28 የአገሬን ልጆች ገድሏል || ቴዎድሮስ ዳኘ (ቴዲ ደነቀ)

28 የአገሬን ልጆች ገድሏል || ቴዎድሮስ ዳኘ (ቴዲ ደነቀ)

ይህ የአይ ሲስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ በአሜሪካ ኃይሎች ከተደበቀበት ተገኝቶ የተገደለው (ሊያዝ ሲል ራሱን ያጠፋው) በዚህ ሳምንት ነው። ይህ ሰው፣ ከሌላው ሁሉ ወንጀሉ፣ 28 የአገሬን ልጆች ገድሏል። አንገታቸውን ቀልቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል።

በዚያ ድንጋጤ አዝነው የሞቱ ቤተሰቦቻቸውንም ገድሏል። ለጊዜው ቢተነፍሱም፣ የገዛ ልጆቻቸው አንገት በቀጥታ እየታየ ሲቆረጥ ያዩ ወላጆች በውስጣቸው ሞተዋል፣ ያዘነው ህዝብ፣ ዕንባ የተራጨው ህዝብ በመንፈሱ በወቅቱ ሞቷል።

እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ወገኖቻችንን አንገት ቆርጦ በመግደሉ፣ በመጨረሻ፣ እንደተባለው እያለቀሰ፣ እየጮኸ፣ የአሜሪካ የሰለጠኑ ውሾች እያሯሯጡት የሞት ሞት ሞቷል።

ለሟቾች ፍትህ ተገኝቷል።

እነዚያ ወገኖቻችን በስደት፣ በበረሃ፣ ያልፍልናል ብለው፣ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ሄደው፣ የሰሜኑ ከደቡብ፣ የደቡቡ ከም ዕራብ፣ የምዕራቡ ከምስራቅ፣ የምስራቁ ከመሃል አገር ተያይዘው ደማቸው በአንድ ፈሰሰ። አንድ ዓይነት ደም ፈስሶ አንድ ዓይነት እንባ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲፈስ አደረገ።

ዛሬም ግን አቡበከር አልባግዳዲ መልኩን ቀይሮ መሃል አገር አለ፣ ወገን ተዘቅዝቆ ሲሰቀል አይተናል፣ ወገን በድንጋይ ተደብድቦ ሲገደል አይተናል።

አቡበከር አልባግዳዲ ያን ሁሉ ሰው አንገት ሲያስቆርጥ እያዘዘ ነበር፣ እሱ ግን ምናልባትም በሰላም ከአንድ የተደላደለ ቦታ ተቀምጦም ይሆናል። በሺ የሚቆጠሩት ተከታዮቹ ሲሞቱ፣ እሱ ራሱን ደብቆ ለጊዜው አተረፈ እንጂ አልታደጋቸውም። እንደ እውነተኛ መሪ ከፊት ሆኖ ቀድሜ ልሙት አላላም። መጨረሻ ላይም አምልጦ በሰላም ለመኖር መውጫ ቀዳዳ ሲፈልግ ነው የተገደለው።

ዛሬም ጃስ የሚሉ ሁሉ ቀድመው የሚያድኑት የራሳቸውን ነፍስ ነው። ፈሪ መሆናቸውን መርሳት አያስፈልግም። ዙሪያዬን በመሳሪያ ካልተከበብኩ፣ ጠባቂዎቼ ሊነኩብኝ ነው እሪ ያሉት ፍርሃት ስላለባቸው ነው፣ አንድ ነገር ጫር አድርገው ወደዋናው መኖሪያቸው ፈጠን ብለው “ነገር እስኪሰክን” የሚሮጡት ፍርሃት ስላለባቸው ነው፣ “ተከበብኩ፣ ድረሱልኝ ኡ ኡ” የሚሉት ፍርሃት ስለወጠራቸው ነው። ዱላቸው ሁሉ የፈሪ ዱላ የሆነውም ለዚህ ነው።

