የዜጎችን ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ከአምባገነንነት ጋር መምታት የለበትም። ከህግ በላይ ሳይሆኑ በህግ አግባብ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት መጠበቅ ይቻላል። እርሱ ግን አንድ መፍትሔ ብቻ ነው። ሌሎች የሃሳብና የድርጊት ትልሞች ያስፈልጉናል።
የብሔሮች መብት አግባብ ያለው ታሪካዊ ጥያቄ ነው። የብሔር መብትን መጠየቅ ዘረኝነት አይደለም። (የህዋሃት/ትህነግ ልሂቃን ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ያለ አግባብ ተቆጣጥረውት ሃይላቸውን በሌሎች ላይ ጭነዋል የሚለው የቅርብ ጊዜ መታገያ ርዕስ የብሔር ጥያቄ ምሳሌ ነው። ሁላችንም የብሔር ጥያቄን አንስተን ነበር ማለት ነው።) ዘረኝነት ማለት የራስን ጎራ አመፃድቆ ሌሎችን ዘሮች/ብሔሮች አሳንሶ መመልከት ነው። ዘረኝነት አንድን ህዝብ/ብሔር ወጥ አድርጎ መሳልና ሌላውን/ሌሎችን ብሔሮች በጅምላ ካልገፋን፥ ካላቀናን/ካላዘመንን፥ ካልተበቀልን፥ ካላፀዳን አንተኛም፤ ነፃነታችን ሌሎችን ባሪያ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በዘመናት ውስጥ አንድ ሆኖ አያውቅም። የሃይለ ስላሴ፥ የደርግና የኢህአዴግ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቶች የተለያዩ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች ነን ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ራሳችንን እንጠይቅ። ፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ሊሞካሽ የሚገባው ቢሆንም፤ አፄያዊ ስርዓቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዛቶቻቸውን ያስፋፉትና ያፀኑት በጦር ሃይል፥ በጎራዴና በጥይት መሆኑን ማመንና በነዚያ ሃይሎች የጠፉትን ጥፋቶች በስመ ሃገር ግንባታ (ኔሽን ቢዩልዲንግ) ከማንቆለጳጰስ በዚያ ታሪክ ተበድለናል ለሚሉቱ እውቅና መስጠት ያሻል። አብሮ ማዘን (ኢምፓቲ) ።
በዚያ አይነት ጥፋቶች ተመስርተው ዛሬ ድረስ በየተቁዋማቱና በየዕለት ህይወታችን ተቀብረው የሚገኙትን አስተሳሰቦችና አሰራሮች እንዲሁም አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የምናገኛቸውን የባህል፥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅሞች መንቀስና መተቸትም ወሳኝ ነው። ራስን ጭምር መተቸትና ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ዳግም በህብረት ለመስራት መጣጣር፥ መታገል። (ይህንን ታሪካዊ በደል እንደ ትህነግ ሆን ብሎ ህዝብን ለመከፋፈልና የራስን የበላይነት በስውር ለመጫን ከሆነ ግን ትርፉ አሁን የምናየውን የመሰለ ማንንም የማይጠቅም (ትህነግንም ቢሆን) ክፉ ፕሮጀክት ነው የሚሆነው።)
የሃብት የበላይነት፥ የድህነት፥ የስርዓተ ፆታ፥ የአካል ጉዳተኝነትና የመሳሰሉት ችግሮች ተብትበውን ሳለ ችግሮቻችንን ሂስ ባልነካው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ሆነ የብሔር መነፅር ብቻ መተንተኑና መፍትሔውንም በሁለቱ መነፅሮች ብቻ ለማምጣት መሞከሩ ከነበሩብን አዙሪቶች እንዳንወጣ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ችግሮች ውስጥ እንድንዘፈቅ ነው የሚያደርገን። የሚያፋጀን።
በዙሪያችን የአሜሪካ፥ የቻይና፥ የፈረንሳይ፥ የጣልያን፥ የእንግሊዝ፥ የባህረ ሰላጤው ሃገራት ስለምን ያንዣብባሉ? ይህስ ማንዣበብ ምን ታሪካዊ ዳራ ነበረው፤ አለው? ብሎ መጠየቁ ችግራችንን የውስጥና የውስጥ ብቻ ከማስመሰልና እርስ በእርስ ከመጠላላት እንዲሁም ከመጠፋፋት ያድነናል።
