ትናንትና ከታላቅ ሰው እግር ሥር ቁጭ ብለን ስንማር ዋልን። እውነት እውነት እላችኋለሁ ከእሳቸው (ከዶ/ር ኃይሉ አርአያ) ጋር አንድ ቀን ሲያወጉ መዋል አይደለም ለ2 ሰዓት በጥሞና ማውራት ዩኒቨርስቲ እንደምግባት ይቆጠራል።
.
ከትናንት በስቲያ ድንገት ሲደውሉልኝ በመደነቅ ጭምር ነበር ስልኬን ያነሳሁት።
“ሄሎ ዶክ” (ቃሊቲ አንድ ክፍል ታስረን በነበረ ጊዜ ነው “ዶክ” እያልን እንጠራቸው የነበረው)
“አሃ ..ስልኬ አለህ ማለት ነው፤ እኔ ግን ያንተን ስልክ ለማግኘት ተቸግሬ በሰው በሰው ሳፈላልግ ነው የከረምኩት” አሉኝና ጤንነቴን ጠየቁኝ።
“ደህና ነኝ፤ እርስዎስ እንዴት ነዎት”
“አሁን ደህና ነኝ፤ ምንም አልል፤ …ለአንድ ጉዳይ ፈልጌህ ነበር፤ መገናኘት እንችላለን ”
“በደንብ ነዋ! …”
እናም በበነጋታው ጠዋት 4 ሰዓት ልንገናኝ ተቀጣጠርን። ትናንት ማክሰኞ ጠዋት መኖሪያ ቤታቸው ሄድኩ።
እንደተገናኘን የባጥ የቆጡን እያነሳን ጥቂት አወጋን። ሀገራችን በየዠገባችበትን አስጨናቂና አሳሳቢ ሁኔታ ተብሰለሰልን፤ ቆዘምን። እንዲህ እንዲያ እያወጋን ምሣ ሰዓት ደረሰ። ከምሣ በኋላ ላፕ ቶፕ ኮምፒውተራቸውን ይዘው መጡና እየከፈቱ እንዲህ አሉኝ፦
“…..አየህ በ1900ዎቹ መጀመሪያ እኛ እና ጃፓን እኩል ደረጃ ላይ ነበርን። ጃፓን አሁን ያለችበትን ደረጃ ታውቃለህ። እኛ ግን የኋሊት እየተፍገመገምን ነው። ሀገራዊ እድገት (ስልጣኔ) ማምጣት አልቻልንም። በዚህ ሁሉ ዓመታት መሀል መሪዎች መጥተው ሄደዋል። ግን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አልተቻላቸውም። ሕዝባችን የራሱ ጌታ ወይም የሥልጣን ባለቤት መሆን አልቻለም። ለምን ይመስልሃል?”
መልስ አልሰጠኋቸውም። ዝም ብዬ ማዳመጥን ነው የመረጥኩት። ቀጠሉ፦
“አዎ ለምን? ለምን፣ ለምን ለምን…..ብለን መጠየቅ አለብን። ችግራችንን መለየት፣ እና አብጠርጥረን መፈተሽ አለብን። ችግራችን መለየትና ማወቅ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ማፈላለግ አለብን። ….እኔም እንግዲህ እነዚህን ሁኔታዎች ለመፈተሽ መጠነኛ ሙከራ አድርጌአለሁ። እና ይህቺን ፅሁፍ እንድታያትና በአርትዖት ሥራ እንድታግዘኝ ነው የጠራሁህ” አሉኝ ኮምፒተራቸውን እያቀበሉኝ።
ገረመኝ። “ትንሽ” ያሉት ፅሁፍ ወደ 300 ገፅ መፅሐፍ ነው። በዚህ ዕድሜአቸው 300 ገፅ ያህል መፃፍ እና መተየብ ከባድ ነው።
“ዶክ፤ ቃሊቲ እስር ቤት ልደትዎን እናከብር ነበር፤ ካልተሳሳትኩ አሁን 80 ዓመት ሳይደፍኑ አይቀርም” አልኳቸው።
“አዎ፤ ደፍኛለሁ። እንደውም በመጪው ወር ሕዳር 83 ዓመት ይሆነኛል”
“ሕዳር ስንት? ቀኑን ያውቁታል?”
“አዎ አውቀዋለሁ። ሕዳር 21 ቀን ነው የተወለድኩት። እንደውም ሴት አያቴ ደጋግማ ‘አንተ የአስተርዮ ማርያም ልጅ ነህ’ ትለኝ ነበር። አየህ በእነሱ ዘመን ቀናትን ለማስታወስ ከሚጠቀሙበት ስልት አንዱ የኃይማኖት ክብረ በዓላትን ነው” አሉኝ እየሳቁ።
እናም የመፅሐፋቸውን ይዘት አለፍ አለፍ እያልን እያየን ተወያየን። ሙግት የታከለበት ውይይት። በውይታችን መሃል እርጋታቸው፤ አዳማጭነታቸው፤ ነገሮችን የሚያብራሩበት ጥሞናዊ ስልት …ወዘተ ፣ ወዘተ፤ ወዘተ፣ እየተደመምኩ ቀኑ ተገባደደ። ከሁሉ በላይ የገረመኝ ግን ብርቱነታቸው ነው። በ83 ዓመት የዳጎሰ መፅሐፍ ለትውልድ ለማበርከት መትጋት ያስቀናል።
እና ምን ልል ፈልጌ ነው?
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር ኃይሉ አርአያ፤ በቅርብ ወራት የዳጎሰ እና የሚያመረቃ መፅሐፍ ያበረክቱልሃል። እኔም፣ ለአርትኦት ሥራ በእሳቸው በመመረጤ ደስ ብሎኛል ልልህ ፈልጌ ነው።
.