረገ “ሂውማን ኦሪጂን ሙዚየም ፋውንዴሽን” የተሰኘየበጎ አድራጎት ድርጅት በይፋ ተመሠረተ። ፋውንዴሽኑ በሲቪል ማህበራት ኤጀንሲ ዛሬ ዕውቅና እና ፍቃድ አግኝቷል።
ሃገራችን የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ በዘመናት ሂደት ያፈራቻቸውን ቅርሶች ለመጠበቅና ለመንከባከብ፣እንዲሁም በሙዚየም ልማት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ፋውንደሽኑ መቋቋሙ አስፈላጊ ሆኗል።
የፋውንዴሽኑ መቋቋም በኢትዮጵያ ያሉትን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
“ሂውማን ኦሪጂን ሙዚየም ፋውንዴሽን” ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፥ ከመንግሥት ጋር በመተባበር በሙዚየም ልማት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ይሠራል። በሙዚየም ግንባታ፣ ቅርሶችን በማደራጀት፣ የዕውቀት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎችን ያከናውናልም ተብሏል።
በፋውንዴሽኑ ምስረታ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የፋውንዴሽኑ መቋቋም የአገሪቱን የቅርስ ሀብት በማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ ያአልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ህብረተሰብም የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል::ፕሬዝዳንቷ የፋውንዴሽኑ የበላይ ጠባቂ በመሆንም ተሰይመዋል።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒሰትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ የፋውንዴሽኑ መመስረት የአገሪቱ የቱሪዝም ሀብቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ እገዛ ያደርጋል ከማለታቸው በተጨማሪ ፤ ቅርሶች ለተመልካቾች ክፍት እንዲሆኑ በማድረግ የቱሪዝም ልማት እድገቱ እንዲፋጠን በማድረግም ጉልህ ሚና ማበርከት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
የፋውንዴሽኑ ምስረታ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሙዚየሞች እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ ከማድረግ በተጨማሪ የፖሊሲ ሃሳቦችን በማመንጨት ለመንግስት የማቅረብ ሚና እንደሚኖረውና ፋውንዴሽኑ አራት መስራች አባላት፣ እንዲሁምከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ 13 የቦርድ አባላትን እንደያዘ በምስረታ ፕሮግራሙ ላይ ሰምተናል።