ሰላምና ደኅንነት በኢትዮጵያ || ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሰላምና ደኅንነት በኢትዮጵያ || ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

በቅድሚያ አንድ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ኤክስፐርት የሆኑ በተናገሩት እንጀምር፤

“በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ የእርስበርስ ጦርነት በተለይም የጅምላ ጭፍጨፋ ሊካሄድ እየተጠነሰሰ ነው፤ … የእርስበርስ ጦርነት በኢትዮጵያ ከተጀመረ በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ዕልቂት የሚያስከትል ይሆናል፤ … የዐባይ ወንዝ ለግብጽና ሱዳን የህይወታቸው ጉዳይ ስለሆነ በኢትዮጵያ የሚከሰተው አለመረጋጋት በጣም ስለሚመለከታቸው እነዚህን አገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጉዳዮቹ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ይገደዳሉ፤ የከሸፉ መንግሥታት ተብለው ከሚታወቁት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ፣ ከቀይ ባሕር ባሻገር ደግሞ የመን እንዲሁም ሱዳንና ኤርትራን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዓለማችን እስካሁን ዓይታው የማታውቀው ዓይነት የተወሳሰበ የደኅንነት ዞን ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ስለ ሰላም እንጸልያለን…”

ከሃያ ሰባት የግፍ፣ የሰቆቃና የመከራ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሊክደው የማይችል ለውጥ ተከስቷል፤ ሆኖም ግን ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ያህል ሲዘራ የነበረው የዘር ፖለቲካና መንግሥታዊ አወቃቀር አገራችንን ከአንድ ጽንፍ ወደሌላ እያላጋት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ መፈናቀል፤ በሺዎች የሚቆጠሩቱን ደግሞ ለጉዳት፣ ለሞትና ለእንግልት ዳርጓቸዋል። ይህም ለውጡ በተፈለገበት ፍጥነት እንዳይሄድ የገታ ብቻ ሳይሆን አገሪቷን ለከፋ የእርስበርስ ዕልቂት እያዘጋጃት ያለ ይመስላል።

በተለይ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከተወከሉበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ የሚሰማው አክራሪ ብሔረተኛነት በብዙዎች ዘንድ “የኦሮሞ ተረኝነት” ተብሎ እንዲጠራ እያደረገው መጥቷል። በዘመነ ህወሓት የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ ወዘተ ጉዳይ በትግራይ ይወሰንና ይቃኝ እንደነበረው አሁን ደግሞ በኦሮሞ እንዲሆን የሚፈልጉ ጥቂቶች አይደሉም። ይፋ ወጥተው አይናገሩት እንጂ ቁጥሩ ጥቂት የማይባል ኦሮሞ ሃሳቡን እንደሚደግፍ ይሰማል። ይህ ዓይነቱ የተረኝነት ሥርዓት ይዘረጋ ዘንድ በጣም የሚመኘውና ለተግባራዊነቱ በተስፋ እየተጋ የሚገኘው ህወሓት መሆኑ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለዚህም ነው የኦሮሞ ብሔረተኝነት አራማጆች በቅርቡ በይፋ በሚታይ መልኩ ከህወሓት ጋር ሲሠሩ የነበሩት።

የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ያሉበትን ችግሮች እየነቀስን ከመነጋገራችን በፊት፣ ሕገመንግሥቱ ያለበት ከፍተኛና የሚታይ ችግር ገና ሲጀምር “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች …” ብሎ መጀመሩ እንደሆነ ብዙዎች ሲናገሩ ተሰምቷል። ከዚህ ይልቅ ቀላል በሆነ መልኩ “እኛ ኢትዮጵያውያን” ብሎ አለመጀመሩን ብዙዎች አግባብ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። ይህ በህወሓት የተተከለና አካሄዱም ሆነ አፈጻጸሙ በህወሓት ሲቀመር የቆየ ጉዳይ አገሪቱን ወደ አስከፊ ዕልቂት እየገፋፋት እንደሆነ በግልጽ ይታያል።

ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ሚዲያ መስተጋብር (ኦኤምኤ) ዳይሬክተር እና ራሱን የቄሮ መሪና የለውጡ መሃንዲስ አድርጎ የሚጠራው አሜሪካዊው ጃዋር መሐመድ “ተከብቤአለሁ” የሚል የኮድ መልዕክት በማስተላለፉ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ፍጹም ተሰምቶ የማይታወቅና ከኢትዮጵያዊ ወጋችን እና ማንነታችን ጋር በርቀት እንኳን የማይገናኝ ግፍና እጅግ አሰቃቂ የግፍ ግድያዎች ተፈጽመዋል።

ይህ ዓይነቱ ድርጊት ወደፊት በስፋት አይቀጥልም ተብሎ ለመናገር የሚቻል ባለመሆኑ አሁን የደረሰውን ጉዳት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ የግድ ሆኗል። የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር የሚመሩት ይህ የጋዜጣዊ መግለጫ ቡድን ሌሎች አራት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን ያካተተ ነው፤ አቶ ነጌሦ ዋቀዮ፣ አቶ ነጋሲ በየነ፣ አቶ ታማኝ በየነ እና ሼክ ካሊድ ናቸው።

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚያሳስበው በቅርብ አብረን የምንሠራ የምናውቀው ጉዳይ ነው። በመሆኑን በአገራችን ላይ ተጽዕኖ የማድረግ ዓቅሙም በዚያኑ ያህል ቀላል አይደለም። ስለዚህ ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የምንጠብቀው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በቅድሚያ መረጃ እንደሚገባ የሌለውን ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋንኛው የጋዜጣዊ መግለጫው ዓላማ ነው። በመቀጠልም ይኸው ማኅበረሰብ በጠ/ሚ/ር ዐቢይ አገዛዝ ላይ ተጽዕኖ እንዲሳድር ለማድረግ ሌላው የመግለጫው ዓላማ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ግንዛቤ የማስጨበጫ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ የሚከተሉት አራት ጉዳዮች ተደማጭነት ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤

• ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በሚደርጉት የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ የአሜሪካ የፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች ለጋስ መንግሥታት ድጋፍ እንዲሰጡ፤ ይህም ሕገመንግሥታዊ፣ ተቋማዊ ተሃድሶዎች እንዲካሄዱ፤ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዕርቅ፣ ፍትሕና ደኅንነት በኢትዮጵያ ሲቀጥልም በአፍሪካ ቀንድ እንዲሰፍን ለማስደረግ፤

• ምዕራባዊ የሚዲያ አውታሮች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የዘር ጽንፈኝነትና ብሔረተኝነት ተገቢውን የዜና ሽፋን እንዲሰጡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፤

• የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በዘር ፖለቲካ ጽንፈኝነት ምክንያት የሚፈጸሙ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲመዘግቡና አነሳሽ፣ አቀጣጣይ፣ አስገዳይ፣ ወዘተ ግለሰቦችን ወደፍርድ እንዲመጡ የማድረጉን ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ

• ኢትዮጵያውያን ወደ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይትና ንግግር ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በማድረግ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ዕርቅ፣ ወዘተ ተባብረው በቅንጅት እንዲሠሩ ለማነሳሳት ነው።

ስለዚህ ሚዲያ ሰዎች ከላይ በተጠቀሰው ቦታ ከሰዓቱ አስቀድማችሁ እንድትገኙ እንጋብዛለን። ወደ ህንጻው ለመግባት የይለፍ ፈቃድ የሚጠይቅ በመሆኑ አስቀድማችሁ ይህንን እንድታዘጋጁ፤

ለበለጠ መረጃ አቶ ኦባንግ ሜቶ በ202-725-1616 ማግኘት ጠቃሚ ነው።

ፈጣሪ አገራችንና ድንቅ ሕዝቧን ይባርክልን!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ የአኢጋን ጋዜጣዊ መግለጫ

ቀን፤ ጥቅምት 19፤ 2012

ትኩረት፤ ሰላምና ደኅንነት በኢትዮጵያ

ቀን፤ ጥቅምት 20፤ 2012 (October 31, 2019 12:00PM until 3PM)

ቦታ፤ National Press Club, 529 14th St. NW, Washington DC 20045

ይህ መግለጫ ለሚዲያ ሰዎች ብቻ ሲሆን ቅድሚያ ምዝገባ ያስፈልጋል

LEAVE A REPLY