ፈሪ ደግሞ፣ ሽጉጥ ተተኮሰ ብሎ፣ ካለው ኒውክሊየር ከመተኮስ አይመለስም። ሶሪያና ኢራቅን ከፍሎ የራሱን “ካላፌት” የመሰረተው፣ መሬት ውስጥ እንደሽለምጥማጥ ቆፍሮ ምሽግ ውስጥ የተደበቀው፣ አንድ ሰሞን ዓለምን ሁሉ በፈሪ ዱላው ያስደነገጠው አል ባግዳዲ ውሻ አሯሩጦ፣ አስለቅሶ፣ አስጩሆ ራሱን አፈንድቶ እንዲሞት አድርጓል።

ሲጀመር አልባግዳዲ ጥሩ ተናጋሪ ነበር፣ የሰዎችን አዕምሮ አፍዝዞ፣ ከድንጋይ ጋር ተላተሙ ቢላቸው የሚላተሙ፣ ከ20ኛ ፎቅ ዝለሉ ቢላቸው የሜዘሉ ተከታዮች አፍርቷል። ግደሉ፣ አንገት ቁረጡ፣ የእርጉዝ ሆድ ቅደዱ ቢላቸው፣ ህጻን ልጅ ሰዉ ቢላቸው ምንም የማያወላውሉ ተክታዮች ነበሩት፣ “የምታገለው ለናንተ ነው” ስላላቸው ብቻ አምነውት፣ ከአውሮፓና አሜሪካ ጭምር የናጠጠ ኑሯቸውን፣ የሞቀ ቤታቸውን፣ ትዳራቸውን ትተው የተከተሉት ሰው ነበር፣ ለ እስልምና ነው የምታገለው እያለ ከገደላቸው ግማሽ የሚሆኑት ግን ሙስሊሞች ነበሩ፣ አይ ሲስ በፈንጂ ያጋየው መስጊድ ብዛት የትየሊሌ ነው። ብዙዎቹን በአፉ አደንዝዟል። ነገር ግን ሁሉን ለሞት ዳርጎ ራሱን ለማዳን ሲል ድንገት ውሻ አሯሩጦ የገደለው ፈሪ ነበር።

የአልባግዳዲ መንፈስ ዛሬም መሃከላችን ግን አለ። ማሳመን የሚችል፣ ማሞኘት የሚችል፣ “ለናንተ ብዬ ነው” እያለ የሚያማልል፣ ነገር ግን ለራሱ እንጂ ለማንም ያልሆነ፣ ግደል፣ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ አቃጥል፣ አማኙን ግደል፣ እርጉዝ ሆስፒታል፣ ገበሬ ገበያ፣ ልጅ ትምህርት ቤት እንዳይሄድ፣ ምግብና መድሃኒት እንዳያልፍ መንገድ ዝጋ፣ … የሚል መንፈስ ሁሉ የአልባግዳዲ መንፈስ ነው።

ይህ መንፈስ በጸበል የማይፈወስ፣ በዱአ የማይመለስ ነውና፣ መንግስት ዜጋውን መጠበቅ፣ መከላከል አለበት። ዝም ስለተባለ ብቻ ከሚሰራው ወንጀል የበለጠ በህግ ቢጠየቅ የሚሰራው ወንጀል የከፋ አይሆንም። እናም ከዚህ የበለጠ ምንም አይመጣም። ይልቁኑ ካንሰሩ በመላው አካል ተሰራጭቶ ይዞ ከመጥፋቱ በፊት፣ መነቀል ይኖርበታል።

በዚህ ጊዜ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት አጥፊዎቹን ያለማመንታት ለህግ እንዲያቀርቡ መገፋፋት፣ ያንን ሲያደርጉም ከጎናቸው እንደምንሆን ማሳየት /do something and we are behind you/ ማለት ይኖርብናል።

LEAVE A REPLY