ለምሳሌ ሁላችንም ጥላቻችንን እርግፍ አድርገን ትተን “በቃ በጋራ በፍቅር ለመበልፀግ ተነስተናል!” ብንል፤ በአንድ ጀምበር ወደብልፅግና የምንሄድ ይመስለናል? በአፍሪካ ሁለተኛ የሚያደርገንን አንድ መቶ አስር ሚልዮን ህዝብ ይዘን፤ ከዚህም ውስጥ ሰማንያ በመቶው በግብርና፥ አስራ ሁለት በመቶው በአርብቶ አደርነት የሚተዳደር ሆኖ፥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የህዝባችን አካሎች እንደ ቀሪዎቹ እድል ያላገኙ ይልቁንም በጭቆና ምክንያት ብዙ እድል የተነፈጉ ሴቶች ሆነው ሳለ፥ ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆነው የህዝባችን አካል ወጣት መሆኑ እየታወቀና ወደ አስራ አምስት ሚሊዮን የሚሆነው በስራ አጥነት እየተመታ፥ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑቱ በየዓመቱ በአዲስ ስራ ፈላጊነት እየተመዘገቡ፥ ሃገሪቱዋ ግን በዓመት ለአንድ ሚሊዮኑ ብቻ ነው ስራ መስጠት የምችለው እያለች፥ ለዚያውም ከሃምሳ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ እዳ አናቱዋ ላይ እያናጠረባት … እውነት መብል መጠጣችንን በወጉ ችለን ሰብዓዊ ክብራችንን የምናስጠብቅ እንሆናለን? ይህንን ሃቅ ይዘን ዛሬ የምንተላለቅበትን ጉዳይ ስናጤነው ኢትዮጵያ ዛሬም በጥቂቶች የስልጣንና የገንዘብ ጥማት እየተድፈቀች እንደሆነ እንረዳለን።
ቢሆንም ሁሉም የመብት ታጋዮች የስልጣን ጥማት የሚነዳቸው ናቸው ማለት የዋህነት ነው። ይልቁንም ከአንድ አምባገነን ስርዓት ወጥተን የተሻለ ፍትህና ርትዕ ወዳለበት ሃገር ለመሸጋገር ስንሰራ ነፃነትን የምንተልምበት የሃሳብ መንገድ እጅግ ወደሁዋላ የቀረ፥ በሂስ ያልዳበረ፥ እቃወመዋለሁ የሚለውን ስርዓት የሚደግም፥ የቀደመውን የጭቆና መስመር ዛሬም አድምቆ የሚያሰምር፥ ቀርነት/ጉድለት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የአስተሳሰብ ችግር ያለበት መሆኑም ነው።
በቅርብ የመጣውን የሚታይ ለውጥ ገፍተው ያመጡት የቅርብ የህዝባዊ እንቅስቃሴ ተዋንያን በተለይ ወጣቶቹ የአውሮፓውያን፥ የህንዶችንና የቱርኮችን የአበባ እርሻዎች እንዲሁም የተለያዩ ፋብሪካዎች ሲያቃጥሉ እንጂ ወገኖቻቸውን ሲያርዱ፥ ሲቆራርጡ፥ ሲገድሉ አላየንም ነበር። ያ ድርጊት ወጣቶቹ በወቅቱ በመንግስት ይሞካሽ የነበረው ልማት ህዝቡን የሚያፈናቅል ብሎም የሚበዘብዝ እንጂ ጥቅም እንዳልነበረው የሚያሳይ ነው። ከዚያም ባሻገር ህዝቦች ለዓለም አቀፉ ካፒታል ጫና በግብር መልስ እየሰጡ ነበር። ሆኖም ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች መንግስትን ገፍተውና አስገድደው ለውጦች በወል መታየት ከጀመሩ ወዲህ መሃከለኛውን ስፍራ በሂስ የተሞላ እውቀትም ሆነ ሰብዓዊ ርህራሄ የሌላቸው ታጋይ ነን ባይ ታጋዮች ወርረውት የህዝቡን ጥያቄ ወደ ብሔርና ብሔራዊነት ብቻ ዝቅ አድርገውታል። የአብዮቱ ዘዋሪ የነበሩትን ወጣቶች የእነሱ ተወርዋሪ ጦር (አርሚ ሪዘርቭ) አድርገው እየሳሉዋቸው፥ እየገመቱዋቸውና እያሰማሩዋቸው ነው። ወጣቶቻችንን ከመንቀፍና ከማነወር ወጥተን የሃገሪቱ ሁኔታ እንደፈጠራቸው ወገኖቻችን ወስደን ሂሳዊ በሆነ ውይይት ልናናግራቸው ብሎም ስራ ልንፈጥርላቸው ይገባል።
ነገን የምንተልምበት መንገድ እስካልተቀየረና በየአቅጣጫው የተለያዩ በሚመስሉ ነገር ግን ተመሳሳይ በሆኑ ጎሬዎች ውስጥ ሆነው የመጠፋፋትን መንገድ እንደ እውቀት የሚያስተጋቡና ተከታይ የሚመለምሉ እስካሉ እንዲሁም እስካልተገሩ ድረስ መጠፋፋት እንደ ሰደድ ይሰፋል። ይህንን ማለት ጥልቅ ሃሳብ ከመሰንዘር አይቆጠርም። ዋናው ጉዳይ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ምን እናስብ፥ ምን እንዳርግ የሚለው ነው።